በዚህ ምድር ላይ እንደ ሰው ያለ የተለየ ባህሪይ ያለው ፍጡር ያለ አይመስለኝም። ትንሽ እንዳትለው ከሁሉ በላይ ሆኖ በፈጣሪው አምሳል ተፈጥሯል፤ እንዳትጠላው እግዚአብሔር ራሱ ከሁሉ አስበልጦ ወዶታል፤ ክፉ እንዳትለው በመልካምነታቸው ዓለምን ያዳኑ ሰዎች አሉ፤ ወንድሙን ወንድሙ ሲገድለው አይተህ አቤት የሰው ጭካኔ ስትል በውሻው ሞት ሲያለቅስ ታገኘዋለህ። እንደዚሁ ሰው የሚጠላውን ሲወድ፣ የሚረግመውን ሲመርቅ፤ የሚመሰገነውን ሲነቅፍ፣ የሚከበረውን ሲንቅ የሚስተዋልባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉ። ከነዚህ በተቃርኖ ቅኔ የተሞሉ የሰው ልጆች ግርንቢጥ ባህሪያት መካከል ታናሹ እግዜር የታዘበውን እኔም ቢገለጥ ይጠቅማል ያልኩትን ለእናንተም ላካፍላችሁ።
በህይወት ውስጥ ራሳቸውን እንደ ሻማ እያቀለጡ ለብዙሃኑ ብርሃን የሚገልጡ፤ ለህብረተሰብ ሁለንተናዊ ዕድገት ቀዳሚ ሚና የሚጫወቱ ክብርና ምስጋና የሚገባቸው የዕውቀት ብርሃኖች፣ የሰው ሻማዎች ቢኖሩም ብዙውን ጊዜ ለዚህ አልታደሉም። ሃኪሞች፣ አስተማሪዎች፣ ጸሃፊዎችና ፈላስፋዎች ዋነኞቹ ናቸው። እነዚህ ብርኃነ ብዙሃኖች በብዙ ልፋትና ጥረት ያጠራቀሙትንና ለህዝብ ይጠቅማል ያሉትን አንዳች ሃሳብ በሚገልጹና በሚሰጡ ጊዜ “ኤጭ፤ ራሳቸው ማድረግ ያልቻሉትን ለሰው ይመክራሉ” በሚል በትችት ይብጠለጠላሉ። በምስጋናና በሽልማት ፋንታ ነቀፌታና ወቀሳን ያስተናግዳሉ። ለዚህ ደግሞ በዋነኝነት እንደ ምክንያት የሚቀርበው ብዙውን ጊዜ “ምሁራኑ በዕውቀታቸው አልተጠቀሙበትም፣ ነገር ግን ራሳቸው ያልተጠቀሙበትን ዕውቅት ለሌላው ይመክራሉ፣ እነርሱ ያላደረጉትን አድርጉ ይላሉ” የሚል ነው። እንደ እኔ ግን ይህ ተገቢም ጠቃሚም አይመስለኝም። ምክንያቱም ለራስ ያላደረጉትን ለሰው ማድረግ ሊያስመሰግን እንጂ ሊያስወቅስ አይገባምና።
‹‹ነገር በምሳሌ፤ ጠጅ በብርሌ›› ነውና እስኪ ነገሩን በምሳሌ አስደግፈን እንመልከተው። አንድ በመስኩ የጠለቀ ዕውቀት ያለውና በሙያው የተመሰገነ ነገር ግን ሲጋራ አጫሽ ዶክተር አለ እንበል። ዶክተሩ እራሱ አጫሽ ስለሆነ ከተማረውና ከሚያውቀው ተነስቶ ሲጋራ ስለሚያስከትለው ከፍተኛ የጤና ችግር ሰውን ማስተማርና መምከር የለበትም ማለት ነው? ሲጋራ ማጨስ አደገኛ የጤና ጠንቅ መሆኑን እኮ ከማንም በላይ እርሱ ያውቀዋል። ስለሆነም ሲጋራ ማጨስ እንደሌለበት ከማንም በላይ ጠንቅቆ ያውቃል።
ህይወቱን አደጋ ላይ ላለመጣልና ራሱን ላለመጉዳት ሲል ማጨሱን እርግፍ አድርጎ መተው እንዳለበትም ሁሌ ያስባል፣ ከዚህ አደገኛ ሱስ መላቀቅን አጥብቆ ይፈልገዋል። ግን መተው አልተቻለውም፣ አጫሽ ነው። ታዲያ ዶክተሩ ማጨስ ማቆም ስላልቻለ፣ እርሱ ስላላደረገው ስለ ሲጋራ ጎጅነትና ሰዎች እንዴት ከሲጋራ ሱስ መላቀቅ እንደሚችሉ መናገርና ማስተማር የለበትም? እንግዲህ ሰዎች መናገር ወይም መጻፍ ያለባቸው የሚያደርጉትን ነገር ብቻ ከሆነ ይህ አጫሽ ዶክተርም መናገር ያለበት ስላደረገው ነገር ማለትም ሲጋራ ማጨስ ማቆም እንደማይቻል መሆን ነበረበት። ግን አላደረገውም፣ ዕውቀቱ ባያድነውም፣ ራሱን ከዚህ መጥፎ ልምድ ማውጣት ባይችልም ለሰዎች የሚያስተምረው ግን ስለ ጉዳቱ ነው።
ቢገባን ኖሮ ከባዱ ነገርም ይኸው ነው። ለራስ ማድረግ ያልቻሉትን መልካም ነገር ለሌሎች ማድረግ! ዶክተሩ በአደገኛው የሲጋራ ሱስ ውስጥ እየማቀቀ፣ ከዚህ ችግር ለመውጣት ዘወትር ፈጣሪውን እየተማጸነ ነገር ግን አልችል ብሎ ያቃተውን “እኔ አልቻልኩምና እነርሱም አይችሉም” ብሎ ተስፋ ሳይቆርጥ ለራሱ ማድረግ ያልቻለውን ሌሎች እንዲድኑ መፈለግና የበኩሉን ማድረግ። ይሄ ታዲያ ያስመሰግን ነበር እንጂ ያስሰድባልን? እናማ ወገኔ እነርሱ ሳይጠቀሙ ሌሎችን የሚጠቅሙ፣ እየሞቱ የሚያድኑ እንዲህ ዓይነቶችን የሰው ሻማዎች ልናከብራቸውና ልናደንቃቸው እንጂ ልንወቅሳቸውና ልንንቃቸው አይገባም?
እንዲያውም በእኔ እምነት መተቸት ያለባቸው ለራሳቸው ያላደረጉትን ለሰው የሚመክሩ ምስኪን የሰው ቤዛዎች ሳይሆኑ “ዕውቀቱ እያላቸው ለራሴ እንኳን ያላደረኩትን ለሰው ለምን እናገራለሁ” የሚሉ ጻድቅ መሳይ ንፉጎች ናቸው። ዕውቀት ለራስ ስላልጠቀመ ብቻ ለሌሎች እንዳይተላለፍ የሚፈልጉ ከግለኝነት አጥር ያልተሻገሩ ራስ ወዳዶች ናቸው ሊተቹ የሚገባቸው። ምክንያቱም ዕውቀት የሚሰጠን ሁልጊዜ ራሳችን ብቻ እንድንጠቅምበት ላይሆን ይችላል። ዕውቀት የሚተገበረውና ጥቅም ላይ የሚውለው ግዴታ በራሳቸው በአዋቂዎች ዘንድም ላይሆን ይችላል። በእኔ ዕምነት ዋነኛው የአዋቂዎች ተግባር ዕውቀትን ለብዙሃኑ ማስተላለፍና ለሁሉም እንዲዳረስ ማድረግ ይመስለኛል። ዕውቀቱ ወደ ተግባር የሚቀየረው ግን በተደራሲው ማለትም በግለሰቡ ወይም በብዙሃኑ ህዝብ ነው።
እናም አዋቂዎች ሁል ጊዜ የሚያውቁትን የሚተገብሩ ላይሆኑ ይችላሉ። ደግሞም አንድ አዋቂ ያገኘውን ዕውቀት ለራሱ ብቻ ቢተገብረው ተጠቃሚ የሚሆነውም ያው ራሱ ብቻ ይሆናል። ይህን ስል ግን አዋቂዎች ዕውቀታቸውን መተግበር የለባቸውም እያልኩ አይደለም። አዋቂው ያወቀውን ዕውቀት ተግባራዊ ማድረግ ይችላል፤ የዕውቀቱ ተግባራዊነት ግን በአዋቂው ግለሰብ ደረጃ ብቻ ከሆነ ዕውቀት ትርጉሙ ይዛባል፣ ትክክለኛ ዋጋውንም ያጣል። ምክንያቱም ዕውቀት በባህሪው ሰብዓዊና “ብዙዋዊ” በመሆኑ ነው። ሰዎች በተፈጥሯቸው ብቸኛ አይደሉም፣ ብዙ ናቸው፣ ማህበራዊ እንስሳ ናቸው። ዕውቀትም እንደዚሁ ለብቻ የሚይዙት፣ በራስ ብቻ የሚተገበር ነገር አይደለም። ከራስ ውጭ እንዳይተላለፍ የሚፈለገው በሽታ ብቻ ነው።
