ከእንግሊዝ ኤምባሲ ወደ መገናኛ በሚወስደው አቋራጭ አስፋልት መንገድ ከደጃፋቸው ላይ አንዲት የተንበረከኩ እናት ተመለከትኩ። መንገዱና የቤታቸው ጣሪያ ያላቸው ርቀት ተቀራራቢ ነው። የመኖሪያ ቤታቸው በር ግማሹ በመንገዱ የተከለለ በመሆኑ ቆመው መግባትም ሆነ መውጣት እንደከለከላቸው የእርሳቸውን ቃል ሳልሰማ ነበር መረዳት የቻልኩት። ቀረብ ብዬም ላወጋቸው ወደድኩ። ተጎሳቁላ ያዘመመችው ቤታቸው ጠባብ ብትሆንም እንኳ እርሳቸው ግን ወደ ውስጥ እንድዘልቅ በፈገግታ ጋበዙኝ። ልገባ አንገቴን ደፋ ሳደርግም አገባቤን እንዳስተካክል ነገሩኝ።
ሁለት ልጆች ወልደው ‹‹እማዬ›› ተብለው መጠራት ቢችሉም፤ የልጅን ጣዕም ብዙም ሳይጠግቡ በሞት መነጠቃቸውን ወይዘሮ ፅጌ በሻህ ይናገራሉ። በተደጋጋሚ ቢወልዱም የልጆቻቸው ሕይወት በማለፉ ይሄ ሁኔታ ከትዳር አጋራቸው ለመለያየት አበቃቸው። ባለቤታቸው ሌላ ሚስት ሲያገቡም የቀበሌ ቤቱንና ንብረት ትተውላቸው እንደሄዱ ይናገራሉ። ነገር ግን ጧሪ ቀባሪ እንደሌላቸውና ከጎናቸው አለሁ የሚል መከታ ባለመኖሩ ከዕለታት በአንዱ ቀን ከወጡበት ሲመለሱ የቤት ዕቃቸው ወጥቶ በምትኩ የማያውቋቸው ግለሰቦች በቤታቸው ዕቃቸውን አስገብተው ይጠብቋቸዋል።
በወቅቱ ያጋጠማቸው ዱብ ዕዳ ምንነት ግራ ያጋባቸው ወይዘሮ ፅጌ፤ ወደ ወረዳው አስተዳደር በማቅናት ጥያቄውን ሊያቀርቡ ቢሞክሩም ምላሽ ሊሰጣቸው የቻለ አካል እንዳልነበር ያስታውሳሉ። ቀደም ብለው እንጀራ በመጋገር ይተዳደሩ የነበሩት እኚህ እናት ከቀድሞ ባለቤታቸው ጋር የሠሩት ማዕድ ቤት ሳይቀር ለግለሰቡ እንደተሰጣቸው ነው የሚናገሩት። ቤቱ በአዋጅ 47/67 ሲወረስም (ሀ) እና (ለ) ብሎም ተከራይም ሆነ ደባል አልነበራቸውም።
በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ አምስት የቤት ቁጥር 013 ውስጥ ከ1970 ዓ.ም ጀምሮ ከ30 ዓመታት በላይ የሕይወታቸውን ግማሽ ቢያሳልፉም እንኳ በአሁኑ ወቅት ግን በቤታቸው ባይተዋር ሆነው ከቀድሞ ባለቤታቸው ጋር ያስገቡት የውሃ ቧንቧና መብራት እንዲሁም ያሠሩት መፀዳጃ ቤትና ማዕድ ቤት ግለሰቡ አጥሮ ወስዶባቸዋል። ሁኔታው ሐዘንን የጫረባቸው ወይዘሮ ፅጌም በተደጋጋሚ ወደሚመለከተው የወረዳው አስተዳደር ሲያመሩ ለመንግስት የሥራ ኃላፊ እንደተሰጠ ማወቃቸውን ይናገራሉ። ጉዳዩ ምንም ዓይነት እልባት ሳይበጅለትም እነሆ ድፍን 10 ዓመታት ያስቆጥራል። ለጥያቄያቸው ምላሽን ፈልገው ባንኳኳቸው የሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ የመንግስት ቢሮዎችም ምንም እንደማያመጡ እንደተነገራቸው ይገልፃሉ። ‹‹ዝም ብለሽ አትዙሪ በእግርሽ ለምንድን ነው የምትመጪው?› ይሉኛል። እኔ ደግሞ ከእግሬ ውጪ በሌላ መንገድ መሄድ አልችልም›› ሲሉም ያጋጠማቸውን ሁኔታ ያስረዳሉ።
