
አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከንቲባ ፅህፈት ቤት ሀሳብ አመንጪነት ተጀምሮ ለመንግሥት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ለሚቀርበው የደብተር ልገሳ ከስድስት ሚሊዮን በላይ ደብተሮች መሰብሰባቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ከንቲባ ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪ ኃላፊ ወይዘሪት ፌቨን ተሾመ በትናንትናው እለት ከበላይ አብሞተርስ የተለገሰውን የ100 ሺህ ደብተሮች ስጦታ በአስተዳደሩ ስም ተቀብለዋል። በርክክቡ ወቅት ኃላፊዋ እንደገለጹት፤ አስተዳደሩ ከመደበው በጀት በተጨማሪ በከተማዋ የሚገኙ ባለሀብቶችን በማስተባበር የደብተርና የሌሎች የትምህርት ቁሳቁሶችን እየተቀበለ ይገኛል።፡ በከተማው ላሉ የመንግሥት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የተጀመረው የትምህርት መርጃ ቁ ሳቁሶች የማሰባሰቡ ሥራ በባለሀብቶች ፈጣን ምላሽ እየተሰጠው ይገኛል። በዚህም ከስድስት ሚሊዮን በላይ ደብተሮች ተሰብስበዋል።፡
እንደ ፕሬስ ሴክሬታሪ ኃላፊዋ ገለጻ፤ በመጪው ዓመት በአዲስ አበባ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎችና ወላጆች በሙሉ ለትምህርት የሚረዱ መሳሪያዎች ወጪ እንዳይኖራቸው ታቅዶ እየተሰራ ነው። ለዚህም ላለፉት ሶስት ሳምንታት በተከናወኑ የልገሳ መርሐግብሮች በርካታ የመማሪያ ቁሳቁሶችን አስተዳደሩ ከተለያዩ አካላት ተረክቧል። የከተማ አስተዳደሩ በከተማዋ ለሚገኙ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ፍላጎት ያላቸውን የከተማውን ባለሀብቶች በማሳተፍ እና ድርጅቶችን በማስተባበር የልገሳ መርሐ ግብሩን አጠናክሮ ይቀጥላል።
በመስተዳድሩ ጥሪ ፈጣን ምላሽ በመስጠት እስከአሁን ድጋፍ ላደረጉ ተቋማትና ባለሀብቶች ምስጋና ያቀረቡት ወይዘሪት ፌቨን፤ ባለሀብቶችና ድርጅቶች ከትርፍ ባሻገር ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት በመቻላቸው ሊበረታቱ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የበላይ አብ ሞተርስ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዘዳእሙ ህገእግዚአብሄር በበኩላቸው በከንቲባው በተደረገው ጥሪ መሰረት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለመርዳት ተሳትፎ በማድረግ የራሳቸውን አስተዋጽኦ በማበርከታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።በህብረተሰቡ ውስጥ ያሉትን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መንግሥት ብቻውን መቅረፍ እንደማይችል ተናግረው፤ ባለሀብቱ ከመንግሥት ጋር እጅናጓንት በመሆን ማህበራዊ ቀውሶችን ላይ አተኩሮ መስራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መረጃ፤ በላይ አብ ሞተርስ ለከተማ አስተዳደሩ ያበረከተው ደብተር በብር ሲሰላ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር ይገመታል።የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመጪው ዓመት በከተማው ለሚገኙ ቁጥራቸው 600 ሺህ ለሚሆኑ የመንግሥት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ዩኒፎርም፣ደብተር እና የተለያዩ የትምህርት ቁሳቁሶችን ለተማሪዎች በነፃ ለማቅረብ እየሰራ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 20/2011
ዳግማዊት ግርማ