“… ሻጭና ገዥ አውቀው ወደው ቢዋዋሉ ነው እንጂ ከዚህ ውጭ ውለታ አይጸናም፣ አይፈጸምም… ሻጭና ገዥ ያለ ግርገራ እጅ ለእጅ ቢቀባበሉ ነው እንጂ ካልተቀባበሉ መሸጥ መግዛት አይጸናም፣ አይፈጸምም…ሻጭ ከብቱን ሰጥቶ ወርቁን ቢቀበል፤ ገዥ ወርቁን ሰጥቶ ከብቱን ቢቀበል ነው እንጂ… ሻጭ ቢወድ በገዥ፣ ገዥ ቢወድ በሻጭ ፈቃድ ይሆናል፤ መሸጥ መግዛት፤ የገዥ መቀበልና የሻጭ መስጠት በሁለቱም ፈቃድ ነውና” ይህ በኢትዮጵያ ከ15ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ አሁን በስራ ላይ ያሉት አብዛኞቹ ሕጎች እስከመጡበት 1960ዎቹ ድረስ አገር ሲመራበት ከነበረውና ከሕጎቻችንም መሰረት ከሆነው ከፍትሐነገስት የተወሰደ ነው።
ሃሳቡ የዛሬውን ጉዳያችንን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። በባለፈው ሳምንት ጽሁፋችን “ውል ለመዋዋል ችሎታ የሌላቸው ሰዎችና የሚያደርጓቸውን ውሎች ውጤት” በሚል ርዕስ አንድ ውል ውጤት እንዲኖረውና በሕግ ፊት ዋጋ እንዲኖረው ከሚያደርጉ አራት መሰረታዊ መለኪያዎች አንዱ የሆነውን የተዋዋይ ወገኖች የመዋዋል ችሎታን ተመልክተናል። በዚህኛው ጽሁፋችን ደግሞ ሁለተኛውን መለኪያ የተዋዋይ ወገኖች ፈቃድ የሚለውን እንዳስሳለን።
“ሰው በቃሉ ይታሰራል”
ከፍትሐነገስት 33ኛው አንቀጽ ተጨልፎ የወጣው የላይኛው ሃሳብ ለመዋዋል አስቀድሞ የግራ ቀኙ ፈቅዶ መስማማት ወሳኝ መሆኑን በግልጽ ያሳያል። የፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 1678/ሀ እንደሚገልጸው አንድ ውል በሕግ ፊት ዋጋ የሚኖረው ለመዋዋል ችሎታ ባላቸው ሰዎች መካከል ጉድለት የሌለው ስምምነት ሲኖር ነው። ይህ ማለት ተዋዋዮች በመካከላቸው በህግ ፊት የሚጸና ግዴታ ለማቋቋምና ግዴታውም በሚያስከትለው ውጤት ለመገዛት ስምምነት ፈቃደኛ መሆናቸውን በይፋ ሲገልጹ ነው። “ውል ፍጹም ነው ለማለት የሚቻለው ተዋዋዮቹ በተስማማ አኳኋን መፍቀዳቸውን ገልጸው ሲገኙ ነው” በማለት በሕጉ በግልጽ ሰፍሮ የምናነበውም ለዚህ ነው። ይህ ሲሆን ተዋዋዮች ፈቅደው ተዋውለዋል እንላለን።
ስለተዋዋይ ወገኖች የመዋዋል ችሎታ ስናነሳ “ችሎታ” የሚል ፍሬ ነገር እንደተመለከትን ሁሉ የተዋዋይ ወገኖችን ፈቃድ ስንዳስስ ደግሞ “ፈቃድ” የተሰኘ መሰረታዊ አነጋገር እናገኛለን። ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ “የኢትዮጵያ የውል ሕግ መሰረተ ሃሳቦች” በተሰኘው መጽሃፋቸው “ፈቃድ”ን ሲያብራሩ ከውል ምስረታ አንጻር ሲታይ ተዋዋዮች የሚዋዋሉበትን ነገር አስመልክቶ የየግል ውሳኔያቸውን በማሳለፍ ረገድ የነበራቸውን ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት የሚያመለክት ገላጭ አነጋገር ነው ይላሉ። በመሆኑም ተዋዋዮች በውል ውስጥ ወደው ፈቃዳቸውን መስጠትና በሚመጣው ግዴታ ሁሉ ለመገዛት የተስማሙ መሆን አለባቸው።
