የእምነት ተቋማት የኢትዮጵያ ውስጣዊም ሆነ ውጪያዊ ችግሮች ሲያገጥሟት ለሰላሟ መጠበቅ፤ ለአንድነቷ መጠናከርና ለህዝቦቿ ህብረት አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ ኖረዋል። በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉትን ግጭቶች፣ መፈናቀሎችንና የዜጎችን ጉዳት ለማስቆም ተቋማቱ ከማንም በላይ አደራ እንዳለባቸው ይነገራል።
የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ መጋቤ ዘሪሁን ደጉ እንዳሉት የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሀገር አቀፍ በክልልና በዞን በየዓመቱ መድረኮችን በማዘጋጀት በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ምእመናን ትምህርት ይሰጣል። ይሁን እንጂ በሰላም ዙሪያ ተሠርቷል ለማለት አያስደፍርም፡፡
ጉባኤው የሀገር ሽማግሌዎች ኅብረት፣ የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት የበላይ ጠባቂዎችና የቦርድ አባላት በጋራ በመሆን በቅዱስ ፓትርያርኩ የሚመራ ኮሚቴ አዋቅሮ ሥራ መጀመሩን ያመለከቱት መጋቤ ዘሪሁን፤ ኮሚቴው ከሁለት ሳምንት በፊት በትግራይ ክልል ህዝቡን በማወያየትና ጥያቄ በመሰብሰብ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መክሯል። ባለፈው ሰኞም ከኦሮሚያ ሁሉም ዞኖች ከተውጣጡ ነዋሪዎች ጋር ውይይት ማድረጉንና በውይይቱ የተነሱትን ጥያቄዎች ይዞ ከኦሮሚያ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳ ጋር ውይይት መደረጉን፤ በተመሳሳይ በአማራ ክልልና በሌሎቹም ከነዋሪዎችና ከየክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት በማካሄድ ችግሮችን የመፍታት ጥረቱን ያጠናክራል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጀመረችው የሰላም ዘመቻ ትልቅ ውጤት የሚያመጣ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ከታኅሣሥ 10ቀን 2011ዓ.ም ጀምሮ 150 የሰላም ልዑካን በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ አጥቢያ ቤተክርስቲያናት እንደሚሰማሩ የገለጹት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅና የክልል ትግራይ ደቡባዊ ዞን ማይጨውና ደቡባዊ ምሥራቅ ትግራይ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አባ ዲዮስቆሮስ ‹‹በኢትዮጵያ በታሪኳ ልጆቿ በሀገራቸው የሚፈናቀሉባት ሀገር ሳትሆን የውጭ ዜጎች በመጠለያነት የሚመርጧት ናት›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አባ ዲዮስቆሮስ ‹‹የባዕድ አስተሳሰብ ከማንነታችን በተቃራኒ ሀገሪቱ የብጥብጥና የሁከት ዜና እንዲሰማባት እያደረገ ይገኛል›› ያሉት አባ ዲዮስቆሮስ፤ ይሄንን የመታደግና ሰላም የማስጠበቅ ኃላፊነት ደግሞ የቤተክርስቲያን እንደሆነ አመልክተዋል።
ልዑካኑ በመላ ሀገሪቱ እንዲሰማሩ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ተወስኖ ወደ ሥራ መግባቱንና ለዚህም አስር ሚሊዮን ብር መመደቡን ተናግረዋል፡፡ ከሀገር ውጭም ተመሳሳይ መርሐግብር ለማካሄድ መታቀዱንም አመልክተዋል፡፡ ህዝቡ በየቦታው የሚታዩት የሰው ሞት፣ መፈናቀልና የእርስ በእርስ ግጭት እንዲቆም የበኩሉን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
የሰላም ሚኒስቴር በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት የተጀመረውን የሰላም ጥሪ ከግብ ለማድረስ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመሆን በእንቅስቃሴ ላይ እንደሆነ የገለጹት በሰላም ሚኒስቴር የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ዘሪሁን ዘውዴ፤ ገልጠው በተለይ የእምነት ተቋማት ህብረተሰብን ወደ አንድ አስተሳሰብ በማምጣትና በሰላም ጉዳይ እንዲመክር በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና እንዳለው፤ የከዚህ ቀደምም የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በነበረበት ወቅት ከሃይማኖት ጉባኤ ጋር በመሆን ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት በሠራው ሥራ በእምነት ዙሪያ የሚነሱ ግጭቶችን በማስወገድ ረገድ ትልቅ ውጤት ማስመዝገቡንም አስታውሰዋል፡፡
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 5/2011