ቅሬታቸው ተገቢውን ምላሽ ባያገኝም እርሳቸው ግን ተስፋ ባለመቁረጥ ትግል ሲያደርጉ እንደቆዩም ይናገራሉ። ሴትነታቸውና ብቸኝነታቸው ለችግር ቢያጋልጣቸውም ዕውነቱ እንዲወጣላቸው ግን ዘወትር ይታትራሉ። የማንም ቤት ሳይነጠቅ እርሳቸው ላይ የተደረገው ድርጊትም ደካማነታቸውን መነሻ ያደረገ ስለመሆኑ ነው የሚገልጹት። ከባለቤታቸው የቀራቸውን ማስታወሻ ቤት እንዴት እንደሆነ ባላወቁት መንገድ መወሰዱም እንቅልፍ ከነሳቸው ቆየት ብሏል። ሕዝብን በእኩልነት ሊያገለግሉ ኃላፊነት ተጥሎባቸው ከተቀመጡ የአስተዳደር አካላት መብታቸውን በመጠየቃቸው ምክንያት ቢሰደቡ፣ ቢገፈተሩ፣ ለውሻ የሚሰጠው ክብር ያክል እንኳ ባያገኙም ፍትሕን ፍለጋ ግን ዝም አላሉም።
ወደ ቤታቸው የሚገቡትም ሆነ ወደ ደጅ የሚወጡት በቤታቸው በውስጥ በኩል በደረደሩት ወንበር አማካኝነት በመሆኑም በቅርቡ የመውደቅ አደጋ ደርሶባቸዋል። ይህም ብዙ ጊዜ ተከስቶባቸው እንደነበር ነው የሚናገሩት። ከዚህ አልፎም እራሳቸው ያስገቡትን ውሃ ተከልክለው ከውጭ ገዝተው ይጠቀማሉ። መፀዳጃ ቤትም መንደር ሄደው እንደሚጠቀሙ ይናገራሉ። አንድ ባልዲ ውሃ ቢያመጡ ለአንድ ራሳቸው ባይቸግራቸውም መፀዳጃ ቤት ግን ሌሊት ቢታመሙ እንኳ ወደየትም መሄድ እንደማይችሉ በምሬት ይገልፃሉ። ችግሩ እየተፈጠ ረባቸው ያለው በፍትሕ መዛባት እንደሆነ በማንሳት፤ መንግስት ተብሎ አገሪቱን ለማስተዳደር ሕዝቡ ሥልጣን የሠጠው አካል በእኩል ፍትሕ መስጠት ይጠበቅበታል ይላሉ። ቅሬታቸውን ከአንደበታቸው ባሻገር ያረጋግጣሉ ያሏቸውን ውሃና መብራት የከፈሉበትን እንዲሁም የቤት ኪራይ ሲከፍሉበት የኖሩትን የሰነድ ማረጋገጫዎችም ያሳያሉ።
ማረጋገጫ
በመዝገብ ቁጥር የካ/ክ/ከ/ቀ15/2274/96 በቀን 2/9/96 ዓ.ም በየካ ክፍለ ከተማ ለቀበሌ 15 ገቢዎች ቢሮ በቀበሌው ማህበራዊና ሲቪል ጉዳዮች ኃላፊ ፊርማ የወጣው ደብዳቤ ይገኛል። በደብዳቤው ሰፍሮ እንደሚገኘው ቀድሞ በቀበሌው ክልል፣ በቀድሞው ወረዳ 16 ቀበሌ 05 በቤት ቁጥር 013 በሆነው የመንግስት ቤት በአቶ ታደለ ገመቹ ስም ተመዝግቦ የሚገኘው ቤት ከግንቦት 1 ቀን 1996 ዓ.ም ጀምሮ በወይዘሮ ጽጌ በሻህ ስም ኪራዩ እንዲከፈል ቋሚ ኮሚቴው ሚያዚያ 28 ቀን 1996 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ጉባዔ ወስኗል። ስለሆነም ይኸው ታውቆ የቤት ኪራዩ በወይዘሮ ጽጌ ስም እንዲከፈል ያሳስባል።
