የዓለማችን ቀላሉ ሥራ ይሄ ‹‹የሥራ ትንሸ የለውም›› የሚባል ነገር ግን ምነው ባስበው ባስበው አልገባህ አለኝ? አተያየቱ እንዴት ቢሆን ነው ግን? እንደአባባሉ ከሆነ እኮ በወር የመቶ ምናምን ሺ ብር ደሞዝተኛ እና የማይሸጥ ዕቃ ይዞ ጎዳና ለጎዳና ሲዞር የሚውል እኩል ናቸው ማለት ነው።ምን እንደምትሉ ልገምት! የሚያስገኘው ገቢ ማነስና መብዛት አይደለም፤ ሥራው ግን ያው ሥራ ነው ልትሉ ነው አይደል? እሺ ይሁንላችሁ!
የምር የምር ግን የሥራ ትልቅ እና ትንሽ የለውም።ትልቅ እና ትንሽ የሚያደርገው ራሱ ባለቤቱ ነው።አንድ የሪልስቴት ባለቤት ከማስቲካ አዟሪነት የተነሳ ሊሆን ይችላል።ስለዚህ ማስቲካ ማዞርን ቀላል ሥራ አንለውም ማለት ነው።አንድ የሪልስቴት ባለቤት ካላወቀበት የዕለት ጉርሱን እስከሚያጣ ድረስ ወደ ድህነት ሊወርድ ይችላል፤ ስለዚህ የሪልስቴት ሥራም ትልቅ አይደለም ማለት ነው።ትልቅ እና ትንሸ የሚያደርገው ባለቤቱ ነው።
ወይ ጣጣ! አሁን ደግሞ፤ ‹‹ስለዚህ ሰው እኩል አይደለም!›› የሚል ጥያቄ ልታነሱ ነው አይደል? ቆይ ግን ሰው ሁሉ እኩል ከሆነ፤ ለምን አንዱ ሰነፍ አንዱ ጎበዝ ሆንን? ይሄም በሰውየው ጥንካሬ ላይ ይወሰናል።
ለማንኛውም አንድ የዓለማችን ቀላል ሥራ አለ፤ እሱም ‹‹ትችት!›› ትችት የዓለማችን ቀላሉ ሥራ ነው ብንል ምንም ማጋነን አይሆንም።በተለምዶ ቀላል ናቸው ከምንላቸው ሥራዎች ሁሉ ቀላል ነው።ትችት ማለት እኮ አንድ ቦታ ቁጭ ብሎ ሌሎች የሰሩትን መተቸት ማለት ነው።በነገራችን ላይ በሬዲዮም ሆነ በጋዜጣ እንደ ትችት የሚሰለቸኝ ፕሮግራም የለም (ያው እንግዲህ የግል አስተያየት ነው)።
ትችት ሲባል ምክንያታዊ የሆነ ትችት እንዳለ አምናለሁ።ያ ማለት የተሰራው ሥራ በትክክልም የሚያስተች ሲሆን ማለት ነው።በሌላ በኩል የሚተቸው ሰው ያንን ድርጊት ራሱ የማያደርገው መሆን አለበት።
ለምሳሌ ቆሻሻ በየመንገዱ መጣልን፣ መጥፎ ስነ ምግባርን፣ ዝሙትን፣ ሱስን… ብዙ ሰው ይተቻል።የሚያናድደው ግን ራሱ የሚያደርገውን ነገር ነው።ሲጠጡ፣ ሲቅሙ፣ ሲያጨሱ ነውር ነገር ሁሉ ሲያደርጉ የማውቃቸው ጋዜጠኞች ሬዲዮ ላይ ወጥተው ይህን ድርጊት ሲኮንኑ ይሰማል።ያንን ድርጊት ይፈጽሙታልና ማበረታታት አለባቸው ወይም ዝም ማለት አለባቸው ማለት አይደለም።ዳሩ ግን መተቸት እንደመተው ቀላል አለመሆኑን ለማሳየት ነው።ያ ስለዝሙትና ስለስካር ሲያወግዝ የነበረው ጋዜጠኛ ራስህ ተወው ቢባል አይተወውም፤ መተቸቱ ግን ቀላል ስለሆነ በየዕለቱ መተቸት ይችላል።
