የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በመቐለ ሰባእንደርታ ሻምፒዮናነት ነበር ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም የተጠናቀቀው። ሊጉ ከወርሃ ጥቅምት 17 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት ዘጠኝ ወራት ቆይታን አድርጓል። ፕሪሚየር ሊጉ አዲስ የተቀላቀለውን ክለብ ሻምፒዮና አድርጎ ከመጠናቀቁ በተጓዳኝ በርካታ ትዕይንቶችን አስተናግዶ ነበር ያለፈው። ከበርካቶቹ ትዕይንቶች ጎልቶ የወጣውና ሊታረም የሚገባው ስፖርታዊ ጨዋነት የተመለከተው ሆኗል።
ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፈተና እየሆነ የመጣው የስፖርታዊ ጨዋነት ጉዳይ ዘንድሮ ፈር በለቀቀ መልኩ በስፋት ታይቷል። የችግሩ ስፋትና ስጋት ምን መልክ እንደነበረው ለቀጣይ ማስተማሪያ ይሆን ዘንድ መለስ ብለን ለመቃኘት ወደድን። በዚህ መሰረትም በዛሬው የስፖርት ገጻችን «ነበር» በሚል ርዕስ ከስፖርታዊ ጨዋነት ጋር ተያይዞ የውድድር አመቱ የነበረው አነጋጋሪና አሳዛኝ ገጽታን እንዲህ ታዝበነዋል።
ጅምሩ ስጋት
የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በወርሃ ጥቅምት 17 በተለያዩ ክልል ከተሞች በተደረጉ ጨዋታዎች ነበር መጀመሩ የተበሰረው። የሊጉ መጀመር በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ሁለት አይነት ስሜትን ፈጠሮ ነበር ማለት ያስደፍራል። በአንድ ጎኑ ደስታን በሌላው ጎኑ ደግሞ ስጋትን። ስፖርቱ ቀዳሚ የመዝናኛ አማራጭ እንደመሆኑ ደስታን ሲፈጥር፤ ከጨዋነት ደንብ መራቁ ትዝ ሲለው ደግሞ ስጋት ፈጥሮበታል።
የስፖርት ቤተሰቡ ለዚህም ማነጣጠሪያ ያደረገው የ2010 ዓ.ም የውድድር ዓመትን ነበር። አምና የሊጉ ስፖርታዊ ጨዋነት ገጽታው በእጅጉ አሳፋሪና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎቸ ወደ ፀብ ማዘውተሪያነት የተለወጡበት ነበር። ደጋፊ በሜዳው ደብዳቢ፣ ከሜዳው ውጪ ተደብዳቢ የሆነበት ትዕይንትን ሲያስመለክት፣ ዳኞች በቡድን መሪ ሜዳላይ እየተሳደዱ ሲደባደቡ፣ በደጋፊ ስድብ፣ ዛቻና ድብደባን ሲቀበሉ በአደባባይ ያስመለከተ ነበር።
በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ በተከናወነው ፕሪሚየር ሊጉ በችግሩ ሲቃ በጽኑ ሲቃትት ታዝበናል። በተለይ ደግሞ እግር ኳሱ ብሔር ተኮር መልክን የመያዙ ሁኔታ የውድድር ዓመቱን አስከፊ ገጽታን እንዲላበስ አድርገውታል። ከትናንት ጥፋት በተሻገረ ስጋት የተጀመረው ሊጉ የእግር ኳስ ባህሪ ከስታዲየም የተሳደደበት፣ ስፖርት ለሰላም፣ ለአንድነት፣ ለወንድማማችነት ………»ይሉት አለም ዓቀፍ እሳቤ ከየስታዲየሙ እየታደነ ተገድሎ የተቀበረበት ጊዜ ነበር።
ከፍየሏ ሞት በላይ የሆነው ለቅሶ