በተለያዩ ወቅቶችም ወይዘሮ ጽጌ ስም የተከ ፈሉና የተደረጉ የቤት ኪራይ ውሎች ከማህ ደራቸው ጋር ይታያሉ። አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ አምስት ነባር የቤት ቁጥር 013 ሴክሽን ሦስት ብሎክ 60 በመቶ የመንገድ ቁጥር 1245 አካባቢ የሚገኝ
ንብረትነቱ የፅጌ በሆነው ቤት የተሰጠው የቤት ቁጥር ተገቢውን ጥበቃ በማድረግ በኃላፊነት የተረከቡ ሲሆን፤ ከጠፋ እንዲሁም ከተበላሸ በክፍያ ምትክ ለመውሰድ ተስማምተው ኃላፊነት መውሰዳቸውን የሚያሳየው ሰነድ ደግሞ ሌላኛው ነው። በሰነዱ እንደተመለከተው የቤት ቁጥር ያለበትን ታፔላ እንደተረከቡና ቤቱም በእርሳቸው ስም ይገኝ እንደነበር ያመላክታል። እኛም እነዚህን ከተመለከትን በኋላ በቅርብ የሚያውቋቸው የአካባቢውን ነዋሪ እንዲሁም የቀበሌ ቤቱ በእርሳቸው ስም ከነበረ እንዴት ለሌላ ሠው ሊካፈል ቻለ? ተካፍሎ ሲሰጥስ የእርሳቸውን የቀድሞ አኗኗር በሚጎዳና በግላቸው ያስገቡት የውሃ ቧንቧና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች ለግለሰቡ እንዴት ሊተላለፉ ቻሉ? የሚሉ ጥያቄዎችን ይዘን ወደ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ አምስት አስተዳደር አቀናን።
በቅርብ ከሚያውቋቸው
ወይዘሮ ስንቅነሽ ሰቦቃ፤ ለበርካታ ዓመታት ወይዘሮ ፅጌን እንደሚያውቋቸው ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅት ቅሬታ የሚቀርብበት የቀበሌ ቤትም ቀድሞ ወይዘሮ ፅጌ ከባለቤታቸው ጋር ይኖሩበት የነበረና እርሳቸው ያቀኑት ነውም ይላሉ። ምንም እንኳ የወላድ መኻን ሆኑ እንጂ ልጆች እንደነበራቸው በመግለጽ፤ የችግራቸው መነሻም ከጎናቸው ደጋፊ የሌላቸው መሆናቸው ነው ይላሉ። ጉዳዩን ለዓመታት ለሚመለከተው አካል ሲጠይቁ እንደነበር በማስታወስም ምላሽ አለማግኘታቸውን ይናገራሉ።
ወይዘሮ ፅጌ፤ የቅርብ ወዳጃቸው ቢሆኑም ቤታቸው ገብተው ቡና ለመጠጣት እንኳ እንደማ ይችሉ ይናገራሉ። ምክንያቱ ደግሞ የቤታቸው ጣሪያ ለመሬት የቀረበ በመሆኑ ወደ ቤቱ ለመዝለቅም በእንብርክክ እየሄዱ መግባትን መጠየቁ ነው ይላሉ። ወይዘሮ ፅጌ በተደጋጋሚ ወደቤታቸው ሲገቡ የመውደቅና የመሰበር አደጋ ያጋጠማቸው በመሆኑም ከፍተኛ ጥንቃቄ ይጠይቃልና ራሳቸውን ለማትረፍ ሲሉ ወዳጃቸውን ከበር አንኳክተው ይጠራሉ። እርሳቸውም አንገታቸውን አስግገው አውርተዋቸው ይመለሳሉ። ይህ አኗኗራቸውም በእጅጉ አሳዛኝና መንግስትም ሊያየው የሚገባ ነው በማለት በሐዘን ሁኔታውን ይገልፃሉ።
