በወጣትነት እድሜያቸው ለበርካቶች የስራ ዕድል መፍጠር ችለዋል። ታታሪነታቸው እና መልካም ባህሪያቸው ለስራቸው እድገት መልካም አስተዋጽኦ እንዳደረገ በርካቶች ይመሰክራሉ። ከመኪና ኪራይ እና ቱሪዝም ዘርፉ ተሳትፎ ባለፈ በቆዳው ኢንዱስትሪ ዘርፍ በተለያዩ የአሜሪካ እና አውሮፓ ሀገራት ተወዳጅነትን ያተረፉ ምርቶችን አዘጋጅተው ይልካሉ።
ለጥራት ቅድሚያ የሚሰጡ ከመሆናቸው ባለፈ የኢትዮጵያን ሃብት ለሌላው ዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ሰፊ ስራን ሲያከናውኑ ቆይተዋል። እኚህ ሰው፣ አቶ ዘላለም መራዊ ይባላሉ። ውልደታቸው አምቦ ከተማ ነው። አባታቸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሰራተኛ ስለነበሩ ለስራ በተመደቡበት አካባቢ ይንቀሳቀሱ ነበር። እርሳቸው አራት ዓመት ሲሆናቸው፣ አባታቸው በቀድሞ ስሟ አዲስ ዓለም ከተማ ወደምትባለው ኤጀርሳ ከተማ ቤተሰባቸውን ጠቅልለው ሄዱ።
አቶ ዘላለም፣ አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በኤጀርሳ ከተማ በቀድሞው በአለቃ ኪዳነ ወልድ /ኤጀርሳ/ ትምህርት ቤት ተከታተሉ። ገና በልጅነት እድሜያቸው ለቴክኒክ ስራዎች ልዩ ፍቅር ነበራቸውና አንድን ነገር መፈታታት እና መገጣጠምን ይወዳሉ። ይህን ፍላጎታቸውን የተረዱት አዲስ አበባ የሚገኙት አጎታቸውም፣ በጋራዥ ስራ ሙያ እንዲቀስሙ በሚል እርሳቸው የሚሰሩበት ቦታ እንዲመጡ ያደርጋሉ።
በመሆኑም አቶ ዘላለም፣ በአዲስ አበባ የድሮው ከርቸሌ የነበረበት የአሁኑ አፍሪካ ህብረት ጀርባ የሚገኝ ጋራዥ ቤት ሙያ ለመቅሰም በነጻ እየሰሩ ከአጎታቸው ጋር ይኖሩ ጀመር። በመካኒክነት ሙያ ቀን እየሰሩ ማታ ላይ ደግሞ በሽመልስ ሀብቴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያቋረጡትን ትምህርት ቀጠሉበት። ለሶስት ዓመታት በጋራዥ ሲሰሩ ቤሳቤስቲን ሳንቲም አይከፈላቸውም ነበር።
በዚህም ምንም ገንዘብ ስለሌላቸው የትምህርት ቤት ክፍያቸውን የሚሸፍኑላቸው አጎታቸው ነበሩ። አቶ ዘላለምም፣ ከስራ መልስ አጎታቸው ቤት ብቻ አይኖሩም ነበር። አክስታቸው እና ሌሎች ዘመዶቻቸው ጋር የተወሰኑ ቀናት ይቆያሉ። በተለይ አክስታቸው ከብቶች የሚያረቡ በመሆኑ ከጋራዥ መልስ ትምህርት ቤት መሄድ ከዚያም ቀጥሎ ላሞቹን እና በሬዎቹን የመንከባከብ ኃላፊነቱን ይወጡ እንደነበር ያስታውሳሉ። ሌሊት 10 ሰዓት ደግሞ ተነስተው ለከብቶቹ ምግብ በመስጠት እና የከብቶቹን ማደሪያ (በረቱን) አጽድተው ሲያጠናቅቁ ነበር ወደ መደበኛ ስራቸው የሚሄዱት።
