
ክረምቱ መግባቱን ተከትሎ በተለይ በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት የሚወርደው ዶፍ ዝናብ ታክሲና አውቶቡስ ለመጠበቅ በተሰለፈው በመዲናዋ ነዋሪ ላይ ይዘንባል። በረጅሙ ሰልፍ ቆሞ እንደጸበል በዝናብ ከሚጠመቀው ሰው መካከል ሴቶቹ በቦርሳቸው ዣንጥላ ስለሚይዙ በያዙት ቄንጠኛ ዣንጥላ ምንም እንኳን መላ አካላቸውን ከሚወርደው ዶፍ ዝናብ መታደግ ባይችሉም ከአንገታቸው በላይ ሲጠለሉ፤ ወንዶች ግን ዝናቡ በላያቸው ላይ ያርፋል።
እንኳንስ መስከረም ሲጠባ የሚያልፈውን የሁለት ወር ዝናብ ቀርቶ የኑሮ ውድነት ዶፍን ለዓመታት የተሸከመው የከተሜው ነዋሪ በኑሮ ውድነትና በዝናብ መደብደብ ልማዱ ቢሆንም፤ ቢያንስ ክረምቱ ከገባ ጀምሮ የጧቱ ቁርና የዋለ ዝናብ የሚፈራረቅበትን የመዲናዋን ነዋሪ የትራንስፖርት ችግር ከስር መሰረቱ መፍታት ባይችል እንኳን በሥራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓት ላይ የትራንስፖርት እጥረት እንዳይኖር የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሲያበረክቱ የነበሩትና ውር ውር ሲሉ የነበሩት ባለቢጫ ቀለሞቹ አልያንስ አውቶቡሶች የት ገቡ? የሚል ጥያቄ በአዕምሮዬ አጫረብኝ።
በአእምሮዬ የተፈጠረው ጥያቄ ጥያቄን ወለደና የመዲናዋ ኗሪስ ባገኝው የትራንስፖርት አማራጭ ተዛዝሎም ቢሆን ከቤቱ ሳይገባ ጎዳና ላይ ያደረ የለም። ለመሆኑ በሥራ ላይ የነበሩት የአሊያንስ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ሠራተኞችስ “ምን ውጧቸው ይሆን?” ብዬ ለራሴ ጠየቅሁኝ።
የድርጅቱ ይሰሩ የነበሩትን ሰዎች ለማግኘት ባደረግሁት ጥረት አቶ ቅዱስ አየለን በስልክ አገኘኋቸው። እርሳቸውም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሎጂስ ቲክ ማኔጅመንት በ2006 ዓ.ም በተመረቁ ማግስት ሶማ ኮንስትራክሽን በሚባል ድርጅት ፕሮጀክት ላይ በግዢ ሠራተኝነት ተቀጥረው ይሰሩ ነበር።
የድርጅቱ የፕሮጀክት ሥራ ሲያልቅና ሠራተ ኞቹን ሲያሰናብት ከተሰናበቱ ሠራተኞች መካከል አቶ ቅዱስ አንዱ ነበሩ። በዚህ መሀል የአሊያንስ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ባወጣው የሥራ ማስታወቂያ ተወዳድረው በማለፋቸው በድርጅቱ የግዢ ሠራተኛ ሆነው በቋሚነት ተቀጠሩ።
እርሳቸውም በድርጅቱ ስድስት ሺህ ብር የተጣራ የወር ደመወዝ ያገኙ እንደነበር ጠቁመው፤ ጥር 28/ 2011 ዓ.ም በድንገት በሥራ ላይ እያሉ የድርጅቱ አውቶቡሶች የባንክ እገዳ ወጥቶባቸው እየታደኑ መሆኑን ከሌሎች ሰዎች መረጃ እንደሰሙ ይናገራሉ።