እዚህ ላይ የሚነሳው ቁልፍ ጥያቄ ታዲያ “አንድ ሰው በውል ለመገደድ ፈቃዱን ሰጥቷል የሚባለው መቼ ነው?” የሚለው ነው። የፍትሐብሔር ሕጉ ተዋዋዮች በጉዳዩ ላይ ሃሳብ ለሃሳብ ከተገናኙ (Meeting of minds) እና በተስማሙበት ጉዳይ ለመገደድ ፈቃደኝነታቸውን በግልጽ ካሳዩ (Agreement to bound by) በውሉ ለመገደድ ፈቃዳቸውን ሰጥተዋል ለማለት እንደሚቻል ያመለክታል። ይህ ፈቃድም ከተራ ስምምነት የተለየና ለአፈጻጸሙም የህግ ዋስትናና ከለላ ያለው ነው። ተዋዋዮች በዚህ መልኩ ፈቃዳቸውን ከሰጡ ፈቅደው ስለተዋዋሉ በውሉ ይገደዱበታል። ለመገደድ ወደውና ፈቅደው፤ ውጤቱንም በቅጡ ተገንዝበው ከገቡበት በኋላ ማፈግፈግ አይገባቸውም፤ ውል የተዋዋዮችን የቅንነትና የመተማመን ግንኙነት መሰረት ያደረገ ነውና። በአገራችን “ሰው በቃሉ ይታሰራል” የሚባለው ብሒለ-አበውም ይህንን አስረግጦ ያስረዳናል። “Pacta Sunt Servanda” (Man’s word is his bond) የሚባለው የሮማውያን ጥንታዊ የህግ አነጋገርም መሰረቱ ይኸው ነው።
የተዋዋዮች ፈቃድ የሚገለጸው በውል አቀራረብና አቀባበል (offer and acceptance) ነው። ግራቀኙ ውል ሰጪ እና ውል ተቀባይ ይባላሉ። ውል ሰጪው ውል የማድረግ ፍላጎቱን ለውል ተቀባዩ በማያሻማ መልኩ የሚገልጽበትን ድርጊት የውል አቀራረብ እንለዋለን። ይህንን ውል ተቀባዩ በሙሉ ሃሳቡና ልቡ ከተቀበለው ደግሞ የውል አቀባበል በመኖሩ በመካከላቸው ያለው የመዋዋል ፍላጎት ተቋጨ ማለት ነው። እዚህም ላይ ወሳኙ ነጥብ “ግራቀኙ የውል አቀራረብና አቀባበላቸውን በምን አኳኋን ይገልጹታል?” የሚለው ነው። ሕጉ እንደሚለው ፈቃድን በቃል፣ በጽሁፍ፣ በተለመዱ ጠቅላላ ምልክቶች ወይም በማያጠራጥር አኳኋን ለማስታወቅ ይችላል። ተዋዋዮች ከእነዚህ በተስማሙበት ዓይነት ፈቃዳቸውን መለዋወጥ ይችላሉ ማለት ነው።
የቃልና የጽሁፍ አቀራረብና አቀባበልን ለመረዳት ቀላል በመሆኑ ልማዳዊ ምልክት እና በማያጠራጥር አሰራር ፈቃድ የሚገለጽበትን አግባብ ማየቱ ጠቃሚ ነው። ፕሮፌሰር ጆርጅ ችችኖቪች Formation and Effects of Contracts in Ethiopian Law በተሰኘው መጽሃፋቸው ልማዳዊ ምልክቶች የሚለውን ለማስረዳት የተጠቀሙትን ምሳሌ አንዋስ። በጨረታ ሂደት ውስጥ አጫራቹ እንደ ጨረታው ደንብና ስርዓት ጨረታውን በመጀመር ውሉን የሚያቀርብ ሲሆን፤ ተጫራቾች እጃቸውን በማውጣት በምልክት ሃሳባቸውን ከገለጹ በኋላ አጫራቹ የተስማማበትን ዋጋ ያቀረበ ተጫራች እጅ ሲወጣለት በመዶሻው ጠረጴዛውን ይመታዋል። በዚህ ወቅት ነው ከስራው ባህርይ አንጻር በተለመደ ምልክት የውል አቀራረብና አቀባበል ተፈጽሟል የሚባለው። በሌላ በኩል በማያጠራጥር አኳኋን ፈቃድን መስጠት የሚባለው በተግባር የሚገለጽ ስምምነትን ማሳያ ሲሆን፤ ባንክ የኤቲኤም ማሽኖችን ሲያስቀምጥ ደንበኞችም ካርዳቸውን በመጠቀም ገንዘብ ሲወስዱ ለዚህ ተግባራዊ የውል አቀራረብና አቀባበል ማሳያ ይሆናል።