ምንም እንኳን ህይወት በዚህ አይነት ዑደት አድካሚ ብትሆንባቸውም፤ በወቅቱ ግን ተስፋ እንዳልቆረጡ ያስታውሳሉ። በሂደትም የጋራዥ ሙያውን ማቀላጠፍ ሲጀምሩ፤ አሰሪያቸውም በሳምንት 15 ብር ለሳሙና በሚል ይከፍሏቸው ጀመረ። በዚህ መልኩ ስድስት አመታትን በአዲስ አበባ እንዳሳለፉ ከአጎታቸው ቤት ወጥተው እራሳቸውን ለመቻል ያቅዳሉ። በመሆኑም በወር የሚያገኟትን ትንሽ ጭማሪ ያሳየችውን የ200 ብር ደመወዝ ይዘው ቡልጋሪያ ማዞሪያ አካባቢ ዛኒጋባ ቤት በ45 ብር ቤት ተከራዩ።
የተከራዩዋት ቤትም ዝናብ የምታስገባ በመሆኗ አንድ ቀን ሃይለኛ ጎርፍ ገብቶ የሳር ፍራሻቸውን በማራሱ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ከውጭ ድንጋይ አስገብተው እርሷ ላይ ተቀምጠው ማንጋታቸውን ይናገራሉ። ከዚህ በተጨማሪም የማታ ትምህርት ቤት ክፍያ እና የቀለብ ወጪ መሸፈን እንደከበዳቸው፤ የሚበላ አጥተውም ጾማቸውን ለሁለት ቀናት ማደራቸውን፤ እና ዳቦ በስኳር የተመገቡባቸውን ቀናት ትልቁ የብቸኝነት ወቅት ፈተናዎቻቸው እንደነበሩ ያስታውሳሉ። በዛን የፈተና ወቅት ግን ተመልሰው አጎታቸው ቤት ጥገኛ መሆን ባለመፈለጋቸው ወጪው ቢከብዳቸውም ተቋቁመው ማለፍን መርጠዋል።
ይህን አይነት መከራ ሲያሳልፉ ግን በጋራዥ ቤቱ የአሽከርካሪነት ሙያን በአግባቡ እየቀሰሙ ነበር። የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ ለኮሌጅ የሚያበቃ ነጥብ ቢኖራቸውም የመንጃ ፍቃድ አውጥተው የስምንት ዓመት የጋራዥ ስራቸውን በቃኝ አሉ። ከዚህ በኋላ የአጎታቸው መኪና ነበረችና እርሷን ይዘው ለመስራት ወስነዋል። ቱኤች የተሰኘችውን የአጎታቸውን ተሽከርካሪ ይዘው በ1994 ዓ.ም ሳትኮም ኮንስትራክሽን በኦጋዴን አካባቢ ለሚያሰራው የግንባታ ስራ በ1ሺ200 ብር አጠቃላይ ክፍያ ስራ ጀመሩ።
ኑሮ በካምፕ ውስጥ ቢሆንም የኦጋዴንን በረሃ እና ሱስ አስያዥ ነገሮችን በ18 ዓመታቸው ተቋቁመው ያሽከረክሩ እንደነበር ያስታውሳሉ። ተሽከርካሪዋ ስትበላሽ እራሳቸው እየጠገኑ የሱማሌን በረሃዎች ተዘዋወሩባቸው። አላማ ነበራቸውና መጠጥ የደረሰበት ሳይደርሱ እንዲሁም አላስፈላጊ ወጪዎችን እየቀነሱ ለሁለት ዓመት ከስምንት ወር ከሰሩ በኋላ አበል እና የተለያዩ ክፍያዎቻቸውን ቆጥበው 70 ሺ ብር አጠራቀሙ።
