
ድሬዳዋ፡- የድሬዳዋ ሞተርስ የቲቪኤስ ባለሶስት እግር ተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ፋብሪካ በአራት ደቂቃ ውስጥ አንድ ተሽከርካሪ እየገጣጠመ ነው።
በድሬዳዋ ሞተርስ የቲቪኤስ ባለሶስት እግር ተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ቡድን መሪ አቶ ኢሳያስ አክሊሉ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፣ መገጣጠሚያ ፋብሪካው በማምረት አቅም፣ ቴክኖሎጂ አጠቃቀምና በሥራ አመራር የተደራጀ በመሆኑ ለሠራተኞቹ ሙያዊ አቅም ማደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ሲሆን፣ በግልም ክህሎቱን የሚያሳድጉ አጋጣሚዎች እንደተፈጠሩለት ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ኢሳያስ ገለፃ በፋብሪካው ተገጣጥመው ወደ ገበያ የሚቀላቀሉት እነዚህ ባለሶስት እግር የቲቪኤስ ተሽከርካሪዎች በመገጣጠም ሂደቱ አስፈላጊውን የጥራት ደረጃ እንዲኖራቸው አድርጎ ከመሰራታቸው በተጨማሪ የጥራት ፍተሻም ይደረግላቸዋል፡፡
የተሽከርካሪዎቹ አካላት በትክክል ስለመገጠማቸው፣ የመቆጣጠሪያ መሳሪያዎችና የእግር ገጠማ ስርዓቱ እንዲሁም የተሽከርካሪው የፍጥነት ልክን ጨምሮ ሌሎችም የቴክኒክ ሥራዎች በሙሉ ተፈትሸው ሲረጋገጡ እያንዳንዱ ተግባር በፈፀመው ሠራተኛ ፊርማ እየተረጋገጠ ወጪ እንደሚሆኑም አቶ ኢሳያስ ጨምሮ ገልጿል።
በመገጣጠሚያ ፋብሪካው የምርት ጥራት ተቆጣጣሪ አቶ ጌቱ ደበበ፣ ከሶስት ዓመት በፊት ወደ ድርጅቱ ሲቀላቀል በመካኒክነት ሙያ ተቀጥሮ እንደነበር አስታውሶ በፋብሪካው ሙያውን እያሻሻለና ክህሎቱን እያዳበረ ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ መድረሱን ተናግሯል፡፡
መገጣጠሚያው አሁን የራሱን ዲዛይን በመስራት አነስተኛ ተሽከርካሪዎችን ወደ ገበያው ለማስገባት ሥራ የጀመረ ሲሆን የቆሻሻ ማንሻ፣ አነስተኛ የጭነት መኪኖችንና ትናንሽ የመጠጥ ማከፋፈያ መኪኖችን ማምረት እንደሚጀምርም አመልክቷል፡፡
ሌላዋ የፋብሪካው ሠራተኛ ዲቦራ ሽመልስ በበኩሏ ከቴክኒክና ሙያ በደረጃ 4 በአውቶሞቲቭ ኤሌክትሪክ ሰርቪስ የትምህርት ዘርፍ እንደተመረቀች ገልጻ፣ በስልጠና ያገኘችውን እውቀት በኩባንያው ወደ ተግባር በመቀየር ተጨማሪ እውቀት እያገኘችና ሙያዋንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደገች ስለመሆኑ ተናግራለች፡፡
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ባስገነባው የኢንዱስትሪ መንደር ውስጥ የሚገኘው ድሬዳዋ ሞተርስ ኢንጅነር ታደሰ አድማሱ በተባሉ የሀገር ውስጥ ባለሀብት በ2009 ዓ.ም ሐምሌ ወር አካባቢ በ1.5 ቢሊዮን ብር ካፒታል ተቋቁሞ ወደሥራ የገባ ሲሆን፣ በአንድ ፈረቃ እስከ 120 ባለሶስት እግር የቲቪኤስ ተሽከርካሪዎችን የመገጣጠም አቅም አለው፡፡ከ 700-1000 ለሚሆኑ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ እድል ፈጥሯል፡፡
አዲስ ዘመን ሀምሌ 20/2011
ድልነሳ ምንውየለት
ፎቶ፡- ፋይል