ርዕሴን አገላብጬዋለሁ። ሲባል የኖረውና ሲሞካሽ የባጀው አባባል “ተገልጋይ/ደንበኛ ንጉሥ ነው” የሚል ስለሆነ። ይህ ደንበኛን በንጉሥነት የሚያንቆለጳጵሰውና ዘመን ያሸበተው አባባል ብዙ ተግዳሮት እየገጠመው እንዳለ እረዳለሁ። መከራከሪያ ሃሳቡ ደግሞ “ደንበኛ/ተገልጋይ ንጉሥ ሳይሆን አጋርና ወዳጅነው” የሚል ነው። ከአገልግሎት ሰጭው ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ይደጋገፋል እንጂ ገና ለገና ደንበኛ ነው ተብሎ “ዘውድ በአናቱ ላይ ሊደፋለት ወይንም ዙፋን ሊዘረጋለት አይገባም” የሚሉ ተሟጋቾች ብዙዎች ናቸው። በአባባሉ ብስማማም በሀገሬ ተጨባጭ ሁኔታ ግን ተገልጋይ ሳይሆን ንጉሥ ሆኖ ካልተከበርኩ ባዩ አገልጋዩ ስለመሆኑ የሚያነታርክ አይደለም።
ወግ ለማሳመር ጠቀስን እንጂ በአባባሉ ተስማማንም አልተስማማን በሀገራችን “የንጉሥ ክብርና ሞገስ” መገለጫ አክሊል ሙዚዬም ከገባ አርባ አራት ዓመታትን አስቆጥሯል። እስካሁን ሳይነካ ያለው የአገልግሎት ሰጭ ግለሰቦችና ተቋማት ንግሥና ብቻ ነው። በአንድ የሀገራችን አንጋፋ ተቋም ዋና መግቢያ በር ላይ የተጻፈው አንድ ማስታወቂያ ለዚህ አባባል በጥሩ አስረጅነት ይጠቀሳል። አነስ ባሉ ሆሄያት “ደንበኛ ንጉሥ ነው” የሚል ማስታወቂያ በተለጠፈበት የዋና መግቢያ በር ጎን “ባለጉዳይ የሚገባው በጓሮ በር ነው!” የሚል ሌላ ማስጠንቀቂያ ተጽፎ አንብቤያለሁ። የመሥሪያ ቤቱ ነገሥታት ሹማምንት በዋና በር፣ ተገልጋዩ በኋላ በር። አይ ተቃርኖ።
ካስፈለገም የኃላፊውን በር እጀታ ባለጉዳዩ እንዳይጨብጥ “መግቢያ በሚቀጥለው በር” የሚል ማስጠንቀቂያም በየቢሮው ሳናነብ የቀረን አይመስለኝም። በማስጠንቀቂያከሚያስደነብሩን ለምን ለቢሯቸው በር መላ እንደማይፈልጉ ሁሌም ግራ ይገባኛል። የV8 መኪናቸውን በጥቁር መሸፈኛ አጥቁረው እነሱ እኛን ተራ ዜጎችን በሚገባ እየመረመሩ እኛ እነሱን የማናያቸውን ጎምቱና አንቱዎችን ብጠቀስ ተንጠራራህ አያሰኝም።
ዛሬም ድረስ በንግሥትና በነገሥታት የሚተዳደሩ እንግሊዝን መሰል ሀገራት አባባሉን ቢጠቀሙ ባልከፋ። ችግሩ ግን እኛ በፕሬዚዳንትና በጠቅላይ ሚኒስትር የምንመራ ሀገር ዜጎች የአባባሉን ዐውድ አሻሽለን “ደንበኛ ፕሬዚዳንት ነው ወይንም ጠቅላይ ሚኒስትር ነው” እንዳንል የትውልድ መሳቂያ እንዳንሆን ሰግተን እንጂ ሳቂታ ባይኖርብን ኖሮ አባባሉ የተሻለ ትርጉም በሰጠን ነበር።
የሀገሬን የአግልግሎት ሰጭ አብዛኛውን ተቋማትና ሠራተኞች ልብ ብዬ ሳስተውል እኛ ተራ ተገልጋይ ዜጎች ንግሥናው እንኳ ቀርቶብን ምነው ከአንድ አፈር እንደበቀሉ ወንድማማች ዜጎች ተከባብረን አገልግሎት ብንቀባበል እያልኩ እቀናለሁ። የንግሥና አክሊል መድፋቱ ቀርቶብን ሳንመናጨቅ ተደስተን የምንወጣበትን ተቋማት እግዜርና መንግሥት ተረዳድተው እንዲያቋቁሙልንም በጸሎት አከል መቃተት እብሰከሰካለሁ።
