በአንድ ቀን 200 ሚሊየን ችግኞችን የምንተክልበት ሐምሌ 22 ቀን አምስት ቀናት ቀሩት። የሃሳቡ አፍላቂና መሐንዲስ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አሕመድ ይህን ካሳኩ በእርግጠኝነት የአጼ ሚኒልክን ራዕይ ካሳኩ የኢትዮጵያ መሪዎች ግንባር ቀደሙ እንደሚሆኑ በግሌ አምናለሁ። እዚህ ላይ የአጼ ሚኒልክ ስም ለምን ተነሳ? በአጭሩ ንጉሠ ነገስታችን የአሁኗ ኢትዮጵያ የደን ሐብት መሠረት ስለሆኑ ነው። አሻራቸውም 125 ዓመታትን ተሻግሮ እነሆ ዛሬም በየቤታችን፣ በየቀዬአችን፣ በየማሳችን… በኩራት ቆሞ እያየነው ነው፤ ባህርዛፍን!
የባህር ዛፍ አመጣጥ፤ እንደመነሻ
አጼ ምኒልክ አማካሪያቸው የነበረውን ፈረንሳያዊውን ሞንዶን ቪዳሌን ጠርተው “ዛፉ አለቀ። እንኳን ለቤት መስሪያ ለማገዶ የሚሆን ጠፋ፣ ምን ይሻላል?” አሉት። “አውስትራሊያ ውስጥ ኤካሊፕቶስ የሚባል አንድ የዛፍ ዘር አለ። ያ ዛፍ ቶሎ የሚደርስ ነው። ያ ዛፍ መጥቶ ቢተከል በ10 ዓመት ውስጥ አገሪቱ ጫካ ትሆናለች” ሲል ምክር ሹክ አላቸው። ምኒልክ በነገሩ ደስ አላቸው። በዛፉ ታሪክ ቢደሰቱም ባንድ ሰው አሳብ እርምጃ አይወስዱም ነበርና ቸናስኪን አስጠርተው የዛፉ ነገር እንዴት ይሁን? አሉትና ሞንዶን ስለነገራቸው ዛፍ ታሪክ አጫወቱት። ቸናስኪም በእርግጥ ጥሩ የዛፍ ዘር መሆኑን መሰከረ። “ይሁን እንዳላችሁት ይሆናል” ብለው ከሸኙት በኋላ ለባቡር ሃዲድ መንገድ ሥራ የመጣውን እንግሊዛዊውን ካፒቴን ኦብሬን አስጠሩትና እንደገና ስለዛፉ ጉዳይ ጠየቁት። ኦብሬም ጥሩ ዛፍ መሆኑን አረጋገጠላቸው። ከዚህ በኋላ ምኒልክ ሦስት የተለያዩ የውጭ ሃገር ሰዎች የመሰከሩለትን የዛፍ ዘር በ1886 ዓ.ም እንዲመጣ አዘዙ።
ችግኙ ተፈልቶ እንደደረሰ ስሙ “የባህር ዛፍ” ተባለ። ከባህር ማዶ የመጣ ለማለት ነው። ምኒልክ ባህር ዛፍ የሚለውን ስም ከሰየሙ በኋላ ሕዝቡ ዛፍ እንዲተክል መቀስቀስ ጀመሩ። እንዲህ ብለውም የአዋጅ ነጋሪት አስጎሰሙ። “የባህር ዛፍ የምትተክል ከሆነ የተተከለበትን መሬት ግብሩን ምሬሀለሁ” ብለው አወጁ። ሕዝቡም በሽሚያ ይተክል ጀመር። እንዲያውም የችግኙ ፈላጊ ከመብዛቱ የተነሳ ተወዶ አርባ ችግኝ ባንድ ጥሬ ብር መሸጥ ጀመረ። አተካከሉም በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በመላ ኢትዮጵያ ተስፋፋ። የአጼ ሚኒልክ ትውልድ ቢያልፍም ያቆዩን የባህር ዛፎች ቅርስ ግን እነሆ ዘመናትን ተሻግሮ ለዛሬው ትውልድ ለመትረፍ በቃ።
ቁጥሮች ይናገራሉ
በኢትዮጵያ በየዓመቱ በአማካኝ 73 ሺህ ሄክታር ደን እንደሚጨፈጨፍ ጥናቶች ይጠቁማሉ። ከ2006 እስከ 2010 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ የተካሄደው ብሔራዊ የደን ምዝገባ ክትትልና ልኬት ጥናት ውጤት መሠረት የአገሪቱ የደን ሽፋን መጠን 15 ነጥብ 5 በመቶ መድረሱ በአዎንታ ቢታይም አሁንም በከፍተኛ ሁኔታ የደን ጭፍጨፋ መኖሩን ጥናቱ ማመላከቱ አስደንጋጭ ሆኗል።