የሚመለከተው አካል
በየካ ክፍለ ከተማ በወረዳ አምስት የመንግስት ቤቶች አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ጌጤነው ደምሌ፤ ጉዳዩን እንደሚያውቁት ይገልፃሉ። ወይዘሮ ፅጌ ለረጅም ዓመታት ቅሬታቸውን ይዘው መመላለሳቸውን ባይክዱም፤ ቅሬታቸው ግን አግባብ እንዳልሆነ ነው የሚጠቁሙት። ችግሩ ሊነሳ የቻለበት ዋነኛ ምክንያትም ከግለሰቡ ጋር ባለአለመግባባት ነው። አስተዳደሩም በጉዳዩ ላይ ምላሽ ሰጥቷቸው የነበረ ቢሆንም ግለሰቧ ግን የተለያዩ የመንግስት ቢሮዎችን በር ማንኳኳታቸውን አላቆሙም። በዚህም ግለሰቧ ላቀረቡት አቤቱታ ከበላይ የመንግስት ኃላፊዎችም ቤቱን አስመልክቶ ለሚነሱ ጥያቄዎች የወረዳው አስተዳደር ምላሽ መስጠቱን ያስረዳሉ።
የቀድሞ ቀበሌ 05 የቤት ቁጥር 013 የሚገኘው የቅሬታ መነሻ የሆነው ቤት ሕጋዊ ተከራይ ወይዘሮ ጽጌ ናቸው የሚሉት አቶ ጌጤነው፤ ስለ ጉዳዩ ያብራራሉ። በወቅቱ ዳኛ ለነበሩ ግለሰብ ተከፍሎ እንደተሰጠም ያስታውሳሉ። ይህም ሲሆን የወረዳ አመራሩ ከአደረጃጀቱ ጋር በመሆን ቃለ ጉባዔ ይዘው ነው የተሰጠው። የተሰጠበት ምክንያት ደግሞ ግለሰቡ በቅርበት ሆነው ሕብረተሰቡን እንዲያገለግሉ ከሚል ሥራን ማዕከል ካደረገ መነሻ ነው።
ጉዳዩ በተደጋጋሚ በመቅረቡም አስተዳደሩ ለማጥራትና ለቅሬታው ምላሽ ለመስጠት በየደረጃው ካሉ መዋቅሮች ጋር ውይይት አድርጓል። በተደጋጋሚ ላነሱት ጥያቄም የሚመለከታቸው አካል ባሉበት ምላሽ ተሰጥቷቸዋል። በዚህም ወይዘሮ ፅጌ ጥያቄያቸው አግባብ እንዳልሆነና ግለሰቡ በሕግ አግባብ እንደተሰጣቸው ተገልፆላቸዋል። ግለሰቡ ዳኛ ስለነበሩ ሕብረተሰቡን በቅርበት ለማገልገል እንዲያስችላቸው ቤቱ ተለይቶ እንደተሰጣቸውም ነው የሚናገሩት።
በመመሪያው መሠረት ለተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች ቤት እንዲሰጣቸው ይደረጋል። ነገር ግን ቤት አሰጣጡ ቀድሞ በቤቱ ይኖር የነበረን ነዋሪ ጉዳት በሚያደርስ መንገድ እንዲሆንስ መመሪያው ይፈቅዳል ወይ? በሚል ላነሳንላቸው ጥያቄ አቶ ጌጤነው፤ ‹‹ቤትን ለሕብረተሰቡ ተደራሽ የማድረግና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር አመራሩ የራሱ ውሳኔ ይኖረዋል›› ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተውናል። መመሪያው ሰፊ ቤት ከሆነ ለሁለትና ለሦስት ሰው መሆን እንደሚችል አመራሩ ካመነበት ሊከፍለው ይችላልም በማለት አክለው ይናገራሉ።