በሀገሬ ተገልጋይ ሳይሆን አገልጋይ ዙፋን ላይ እንደተቀመጠ ለመግባባት ምስክር መጥራት አያስፈልግም። ንግሥናን እንጂ የማገልገል ሕዝባዊ አደራ ላልገባቸው ወገኖቼና ተቋማት ለምን አባባሉን አፋልሼ ተገልጋይን በተራ መንበር ዝቅ አድርጌ፣ አገልጋይን በዙፋን ላይ ልሰይም ስለቻልኩበት ጉዳይ መከራከሪያዬን ከቀደምት ታሪክ ጋር እያዋዛሁ ምልከታዬን በጥቂቱ ላጋራ።
ንጉሥ ጥሎበት ደጅ ጠኝ ይወዳል። መማለጃና እጅ መንሻ (ያውም በድርድር) ባህሉ ብቻ ሳይሆን የክብሩ መገለጫ ጭምር እንደነበር ፀሐይ የሞቀው እውነታ ነበር። የንጉሥ ግብር እንኳ የሚበላው በሰልፍና በመራኮት አሸናፊ ሆኖ እየተወጣ መሆኑን በቀደምቱ መጣጥፌ ማስነበቤ አይዘነጋም። ንጉሥ ከሕዝብ እርካታ ይልቅ የራሱን ጥቅምና ክብር ይጠብቃል። ቀዳሚዎቹ የሀገራችን ነገሥታት “የሚያስጨንቅ አዋጅና መመሪያ ካወጡ በኋላ የአሳረኛውን ዜጋ ብሶት የሚሰልሉት እረኛ ምን አለ” እያሉ እንደነበር የታሪክ መጻሕፍትን ያላነበበ ወይንም በአፍ ሲተረክ ያልሰማ ይኖራል ተብሎ አይገመትም።
የሀገሬ አገልግሎት ሰጭ ተቋማትና ሠራተኞች የአገልግሎት አሰጣጥ ፍልስፍና በሙሉ የተቃኘው በዚህ መልኩ ነው ለማለት በፍጹም አልደፍርም። ባይሆን ቁጥራቸው አነስ ይላል እንጂ የምር አገልጋዮችማ አይጠፉም። የባለጉዳይ እንግልት የሚከብዳቸው፣ ለተቀመጡበት ኃላፊነትና ለህሊናቸው ክብር የሚሰጡ፣ በዋሉበት የሥራ መስክ ተገልጋዩን አስደስተውና ተመርቀው የሚሸኙ የተባረኩ ባለሙያዎች እዚህም እዚያም እንደ ፈርጥ ፈንጠርጠር ብለው ስለመገኘታቸው ባልመሰክር ጨለምተኛ ያሰኘኛል።
ፊታቸው ለአገልግሎት የፈካ፣ ለጎበኛቸው ባለጉዳይ በሙሉ የመ/ቤታቸውን ገበና የማይዘከዝኩና የደመወዛቸውን አናሳነት እያሳበቁ የተገልጋዩን አንጀት የማይበሉ “ህሊና አደር” ትጉሃን ስለመኖራቸውም በፍጹም አልጠራጠርም። የደመወዝና የጥቅማጥቅማቸው አናሳነት “ደመ ሙቅ” ያላደረጋቸውና ተገልጋያቸውን ተፍለቅልቀው አገልግለው በትህትና የሚሸኙ አብነቶችም ይጠፋሉ ብል እውነትን መቃረን ይሆንብኛል። ከጣሪያ እስከ ድምድማት እነዚህን መሰል ጥቂት መልካሞች አነሱብን እንጂ ቢበዙልን በማን ዕድል። ኢትዮጵያም ጎምጅታ እኔንም አስጎመጀችኝ።
