ሆሳዕና ተወልዶ ያደገው መኮንን ዋለ በትምህርቱ ከአምስተኛ ከፍል በላይ አልዘለለም። ሁሌም ግን ራሱን ለመለወጥ የተለየ ፍላጎት ቢኖረውም፣ሁኔታዎች እንዳሰበው አልሆን ይሉታል፤ አሁንም አርቆ ማሰብ ይጀምራል፤ ተቀምጦ ከመዋል ሰርቶ ማደር እንደሚበልጥ ገባው። ይህን ሀሳቡን ለመፈጸምም ካለበት አካባቢ ወጣ ማለትን ይመርጣል፤ ቀኑን ማመቻቸትና ጓዙን ማመቻችትም ይይዛል።
አሁን መኮንን ሆሳዕናን ትቶ ሊሄድ ግድ ሆኗል። ይህን ለማድረግ ደጋግሞ ማሰቡም ውሳኔውን አፋጠነው። የሚቀረው ቢኖር ወዳሰበው ስፍራ መሄድ ብቻ ነው። ምርጫው እንደሌሎቹ የአገሩ ልጆች ወደ አዲስአበባ ተሻግሮ ሰርቶ መመለስ ሆኗል። አዲስአበባ ለብዙዎች መልካም አንደሆነች ሰምቷል። እሱንም እንደማታሳፍረው እርግጠኛ ሆነ።
መኮንን ይህን እምነቱን ይዞ ካሰበበት ሲደርስም ሁኔታዎች አልከፉበትም። ያገኛቸው ሰዎች ሁሉ መልካም ሆኑለት፤ ሰፈር መንደሩን ወደደው፤ መውጫ መግቢያውን ለመደው።
የህይወት ጅማሬውን በቀን ስራ አድርጎ ኑሮን ማጣጣም ሲጀምር ብዙዎቹን አወቀ፤ እነሱም ከሌሎች አገናኙት።
አሁን መኮንንና አዲስአበባ ይበልጥ ተዋውቀዋል። የከተማውን ውጣ ውረድና የኑሮን ፈታኝ መንገድ የለየው ወጣቱ፣ ለራሱ የሚበጀውን፣ ለሌሎችም የሚጠቅመውን ለይቷል።
መኮንን ኑሮውን ልደታ ሰፈር ከመሰረተ ጀምሮ ከሚያውቃቸው ባልንጀሮቹ ጋር አብዛኛውን ጊዜውን አብሮ ያሳልፋል። ይህ ቅርበቱ የፈጠረለት አጋጣሚም ያቋረጠውን ትምህርት አንዲቀጥል ለሚያስችል ዕድል አበቃው።
አንድ ድርጅት ውስጥ መቀጠሩም ለወር ደሞዝተኛነት አደረሰው፤ ትምህርቱንም መለስ ብሎ እንዲያስብ አደረገው። ውሎ ሳያድርም ደብተሩን አንስቶ ያቋረጠውን ትምህርት ቀጠለ።
በዚህ ተስፋው ግን ብዙም መቀጠል አልቻለም። ጥቂት ጊዜ የዘለቀው የመኮንን የስራና ትምህርት ቆይታ ባጋጠመው ከሰዎች ያለመግባባት ችግር ሊቋረጥ ግድ ሆነ። ይህን ተከትሎም ራሱን ለማቆየት በሌሎች አማራጭ ስራዎች ሲሯሯጥ ቆየ።
ከትንሽ ጊዜ ቆይታ በኋላ ደግሞ መልካም የሚባል ህይወት ውስጥ ገባ። የተቀጠረበት አዲስ ፋብሪካ ማደሪያውን ጭምር አመቻችቶ ኑሮውን አቀለለት። መኮንን ለጊዜው እፎይታ ተሰማው። አሁንም ግን ነገሮች እንደታሰበው ሆነው አልዘለቁም፤ ከአሰሪዎቹ ጋር ይጋጫል፤ ስራውንም ለመተው ይገደዳል።
መኮንን እንደገና ለጥቂት ጊዚያት ወደቀን ስራ ይመለሳል። ከአንድ ግለሰብ ቤት ለማደሪያው በቀን ሂሳብ እየከፈለም ቀናትን በድካም ተሻገረ። ውሎ አድሮ ደግሞ ከባለሙያዎች ቀረበ። ይህ ቅርበቱም ከብረታብረት ስራ ጋር አላመደው። የሚሆነውን ሁሉ በአትኩሮት እያየ ሙያውን ማወቁም ወደ ስራው እንዲጠጋ ሰበብ ፈጠረለት።