ይህ የደን ሽፋንን የመለካትና የማወቅ ሥራ የደን ጭፍጨፋ የሚካሄድባቸውን ምክንያቶች ለይቶ ለማወቅ ትልቅ ጠቀሜታ አለው። በተከናወነው የልኬት ሥራ በአገሪቱ በዓመት 92 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ደን የሚጨፈጨፍ ሲሆን በምትኩ የሚተከለው የደን ሽፋን መጠን 19 ሺህ ሄክታር ብቻ ነው።
ይህም መልሶ ከሚተከለው የደን መጠን አንጻር ሲታይ በዓመት ውስጥ የሚጨፈጨፈው የደን መጠን በአማካኝ 73 ሺህ ሄክታር ደን እንደሚወድም ያሳያል። ከእርሻ መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሚመጣው የደን ጭፍጨፋ ቀዳሚውን ሥፍራ እንደሚይዝ፤ ይህን ለመከላከል አገሪቱ ባላት መሬት መስኖን በመጠቀም የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ በእርሻ መስፋፋት የሚከሰት የደን ጭፍጨፋን መከላከል እንደሚገባ ጥናቱ አመላክቷል።
በተጨማሪም ለማገዶ በሚል የሚጨፈጨፈው የደን መጠን ከፍተኛ ነው። ይህንንም ለመከላከል የተሻሻሉ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን በመጠቀም ችግሩን መቀነስ እንደሚቻል ጠቅሰዋል። አማራጭ ማግኘት በማይችሉ የገጠር አካባቢዎች ደግሞ የተፈጥሮ ደንን ሳይሆን በሰው ሰራሽ መንገድ የሚተከሉ ዛፎችን ለማገዶነት እንዲጠቀሙ ማድረግ ይገባል።
የጠ/ሚኒስትር ዓብይ አሕመድ የአረንጓዴ ልማት ዕቅድ
ባለፈው ግንቦት ወር አጋማሽ በተካሄደው የግብርናውን ዘርፍ የማዘመን ሀገር አቀፍ የንቅናቄ መድረክ ማጠናቀቂያ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አሕመድ አሁን ላይ ያለው የኢትዮጵያ ደን ሽፋን ሀገሪቱ ካላት የቆዳ ስፋት አንፃር ዝቅተኛ መሆኑን አንስተው መንግሥት የደን ሽፋንን ለማሳደግ የረዥም እና የአጭር ጊዜ ዕቅድ መንደፉን ጠቆም አድርገው ነበር።
እሁድ ግንቦት 18 ቀን 2011 ዓ.ም የ4 ቢሊየን ችግኝ ተከላ መርሐ ግብርን በይፋ ያስጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የችግኝ ተከላ ሂደቱ የሀገሪቱ ወቅታዊ የደን ሽፋን እና መራቆት ያገናዘበ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ካባ ኡርጌሳ የዘንድሮው ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ካለፉት ዓመታት የተለየ መሆኑን አንስተዋል። ዶክተር ካባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሃላፊነቱን ራሳቸው ወስደው ያስቀመጡት አቅጣጫ ከተለመደው አሰራር የሚያስወጣ መሆኑን ይናገራሉ።
የ4 ቢሊየን ችግኝ ተከላ ፕሮግራም ወሰን የገጠርና የከተማ የመሬት ገፅታን አረንጓዴ ማድረግ ሲሆን፥ ለመርሐ ግብሩም ከ11 ቢሊየን ብር በላይ ተመድቦለታል። ከዚህ ውስጥም 45 በመቶው የህዝብ ተሳትፎ በጉልበት አስተዋፅኦ ማድረግ መሆኑ ተገልጿል።