እስኪ ጥቂቶቹን ብቻ ላንሳ፤ ትራፊክ፣ ውሃና መብራት። የትራፊክ መ/ቤትም ሆነ ከውሃና መብራት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት መካከል እነዚህን መሰል ትጉህ ዜጎች ስለመኖራቸው በቅድሚያ ይሰመርልኝ ብዬ ማስታወሻ አኖራለሁ። ስለእውነት ከሆነም እዚህን መሰል መልካም አገልጋዮች በየተቋማቱ ባይኖሩ ኖሮ ውሎ አዳራችን በሙሾ እዮታ እየታጀበ ለሀዘን መሰባሰቢያ ድንኳን ውስጥ ተኮራምተን እንውል ነበር? ይመስለኛል። እናንተን መሰል ሰዎች ዕድሜና ክብረት ይስጥልን።
“ምናለ ደጋጉን ዳግመኛ ቢፈጥረው” የሚለውን የጥላሁን ገሠሠንዜማ ለጊዜው ከማንጎራጎር ተገትቼ የታችኛውን ኅብረተሰብ በየተቋማቱ በገፍ ስለሚያጋጥሙትና መፍትሔ ስለጠፋባቸው ጥቂት ማሳያዎች ልተንፍስ። ተቋማቱን የመረጥኩት የሁሉም ዜጎች የየዕለት የብሶት እንጉርጉሮ ስለሆኑ እንጂ በሌላ የተለየ ምክንያት እንዳልሆነ የመቅድም አቤቱታ አስቀድሜ ወደ ጉዳዬ አዘግማለሁ።
ትራፊኮቻችንና ተቋማቸው
መቼም የመኪና መሪ በጨበጡ በርካታ ዜጎች የሚፈጠሩትን የአደጋዎች ብዛትና አሰቃቂነት፣ የሰውን ሕይወት መና መቅረትና የንብረት ውድመትና በርካታ የአካል ጉድለት የሚያስከትሉ አደጋዎች በምድራችን ላይ የገፍ ጥፋቶች እንደሆኑ አይጠፋኝም። በርካታ አሽከርካሪዎችም ከትራፊክ ፖሊሶችና ከህሊናቸው ጋር የተዘወተረ ድብብቆሽ እንደሚጫወቱም ይገባኛል። እኔም ጸሐፊው የጥፋቱ አካል ሆኜ ተቀጥቼ አውቃለሁ። አዎን የቅጣቱ ቲኬት ሽልማት ይገባኝ ስለነበረ የገንዘብ መቀጮ ከፍያለሁ። ይህን ሁሉ ሃሳብ መደርደሬችግሩ እንደማይጠፋኝ ለማሳመን በማሰብ ነው።
እንደመታደል የምቆጥረውን አጋጣሚም ባስታውስ ክፋት የለውም። ለተወሱኑ ዓመታት በውጭ ሀገር ትምህርት ላይ በነበርኩ ጊዜ የትርፍ ሰዓት ሥራዬ የትራፊክ ማስተናበር ተግባር ነበር። ያውም ቁርጥ የሀገሬውን ዜጋ በሚመስል አለባበስና ትጥቅ። የሙያ ሥልጠናውን የወሰድኩትም እንደ ትርፍ ጊዜ የተማሪ ድጋፍ ሰጭ በጎ ፈቃደኛ ሳይሆን እንደ ዋና ተከፋይ ባለሙያ ተቆጥሬ ነበር። ለነገሩ ክፍያዋም ጠብሰቅ ያለች ነበረች። የሀገሬው የትራፊክ ሙያ ሥነ ምግባርና የአገልግሎት መርህ ደረጃውን የጠበቀ ብቻ ሳይሆን “የትራፊክ ኦፊሰር ነኝ” ማለት በራሱ ክብር ነበር።
ከሀገራችን የትራፊክ ፖሊስ አባላት መካከልም መሰል ባለሙያዎች እንደማይጠፉ አምናለሁ። በርካታ ውስንነቶችና ያልተቀረፉ ችግሮች ቢኖርባቸውም። ሕዝብን ለማገልገል ሰፊ ትከሻ የታደሉትን እነዚህን መሰል የትራፊክ ባለሙያዎች ፊሽካቸውን ሰብስበን ፊር እያደረግን ብናመሰግናቸውና ብንሸልማቸው ያንሳቸዋል እንጂ አይበዛባቸውም።
አንዳንድ ትራፊኮቻችን የሚታሙባቸው የእጅ መንሻና የሕግ ማኮሰሻ ተግባራት ቀንሷል በሚባልበት ደረጃ ያለመድረሱን ሾፌሮች ሲሰባሰቡ የሚያሙበት ዋነኛ አጀንዳቸው ነው። “ደመወዛችን እንኳንስ ለወር መዳረሻ ቀርቶ ለዕለት ጉርስም አይበቃንም” በማለት አንድ ትራፊክ ወዳጄ በቅንነት ያጫወተኝን ምክንያት ትራፊኮቻችን “እጃቸውን ወደ ተገልጋዩ እንዲዘረጉ” ዋነኛ ማመካኛ ይመስለኛል።