እያደርም የተመሰገነ የብረታ ብረት ባለሙያ ወጣው። በቀላሉ ደንበኞችን እየሳበም ገበያን ማግኘት ቻለ። ይህ ምቹ ሁኔታ አሁንም ያቋረጠውን ትምህርት መልሶ እንዲቀጥል አስቻለው።
አሁን መኮንን ተረጋግቷል። ከትናንትናው በተሻለም ጥሩ የሚባሉ ባልንጀሮች አፍርቶ ውሎውን አሳምሯል። አጃቢዎቹ በዝተውም በግርግር መሀል ይውላል። የሚሰሩና የሚቦዝኑ፣ የሚያወሩና የሚሯሯጡ፤ አመላቸውን ለሱስ፣ እጃቸውን ለልመና የሚዘረጉ ሁሉ በዙሪያው መዋል ጀመሩ።
ከባልንጀሮቹ መሀል አንደኛው ስራ ያሉትን ጉዳይ ማየትን አይሻም። ቀኑን ሙሉ ተጎልቶ ወጪ ወራጁን በልመና ሲያታክት ይውላል። አብሮት የኖረው የሱስ አመሉ ከብዙዎቹ ፊት ያደረሰው ዘነበ የተባለው ይህ ባልንጀራው፣ አብዛኞቹ ጓደኞቹም በሁኔታው የሚበሽቁበት ወጣት ነው።
ዘነበ ዘወትር ከመኮንን ስር ጠፍቶ አያውቅም። አጠገቡ የመዋል ሚስጥሩ ደግሞ ሙያ ለመማር አልያም ስራ ለማገዝ አይደለም። የእሱ ዋንኛ ዓላማ ለዕለት ሱሱና ውሎው የሚያስፈልገውን ገንዘብ ማግኘት ብቻ ነው።
የዘነበን ፍላጎት የሚያውቀው መኮንን የጠየቀውን ሁሉ ነፍጎት አያውቅም። ለ ሲ ጋ ራ ው ም ፣ ለ መ ጠ ጡ ም ፣ ለ ጫ ቱ ም የአቅሙን ያህል ይሰጠዋል። የእርሱን ድርጊት የሚያስተውሉ ሌሎች ግን ሃሳቡን ተቃውመው ልማዱን ይኮንኑታል።
የዘወትር ድርጊቱን ከአጉል ችሮታ የሚቆጥሩት የቅርብ ባልንጀሮቹ ‹‹ዘነበ ሊሰራ እንጂ ለምኖ ሊያድርና በሱስ ሊጠመድ አይገባም›› ሲሉ ሁሌም ይቃወማሉ። መኮንን ወቀሳው ትክክል መሆኑን ቢያውቅም፣ በዘነበ ላይ ፈጥኖ መወሰን ግን አልቻለም። እያደር ግን ወቀሳው ትክክል መሆኑን እያመነበት መጣ። ቀስ በቀስም ‹‹አጉል›› የተባለውን ልግስናውን ትቶ እጁን መሰብሰብ ጀመረ።
ዘነበ ከመኮንን የሚሰጠው የገንዘብ ልግስና ድንገት በተቋረጠ ጊዜ ከልብ ተበሳጨ፤ ድርጊቱን ከንቀት ቆጥሮም ጥርሱን መንከስና መናደድ ያዘ። ሁኔታውን ያስተዋሉ ሌሎቹ የመኮንን ባልንጀሮች የእስከዛሬውን ቆይታ አስታወሰው መኮንን በድርጊቱ እንዲቆጭ አደረጉት። ዘነበም ይህን ባወቀ ጊዜ ተበሳጭቶ በግልምጫውና አሽሙሩ ቀጠለበት።
የሁለቱን መቀያየም የተመለከቱ አንዳንድ ባልንጀሮቻቸው ከመሀል ገብተው ጉዳዩን ለማርገብ ሞከሩ። ሁለቱን ለማስታረቅ ያደረጉት ሙከራም ለጊዜው ተሳክቶ ከአንገት በላይ ሰላም መባባል ጀመሩ።