ዕውቀት ግን ለራስ መጥቀም ያለበት ቢሆንም እንኳን፣ በዚህ ብቻ አይረካም፤ የብዙዎች መሆን ይፈልጋል። ዋጋ የሚኖረውም ከራስ በአሻገር ለብዙዎች ሲያስተላልፉት፣ ሲካፈሉት፣ ሲሰጡት ነው። ስለዚህ የአዋቂው ሚና መሆን ያለበት ያገኘውን ዕውቀት መተግበሩ ላይ ብቻ ሳይሆን ማስተላለፉም ላይ ሊሆን ይገባል የምልበት አመክንዮም መነሻው ይኸው ነው። ስለዚህ በአንድ ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ዕውቀት ያለው አንድ ምሁር እርሱ ያድርገው አያድርገው ዕውቀቱን ማስተላለፉ ግን ሊያስተቸው አይገባም ብየ አምናለሁ። ደግሞስ አዋቂው ዕውቀቱን ባይጠቀምበት የተጎዳው እርሱ ራሱ እንጂ እኛ ምን ቀረብን?
“ራሱ ያላደረገውን” በሚል አጉል ትዕቢት ተወጣጥረን ጠቃሚ የሆነውን ዕውቀት ተቀብለን ተግባራዊ ባለማድረጋችንስ የሚጎዳው ማን ነው? እርሱማ “ራሴን ሳልጠቅም እንዴት ዕውቀቴን ለሌላ አሳልፌ እሰጣለሁ” በማለት ሳይሰስት ያለውን በለጋስነት ሰጥቷል። እርሱ ባይጠቀምም ሌሎች ሰዎች እንዲጠቀሙለት ዕውቀቱን በቅንነት አካፍሏል። እናም እውነቱ ይሄ ሆኖ ሳለ “ለራሱ ሳይሆን” በሚል ሰዎች የአዋቂዎችን ምክርና ሃሳብ የሚነቅፉበትና የማይቀበሉበት ምክንያት ራሱ አላዋቂነት ይመስለኛል።
ነገሩን በቅጥ ሳያስተውሉ በግብዝነት ለነቀፋና ለሃሜት ከመሮጥ ይልቅ “ብልህ ጠቢባንን በመስማት ዕውቀቱን ይጨምራል” እንዲል መጽሃፉ አዋቂነት ማለት የሚተላለፈውን ዕውቀት በመስማት አዋቂዎቹ ባይተግብሩት እንኳን የእነርሱን ቃል ሰምቶ መተግበርና በዕውቀቱ መጠቀም ነው። ያኔ ዕውቀት ተግባር ላይ የሚውለው በሰጭው ሳይሆን በተቀባዩ፣ በአዋቂው ሳይሆን በብዙሃኑ መሆኑን እንገነዘባለን። ወትሮውኑም አዋቂ ጠቃሚ ነው፣ ተጠቃሚ አይደለም፤ ሰጭ እንጂ ተቀባይ አይደለም። እናም ዕውቀትና ጥበብን ይሰጣል፣ በእነርሱ አማካኝነት ለብዙዎች ይዳረሳል በዚያም ይተገበራል። የዓለም ታሪክም ይህንኑ ይመሰክራል።
ዲሞክራሲና መልካም አስተዳደር የሰፈነባቸው አገራት መንግስታት ለመመስረት የመሪነ ትን ቁልፍ ሚና ተረድተው አገር መሪዎችን ሲያስተምሩ የነበሩት ታላላቆቹ የግሪክ ፈላስፎች መሪ ዎች አልነበሩም። ህዝባቸው ግን “አገር መሪ ሳይሆኑ ስለ አገር መሪነት ያስተምራሉ” ብሎ ትምህርታቸውን አንቀበልም አላለም። ይልቅስ እነ ፕላቶ ስለ ህዝባዊ መንግስትና ፍትሐዊ የህዝብ አስተዳደር ስርዓት ሲያስተምሩና የተሻለ መሪ መሆን የሚቻልበትን ጥበብ ሲጠቁሙ ብዙሃኑ አደባባይ እየወጣ ያዳምጣቸው ነበር። በዚያም ከህዝቡ መካከል እነ ፕላቶ የሚሉትን ሰምቶ የሚተገብር በመውጣቱ ህዝቡ ተጠቀመ። እናም ከራሳቸው አልፈው ዛሬም ድረስ ዓለም የሚያጨበጭብለትን ዲሞክራሲ የሚባለውን የመንግስት ሥርዓት ለዓለም ህዝብ ማበርከት ቻሉ።