ከዚህ ቀን ጀምሮ ድርጅቱ ምንም ገቢ ስላልነበረው ለሠራተኛው የአንድ ወር ደመወዝ ከየትም ፈልጎ በመስጠት እንዳሰናበተ የሚናገሩት አቶ ቅዱስ፤ በወቅቱ እርሳቸው ከሥራ ሲሰናበቱ ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት፤ እንዲሁም ከእርሳቸው ጋር የሚያሳድጉት አንድ ልጅ እንዳለ ይናገራሉ።
አቶ ቅዱስ እንደሚሉት፤ ሥራ ከፈቱ አምስት ወር አስቆጥረዋል። በአገሪቱ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ሥራ ፈልጎ ለማግኘት ከብዷቸዋል። ባለቤታቸውም ሥራ ስለሌላቸው የእርሳቸውን እጅ አይተው ነው የሚያድሩት፤ በዚህ የኑሮ ውድነት ያለምንም ገቢ ቤተሰብ ይዘው አውላላ ሜዳ ላይ መውደቃቸውን ይናገራሉ።
አክለውም፤ ከቤት የሚላስ የሚቀመስ ሲጠፋ እና ሥራ ተዘዋውረው ለመፈለግ መንቀሳቀሻ ሲያጡ፤ ለኮንዶሚኒም ቤት የቆጠቡትን ገንዘብ አውጥተው እየተቃመሱ እያደሩ እንደሆን ተናግረዋል።
“አሁን ላይ ለኮንዶሚኒየም ቤት የቆጠብኋት ገንዘብም እያለቀች ነው” የሚሉት አቶ ቅዱስ፤ ቤተሰቡ ነገ ላይ ምን እንበላ ይሆን? ለቤት ኪራይስ ምን እንከፍል ይሆን? በሚል ጭንቀት ውስጥ ናቸው። ባለቤታቸውም ሁላችንም እዚህ በርሃብና በጭንቀት ከምንታመስ ወደ ክፍለ አገር ቤተሰቧቼ ዘንድ ካልሄድኩ እያለች ትገኛለች ብለዋል። በአጠቃላይ ትዳራቸው ሊፈርስና ሜዳ ላይ ሊበተኑ ጫፍ መድረሳቸውን የሚናገሩት እኝህ ሰው፤ የድርጅቱን ሥራ መጀመር በጉጉት እየተጠባበቁ ይገኛሉ።
የአሊያንስ ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር አዲል አብ ዴላ በበኩላቸው፤ ድርጅቱ በሁለት ሺህ 500 የአክሲዮን ባለድርሻዎች የተቋቋመ ሲሆን፤ በ2005 ዓ.ም መጨረሻ ገደማ በ25 አውቶቡሶች በአዲስ አበባ ሥራውን እንደጀመረ ይናገራሉ።
ድርጅቱ ለመዲናዋ ነዋሪ የትራንስፖርት አገልግሎቱን እየሰጠ እያለ በ2007 ዓም የትራንስፖርት ሚኒስቴር አንድ መመሪያ አውጥቶ ነበር የሚሉት ዶክተሩ፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ለሚሳተፉ ማህበራት የቀረጥ ነፃ መብት፣ የባንክ ብድር፤ እንዲሁም ለአው ቶብሶች የማቆሚያ፣ የማደሪያ፣ የመጠገኛ (የጋራዥ) እና የነዳጅ ማደያ ቦታዎችን እንደሚያቀርብ ቃል በመግባቱ፤ 30 በመቶ ከአክሲዮን ባለድርሻዎች 70 በመቶ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብድር በመውሰድ አክሲዮን ማህበሩ ተጨማሪ መቶ አውቶብሶችን ገዛ።
እነዚህን አውቶቡሶች ገዝቶ ሥራ ላይ አሰማርቶ እየሰራ ባለበት ወቅት ከተማ አስተዳደሩ ከላይ የተጠቀሱትን መሰረተ ልማቶች ባለማሟላቱ ድርጅቱ በርካታ ችግሮች እንደተጋረጡበት የሚናገሩት ዶክተሩ፤ በኋላ የከተማ አስተዳደሩ ከከተማው ወጣ ብሎ ለገጣፎ አካባቢ መሰረተ ልማት ያልተሟላበት የእርሻ ቦታ ላይ ልቀቁ በሚባሉበት ጊዜ እንደሚለቅቁ በማሳሰብ በጊዜያዊነት የመኪና ማቆሚያ ቦታ እንደሰጣቸው ገልጸዋል።