አቶ ዘላለም፣ ቀደም ሲል አዲስ አበባ እያሉ ጋራዥ ተሽከርካሪዎቻቸውን ሊያስጠግኑ ከሚመጡ የቱር ኦፕሬተሮች ጋር ጥሩ ተግባቦት ነበራቸው። እናም ከኦጋዴን ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ የትጠፍተው እንደነበር ቱር ኦፕሬተሮቹ ይጠይቋቸዋል። እርሳቸውም የጠፉት በሹፌርነት ስራ ሄደው እንደነበር ሲያጫወቷቸው “ለምን የቱር ኦፕሬተር ሹፌር አትሆንም” የሚል ጥያቄ ያቀርቡላቸዋል። እርሳቸውም በጥያቄው ተስማምተው በወጣትነታቸው አዲሱን ዘርፍ ተቀላቀሉ። በወር የ600 ብር ክፍያ እና ለጉዞ በሚወጡበት ወቅት ተጨማሪ አበል እየታሰበላቸው መላ ኢትዮጵያን ይዞሩ ጀመር።
በዚህ ስራቸውም ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ የውጭ ዜጎችን ከማጓጓዙ በተጨማሪ፤ የማስጎብኘቱንም ስራ ይከውኑ ነበር። ከውጭ ዜጎቹ ጉርሻ ክፍያ ሲሰጣቸው ግን “እኔ የምፈልገው ጉርሻ ሳይሆን ወደፊት የእራሴ ቱር ኦፕሬተር ድርጅት ባለቤት መሆን ስለሆነ ጎብኚዎችን እንድትልኩልኝ ነው” በማለት ቃል እያስገቡ አድራሻቸውን ይቀበሉ ነበር።
ወደ ሰላሳዎቹ የዕድሜ ክልል ሲጠጉ እና የገንዘብ አቅማቸው መሻሻል ሲያሳይ ደግሞ የአጎታቸው ተሽከርካሪ ለሽያጭ ልትቀርብ መሆኑን ይሰማሉ። እናም የእራሳቸው ተሽከርካሪ ባለቤት በመሆን የቱሪዝም ድርጅት ለመክፈት ያስባሉ። አጎታቸውን አነጋግረው በ140ሺ ብር ተሽከርካሪዋን ገዝተው ግማሹን ክፍያ ግን እየሰሩ እንደሚከፍሉ በመስማማት ውል ተዋዋሉ።
ጨርቆስ አካባቢ በ350 ብር ቢሮ ተከራይተው በ1998 ዓ.ም የቱሪዝም አስጎብኚ ድርጅታቸውን ከፈቱ። ስራ ሲመጣ እና ተጨማሪ ተሽከርካሪ ሲያስፈልግም ከሌሎች ሰዎች እየተከራዩ ጥሩ አገልግሎት መስጠቱ አልከበዳቸውም። ይህ ወቅት ትዳር መስርተው አንዲት ሴት ልጅ የወለዱበት ጊዜ ነው። አንድ ቀን ግን ህይወታቸውን በእጅጉ የሚቀይር አጋጣሚ ተፈጠረላቸው። የቀድሞው ውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር አንድ ጨረታ ያወጣል።
ጨረታውም “በመላ አገሪቷ በሚገኙ ዋና ዋና ተፋሰሶች ላይ የመስኖ ግድብ ዲዛይን ለማስጠናት የ60 ተሽከርካሪዎች ኪራይ አገልግሎት እንፈልጋለን” የሚል ነበር። አቶ ዘላለምም አንድ መኪና ይዘው ቀሪውን በኪራይ አሟላለው ብለው ለእራሳቸው ነግረው ጥሩ ሰነድ በማዘጋጀት ጨረታውን ቢወዳደሩ ለአንድ ተሽከርካሪ በ425 ብር አሸናፊ ሆኑ። በወቅቱ ግን ለጨረታ ማስከበሪያ የሚያስይዙት አምስት ሺ ብር እንኳን አልነበራቸውምና ከሚኒስቴሩ ቢሮ በሃዘን ሲወጡ ያየ አንድ ሰራተኛ ችግራቸውን ጠይቆ ከደመወዙ ላይ 3ሺ 500 ብር ሰጣቸው። እርሳቸው ደግሞ በኪሳቸው የነበራቸውን 1ሺ500 ብር ጨምረው ማስከበሪያውን በማስያዝ ውል ተዋዋሉ።