የዚሁ አረንጓዴ አሻራ አካል የሆነው ፕሮግራም የፊታችን ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በአንድ ቀን 200 ሚሊየን ችግኞችን የመትከል ዕቅድ አስከትሏል። ይህ ታሪካዊ ክንውን ለማሳካት በራሳቸው በጠ/ሚኒስትሩ ፊት አውራሪነት የተለያዩ ቅስቀሳዎች ሲካሄዱ ከርመዋል። ብዙ ኢትዮጵያውያን የጠ/ሚኒስትሩ ዕቅድ እንዲሳካም ከወዲሁ የአቅማቸውን በማበርከት ላይ ይገኛሉ።
የደን ይዞታን የማሻሻል ጥቅም
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ወልደአምላክ በውቀት በአንድ ወቅት የአየር ንብረት ተለዋዋጭነትና አስከፊ ክስተቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ያስከተሉትን ተፅዕኖ የሚዳስስ ጥናት ሰርተዋል። ለአብነት ያህል በ1970ዎቹ የተከሰተው ድርቅ 7 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዜጐች ላይ ጉዳት ሲያደርስ ከ300 ሺ በላይ ሰዎችን ለሞት የዳረገ እንደነበር ጥናታቸው ይናገራል። በ1994 ዓ.ም የተከሰተው ድርቅ ደግሞ ምንም አይነት የሞት አደጋ ባያስከትልም 13 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጐች ላይ ጉዳት ያደረሰ ሆኖ አልፏል። በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለው ድርቅም እስካሁን ምንም የሞት ጉዳት እንዳላደረሰ ቢጠቀስም ከ10 ሚሊዮን በላይ የሆኑ ዜጐች ላይ ጉዳት እንዳስከተለ ይነገራል። ጥናቶች እንደሚጠቁሙትም በአብዛኞቹ የአገሪቷ አካባቢዎች በየትኛውም ዓመት ድርቅ ሊከሰት የሚችልበት ዕድል ከ 40 በመቶ በላይ እንደሆነ ነው።
በአገራችን የድርቁን ያህል ተሰልቶ ጉዳቱ ባይታወቅም፣ ሌላኛው አስከፊ የአየር ንብረት ክስተት ተፅዕኖ የሆነው የጐርፍ አደጋ ነው። ሆኖም ከጥቂት የተገኙ መረጃዎች አንፃር በ1953 ዓ.ም 10 ሺ የሚሆኑ ቤቶችን በከፊልና ሙሉ ለሙሉ በማውደም ከ15 ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎችን ቤት አልባ ያደረገ ጐርፍ ተከስቶ እንደነበር ይታወቃል። በ1986 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተከሰተው ጐርፍም 31 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚገመት የቤት ንብረት ውድመትን አስከትሏል። ሌላው አሰቃቂና በመራር ሐዘን የምናስታውሰው በድሬዳዋና ደቡብ ኦሞ እንዲሁም ሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ በአንድ ወቅት ተከስቶ የነበረውና በንብረትና የብዙ ሰው ህይወት ላይ የሞት አደጋ ያስከተለውን ጐርፍ መጥቀስ ይቻላል።
እንግዲህ እነዚህን ተለዋዋጭነቶች፣ አስከፊ የአየር ንብረት ክስተቶችና የሚያስከትሉትን ጉዳት ነው ካለፈው ጊዜ ክስተት ተምረን ለወደፊቱ መዘጋጀት ያለብን። ተለዋዋጭነት እየጨመረ፣ አስከፊ ክስተቶች በተደጋጋሚና በከፍተኛ መጠን እንዲጨምሩ የሚያደርግ የአየር ንብረት ለውጥ ይጠበቃል። በዚህም የተነሳ ከላይ የተጠቀሱት አይነት ጉዳቶች በላቀ መጠን መከሰታቸው አይቀሬ ይሆናል ማለት ነው።