ዘነበም ሁኔታዎች ወደ ቀድሞው የሚመለሱ መስሎት ጥቂት ቀናትን በተስፋ ጠበቀ። በገንዘብ እርጥባኑ በኩል የመጣ ለውጥ የለምና አሁንም በንዴት ጦፈ።
አሁን በሁለቱ መሀል የተጀመረው ቅራኔ ተባብሷል። መኮንን ስራውን እንደቀድሞው ቢያያዘውም፣ ዘነበ ግን በቂምና ጥላቻ ዕንቅልፍ ካጣ ሰንብቷል። ከመንገድ ዳር ተቀምጦ ወጪ ወራጁን ሲቃኝ የሚውለው ስራ ፈቱ ወጣት፣ ቂምን በልቡ እንዳዘለ ከተቀመጠበት ውሎ ያመሻል።
ህዳር 3 ቀን 2005 ዓ.ም
በሰፈሩ ከተጣለው ሰፊ የሰርግ ድንኳን የሚሰማው ዘፈን ማርፈጃውንም እንደደመቀ ቀጥሏል። ጥሪው ከደረሳቸው እንግዶች ባላነሰ በዙሪያው ከበው የሚታዩት የሰፈሩ ልጆች የፈለጉትን ያገኙ አይመስልም። አሁንም ከወዲያ ወዲህ ማለታቸውን ይዘዋል።
ለሰርጉ ከተጠሩት እንግዶች መሀል መኮንንና ጥቂት ጓደኞቹ ድንኳኑን ከበው ቆመዋል። ሙሽራው በታሰበው ሰአት ባለመድረሱ ወጣ ብለው መጠበቅ ፈልገዋል።
በተቃራኒው ደግሞ ዘነበና ሌሎች ጓደኞቹ በአንድ ስፍራ ሆነው የድግሱን ምግብ ይጠብቃሉ። ይህ ከመሆኑ በፊት በደንብ መጠጣት የፈለገው ዘነበ ግን ደጋሾቹ አስበው እስኪሰጡት መታገስ አልቻለም። አብረውት ከነበሩት መሀል አንዱን ጠርቶ መጠጡን ከውስጥ ይዞለት እንዲመጣ ማሰገደድ ይጀምራል።
መጠጡን እንዲያመጣ የተላከውና ዘነበ ፈጽሞ መግባባት አልቻሉም። ጥያቄውን ከትእዛዝ የቆጠረው ትንሽ ልጅ በእምቢታ ጸንቶ ‹‹አሻፈረኝ›› ማለት ጀመረ። ይህን ያስተዋለው ዘነበ ብሽቀት ተናነቀው። ድርጊቱን ከንቀት ቆጥሮም ልጁን ክፉኛ መደብደብ ያዘ። እጁን ጠምዝዞና ከመሬት ጥሎም በቦክስ እያጣደፈ አንገላታው።
ወዲያው ጩኸትና ግርግሩን የሰሙ ሰዎች ሮጠው ደረሱ። ድርጊቱን ለማስቆምም ከመሀል ገብተው ገላገሉ። ይህን ካደረጉት መሀል አንዱ መኮንን ነበር። እሱ ከመገላገል አልፎ የቀድሞ ባልንጀራውን ሊገስፅ ሞከረ። ሁኔታውን አይቶም የድርጊቱን ተገቢ አለመሆን ደጋግሞ ነገረው። ዘነበ የእሱን ምክርና ግሳጼ ሲሰማ ይበልጥ በንዴት ጋየ። የትናንቱን ቅያሜም አስታውሶ ጸያፍ ስድቦችን ያወርድበት ጀመር።
ጉዳዩን በትዕግስት ለማለፍ የሞከረው መኮንን በዝምታ ተውጦ ያለውን ሁሉ አዳመጠው። ከድንገቴው ቦክስና እርግጫ ግን በቀላሉ ማምለጥ አልቻለም። በዘነበ እጆች ተገፍትሮ ከቆመ መኪና ጋር ሲጋጭ ጉዳቱ የከፋ ሆነ። ከዚህ በኋላ በሁለቱ መሀል ውዝግብና ድብድቡ ቀጠለ። ማንነቱን የሚያውቀው መኮንንም ዘነበን ‹‹ጠጃም›› ሲል ደጋግሞ ሰደበው።
