
አዲስ አበባ፡- በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች እየተነሱ ላሉ የአደረጃጀት ጥያቄዎችን በጥናት ለመመለስ የተቋቋመው አጥኚ ቡድን የጥናት ውጤቱን ከምሁራን ጋር ውይይት እያካሄደበት ነው፡፡
በክልሉ ለተነሱት የአደረጃጀት ጥያቄዎች ሳይንሳዊ ምላሽ ለመስጠት የተቋቋመው አጥኚ ቡድን ጥናቱን መሰረት በማድረግ ከምሁራን ጋር ትናንት ውይይት ያደረገ ሲሆን፤ በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፋሬስ ደሊል ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳሉት፣ ጥናቱ ተገቢነት ያለው ነው፡፡ በክልሉ ለተፈጠረው ችግር መልስ ለመስጠት ጥናት አድርጎ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መፍትሄ ለመፈለግ መሞከሩም ሊበረታታ ይገባል ብለዋል፡፡
ሆኖም በጥናቱ አንፃራዊ ሰላም ያለባቸው ናቸው በሚል ያልተካተቱ አካባቢዎች መኖ ራቸው የጥናቱ ትልቅ ክፍተት መሆኑን የጠቆ ሙት ዶክተር ፋሬስ ፤ በጥናት ቡድኑ የቀረበው የመፍትሄ ሃሳብም መልካም መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዶክተር ፋሬስ ከቀረቡት የመፍትሄ ሃሳቦች ውስጥ የትኛው ይሻላል የሚለውን ለመወሰን እንደሚከብዳቸው ጠቁመው፣ በዋናነት ግን በህዝብ ይሁንታና ፍላጎት እንዲሁም ህጋዊ መንገድን ተከትሎ መሄድ ያስፈልጋል ሲሉ ገልፀዋል፡፡ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት ገ/ማርያም ጥናቱ የሲዳማ ዞንና የሀዋሳ ከተማን አለማሳተፉ ቅር እንዳሰኛቸው ጠቁመዋል፡፡
ዶክተር አስራት የተነሱ ጥያቄዎችን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ህገ መንግሥታዊ መሰረት ላይ መቆም ይገባል ካሉ በኋላ፤ ህገመንግሥቱ ዘጠኝ ክልሎች አሉ እያለ የክልል እንሁን ጥያቄን መመለስ ከባድ ነው። ጥያቄዎቹን ለመመለስም ህገመንግሥቱ ቀድሞ መስተካከል አለበት የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል።
የጥናት ቡድኑ ባደረገው ገለፃ ላይ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጡ የደቡብ ክልል ተወላጅ ምሁራን እንዲሁም በክልሉ ያሉ ምሁራን የታደሙ ሲሆን፤ የክልል እንሁን ጥያቄዎችም በሰከነ መንፈስ መታየት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሀምሌ 19/2019
ዳግማዊት ግርማ