ከውል አቀራረብና አቀባበል ጋር በተያያዘ ትኩረት ሊደረግበት የሚገባው ሌላው ጉዳይ ዝምታ ነው። በመርህ ደረጃ የውል ሃሳብ ሲቀርብለት ዝም ያለ ሰው የቀረበለትን የውል ሃሳብ እንደተቀበለው አይቆጠርም። ለዚህ ነው የውል አቀራረብና አቀባበሉም ሕጉ ከላይ ባስቀመጣቸው አኳኋኖች በግልጽ መፈጸም የሚገባው። እናም ዝምታ ውልን መቀበል አይደለም። መርሁ ይህ ቢሆንም ቅሉ ዝምታ እንደውል መቀበል የሚቆጠርባቸውን ልዩ ምክንያቶች ግን ሕጉ አስቀምጧል። አንደኛው የመቀበል ግዴታ ነው። እንደ ኢትዮ ቴሌኮምና መብራት ኃይል ያሉ የመንግሥት አገልግሎት አቅራቢ ተቋማት ለደንበኞች የሚሰጡትን አገልግሎት ደንበኞች ከተቀበሉ በመካከላቸው ውል ተፈጽሟል ማለት ነው። በመሆኑም ፈቃዴን ሳልሰጥህ ነው አገልግሎቱን የሰጠኸኝ የሚል የዝምታ መከራከሪያ ማቅረብ አይቻልም።
ሁለተኛውና ዝምታ ውልን እንደመቀበል የሚቆጠርበት ሁኔታ አስቀድመው ካሉ ውለታዎች ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ማሻሻያዎችን በዝምታ መቀበል ነው። ቀድሞ የነበረን የውል ዘመን ለማስረዘም፣ ለማሻሻል ወይም ተጨማሪ ውል ለማድረግ አንደኛው ተዋዋይ ያቀረበውን ሃሳብ ሌላኛው ወገን ዝም ካለ ውሉ በዝምታ ተቀባይነት አግኝቷል ማለት ነው። በተጨማሪም የማሻሻያ ሃሳብ አቅራቢው ተዋዋይ ለሌላኛው ወገን ሃሳቡን የማስታወቂያ ጊዜ ቆርጦለት አስታውቆት ከሆነና በዚሁ ጊዜ ውስጥ ይሆናል/አይሆንምን ካላስታወቀው እንደተቀበለው ይቆጠራል።
በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሕዳር 26 ቀን 2007 ዓ.ም. የተቋጨው ክርክር ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። ወይዘሮዋ በ2ሺ ብር ወርሃዊ ከፍያ ለሦስት ወራት ቤት ተከራይተው ጊዜው ሲጠናቀቅ ቤቱን ለአከራይ ሊያስረክቡ ይዋዋላሉ። ይሁንና በውሉ መሰረት ጊዜው ሲጠናቀቅ ቤቱን እንዲለቁ ሲጠየቁ ባለመልቀቃቸው ባለቤቱ ቤቱን እንዲለቁ ካለበለዚያ ግን በየወሩ 5ሺ ብር ኪራይ እንዲከፍሉ ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸዋል። ነገር ግን ወይዘሮዋ ማስጠንቀቂያውን ተቀብለው ቤቱን ሳይለቁ ወይም የተጠየቁትን የኪራይ ገንዘብ ሳይከፍሉ ጆሮ ዳባ ልበስ በማለታቸው አከራይ ዶሴያቸውን ሸክፈው ወደ ፍርድ ቤት አቀኑ። ከሥር ፍርድ ቤቶች ጀምሮ የተደረገው ክርክር በመጨረሻ መቋጫው በሰበር ችሎት ሆነ። በውጤቱም ወይዘሮዋ ተከራይ የኪራይ ጭማሪውን አውቀው ቤቱን በዝምታ መጠቀም በመቀጠላቸው የተጨመረውን ገንዘብ እንደተቀበሉ ግምት ተወስዶ፤ በላዩ ላይ ደግሞ በኪራይ ሕጋችን መሰረት ውሉ ላልተወሰነ ጊዜ እንደታደሰ ተቆጥሮ 5ሺ ብር ኪራይ ታስቦ ውዝፍ ጭምር እንዲከፍሉ ነው የተወሰነባቸው። ከዚህ የምንረዳው ታዲያ ዝምታ በውል ውስጥ የቱን ያክል መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ነው።
የተዋዋዮች ፈቃድ ጉድለት አለበት የሚባለው መቼ ነው?