ይህን መሰል ውሳኔዎች ሲተላለፉ አመራሩ ብቻ ሳይሆን የኤጀንሲውን መመሪያም መሠረት ባደረገ መልኩ ነው። ቤት ቁጥር የሚሰጠውም ሆነ የኪራይ ተመን የሚያወጣው ኤጀንሲው እንደሆነም ቡድን መሪው ያብራራሉ። በዚህም መመሪያው በሚፈቅደው መሠረት እንጂ በማን አለብኝነት ከፋፍሎ መስጠትም አይቻልም። ነገር ግን አመራሩ ያመነበት ከሆነና ክፍለ ከተማ ሄዶም ከፀደቀ ቤት ቁጥርም ከተሰየመ ማከራየት ይቻላል።
የቀበሌ ቤት ስለሚተላለፍባቸው ሕጋዊ መንገዶች ሲያስረዱም፤ የሚከራየውም ሆነ የሚሰጠው ቤት አመራሩ በቅርበት ለሕብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጥ ታሳቢ በማድረግ አልያም ደግሞ ‹‹የደሃ ደሃ›› በሚል ሕብረተሰቡ አምኖ ለሚለያቸው በኢኮኖሚ ዝቅተኛ የአኗኗር ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ወይንም ደግሞ በጤናና መሰል ጉዳዮች አስከፊ ሁኔታ ውስጥ ኑሯቸውን ለሚገፉ ዜጎች ነው። በመሆኑም ቅሬታው እንደቀረበ ለግለሰቡ ቤቱ እንዴት ተከፍሎ ሊሰጣቸው ቻለ? በሚል ብዙ መረጃዎችን የማፈላለግ ሥራ መሠራቱን አቶ ጌጤነው ያስረዳሉ። ግለሰቦችንም የማጠያየቅ ሥራ ተሠርቷል። ለዚህም የሚሆን የተገኘው አሳማኝ ማስረጃ ግለሰቡ በወረዳው ይሠሩ ስለነበር በቅርበት ሕዝብን እንዲያገለግሉ ታስቦ ቤቱ ተከፍሎ እንዲሰጣቸው መወሰኑን የሚያስረዳ ቃለ ጉባዔም ተገኝቷል። አካሄዱም ትክክል እንደሆነ ይናገራሉ። በወቅቱ የነበረው ውሳኔ መስጠት የሚችል አካል የወሰነውም ነው ይላሉ። ነገር ግን በሌላ በኩል ግለሰቧ ለቅሬታቸው ምላሽ ቢሰጣቸውም የተለያየ ቅሬታ እንደሚያቀርቡና ብዙም ተጨባጭ እንዳልሆነም ያነሳሉ። በውሳኔውም እርሳቸውን የሚጋፋ የመብትና የጥቅም ጉዳይም አለመኖሩንና ጥያቄው አስፋፍቶ ለመያዝ ከሚመነጭ ፍላጎት እንደሆነ ያረጋግጣሉ።
ግለሰቧ የሚያቀርቡት ጥያቄ ትክክል አለመሆኑን በአካል ቦታው ድረስ ወርደው ማረጋገጣቸውንና የሚኖሩበት ቤት እርሳቸውን የሚጎዳ አለመሆኑንም አቶ ጌጤነው ይገልፃሉ። መጀመሪያ ጥያቄው ሲቀርብ ተጎድተው እንደሆነ በማሰብ ትክክል ሊሆን ይችላል ከሚል እሳቤ ተወርዶ ሲታይ እርሳቸውን የሚጎዳ ሆኖ አልተገኘም። በዚህም ዳኛውን ለመጥቀም እርሳቸውን ለመጉዳት የተደረገ ውሳኔ እንዳልሆነም በምልከታ ማረጋገጥ መቻሉን ያስረዳሉ።