ክለቦች የማንነት ማግነኛ እና የራስ ኩራት መገለጫ መድረኮች በመሆን ክለብ ተኮር ሳይሆን ብሄር ተኮር ግጭቶችን በበርካታ ስታዲየሞች ተስተውለዋል። ከዳኝነት ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር በዳኞች አንደበት «ኳስን ሳይሆን ብሄርን መዳኘት ነው ያቃተን» እስከመባል ተደርሷል። የብሄራዊ ፌዴሬሽን የሚወስዳቸው የዲሲፕሊን እርምጃዎች የሚቀበል ክለብ ጠፋ። «በብሔሬ ምክንያት ለቅጣት ተዳረኩ» ይሉት ምክንያት ሲቀርቡ ታዘብን።
በሽንፈቱ የሚደፋው አንገት ማንነትን ይዞ ዝቅ ማለትን፣ መብሰልሰልን፣ መቆዘምን ያመጣ ነበር። በእግር ኳሱ ላይ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚሰጡት አጉል ትንታኔዎች፣ ትችቶች፣ በጨዋታ ድልና ሽንፈት የሚንፀባረቁ ስሜቶች ከእግር ኳሱ የመነጩ ናቸው ለማለት አዳጋች ነበሩ። ጩኸቶች ያ አብዲ ኢሌ እንዳለው ‹‹ለቅሶው ከፍየሏ በላይ ነው ሲል በአንድ መድረክ ላይ የተናገራትን አባባል ትዝ የሚያስብል ነበር።
ስፖርቱ ውስጥ ዘው ብሎ የገባው ፖለቲካው የእግር ኳስን ሽንፈት ሆነ ድል በእጅጉ አጋነነው። የደጋፊዎች መከፋትና መደሰት ወደር አልባነት ስንመለከት ይህ አይነቱ ጩኸት ከኳስ በላይ ነበር። አክቲቪስት ነን ባዮች ጭምር እግር ኳሱ ላይ ትንታኔ ሲሰጡ ስንመለከት ደግሞ ስፖርቱ ተጠልፏል ወደሚል ድምዳሜ ያደርሳል። ኳሱ በአየር ተሞልቶ እንደሚንከባለለው ሁሉ፤ ደጋፊው በፖለቲካ አጀንዳዎች ተሞልተው መነሁለላቸውን ለመታዘብ ያስቻለን ነበር። ስፖርቱ ላይ የሚሰነዘሩት አጉራ ዘለል ትችቶች እውነት ከስፖርቱ ስሜት በመነሳት? ወይስ እንደ አባባሉ ጩኸቶቹ ከፍየሏ በላይ ነበርን ? ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት እውነትን መጋፈጥ ያስፈልጋል።
ከሰሜን እስከ ደቡብ የነበረው ሃቅ
የእግር ኳሱን በሰሜን እና በደቡብ ክለቦች መካከል የነበሩትን በርካታ ሁነቶች ዘወር ብለን በማሳያነት መመልከቱ ሃሳብን ያጠናክራል። በመጀመሪያ ወደ ሰሜን በመጓዝ የአማራ ክልልና ትግራይ ክልል ክለቦች እርስ በእርስ በተገናኙባቸው አጋጣሚዎቸ የነበሩ ክስተቶችን እንደማሳያ ብናነሳ ይሄንኑ ምስል ይሰጡናል። በሊጉ 23ኛ ሳምንት በመቐለ ከተማ በሚገኘው ትግራይ አለም ዓቀፍ ስታዲየም በደደቢት እና ፋሲል ከነማ ጨዋታ አካሂደዋል። በዚህ የጨዋታ ክዋኔ ወቅት የነበረው ሁኔታ በሁለቱ ክልል ክለቦች መካከል ያለውን ውጥረት በግልጽ ያስመለከተ ነበር።
በተመሳሳይ በባህር ዳር ስታዲየም ስሁል ሽረ ከባሕር ዳር ከተማ በነበረው ጨዋታ የነበረውን ሁኔታ በእጅጉ የሚያስተዛዝብና እግር ኳሱ በብሄር ጥላ ውስጥ እየቧቸረ የመሆኑን እውነታ አመላክቶ አልፏል። ስፖርቱ በብሄርተኝነት ቀንበር ውስጥ የመውደቁን እሳቤ የሚያጠናክርልን ሌላው ክስተት በ30 ኛው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በፋሲል ከነማ እና ስዑል ሽረ ጨዋታ ነው። ለሻምፒዮናነት ከመቐለ ሰባ እንደርታ እኩል እድልን ይዘው ስዑል ሽሬን የገጠሙት ፋሲሎች በደጋፊዎች ከፍተኛ የሆነ ጫና ሲደርስባቸው እንደነበር አስታውቀዋል። ከስዑል ሽረ ደጋፊዎች በኩል የነበረው ጥቃትና ጫና የሻምፒዮናነት እድልን እንዳሳጣቸው በቁጭት በክለቡ ማህበራዊ ገጽ አስታውቀዋል።