ፕሮፌሰር በአምላክ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ተለዋዋጭነት ሳቢያ ጉዳት እየደረሰባት ያለች አገር መሆኗን ይጠቅሳሉ። ድርቅ ከአየር ንብረት ተለዋዋጭነት፣ ድርቅና ጎርፍ ጋር በመጎዳኘት ከአየር ንብረት ጋር ተያያዥ የሆኑ አስከፊ አደጋዎችን ያስከትላሉ። ወደፊትም በከፍተኛ ደረጃ መጠኑን በመጨመር በተደጋጋሚ ሁኔታ ይከሰታል ተብሎ ይጠበቃል። ይህንን ግምት ውስጥ በማስገባት የአገራችን መንግሥት የአየር ንብረት ተስማሚነት አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችል መሠረት በመጣል እመርታ አሳይቷል። ሆኖም ይህንን ርዕይ መሬት ላይ አውርዶ ለመተግበር የሚገቱ ብዙ ተግዳሮቶች አሉ። ይህንን ተግዳሮት ለማሸነፍ የሁላችንንም ጥረት ይጠይቃል ይላሉ።
እርግጥ ነው፤ ከደን ይዞታችን መመናመን ጋር ተያይዞ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ መሆናችን በአሁን ሰዓት ውጤቱ የሚታይ፤ የሚዳሰስ እየሆነ ነው። አዲስ አበባን ጨምሮ የከተሞች ሙቀት ወይ ጨምሯል ወይንም በተቃራኒው ቀንሷል። የዝናብ ሁኔታውም ከተለመደው ውጪ መሆኑ አኗኗራችንን አናግቶ የዝናብ ጥገኛ የሆነውን ኢኮኖሚያችንን ክፉኛ እየተፈታተነው ይገኛል። በአሁኑ ወቅትም ከ8 ነጥብ 5 ሚልየን በላይ ወገኖቻችን የእለት ዕርዳታ ፈላጊ የሆኑት የአየር ንብረት ለውጡ ካመጣብን ጣጣ ጋር በቀጥታ የተሳሰረ ስለመሆኑ አስረጂ አያስፈልገውም።
በአሁን ሰዓት በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ያለው የችግኝ ተከላ የአየር ንብረት ለውጥ በየጊዜው የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቋቋም፣ በርካቶችን ከቀያቸው የሚያፈናቅለውን ጎርፍ እና የድርቅ አደጋን ለመቀነስ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ የሚሆነው ከዚሁ አንጻር ሲመዘን ነው።
እንደመቋጫ
የአረንጓዴ አብዮት ወይንም ችግኝ ተከላው አገራዊ ፋይዳ ላይ ማንም ጤነኛ ሰው የቅሬታ አስተያየት አይኖረውም። ነገር ግን ከ11 ቢሊየን ብር በላይ ጉልበትና ገንዘብ የፈሰሰባቸው ችግኞችን በአግባቡ እና በባለሙያ ምክርና ታግዞ ማከናወኑ ለውጤታማነቱ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው መናገር ለቀባሪ ማርዳት ቢሆንም ማስታወሱ ይጠቅማል።
አንዳንድ ባለሙያዎች ወደኋላ ሄደው ጭምር በዘመቻ የተካሄዱ የችግኝ ተከላዎችን ከውጤት አንጻር ይመዝናሉ። ውጤቱ ሲያንስባቸውም ሒደቱን “ችግኝ ተከላ ሳይሆን ችግኝ ቀበራ ነው” ሲሉም ጠንከር ያለ ትችት ያቀርባሉ። ሥራው በባለሙያዎች የታገዘ (የሚመራ) እና ሳይንሳዊ አለመሆኑ የትችታቸው መነሻ ነው።
እናም ምን ይደረግ?