መኮንን ከዘነበ ጋር ከተገላገለ በኋላ የደማውን አፉን እያሻሸ ከቤቱ ደረሰ። ቀድሞ በሆነው ሁሉ ንዴት ገብቶታል። ይህን እያሰበ ሳለ ድንገት የባልና ሚስት ጎረቤቶቹን ጭቅጭቅ ሰማ።
ሁሌም ቢሆን የእነሱን ጠብና ውዝግብ ተላምዶታል። የዛሬው ከወትሮው ቢለይበት ግን ከቤታቸው ዘለቀ። ባልና ሚስቱ በየራሳቸው ቢላዋና፣ ዘነዘና ይዘው ለፍልሚያው ሲዘጋጁ አገኛቸው። ከመሀል ገብቶ ከገላገለ በኋላ ከሚስት እጅ የነበረውን ቢላዋ ተቀበላት።
ይህን ማድረጉ ነገር ለማብረድ በሚል ነበር። በእጁ ላይ ቢላዋው ሲቆይ ግን ውስጡ ሌላ ነገር አሰበ። ወዲያው ስለቱን ጨብጦ በጥድፊያ ተመልሶ ወጣ። አሁን ዘነበን መበቀል እንዳለበት እየገባው ነው። ደግ በሰራለት በአደባባይ አዋርዶታልና ጥቃት ተሰምቶታል።
በንዴት እንደጋለ ካሰበው ሲደርስ ዘነበን በርቀት አየው። እሱም ቢሆን ጠበኛውን እየፈለገ ነው። ከወዲያ ወዲህ እያለ ጥርሱን ይነክሳል፣ እጁን በእጁ እየመታም በዓይኖቹ አሻግሮ ይቃኛል።
መኮንን ጠጋ ብሎ ሊፋለመው ፈለገ። ይህን ከማድረጉ በፊት ግን ዘነበ ከበስተኋላው ገጀራ ሸሽጎ መያዙን አስተዋለ። ድንጋጤው ቢያይልም በድፍረት ተንድርድሮ ቀረበው። ሁኔታውን ያየው ዘነበም ገጀራውን በፊቱ እያወዛወዘ ሊያስፈራራው ሞከረ።
ፊት ለፊት የተፋጠጡት ባልንጀሮች ሀይላቸው ጨምሮ ለገላይ አዳግተዋል። በሁለቱም እጆች የሚታዩት መሳሪያዎች አደገኛነትም ብዙዎች እንዲፈሩ አረገ። ያም ሆኖ ግን በትንቅንቅ መታገላቸውን አላቆሙም። ሁለቱም ቀድሞ ላለመውደቅ መፍጨርጨር ይዘዋል።
በድንገት ግን ዘነበ ከመሬት መውደቁ ታየ። በዚህ አፍታም የመኮንን እጆች ቢላዋውን ሰንዝረው ከአካሉ አድርሰውት ነበር። ከጎኑ የተሻጠው ስል ቢላዋ አሁንም ሰራ አልፈታም። በመኮንን እጆች አየታገዘ ደጋግሞ በዘነበ አካል ላይ ተመሰገ።
ይህን ያዩ የአካባቢው ወጣቶች ሮጠው ሲደርሱ ተጎጂው እየተንፈራገጠ ነበር። ጥቂት ቆይቶ ደግሞ እስትንፋሱ ቀጥ አለች። የጊዜው መጨለምና የግርግሩ ማየል የረዳው መኮንን ከአካባቢው ፈጥኖ ለመሰወር ጊዜ አልፈጀበትም።
ከልደታ በጎላ ሚካኤል ወስጡን አቋርጦ አወቶቡስ ተራ የደረሰው ገስጋሽ፣ አዳሩን ከአንድ ተራ አልጋ ቤት አደረገ። ሌሊቱን በጭንቀት ካሳለፈበት የ‹‹ኬሻ በጠረባ›› ማረፊያ ማለዳውን ተነሰቶም ወደ ወልቂጤ ጉዞ ጀመረ።