ዳኛው የሚኖሩበት ቤትም ይሄን ያክል የተጋነነ አይደለም የሚሉት አቶ ጌጤነው፤ ይበልጥ ድጋፍ መደረግ ያለበትም ዝቅተኛ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ለሚኖሩት በመሆኑ አስተዳደሩ ጥያቄያቸውን ለመመለስ የተለያዩ ሥራዎችን ሠርቷል። ወረዳው ላይ በተለያየ ጊዜ የተቀያየሩ ሦስት ዋና ሥራ አስፈፃሚዎች፣ የቤቶች፣ ከክፍለ ከተማ እስከ ወረዳ ድረስ ያገባናል የሚል አካል ምላሽ የሰጠበትም ጉዳይ ነው። በአሁኑ ወቅትም ተከፍሎ የተሰጣቸው ግለሰብ ውል ተዋውለው 013 /ለ/ በሚል ሕጋዊ ሆነው እየኖሩ ነው። ጉዳዩን ለማጥራት በተደረገው ሥራም በወረዳው ያሉና ጉዳዩን የሚያውቁ አደረጃጀቶችን ጭምር በማወያየት በወቅቱ በምን ዓይነት መልኩ ቤቱ ለግለሰቡ እንደተሰጠ ጥያቄ ቀርቦ ምላሽ ያገኘ ነው። ሂደቱም ትክክል እንደነበር አደረጃጀቶችም ምላሻቸውን መስጠታቸውን ያስታውሳሉ።
ከመመሪያ አንፃር
በየካ ክፍለ ከተማ የወረዳ አምስት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አብርሃም ኪዳነማርያም፤ በወረዳው በዚህ ዓመት የመጡ በመሆናቸው ጉዳዩን በቅርበት እንደማያውቁት ነው የሚናገሩት። ሆኖም ግን ከመመሪያ አንፃር በዚህ ዓይነት መልኩ ቤቶች ሊተላለፉ ይቻላል ወይ? ስንል ጥያቄያችንን አቀረብንላቸው። የቀበሌ ቤቶችን የማስተዳደር ሥልጣን ያለው የወረዳ አስተዳደሩ ሲሆን፤ በተለይም በአሁኑ ወቅት ካለው ከፍተኛ የቤት ፈላጊ ቁጥርና የቤት አቅም አንፃር አስተዳደሩ ካመነበት ቤቶችን ከፍሎ መስጠት እንደሚቻል በምላሻቸው ይገልፃሉ።
ዋና ሥራ አስፈፃሚው ነባራዊ ሁኔታውን እንደሚናገሩት፤ በወረዳው በአሁኑ ወቅት 1 ሺህ 200 የቤት ፈላጊዎች ‹‹በደሃ ደሃ›› ተመዝግበው ተራ እየተጠባበቁ ይገኛሉ። በመሆኑም ያለው አቅምና የፍላጎቱ መጠን የሚመጣጠን ባለመሆኑ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ቤቶቹን የማስተዳደር ሥልጣን ያለው አስተዳደሩ ቤቶቹን መክፈልና መስጠት ይችላል። ከመመሪያ አንፃር የቤቶች ኤጀንሲ ያስቀመጠው መመሪያም ሌላው ለሥራው አጋዥ ተደርጎ ይወሰዳል። በዚህም ኪራይ ተመን ማውጣትም ሆነ በህዝባር መክፈል የኤጀንሲው ሥልጣን ተደርጎ ተሰጥቶታል።