እርሳቸውም ይሄንን ለመኪና ማቆሚያ በጊዜያዊነት የተሰጣቸውን ቦታ መሰረተ ልማት አሟልቶ የመኪና ማቆሚያ ለማድረግ ከ15 ሚሊዮን ብር ያላነሰ ወጪ ይጠይቃል። ስለዚህ ከቦታው በማንኛውም ሰዓት ላይ እንደሚነሱና ሊሸጥ እንደሚችል ስለተነገራቸው ይሄን ሁሉ ወጪ አውጥተው ቦታውን ለማዘጋጀት እንዳልቻሉ ተናግረዋል።
እንዲሁም፤ አዲስ አበባን በዙሪያዋ ካሉ የኦሮሚያ ከተሞች ጋር አውቶቡሶቹ የማገናኘት ሥራ እንዲሰሩ ለድርጅቱ ኃላፊነት ተሰጥቶት በነዚህ ቦታ እየሰራ ነበር። ነገር ግን በወቅቱ በተለይ ከ2009 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ በአገሪቱ ከፍተኛ የፖለቲካ አለመረጋጋት ስለነበር አውቶቡሶቹ ከአዲስ አበባ ወጥተው ሥራ ለመስራት ተቸግረው ነበር። በዚህ ምክንያት በየቀኑ አውቶቡሶቹ ሥራ ከሚሰሩበት ይልቅ የማይሰሩበት ጊዜ ይበልጥ ነበር ብለዋል።
በአጠቃላይ ከላይ በተዘረዘሩ ችግሮች ምክንያት ድርጅቱ ከባንክ የተበደረውን እዳ በአግባቡ እንዳይከፍል ተግዳሮት ሆኖበታል ይላሉ ዶክተሩ፤ በወቅቱ ባንኩም በውሉ መሰረት እዳው አልተመለሰልኝም ብሎ ብዙ ጥያቄዎች እያቀረበ ነበር። በድርጅቱ በኩል የነበረውን ነባራዊ ሁኔታ ለማስረዳትና ችግሩን ለማስተካከል የሚቻልበትን መንገድ ድርጅቱ ሞክሯል። እንዲሁም ከባንኩ ጋር ብቻ ሳይሆን ጉዳዩን እስከ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ቢሮ ድረስ በማድረስ ለጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ የአመራር ቦርዱ ጥሮ ነበርም ብለዋል።
በተለይ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ችግሩን በመረዳት ባንኩ ትብብር እንዲያደርግ ግፊት ቢያደርግም፤ ባንኩ መጨረሻ ላይ ገንዘቤን አልከፈላችሁኝም ብሎ አውቶቡሶቹን ከጥር 28 /2011 ዓ.ም ጀምሮ አቁሟቸዋል።
ስለዚህ ከባንኩ ጋር እንዴት እዳውን መክፈል እንዳለብን ተደጋጋሚ ውይይቶችን እያደረግን ነው የሚሉት ዶክተሩ፤ ድርጅቱ ባንኩ የሚጠይቃቸውን ቅድመ ሁኔታዎች በሙሉ እያሟላ ሲሆን፤ ባንኩ ዳግመኛ ጥናት አስጠንተን እንድናመጣ በማዘዙ ደግመን አስጠንተን ሰነዱን አቅርበናል። የባንኩ አመራሮችም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ነው። ስለዚህ ባንኩ ውሳኔውን አስር ቀን ባልሟላ ጊዜ ውስጥ የሚያሳውቀን ይሆናል።
በአጠቃላይ ከባንኩ ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን በማድረግ መግባባት ላይ ስለደረስን ድርጅቱ ከ15 እስከ 20 ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ሥራውን ይጀምራል። በዚህም 400 የሚሆኑ የድርጅቱ ሠራተኞች ወደ ቀድሞ ሥራቸው የሚመለሱ ይሆናል ሲሉ ዶክተር አዲል አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 19/2019
ሶሎሞን በየነ