የተዋዋዮች የፈቃድ ጉድለት የውልን ሕጸጽ ያሳያል። የውል አቀራረብና አቀባበል ከላይ በተገለጸው መልኩ በሕጉ አግባብ ቢከወን እንኳን የፈቃድ አሰጣጡ ውል የተዋዋዮችን የቅንነትና የመተማመን ግንኙነት መሰረት ያደረገ ሊሆን ይገባዋል በሚል ካብራራሁት መለኪያ አንጻር ምሉዕ ሆኖ መገኘት አለበት። ይህም ማለት ተዋዋዮች በእርግጥም እርስ በእርሳቸውና በጉዳዩም ላይ ጭምር ሃሳብ ለሃሳብ የተገናኙ መሆናቸው ሊረጋገጥ ያስፈልጋል። በፍትሐነገስቱ እንደተገለጸው አንዱ ወዶ፣ ሌላውም ፈቅዶ፤ ሃሳባቸውም በነጻነት ካንዳቸው አንደበት ወደሌላኛው ጆሮና ሕሊና ደርሶ፤ በሚዛናዊ ህሊና ነጥሮ ሲስማሙ ነው ሕጸጽ አልባ ውል የሚቆመው። ካለበለዚያ ግን ፈቃዳቸው ጉድለት ከተገኘበት ውሉን ለማፍረስ ምክንያት ተገኘ ማለት ነው።
የተዋዋይ ወገኖች የፈቃድ ጉድለት የሚመነጨው ከስህተት፣ ከተንኮል፣ ከመገደድ ወይም ከመጎዳት ነው። መሳሳት የሚባለው ተዋዋዮች ሁለቱም ወይም አንዳቸው በውላቸው ስለተገለጸው ፍሬ ነገር ወይም አንዳቸው ስለሌላኛው ትክክለኛ ያልሆነ ነገር በመጨበጥ በቅን ልቡና ውል አድርገው ከሆነ ነው። ተዋዋዮች እውነቱን አውቀውት ቢሆን ኖሮ ፈቅደው ወደ ውሉ አይገቡም ነበር የሚያስብልን ጉዳይ ነው ሕጋችን ስህተት የሚለው። ይህም የውሉን ውጤት ከተዋዋዮች ፈቃድና ፍላጎት ውጭ ያደረገ ክስተት ነው ማለት ነው። ከዚህ ውጭ ግን የትኛውም ስህተት (የሒሳብ ስህተት እና ለመዋዋል ምክንያት በሆኑት ነገሮች ላይ መሳሳት) ለውል መፍረስ ምክንያት ሊሆን አይችልም።
በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1699 እንደተመለከተው ግራቀኙን ለመዋዋል ያደረሳቸው ስህተት ውሉን ሊያፈርስ የሚችልበት አንደኛው ምክንያት ተዋዋዮች በውሉ ዓይነት ወይም ጉዳይ ላይ የተሳሳተ ግንዛቤ ከያዙ ነው። ቤቱን ያከራየ የኪራይ ውል ነው የፈረምኩት ብሎ በማመን የሽያጭ ውል ቢፈርም፤ የአደራ ውል እየገባ የመሰለው ሰው የስጦታ ውል ቢያደርግ፤ ለመቄዶንያ የአረጋውያን መርጃ ድርጅት የበጎ ፈቃድ ገንዘብ እየሰጠ መሆኑን አምኖ ለአበዳሪ ሰው የእዳ መመለሻ ክፍያ ሰነድ ላይ የፈረመ… እነዚህን የመሳሰሉ ስህተቶች በውሉ ዓይነት (Nature) ላይ መሳሳት ናቸው። በውድድር ሜዳ ሽምጥ ሲጋልብ ያየውን ሰንጋ ፈረስ የገዛ መስሎት የጭነት አጋሰስ የገዛ ሰው ደግሞ በውሉ ጉዳይ (Object) የተሳሳተ ሰው ነው። ከዚህ መነሻ ተዋዋዮች አንድን የተለየ ንብረት በተመለከተ የሚዋዋሉ ከሆነ የንብረቱ ጥራት፣ ዓይነትና ባህርይም ለመሳሳት ምክንያት ይሆናል ማለት ነው።