ፋሲል ከነማ በዘንድሮውም ሆነ በቀጣዩ የውድድር ዓመት ወደ ትግራይ ክልል ሄዶ እንደማይጫወት እስከ ማስታወቅ ደርሷል። በማሳያነት የቀረቡት እነዚህ ክስተቶችን ስናሰላስል ስፖርቱ በሃገሪቱ ወቅታዊ ፖለቲካ ተጠልፎ መውደቁንና ይሄንኑ ዳና እየተከተለ ስለመሄዱ ያረጋግጥልናል። በሁለቱ ክልሎች መካከል በተለይ ከባለፈው አንድ ዓመት ወዲህ ያለው ውጥረት ስናስብ እውነታውን እናገኘዋለን።
በሁለቱ ክልሎች መካከል በተለይ ከባለፈው አንድ ዓመት ወዲህ ውጥረት መኖሩ ሃቅ ነው። በአመራሮች መካከል ያለው መፋጠጥ የወለደው ውጥረት በስፖርቱ ሳይቀር የተንጸባረቀ ነበር። በዚህም ምክንያት የሁለቱ ክልል ክለቦች ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በገለልተኛ ሜዳ ሲጫወቱ መቆየታቸው። የሁኔታው አሳሳቢነት በዘንድሮው የውድድር ዓመት የተሸጋገረ ሲሆን፤ ክለቦቹ እርስ በእርስ የሚያደረጉትን ጨዋታ በሜዳቸው ያደርጉ ዘንድ መግባባት ለመፍጠር ብዙ ርቀት አስፈልጓል። በብሄራዊ ፌዴሬሽኑ እና በመንግስት በኩል በተሰራው የማቀራረብ ስራ ፖለቲካዊ መፍትሄ በመስጠት በሜዳቸው ጨዋታዎች ማከናወን ችለዋል።
ከሰሜን ወደ ደቡብ ክለቦች ስናቀና በውድድር ዓመቱ የእግር ኳሱ ጉዞ በእጅጉ አሳዛኝና ከስፖርት አውድ ውጪ መሆኑን ያመላክተናል። በክልሉ የሚገኙ የወላይታ ዲቻ፣ ሲዳማ ቡና፣ ሃዋሳና ደቡብ ፖሊስ ደጋፊዎች የስታዲየም ውሎን እናገኛለን። በወላይታ ዲቻ እና የሲዳማ ቡና ደጋፊዎች መካከል የነበሩት መፋጠጦችና ከእግር ኳስ ስሜት በላይ የሆኑ ድርጊቶች በግልጽ ተስተውለዋል። በሃዋሳና ሲዳማ ቡና ደጋፊዎቸ መካከል፣ በደቡብ ፖሊስና በሲዳማ ቡና ደጋፊዎች መካከል የነበሩትን ውጥረቶች በሰሜን ብቻ ሳይሆን በደቡብ ሳይቀር ያለውን ውጥረት ያመላክተናል። ለዚህም በፕሪሚየር ሊጉ በ21ኛ ሳምንት የነበረውን ሁነት ማንሳቱ ለዚህ እንደ ማሳያ ይሆናል።
ሚያዚያ 12 ቀን 2011 ዓ.ም በሐዋሳ ስታዲየም ወላይታ ድቻና ደቡብ ፖሊስ በነበራቸው በዚህ ጨዋታ የሁለቱ ክለብ ደጋፊች ወደ ጸብ ለማምራት የጨዋታውን መጀመር እራሱ አልጠበቁም ነበር። ስፖርታዊ መሰረት ባልነበረው መልኩ ግጭት መፈጠሩ ጨዋታውን ወደ ሌላ ጊዜና በዝግ በአዲስ አበባ ስታዲየም እንዲካሄድ እስከመወሰን ነበር የተደረሰው። በደቡብም እግር ኳሱ መሰረቱን አጥቶ ፖለቲካዊ አጀንዳ ማስፈጸሚያ ሲሆን ታዝበናል።
አሳፋሪው ድርጊት