በሳይንስና ቴክኖሎጂው ዘርፍም ቢሆን ያለው ከዚህ የተለየ አይደለም። አንድ ምሳሌ ብቻ እናንሳ። በመገናኛ ዘርፉ ከተከናወኑ ታሪክ ቀያሪ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች መካካል በግንባር ቀደምትነት ስለሚጠቀሰው ስልክ ግኝት ቀድሞ ማሰብና ማውራት የቻለው መስማት የማይችለው አሌክሳንደር ግራሃምቤል ነበር፤ የስልክ ቴክኖሎጂን የፈጠረልንም እርሱ ነው። ያኔ መስማት የማይችለው ግርሃምቤል “በሺህ የሚቆጠር ኪሎ ሜትሮች ርቀት ተቀምጦ ማውራትና መሰማማት ይቻላል” ብሎ ሲነሳ “እርሱ መስማት ሳይችል እንዴት እንዲህ ይላል፤ እርሱ ማድረግ ያልቻለውን ለሰው ያስባል” በሚል አላዋቂነት ዓለም ታብያ ግራሃምቤልን “አልሰማህም” ብላው ብትሆን ኖሮ የመላው የሰው ልጅ ስልጣኔ ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት አይከብድም። አዋቂው ግራሃምቤል ግን “እኔ መስማት አልችል፤ ምን ያደርግልኛል” አላለም። እኔ ራሴ በዕውቀቴ ካልተጠቀምኩበት ለሌሎች አልመክርም ብሎ አላሰበም። ራሱን ባይጠቅምበት እንኳን ዓለሙን ጠቀመበት፤ የሰው ልጆችን ህይዎት ቀየረበት። አዋቂ እንዲህ ነው ራሱ ባይጠቀምም ሰዎችን ይጠቅማል፤ ዕውቀቱን ባይጠቀምበትም ሌሎችን ይጠቅምበታል!
አልበርት አንስታይንን የመሰለ የምድራችን ኃያል ሳይንቲስት እኮ አንድ ማንበብና መጻፍ የማይችል የአሜሪካ ገበሬ ማሽከርከር የሚችለውን መኪና እርሱ መንዳት አይችልም ነበር። ከመኪና ሞተር አሰራር ህግ ሚሊዮን ማይልስ ርቀው የሄዱ ረቂቅ የፊዚክስ ህጎችን ግን ቀምሯል። እውነት አንስታይን መኪና ልንዳ ቢል አቅቶት ይመስላችኋል? ታዲያ አንስታይን እንኳን ስለ መኪና ሞተር አሰራር ፅንፍ ዓለም ራሱ (ዩኒቨርስ ይሉታል እነርሱ) የሚሰራበትን ሚስጥራዊ ህግ ያወቀውን አስተምሯል። እንዲያውም “ማወቅ የምፈልገው ፈጣሪ ይችን ዓለም የፈጠረበትን ሚስጥር ነው፤ ከዚህ ውጪ ያለው ሌላው ነገር ሁሉ ለእኔ ተራና ዝርዝር ነው” በማለት በራሱ አንደበት ተናግሯል። ታዲያ አንስታይን መኪና እንዴት ማሽከርከር እንደሚቻል ቢያስተምር “ለራሱ የማያውቀውን” ይባላልን? ባለው ዕውቀት ልክ ራሱን ጠቅሞ ይኖር የነበረ ሰው እንዳልነበረም የህይወት ታሪኩ ይመሰክራል። አንስታይን አብዛኛውን ጊዜ የረባ ልብስ አይለብስም ይባላል። ጫማውም ነጠላ ጫማ ነበር። ሥር የሰደደ በፒፓ የማጨስ ሱስም ነበረበት። ሆኖም በዘመናዊው ዓለም የአንስታይንን ያህል ለዓለማችን ዕድገት ታላቅ አስተዋፅኦ ያበረከተ ሰው የለም። እርሱ ራሱ አብዝቶ የሚታወቅበት አባባሉም “ለሌሎች መኖር ያልቻለ ሰው በራሱ ሰው መሆኑን እጠራጠራለሁ” የሚል ነው። እናስ አንስታይን እንዴት ለውጥ ማምጣትና ስኬታማ መሆን እንደሚቻል ቢያስተምርና ሰዎችን ቢመክር “መጀመሪያ ደህና ኑሮ በኖረ” በሚል ንቀት ምክሩን ላንቀበለው ነው?