ከሰሞኑ የማህበራዊ ገጾች መነጋገሪያ የነበረውን አንድ ክስተት ምሳሌ እናንሳው።አንዲት አርቲስት በአንድ ባለትዳር ቤት ውስጥ ገብታ ስትወሰልት በሰውየው ሚስት ተቀረጸ የተባለ ቪዲዮ ተለቆ ነበር።አርቲስቷም በሬዲዮ ተጠይቃ አስተባብላለች።ድርጊቱ እውነት ነው ሀሰት የሚለውን እንተወው! ምሳሌ ማድረግ የፈለኩት ድርጊቱን ተከትሎ የነበረውን የሰዎች ክርክር ነው።
አንዳንዶቹ፤ ‹‹ሁላችንም ስላልተያዝን ነው እንጂ እናደርገዋለን›› አሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ነውረኝነቷን ከቁጣ ጋር አወገዟት።ሁሉም የመሰለውን የተናገረ መተቸት ቀላል ስለሆነ ነው።እነዚያ ሲያወግዟት የነበሩት ሰዎች በትዳራቸው ላይ የሚወሰልቱ ሊሆኑ ይችላሉ።ያወገዟት ዕለት ማታ ራሱ ከትዳራቸው ውጭ ሊወሰልቱ ይችላሉ።
አንድ ነገር ግን ያስማማናል! በማህበረሰቡ ዘንድ ነውር የሆነ ነገር ሲከሰት ‹‹እኔም አድርጌዋለሁና አልተችም›› አይባላም።ባንተች እንኳን የድርጊቱን ባለቤት የተቹትን ልናወግዝ አይገባም።በአርቲስቷ ላይ በተከሰተው ነገር የታዘብኩት ነገር ይሄን ነበር።ድርጊቱን ነውር ነው ያሉ ሰዎችን የሚሳደቡ ነበሩ፤ ይሄ ድርጊቱን ከማበረታታት አያንስም! በውስጣቸው እንዲህ አይነት ነገር ነውር መሆን እንደሌለበት ያምናሉ ማለት ነው።
ሌላም አንድ ማሳያ ልናገር
ብዙ ጊዜ በቀልድም ይሁን በቁም ነገር ሲጋራ የሚያጨስ መምህር ስለሲጋራ ጉዳት ሲያስተምር የሚለው ነገር ይነሳል።ራሱ መተው ያልቻለውን እንዴት ለሌሎች ጎጂ ነው ብሎ ያስተምራል ለማለት ተፈልጎ ነው።
ሲጋራ የሚያጨስ መምህር ስለሲጋራ ጎጂነት ድብን አድርጎ ማስተማርና መምከር ይችላል! እሱ መተው አልቻለም ማለት ሌሎችም አይችሉም ማለት አይደለም።እሱ መተው ባለመቻሉ ደካማነቱን እየገለጸ ያለውን አስከፊ ጉዳት መናገሩ ግን እንዲያውም ከማያጨሱት የበለጠ አሳማኝ ይሆናል።ይሄ ሰው እኔ እያጨስኩ እንዴት ስለሲጋራ ጎጂነት እመክራለሁ ማለት የለበትም! ቢችል መተው፤ ካልቻለ ግን ሌሎች እንዳያጨሱ መምከር!
ገጠር ውስጥ ቤተክርስቲያን ቄሶች ሲሰብኩ አንድ የምሰመው ነገር ነበር።‹‹ቄስ ሲሰክር አየን ብላችሁ አትስከሩ፣ ቄስ ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ሲወሰልት አየን ብላችሁ አትወስልቱ፤ በምድርም በሰማይም የሚዋረደው ራሱ ነው›› ይሉ ነበር።
እርግጥ ነው አርዓያ ሆኖ መገኘት ምንም አያከራክርም! ያ ካልሆነ ግን ያ ሰው መምከር የለበትም ማለት አይደለም።በራስ መተማመን ካለን ከሰውየው የምንወስደው ሳይንሳዊ እውነታውን ነው።በነገራችን ላይ ‹‹እገሌ ራሱ ያደርገው የለ እንዴ!›› የምንለውም ትችት ቀላል ስለሆነ ነው።እኛ ልናደርገው ስንፈልግ ነው በእሱ የምናሳብብ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሀምሌ 20/2011
ዋለልኝ አየለ