በወቅቱ ደህና የሚባል የቢሮ አደረጃጀት እና አቅም ባይኖራቸውም እንኳን በከተማው ውስጥ የሚገኙ ተሽከርካሪዎችን በ400 ብር ተከራይተው አቀረቡ። በመላ አገሪቷ ተሽከርካሪ አሰማርተው ከአንዱ የ25 ብር የቀን ትርፍ ያገኙ ጀመር። በእንዲህ አይነት ሁኔታ የወር ገቢያቸው በሺዎች በመድረሱ ከወራት በኋላ የእራሳቸውን ተሽከርካሪዎች ቁጥር ሁለት እና ሶስት ማድረስ ቻሉ።
ለግድብ ጥናቱንም በጊዳቦ፣ መገጭ፣ እና በርካታ ትላልቅ ወንዞች አካባቢ ተሽከርካሪ በማሰማራት ለሁለት ዓመታት ሰሩ። ከዚህ በኋላ የገንዘብ አቅማቸውም በማደጉ ዘላለም ቱር ጉዞና የመኪና ኪራይ ድርጅት ታዋቂነቱ እየጨመረ መጣ። ድርጅቱ በየወቅቱ ቱሪስቶችን በማጓጓዝ እና የኪራይ መኪናዎችን በማቅረብ አገልግሎቱን ማስፋት ቻለ።
አቶ ዘላለም፣ በዚህ ብቻ መወሰን ባለመፈለጋቸው ኬሬዢ ኢትዮጵያ የተሰኘ የቱሪዝም ማስተዋወቂያ ድርጅት አቋቁመው ስለኢትዮጵያ መስህቦች የሚያስተዋውቅ ድረገጽ ከፈቱ። ድረገጹ በዓመት አምስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ጎብኚዎችን በማስተናገድ ቱሪዝሙን ማስተዋወቅ እንደቻለ ይናገራሉ። ከዚህ ባለፈ ግን ስለኢትዮጵያ መስህቦች ሙሉ መረጃ የሚሰጥ እና በካርታ የተደገፈ መጽሃፍ በማሳተም በመላው ዓለም 80 ሺ ኮፒዎችን ማሰራጨት ተቻለ። የተለያዩ የቱሪስት አመላካች መጽሔቶችን እና ጽሁፎችንም አሳትመዋል።
መልካም ገጽታ ግንባታ ሳይሆን በጎ ነገራችን ስለሚበዛ የመልካም ገጽታችንን ማስተዋወቅ የሚለው አካሄድ እንደአገር ያስፈልገናል የሚል መሪ ሃሳብ በማንገብ ሰፊ ስራ በማከናወናቸውም፤ ድርጅታቸው እ.አ.አ. በ2014 በቱሪዝሙ ዘርፍ ስዊዘርላንድ ጄኔቫ ዓለም ዓቀፍ የወርቅ ተሸላሚ ሆኗል። ሆኖም በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ግርግር እና ሁከት በመበራከቱ የቱሪዝም ስራው መዳከም ጀመረ።
ችግሩ የእርሳቸውም ድርጅቶች ላይ ተጽእኖ በማሳደሩ የቱሪዝምና ማስተዋወቅ ድርጅታቸውን እና ሰራተኞቻቸውን ሳይበትኑ ወደሌላ ዘርፍ መቀላቀል እንዳለባቸው ወሰኑ። የመኪና ኪራይ እና ቱሪስት አስጎብኚ ድርጅቱን ስራ ሳይለቁ ጥናት ሲያደርጉም የቆዳው ዘርፍ በጥራት እና በዘመናዊ መልክ ከተሰራበት ሊያዋጣ እንደሚችል ተገነዘቡ።