ቤት ሲተላለፍ ለከፍተኛ አመራሮችና ‹‹በደሃ ደሃ›› ተለይተው ለሚጠባበቁ የሕብረተሰብ ክፍሎች ቢሆንም ይህ ቅሬታ የሚቀርብበት ቤት የተላለፈው ግን ለዳኛ ነው ይህ እንዴት ይታያል? የሚል ሌላው ለአቶ አብርሃም ያነሳንላቸው ጥያቄ ነበር። ቤቱ ለከፍተኛ አመራር ሳይሆን ለዳኛ ነው የተሰጠው። ይህ ደግሞ ከመመሪያ አንፃር ማድረግ ይቻላል በማለት ማሳያዎችን በማንሳት ያስረዳሉ። መንግስት ካከራያቸው ውጪ ብዙ አስፍተው የያዙ ግለሰቦች ይገኛሉ። ይህንንም ካቢኔው ከተስማማበትና ከተወሰነበት ለቤቶች ኤጀንሲ በህዝባር እንዲከፈልና የኪራይ ተመን እንዲወጣለት በሚል ጥያቄዎችን ይልካል። የቀረበው የውሳኔ መነሻም አሳማኝ ሆኖ ከተገኘ ምላሽ ያገኝና የሕብረተሰቡን የቤት ጥያቄ በዚህ መልክ ለማቃለል ይሠራል።
በአሁኑ ወቅት 1 ሺህ 200 የሚጠጋ ቤት ጠያቂ መኖሩን በመግለጽ፤ ወረዳው ይህንን ጥያቄ ማስተናገድና የሕብረተሰቡን ፍላጎት ለማርካት ያለው አቅም ስለሚገድበው በህዝባር በመለየት ቤት እንዲያገኙ የተደረጉ አሉ በማለት አሠራሩ የመልካም አስተዳደር ችግርን ለማቃለል የሚደረግ አማራጭ እንደሆነ ያስረዳሉ። ከመመሪያው ውጪም አንዳንዴ በአስተዳደር ተወስኖ ካለው የችግር ግዝፈት አንፃር ይወሰናል። በተያያዘ የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ ደርሷቸው ከወረዳው ቤት ለቀው የሚሄዱ የሕብረተሰብ ክፍሎች ሲኖሩ ቀድሞ አንድ ቤተሰብ ብቻ ሲስተናገድበት የነበረው ቤት ለሦስትም ለአራትም የቻለውን ያክል በመከፋፈል ሊሰጥ ይችላል።
በዚህ ሂደት ውስጥ ግን ሥራው ሲሠራ አንዱን የበላይ ሌላውን የበታች በሚያደርግ መልኩ መሆን የለበትም። ቤቶች ሲከፈሉ አንደኛውን ለመጉዳት ሌላውን ለመጥቀም ሳይሆን ያለውን የአቅም ውስንነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ቅሬታ አቅራቢዋ ላይ ችግር ተፈጥሮ ከሆነና ክፍተት ካለም አይቶ ማስተካከል እንደሚቻል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ይመለክታሉ።
ማጠቃለያ
ቅሬታ አቅራቢዋ እንደገለጹልን እኛም በቦታው ሄደን እንደተመለከትነው አኗኗራቸው አሳዛኝና ራሳቸውን ለአደጋ ያጋለጠ ነው። ጉዳዩን አስመልክቶ ምላሽ የሰጠን የወረዳው አስተዳደርም ቤቱን ከፍሎ እንደሰጠ አምኗል። ይህም ከመመሪያ አንፃር እንደሚቻል በማሳያ ተነግሮናል። ነገር ግን ሥራው ሲሠራ የትኛውንም አካል ጉዳት ላይ በማይጥል መልኩ እንደሆነ ነው የተገለጸልን። ከዚህ አንፃር ወይዘሮ ጽጌ ራሳቸው ባስገቡት የቧንቧ ውሃ መስመር እንኳ ተጠቃሚ ያልሆኑበት ብሎም ለሠው ልጅ አስፈላጊ የሚባሉ የመፀዳጃ ቤት መሠረታዊ ግልጋሎቶች ተነጥቀው እንደተሰጡባቸው ተመልክ ተናልና የሚመለከተው አካል መፍትሄ ቢሰጣቸው በሚል እናብቃ።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 17/2011
ፍዮሪ ተወልደ