መኮንን በመንገዱ ሁሉ ያደረገውን እያሰበ መጨነቁ አልቀረም። ያቺን ደቂቃ መታገስ አቅቶት ለዚህ ክፉ አጋጣሚ መዳረጉም ውስጡን ዘልቆ ያስጨንቀው ይዟል። በታላቅ ስጋትና መሸማቀቅ ወልቂጤ ሲደርስ ውስጡ በፍርሀት እንደራደ ነበር። የሚያዩት ሁሉ የሰራውን ያወቁበት አስኪመስለውም በጥርጣሬ ሲገላመጥ ቆየ።
መኮንን አሁን ራሱን ለማረጋጋት እየሞከረ ነው። ለማንኛውም ሲል የእጅ ስልኩን ክፍት አደረገው። ስልኩ ግን እስካሁን ምንም ወሬ አላደረሰውም። ምሽት ላይ ድንገት በጮኸው ሞባይል የሰማው መልዕክት ግን ርቆ የመውጣት ውሳኔውን ሊያስለውጠው ግድ አለ።
ህይወት ባጠፋበት ምሽት ቀድመው ጠብ ላይ የነበሩት ባልና ሚስት በዘነበ ሞት በመጠርጠራቸውና የድምጽ የለሽ መሳሪያው የመገኛ ምንጭ በመሆናቸው በህግ ቁጥጥር ስር ውለዋል። ይህ የሆነው ደግሞ እራሱ በፈጸመው ድርጊት መሆኑን ልቦናው ያውቀዋል።
መኮንን የእነሱን መታሰር ካወቀ ወዲህ ይበልጥ ሰላሙን አጣ። ከዚህ በኋላ መሸሹ እንደማያዛልቅ ሲረዳም ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ በፈቃደኝነት እጁን ሰጠ። ተፈላጊው በፖሊስ ኮሚሽኑ ደርሶ የሆነውን ሲያስረዳ ህይወት በማጥፋቱ የደረሰበትን ጸጸት አልደበቀም።
የፖሊስ ምርመራ
ተጠርጣሪው እጁን ለህግ ከሰጠበት ዕለት አንስቶ ምርመራውን የጀመረው ፖሊስ ግድያውን ስለመፈጸሙ የሚያስረዱ ማሳያዎችን በማስረጃዎች አስደግፎ አጠናከረ። አሁን በፖሊስ መዝገብ ቁጥር 533/05 ተያይዞ በዋና ሳጂን ግርማ በቀለ መርማሪነት ወንጀሉ በአግባቡ ተጣርቶ ተጠናቋል።
የህከምና ማሰረጃዎችን ጨምሮ የአይን ምስክሮችን መረጃና የቴክኒክ ሂደቶችን በማያያዝም ተጠርጣሪውን ለህግ የማቅረቡ ሂደት ቀጥሏል። ተገቢ ማስረጃዎችን በተገቢው ሁኔታ የደረሰው ዓቃቤ ህግም በግለሰቡ ላይ ክስ መስርቶ ለውሳኔ ለማቅረብ ዝግጅቱን አጠናቋል።
ውሳኔ
የካቲት 3 ቀን 2005 ዓ.ም
ከፖሊስና ከአቃቤ ህግ የምርመራ መዝገብ ተጠናቅሮ የደረሰውን ማስረጃ በአግባቡ የመረመረው የልደታው ከፍተኛ ፍርድ ቤት 3ኛ የወንጀል ችሎት የተከሳሽን የወንጀል ድርጊት በአግባቡ መርምሮ ለመጨረሻው ውሳኔ ተሰይሟል።
ተከሳሸ የፈፀመውን ድርጊት በማመኑና መከላከል ባለመቻሉ በህግ ጥፋተኛነቱ ተረጋግጧል። ፍርድቤቱ መረጃዎችን ከህግ ጋር አገናዝቦ ባስተላለፈው ውሳኔም ‹‹ተከሳሽ መኮንን ዋለ ሆነ ብሎ በፈጸመው ከባድ የሰው መግደል ወንጀል በአስራ አራት ዓመት ጽኑ እስራት ይቀጣልኝ›› ሲል በይኗል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሀምሌ 20/2011
መልካምስራ አፈወርቅ