ሁለተኛው ውልን ሊያፈርስ የሚችል ስህተት በተዋዋዩ ማንነት መሳሳት ነው። ይህም በሕጉ አንቀጽ 1700 ላይ የሰፈረ ሲሆን፤ ተዋዋዩ ማን እንደሆነ እንዲሁም ስራና ሙያው ምን እንደሆነ ካለማወቅ የሚፈጠር ስህተት ነው። ስህተቱ ለውል ማፍረስ ምክንያት የሚሆነውም የተዋዋይን ማንነት ማወቅ ለውሉ አስፈላጊ ጉዳይ ሲሆን ነው። በችግሬ ሳለሁ የደረሰልኝ ወዳጄ እሱ ነው በሚል ለሌላ ሰው ጥማድ በሬዎቹን በስጦታ የሚሰጥ፤ የሰርጌ ለታ በአዳራሽ ተገኝተህ ዝፈንልኝ በሚል ኮሜዲያን የቀጠረ፤ የዓመት የንግድ ሒሳቡን ለማሰራት ከዚህ ቀደም ሀሰተኛ ሰነድ በመፍጠርና በመገልገል የተቀጣን አካውንታንት የቀጠረ ሰው… በተዋዋዩ ማንነት ላይ የተሳሳተ በመሆኑ የውል ይፍረስልኝ ጥያቄ መጠየቅ ይችላል። የተሳሳተ ተዋዋይ “ተሳስቻለሁ ግን ውሉ ይቀጥል” ብሎ ፈቃዱን ከሰጠ ግን ውሉ ከመፍረስ እንደሚድን ልብ ይሏል።
የተዋዋዮችን የፈቃድ ህጸጽ የሚያመጣው ሁለተኛው ምክንያት ተንኮል ነው። ስህተት ከግንዛቤ እጥረት የሚመነጭ ነው። ተንኮል ግን አንዱ ተዋዋይ ወይም ሌላ ሦስተኛ ወገን በሌላኛው ተዋዋይ ላይ የሚፈጽመው እኩይ ስራ ወይም የሸር ተግባር ነው። ተንኮለኛው ወገን በየዋሁ ተዋዋይ ላይ በሰራው ተንኮል ምክንያት የሌላውን ወገን ፈቃድ አግኝቶ ከሆነ ይህ የውል ማፍረስ ምክንያት ይሆናል። ተንኮል በማታለል፣ በሀሰት ንግግር፣ እውነትን በመደበቅ፣ በማስመሰል፣ በማግባባት ወዘተ… ይፈጸማል።
በፍትሐብሔር ሕጉ እንደተቀመጠው ተንኮል ለውል ማፍረስ ምክንያት የሚሆነው የዋሁ ተዋዋይ ተንኮል ባይፈጸምበት ኖሮ ወደ ውሉ የማይገባ መሆኑ በተረጋገጠ ጊዜ ነው። በተጨማሪም ተንኮሉ በውሉ መሰረታዊ ጉዳይ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ መመዘን አለበት። ለሞት የሚያበቃ ሕመም እያለበት ይህንን ደብቆ ሀሰተኛ የጤናማነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ለመድን ሰጪ ኩባንያ በማቅረብ የሕይወት ኢንሹራንስ የገባ ሰው፤ በቀድሞ መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ ገንዘብ ይከፈለው እንደነበር የሚገልጽ ሃሰተኛ ሰነድ በማቅረብ በአዲሱ ቀጣሪው ዘንድ ይህንኑ በመደራደሪያነት አቅርቦ የላቀ ተከፋይ የሆነ ተቀጣሪ፤ ከስሮ ሳለ ሃሰተኛ የባንክ ሂሳብ በማሳየት የብድር ውል የገባ ሰው… ለዚህ ጥሩ ማሳያ ይሆናሉ።
ከተንኮል ጋር በተያያዘ ሳይጠቀስ ሊታለፍ የማይገባው ጉዳይ ተንኮሉ የተደረገው ከተዋዋዮች ውጪ በሆነ ሰው ከሆነ የዋሁ ተዋዋይ በውሉ የማይገደደው ሌላኛው ተዋዋይ ወገን ተንኮል የተፈጸመበት መሆኑን ካወቀለት ወይም ማወቅ ይገባው እንደነበር ከተረጋገጠ ነው።