ስለሆነም በዕውቀትና በአዋቂ መካከል ያለውን ልዩነት ማወቅ ያስፈልጋል። ዕውቀት ብዙዋዊ፣ አዋቂነት ግላዊ ነው። በመሆኑም በብዙዋዊነት ባህሪው ዕውቀት የሚተገበረው በህዝብ፣ በብዙነት ነው የሚተገበረው። አዋቂው ደግሞ እንደ ግላዊነቱ ዕውቀትን በግሉ ለራሱ ብቻ ቢተገብራት ዋጋ ስለማታስገኝለት በእውነተኛ ባህሪዋ-በብዙዋዊነቷ ለተገቢው ዓላማ ጥቅም ላይ እንድትውል ወደ ህዝቧ ወደ ብዙሃኑ ያስተላልፋታል። እናም አዋቂው ዕውቀቱን የማስተላለፍ እንጂ የመተግበር ግዴታ የለበትም። ለራሱ ቢተገብረው ባይተገብረው ለውጡ ያው ለአንድ ሰው ነው።
ይህ ደግሞ ከእውቀት እውነተኛ የብዙዋዊነት ባህሪ ጋር የሚቃረን በመሆኑ ፋይዳው ያን ያህል ነውና ሁል ጊዜ የአዋቂው ትኩረት ዕውቀቱን ማስተላለፉ ላይ ይሆናል። እናም አዋቂዎች ያላቸውን ዕውቀት ለብዙሃኑ ህዝብ ለማስተላለፍ ወይም ለማስተማር ወይም ለማሳወቅ ዕውቀታቸውን የግድ መተግበር አይጠበቅባቸውም። ምክንያቱም ዕውቀትን ለማስተላለፍና ሌሎችን ለማሳወቅ ወሳኙ ነገር መተግበር ሳይሆን ማወቅ (ዕውቀቱን ይዞ መገኘት) ነው። የሚያስተቸውም ለራስ የማያደርጉትን መምከር ሳይሆን ለራስ የማያውቁትን ለሰው መምከር ነው። የሚያውቁትን ነገር ግን የማይተገብሩትን ነገር በማሳወቅ ውስጥ ቢያንስ ሌሎችን ማሳወቅ አለ። ይህም ከጥቅም በስተቀር ሌላ ምንም ጉዳት የለውም። ለራስ የማያውቁትን ለሌሎች መምከር ግን ጥፋት ነው፤ ከጥፋትም በላይ ወንጀል፣ ኃጢአትም ነው።
ምክንያቱም አለማወቅ ልክ እንደ በሽታ ነው። በሽታ ደግሞ ከላይ እንደገለጽነው ጎጅ በመሆኑ ለራስ ብቻ ሊይዙት የሚገባ እንጂ ከሰው ጋር ሊካፈሉት የሚችሉት አይደለም። ጉዳትን ለሌሎች ማካፈል ትርፉ ጥፋት ነውና! ስለሆነም ራሱ የማያውቀውን ለሌሎች የሚመክር እርሱ ነው መወቀስ ያለበት። አላዋቂ አላዋቂነቱን ይዞ ዝም ቢል አይንቁትም፤ ነገር ግን አላዋቂነቱን ለማስተላለፍ የማያውቀውን ለሌሎች ቢመክር እርሱ የጥፋት መካሪ ነውና ሊወቀስና ሊወገዝም ይገባል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 17/2011
ይበል ካሳ