ሰዎች በመ/ቤት፣ በአካባቢ፣ በቀበሌ ወይንም በጓደኝነት… ተሰባስበው ችግኞችን መትከላቸው አዲስ ነገር አይደለም። እንዲህ ክረምት በመጣ ቁጥር የሚታየው የችግኝ ተከላ ሥራ ሁሌም ጥድፊያ የተሞላበት ነው። ብዙ ሰዎች ችግኞቹ የተሸፈኑበትን ፕላስቲክ ሽፋኖች እንኳን ሳይገልጡ አፈር መለስ መለስ አድርገው ቀብረው የሚሄዱበት ሁኔታ ጥቂት የሚባል አይደለም። መጀመሪያ ችግኞች ከመተከላቸው በፊት የጉድጓድ ቁፋሮ ዝግጅቱ ቢያንስ ከተከላው ሶስት ቀናት በፊት መከናወን እንዳለበት ባለሙያዎች ይመክራሉ። የተዘጋጁ ችግኞች ለአካባቢው ምን ያህል ተስማሚ ናቸው የሚለው አስቀድሞ በባለሙያዎች መረጋገጥ ይኖርበታል። የተገኘ ችግኝ ሁሉ አንስቶ ተክሎ መሄድ ውጤታማ አያደርግም። ከተከላ በፊት ወደስፍራው የመጡ በጎ ፍቃደኞች መጠነኛ የአተካከል ምክር (ኦሬንቴሽን) በባለሙያዎች ሊሰጣቸው ይገባል። ይህ መሆኑ ችግኞች እንዴት ነው የሚተከሉት የሚለውን ሁሉም እኩል አረዳድ እንዲኖረው ያግዛል። የችግኝ ተከላ ብቻውን ችግኞች እንዲያድጉ አያደርግም። ችግኞች ልክ እንደሰው ልጅ ናቸው፣ ከውልደት እስከ ዕድገታቸው እንክብካቤና ክትትልን ይፈልጋሉ። ሰዎች በየጊዜው መከታተል ባይችሉ እንኳን ከተከላ በኋላም ቢያንስ በወር አንድ ቀን ችግኞችን የመጎብኘትና የመንከባከብ የውዴታ ግዴታን ማስገንዘብ ይገባል።
በእስካሁኑ ተሞክሮ ይህ ሒደት በተሟላ መልኩ እየተተገበረ አይደለም። በመሆኑም ከፍተኛ ጉልበትና ገንዘብ የወጣባቸው የችግኝ ተከላ ፕሮግራሞች ውሃ በልቷቸው ቀርተዋል። አንዳንድ ችግኞችም እንዲሁ በገጠመኝ ሊጸድቁ ቢችሉም ከፈሰሰባቸው ጉልበት፣ ገንዘብና ሐብት አንጻር ሲመዘኑ ውጤታቸው እዚህ ግባ የሚባሉ አለመሆናቸውን ባለሙያዎች በየጊዜው በቅሬታ መልክ ሲናገሩበት የቆዩት ጉዳይ ነው። አንዳንዶች ሒደቱ ከምንም ይሻላል ዓይነት መሆኑንም በመጥቀስ በአጠቃላይ የዘመቻ አካሄድ ሙሉ በሙሉ ወደማውገዝ አድርሷቸዋል።
አሁንም ቁምነገሩ፤ 200 ሚሊየን ችግኝ ወይንም 4 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ማሰብ ብቻ አይደለም። ቁምነገሩ እነዚህን የምንተክላቸውን ችግኞች እንደልጆቻችን እንዴት ተንከባክበን ልናሳድጋቸው፣ እንደሃሳባችን ለፍሬ ልናበቃቸው እንችላለን የሚለውን በእርግጠኝነት መመለሱ ላይ ነው። ይህ ጉዳይ በግልም ሆነ በጋራ ሊያሳስበንና ለመፍትሔውም ልንንቀሳቀስበት የሚገባ ጉዳይም ነው። አጼ ሚኒልክ ካስረከቡን የባህርዛፍ ቅርስ መማር የምንችለው ትልቅ ቁምነገር ቢኖር ትውልድ ተሻጋሪ ሥራ የማከናወን ግዴታ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን ነው። (የጸሐፊው ማስታወሻ፡- ለዚህ ጽሑፍ የጳውሎስ ኞኞ- አጤ ሚኒልክ መጽሐፍ፣ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ፣ www.reliefweb.int, www.fao.org ,የፋና…ዜናና ዘገባዎችን በግብዓትነት መጠቀሜን ከምስጋና ጋር እገልጻለሁ::)
ይህ ዓምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ አስተያየታቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሑፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 17/2011
በፍሬው አበበ