የተዋዋዮች ፈቃድ ጉድለት አለበት የሚያስብለው ሦስተኛው ምክንያት መገደድ ነው። በህጉ በግልጽ እንደተመለከተው መገደድ የኃይል ስራ ነው። የኃይል ስራውም በተደላደለ አዕምሮው ፈቃዱን ሊሰጥ የሚገባውን ሰው የሚያሰጋው መሆን አለበት።፡ መገደድ ለውል ማፍረሻ ምክንያት የሚሆነውም አንደኛውን ወገን ራሱን ወይም ወላጆቹን ወይም ተወላጆቹን ወይም ባልን ወይም ሚስትን ከባድና የማይቀር አደጋ በሕይወቱ፣ በአካሉ፣ በክብሩ፣ በመብቱ ወይም በንብረቱ እንደሚመጣበት ያሳመነው ሲሆን ነው። በሕጉ “ከባድና የማይቀር አደጋ” የተባለው በምክንያታዊ ሕሊና ሲመዘን አንድን ሰው አካላዊ ወይም ስነ ልቡናዊ ጫና ውስጥ በመክተትና ያለአማራጭ በማስቀረት ያልፈለገውን ነገር ለማድረግ የሚያስገድደው አይቀሬ ሁኔታ ነው። ይህም የሚለካው በተገዳጁ ሰው ዕድሜ፣ ጾታ ወይም በወቅቱ የነበረበትን ሁኔታ በመመዘን እንደሆነ ሕጉ ይናገራል።
በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ሕዳር 17 ቀን 2003 ዓ.ም. የተቋጨን ክርክር በአጭሩ እንመልከት። ከሳሽና ተከሳሽ ባልና ሚስት ነበሩ። ትዳራቸው የ11 ዓመት የልጅ ፍሬ ቢያስገኝም የኋላ ኋላ ባለመስማማታቸው ሚስት የፍቺ ጥያቄ ስታቀርብ መርማሪ ፖሊስ የነበረው ባል ገንዘብ ካልሰጠሽኝ አይሞከርም በማለት በሕይወትና በንብረቷ ላይ አደጋ እንደሚያደርስ በተደጋጋሚ በማስፈራራትና በመዛት በመጨረሻ ምስክሮች ባሉበት ገንዘብ ሳያበድራት የ200ሺ ብር የብድር ውል ያስፈርማታል። በፍጻሜውም ባል ሚስቱን በመክሰስ በስር ፍርድ ቤቶች ብድሩን ከነወለዱ እንድትከፍል ቢያስወስንባትም በፍጻሜው መዝገቡን የመረመረው የፌዴራሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ግን ውሳኔዎቹን በመሻር የከሳሽና የተከሳሽን ልዩ ግንኙነት (ትዳር)፣ የሴትየዋን የትምህርት ደረጃና የነበረችበትን ሁኔታ በመመልከትና ጉዳዩን በመመርመር በማስገደድ የተደረገ ውል በመሆኑ ፈራሽ እንዲሆን በመወሰን ሴትየዋን በነጻ ወደ ቤቷ ሸኝቷታል። ከዚህ የምንረዳውም መገደድ ለውል ማፍረስ ምክንያት መሆኑን ነው።
አራተኛው የፈቃድ እንከን ማሳያ መጎዳት ነው። በመሰረቱ መጎዳት ለውል ማፍረስ ምክንያት አይሆንም።ይሁንና አንድ ውል ላንደኛው ወገን የበለጠ ጥቅም ሰጥቶ ለሌላኛው ደግሞ ከፍ ያለ ጉዳት ያሸከመው ከሆነ ለውል ማፍረስ ምክንያት ይሆናል። እንዲህ ያለ ሁኔታ የሚፈጠረው ደግሞ የተጎጂው ተዋዋይ ፈቃድ የተገኘው ችግሩን፣ መጃጀቱን፣ የመንፈስ ልልነቱን ወይም በንግድ ስራ ግልጽ የሆነ የልምድ ጉድለት ያለበት መሆኑን በመጠቀም ነው። ፕሮፌሰር ችችኖዊች ማዕበል እያዳፋው ለሞት የተቃረበውን የጭንቅ ሰው አንድ ሚሊዮን ብር በመቀበል ነፍሱን ያተረፈለት ዋናተኛ፣ ጦርነት ተነስቶ የላቡ ፍሬ ከሚወድም በሚል እጅግ ዝቅተኛ በሆነ ዋጋ የሽያጭ ውል የገባን ሰው በምሳሌነት በማንሳት መጎዳትን በግልጽ ያስረዳሉ። ለዚህም ነው መጎዳት የፈቃድ ሕጸጽን ያሳያል የተባለው።
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ሀምሌ 17/2011
ከገብረክርስቶስ