የ2011 ዓ.ም የፕሪሚየር ሊጉ ጉዞ ከስፖርት አውድ ውጪ በሆነ መልኩ ፖለቲካን የማራመጃ ዋነኛ መሳሪያ ወደመሆን የተሸጋገረ ጭምር እንደነበር ወደ አዲስ አበባ መለስ ብለን እንመልከት። በኘሪምየር ሊጉ 27ኛ ሳምንት በአዲስ አበባ ስታዲየም በተከናወነው የኢትዮጵያ ቡና እና መቐለ ሰባ እንደርታ ጨዋታ የዚሁ ክስተት ባለቤት ነበር። ጨዋታው በብዙ ስጋት ታጅቦ የተጀመረው ስፖርታዊ ጨዋነት በነገሰበት መልኩ በአቻ ውጤት መጠናቀቅ ነበር የቻለው። ከጨዋታው በኃላ የነበረው ሁኔታ ግን በእጅጉ አንገት ያስደፋ ነበር። በተለይ ከመቐለ ሰባ እንደርታ በኩል የነበረው ድርጊት ብዙዎችን አሳዝኗል። ጨዋታው ሲጠናቀቅ የመቐለ ሰባ እንደርታ አሰልጣኝ ገብረመድህን ሃይሌ ተጫዋቾቹን ሰብስቦ ፑሽ አፕ ያሰራበት ሁናቴ በእርግጥም ምን ይሉት ፌዝ ነው።በስፖርታዊ ጨዋነት ነግሶ ቢጠናቀቅም ድርጊቱን ተከትሎ የአዲስ አበባ ስታዲየምን ድባብ ጭምር የረበሸ ሆኖ አልፏል።ከአሰልጣኙ ትዕዛዝ የተሻገረው የተጫዋቾቹ ተግባር በዕርግጥም ከንፈርን መጥጦ ከማለፍ ውጪ ምን ማለት የሚያስችል ነበር? አላያችሁንም እንጂ ያላየነው የለም
እግር ኳስ ከፖለቲካ፣ ከኃይማኖትና ከዘር የፀዳ መሆን እንዳለበት የሚያስረዳው ዓለም አቀፍ መርኅ አለ። በኢትዮጵያ እግር ኳስ የዘንድሮው የውድድር ዓመት የነበረው ገጽታ ከዚህ ፍጹም የራቀ እንደመሆኑ የችግሩ ዳፋ ሃገሪቷን ሊያሳጣትና ሊያስቀጣት እንደሚችል የታሰበ አይመስልም ነበር። ምናልባትም «አላያችሁንም እንጂ ያላየነው የለም» እንዲሉ አበው መቼም በ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አላዩትም እንጂ ስፖርትና ፖለቲካ ፍቅር ሲሰሩ ቆይተዋል።
ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ማህበር ስፖርትና ፖለቲካ ለየቅል እንደሆኑና ፖለቲካው ስፖርቱ ውስጥ ገብቶ ቢገኝ ከባድ ቅጣት እንደሚጣል በህግ ደረጃ አስቀምጦታል። ታዲያ የዘንድሮውን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁኔታ «አላያችሁንም እንጂ ያላየነው የለም» በመሆኑ እንጂ ፊፋ ከባድ ቅጣት ሊያስተላልፍ እንደሚችል ማሰቡ አይከፋም። በ2011 ዓ.ም የውድድር ዘመን የነበረው ገጽታ አሳሳቢነቱ ቤተ መንግስት ድረስ አንኳኩቶ መግባቱ ልብ ይሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ የ2011 ዓ ም የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 24 ቀን 2011 ዓ.ም. ባቀረቡበት ወቅት «በአብዛኛው መንግሥት በሚበጅተው በጀት የሚተዳደሩ ክለቦች፣ ያውም ውጤት ሳይኖራቸውና በስፖርቱ ሌሎች አገሮች የሚያሳዩትን ሙያዊ እንቅስቃሴ ሳያሳዩ ለረብ የለሽ የዘር ፖለቲካ ማቀንቀኛነት ውለዋል። ስፖርቱ ዓለም አቀፋዊ የሆነ መርህና ሙያዊ ዲሲፕሊን ቢኖረውም ያንን ጠብቆ እየሄደ አይደለም፡፡ ስታዲዮሞች በኳስ ቴክኒክና ታክቲክ ያበዱ ታዳጊ ወጣቶች የሚስተዋልባቸው መሆን ተስኗቸዋል» ሲሉ የችግሩ አሳሳቢነት እርሳቸውን ጭምር ያሰጋ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡ ዶክተር አብይ ነገሮች በዚህ ከቀጠሉ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ የበላይ አካል /ፊፋ/ ሳይቀር ዕርምጃዎችን ሊወስድ እንደሚችል ጭምር በመግለጽ ነበር አካሄዱ አለም ዓቀፋዊ መዘዝን ይዞ እንደሚመጣ ያመላከቱት። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቁጭት ንግግር ሆነ በውድድር ዓመቱ የነበረው ገጽታ በብዙ መልኩ አክሳሪና አሳፋሪ የመሆኑን እውነታንም ጭምር በተጨባጭ ያስረዳል።
ለዚህ ነበር በሬዬን ያረድኩት
የአምናው የፕሪምየር ሊግ «ዋንጫ» የት እንደሚገኝ ያውቃሉ? ሲል ሶከር ኢትዮጵያ ያወጣውን ዘገባ ሳስታውስ «ለዚህ ነበር በሬዬን ያረድኩት» የሚለው የሃገሬን ተረት አሰብኩት። የሶከር ዘገባ እንዲህ ይነበባል። የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሀገሪቱ ከፍተኛው ውድድር ቢሆንም የጨዋታዎቹ እና በዙርያው የሚገኙት ነገሮች የወረደ የጥራት ደረጃ፣ ለአሸናፊው የሚበረከተው ሽልማት እና ቻምፒዮን በመሆኑ የሚያገኛቸው የፋይናንስ እና ሌሎች ጥቅሞች በውድድር ዓመቱ ከተጫዋቾች ዝውውር ለደመወዝ፣ አስተዳደራዊ ወጪዎች እና ለመሳሰሉት ከሚያፈሱት ገንዘብ ጋር በእጅጉ የማይመጣጠን ነው። የሚበረከተው ዋንጫም “ተራ” በሚባል ደረጃ ላይ የሚገኝ ከስፖርት ሱቆች ተገዝቶ የሚሰጥ፣ የተለየ መለያ የሌለው እና በየዓመቱ የሚቀያየር በመሆኑ ዋንጫውን ትርጉም የለሽ ያደርገዋል። በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ ቡድኖች የሚያስመዘግቧቸው ስኬቶች ከዕለት ደስታ ያለፈ ትርጉም እንዳይሰጣቸው ሲያደርጋቸው እያስተዋልን እንገኛለን። ለዚህም እንደ ዓብነት የምንመለከተው የአምናው የፕሪምየር ሊግ አሸናፊው ጅማ አባ ጅፋር የተበረከተለት ዋንጫን ነው።
ዋንጫው በክለቡ ፅህፈት ቤት የሚገኝ ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል። ይልቁንም በሐምሌ ወር አጋማሽ ባዘጋጁት አንድ ዝግጅት ላይ በጅማ ከተማ በሚገኝ አንድ ሆቴል ተረስቶ እና አስታዋሽ አጥቶ በፕላስቲክ ከረጢት (ፌስታል) ተቀምጦ ይገኛል። የሆቴሉ ሰራተኞች ሁኔታውን ተመልክተው ክለቡ ዋንጫውን እንዲወስድ ቢጠይቁም እስካሁን ወሳጅ አጥቶ በሆቴሉ እንደሚገኝ ታውቋል ሲል አስነብቧል። የዘንድሮው ሻምፒዮና መቐለ ሰባ እንደርታ ቢሆንም ሲያጠናቅቅ ከብሄራዊ ፌዴሬሽኑ የተበረከተለት ሽልማት ከ150 ሺህ ብር የማይበልጥ ሲሆን፤ የክለቡ ወጪ ደግሞ እስከ 40 ሚሊየን ብር ገደማ እንዲሚደርስ ይጠበቃል። ታዲያ አሁን ነው ‹‹ለዚህ ነው በሬዬን ያረድኩት?›› ማለት። ከየስፖርት ሜዳው ሳይጠፋ ድጋፉን የቸረው ደጋፊም የተፈነከትኩት፣ የተደበደብኩት፣ የወጣሁት፣ የወረድኩት …..ለዚሁ ነው እንዴ? ሲል መጠየቅ ቢችልም «ነበር» ሆኖ አልፏል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 17/2011
ዳንኤል ዘነበ