
ቢሾፍቱ፡- በ2011 ዓ.ም በጀት ዓመት ከጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው 153 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢንስቲትዩት የበጀት ዓመቱ አፈጻጸም ትናንት በቢሾፍቱ ከተማ ሲገመግም እንደገለጸው፣በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ 240 ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት አቅዶ 63 በመቶ በማሳካት 153 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር አግኝቷል።ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ44 ነጥብ 47 ሚሊዮን ዶላር ጭምሪ አድርጓል፤ ይህም የ40 ነጥብ 8 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን በሪፖርቱ ተገልጧል፡፡
የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ለማ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ የውጭ ምንዛሪ ዕድገቱን ለመጨመር የበቃው በሥልጠና እና በቴክኖሎጂ የታዘገ የሰው ኃይል በመጠቀሙ ነው።ለዚህም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ከሌሎች የምርምር አካላት ጋር በቅንጅት ሰርቷል።ተቋሙ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ብቻ ሳይሆን ለህብረተሰቡ የሥራ ዕድል በመፍጠርም ዕድገት ማሳየቱን ገልጸዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ኢንስቲትዩቱ ዘርፉን ለማሳደግ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ጋር እየሰራ ነው።ግንባታቸው የተጠናቀቁ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለባለሀብቶች ለመስጠት እየተሰራ ነው።በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያዎች ተገቢውን ክህሎት እንዲኖራቸው ተከታታይ ሥልጠና ይሰጣል።
ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጨርቃጨርቅ ዘርፍ የትምህርት ክፍል የሚሰለጥኑ ተማሪዎች ከመመረቃቸው በፊት ከኢንስቲትዩቱ ሥልጠና እንደሚያገኙ አቶ ስለሺ ገልጸዋል።የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች ባሉበት ቦታ የተግባር ልምምድ ያደርጋሉ።የመመረቂያ ጽሑፋቸውንም የሚሰሩት በፋብሪካዎች ላይ ነው።ተማሪዎቹ ለተግባር ልምምድ በወጡበት ፋብሪካም ሊቀጠሩ ይችላሉ።
በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሚሰጠው የጨርቃጨርቅ ትምህርት ክፍል ኢንስቲትዩቱ የሥርዓተ ትምህርት ቀረጻ ላይ እንደሚሳተፍም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። በ2011 ዓ.ም በጀት ዓመት ከሀገር ውስጥ ባለሀብቶች 60 ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 43 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 20/2011
ዋለልኝ አየለ