አንድ የትራፊክ ፓሊስ አባል አጥፊን በመቅጣት ሥልጣኑና “ሉዓላዊነቱ” ላይ በፍፁም አልደራደርም። ተግባሩና ግዴታው ነውና። ነገር ግን በአቀጣጡ ላይ ሥነ ምግባርና ወታደራዊ ዲሲፒሊን ሲጓደል እንዴት ያሰኛል። አንዳንዴ የቅጣቱን አፈጻጸምና የተቀጭውን ሁኔታ ያስተዋለ ሰው ልክ በሀገር ላይ የከፋ ክህደት እንደፈጠረ ሰው ወይንም በሕዝብ ላይ ከፍ ያለ ወንጀል እንደፈጸመ ተደርጎ ሲስተናገድ ማየት ያማል።
ምሳሌ ልጥቀስ። ባለፉት አራት ወራት ውስጥ ያልተገባ ሥነ ምግባር ባሳየች አንዲትየሴት ትራፊክ አባልና የጉለሌ ክፍለ ከተማ የትራፊክ ፓሊስ አባላት የሆኑ ጥቂት ግለሰቦች ስላሳዩት ያልተገባ ድርጊት ሁኔታውን በዝርዝር ጠቅሼ ለየክፍላቸው በጽሑፍ ለማድረስ ችያለሁ። ሙያው ግድ ስለሚለኝ። የትራፊክ ፖሊስ ባልደረቦቹም እንዲታረሙ ካለኝ ፍላጎት በመነሳት። የተወሰደው እርምጃ ምን እንደሆነ ከአለቆቻቸው ባለመገለጡ ግን ትንሽ ቅር መሰኘቴ አልቀረም። ቢያንስ በትራፊክነት ስሰለጥንእንዲህ እንደሚደረግ ተምሬያለሁ።
ሌላው የተቀጣው አሽከርካሪ ቅጣቱን ለመክፈልና የመንጃ ፈቃዱን ለመውሰድ ያለውን መከራና አሳር መተግበሩ ሳይሆን ማሰቡ በራሱ ያንገሸግሻል። እጅግ የሚያሳዝነውና የሚያሳፍረው አሰራር አንዳችም መሻሻል ሳያሳይ ለዓመታት እንደነበር መቀጠሉ ነው። የተቀጡ አሽከርካሪዎች የመንጃ ፈቃድ የሚከማችበት ሁኔታና ተመርጦ የሚሰጠበት አሠራር ወይ ሀገር ያሰኛል።
ቴክኖሎጂው በተራቀቀበት ዘመን፤ ያውም በፖሊስ ቤት፤ አጀብ። ተደብቆ በራዳር በሚቀርጽ የትራፊክ ፖሊስ አባል ሁለት ኪሎ ሜትር አሳልፈሃል ተብሎ የተቀጣ አንድ ወዳጄ ብግን ብሎ ትራፊክ ፖሊሶቻችን እየተደበቁ ለመቅጣት ከሚሽቀዳደሙ ምናለ ማስተማሩና በቢሯቸው ማደራጀት ላይ ቢረባረቡ ያለኝን አልዘነጋውም። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን እንደፈረደባቸውና እንደለመዱት የትራፊክ ፓሊስ ጽ/ቤቶችንና አሠራራቸውን ጎራ ብለው እንዲጎበኙልኝ እማጠናለሁ።
ከወርልድ ቪዥን መ/ቤት በስተጀርባ ያለውን የቦሌ ትራፊክ ፖሊስ ጽ/ቤትና የጉለሌ ክፍለ ከተማን ብቻ በማየት የትራፊክ ፖሊስ ጽ/ቤቶችን ይዞታ ምንነት በአጭሩ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ዓይቶ መፍረድ ይቻላል። በተለይም ታራሚዎች ባሉበት ግቢ ውስጥ ተዳብሎ ያለውና ተገልጋይ ከእስረኛ ጠያቂዎች ጋር ሰልፍ ይዞና ተጋፍቶ የሚገባበት የቦሌ ክፍለ ከተማ ትራፊክ ጽ/ቤት በኃላፊዎች መታየት ብቻ ሳይሆን በፍጥነት ታርሞ ርምጃው ቢገለጽልን አይከፋም። በቅርቡ ተጀመረ የተባለውና በንግድ ባንኮች ቅርንጫፍ እንዲከናወን የተወሰነው የሙከራ የክፍያ ሥርዓትም በሚገባ ውጤቱ ቢፈተሽ አይከፋም። መቶ ሺህ ብርና የመቶ ብር የትራፊክ ቅጣት የሚከፍሉና የሚያንቀሳቅሱ ባለጉዳዮች ሲተረማመሱ መመልከት ያስፈልጋል። አንድ የባንክ ሱፐርቫይዘር ቅርንጫፎቻችን “የአነስተኛና ጥቃቅን አገልግሎት መስጫ ተቋማት ሆነዋል” ሲሉ ያደመጥኩት ምናልባት ከላይ ስለጠቀስኩት ምክንያት ይሆን እንደሆን ብዬ ገምቻለሁ።
የውሃና የመብራት ፍጆታ አከፋፈልም የሕዝቡን ናላ ያዞረ ሌላው አበሳ ነው። በየቤቱ የሚያግዙ የቤት ሠራተኞች የሰማይ ያህል በራቁበት ሁኔታ በር እየተቆለፈ ሕይወትን በየፊናው ለማሸነፍ ምድረ አዳም በሚራወጥበት ወቅት “መጥተን በሩ ዝግ ስለሆነ የውሃና የመብራት ቆጣሪ ሳናነብ ሄደናል” የሚሉ ፎካሪዎች ሁኔታውን አለማገናዘባቸው ማስተዛዘብ ብቻ ሳይሆን ያበሳጫልም። ወርሃዊ ፍጆታን ለመክፈል ያለውን አበሳ ለማየትማ ወደ ምኒልክ ት/ቤት ገደማ ጎራ ብሎ እንደ ስጥ የሚንቃቃን ተገልጋይ ማየቱ ብቻ መልስ ይሆናል። በዘመነ ቴክኖሎጂ፣ በርካታ ባለምጡቅ አእምሮ ኢኖቬተርስና ቴክኖሎጂስቶች ከትምህርት ቤት እየተመረቁ ባለበት ሀገር ለዚህን መሰሉ ዘመን ያሸመገለ ችግር መፍትሔ ጠፋ ብሎ ማውራት የእንቆቅልሻችንን ግዝፈትና ረቂቅነት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ በሚገባ ያሳያል።
ሕዝብ በኑሮ ውድነት ተማሯል። ሕዝብ በአገልግሎት ሰጭ “ነገሥታትና” ተቋማት ተማሯል። ሕዝብ በፓለቲካ ትርምስና ዕለት በዕለት ስለሚሰማቸው ሀገራዊ ትራዠዲዎች ተሳቋል። ምን ቀረን። እኔ እንጃ።
በማጠቃለያ ምኞት ልሰነባበት። ሙያና ሙያተኞች በብቃት እንጂ በፖለቲካ ሹመት ብቻ ወንበር ላይ የማይኮፈሱበት ሀገር ተፈጥራ ማየት። ሥራውን መሥራት የማይችል “ንጉሥ አገልጋይ” አቅሜ ከተሰጠኝ ወንበር ጋር አይመጣጠንም ብሎ በገዛ ፈቃዱ ሹመቱንም ሆነ ሥራውን ለቀቅሁ ሲል ማድመጥ። በተገልጋዮች የሚሾምና የሚሸለም ታታሪና ጨዋ አገልጋይ በዝቶ መመልከት። ይህ ምኞቴ ለትራፊክ ፖሊሶቻችንም፣ ለውሃና መብራት አገልግሎት ሰጪዎችም፣ እና ለሌሎችም የሚተርፍ ነው። ሰላም እንሁን።
ይህ ዓምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ አስተያየታቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሑፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 17/2011
በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