በቆዳ ዘርፍ 25 ሰራተኞች በቂ ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ በኬሬዢ ስም የቆዳ ውጤቶች ማምረቻ ድርጅት ከፈቱ። አሁን ላይም ድርጅቱ በዘመናዊ መልክ ጥራታቸውን የጠበቁ የግመል ቆዳ እና የከብት ቆዳዎችን ከፋብሪካዎች በመረከብ በዲዛይናቸው በዓለም ላይ ተወዳዳሪ የሆኑ ምርቶችን እያዘጋጀ ይገኛል። አንድ የቆዳ ጃኬት በ200 የአሜሪካን ዶላር ለተለያዩ የአውሮፓ እና አሜሪካ አገራት ያቀርባሉ። ቦርሳዎችን እና የተለያዩ የቆዳ ምርቶችንም በመላክ ለሀገር የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ላይ ናቸው። አይነ ግቡ በሆኑ አዘገጃጀቶች ያማሩ ምርቶችንም ይዘው በቅርቡ አሜሪካ ቬጋስ በሚካሄድ የቆዳ ፋሽን ትርኢት ላይ የኢትዮጵያን ምርቶች ለማስተዋወቅ ደፋ ቀና እያሉ ይገኛል።
የዘላለም ቱር፣ ጉዞና መኪና ኪራይ ድርጅታቸው በበኩሉ፤ የተሽከርካሪዎቹን ቁጥር 10 በማድረስ እና በየወሩ እስከ አርባ ተሽከርካሪዎችን ከሰዎች ላይ በመቀበል ስራውን ያከናውናል። ወጣቱ ባለሃብት አሁን በአጠቃላይ 37 ሰራተኞች አሏቸው። በመስቀል አደባባይ፣ ካሳንቺስ፣ ቦሌ እና ብሔራዊ አካባቢ በከፈቷቸው ቢሮዎቻቸው ንግዳቸውን እያከናወኑ ይገኛል። በቅርቡም ተጨማሪ ቢሮዎችን በመክፈት በዋናነት ደግሞ ከአጋሮች ጋር በመስራት የአገር ውስጥ ገበያውንም ለማዳረስ እየሰሩ ነው። ከምርት እና አገልግሎት ስራዎቻቸው በተጨማሪ በማህበረሰብ አቀፍ ስራዎች መሳተፍ የሚወዱት አቶ ዘላለም፤ ቤተመንግስት፣ ብሔራዊ ቴያትር፣ ስታዲየም እና ሌሎች አካባቢዎች ላይ ከ500 ሺ ብር በላይ በማውጣት ባከናወኗቸው የመናፈሻ ግንባታዎች ይታወቃሉ።
እራስንና ሀገርን የመጥቀም አላማ ይዘው የሚሰሩት አቶ ዘለላም፤ 500 ካሬ ቦታ ገዝተው ከመሬት በላይ ባለ አምስት ወለል ዘመናዊ የቆዳ ኢንዱስትሪ ወርክሾፕ እና ማሰልጠኛ በመገንባት ላይ ናቸው። ይበል የሚያሰኘው ስኬታቸውን በማሳደግ የኢትዮጵያን የቆዳ ምርቶች በይበልጥ ለማሳደግ ወጥነዋል። እንደ እርሳቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ከቱሪዝሙ ጀምሮ እስከ በርካታ የተፈጥሮ ሃብቶችን በመጠቀም ማደግ ይቻላል።
“እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን በሚል አሰተሳሰብ ወጣቱ በመወጠሩ ኢትዮጵያን ብሎም እራሱን ወደኋላ መጎተቱን መተው አለበት። ሰላም እና መዋደድ ተፈጥሮ በጥረት መስራት ከተቻለ እራስን ብቻ ሳይሆን ለሀገር የሚበጅም ስራ መስራት ይቻላል፤” የሚለው ደግሞ ምክራቸው ነው። ቸር እንሰንብት!!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሀምሌ 20/2011
ጌትነት ተስፋማርያም