ትችት ሰዎች የሚሰጡን አስተያየት ነው። ይህን አስተያየት ጥሩም መጥፎም የሚያሰኘው ዓላማውና አቀራረቡ ነው። የስነ ልቦና ምሁራን እንደሚሉት ብዙ ጊዜ ሰዎች በመተቸታቸው አይደሰቱም። በዚህ ምክንያትም ለትችቶች የሚሰጡ ምላሾች በጎ አይደለም። የሚያገኙት ምላሽ ጣፈጠም መረረ ተችዎች ምንጩ እንደማይደርቅ ወንዝ ትችት ማፍሰሳቸውን አያቆሙም።
በተለይ “ ወጣ ወጣ ያለች ማሽላ አንድም ለወፍ አንድም ለወንጭፍ “ ብሎ በሚተርት ማህበረሰብ ውስጥ ትችት ዝነኞች፣ ባለስልጣናት፣ ባለሀብቶችና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ተገደው የሚጋቱት ኮሶ ነው። እኛም አይቀርልንም። ሼክስፒር እንዳለው እንደበረዶ ብንነጣም ከትችት አናመልጥም! ታዲያ በወረደባቸው ትችት ከነበሩበት ማማ የሚወርዱ ጥቂቶች አይደሉም። በተወረወረበት ድንጋይ ቤት የሚሰራም አለ።
ዶክተር ኢዮብ ማሞ “የአለማችን አስቸጋሪ ሰዎች” በተሰኘ መጽሐፉ ትችት ማቅረብ የሚቀናቸውን ሰዎች ስውር ወቃሾች፣ አይን አውጣ ወቃሾች እና ሁሉን ወቃሾች በሚል በሶስት ይከፍላቸዋል።
ስውር ወቃሾች በሚተቹት ሰው ፊት ምንም ሳይተነፍሱ ፍጹም ወዳጅ ሆነው የሚቀርቡ፤ ለሌሎች ሰዎች ግን ለተከሰቱ ችግሮች ሁሉ ያን ሰው ተጠያቂ አድርገው ወሬ የሚነዙ ሲሆኑ፤ አይን አውጣ ወቃሾች ደግሞ በሚተቹት ሰው ፊት ሆነው ካለማቋረጥ በሆነ ባልሆነው ክስ ያቀርባሉ። ሁሉን ወቃሾች የሚባሉት የመውቀስ ሱስ ተጠናውቷቸው የአገር መሪን፣ የሃይማኖት አባትን፣ ቤተሰባቸውን፣ የስራ ባልደረቦቻቸውን … አንድም ሳይቀራቸው ሲተቹ የሚውሉቱ ናቸው። አንድን ችግር ለመፍታት ስብሰባ ቢቀመጡ በቅድሚያ ለችግሩ መፈጠር ምክንያት የሆነውን ሰው ጠቅሰው ወቀሳ ካላቀረቡ በስተቀር አንዳች ሀሳብ ጠብ አይላቸውም።
“አንድ ሰው የሚያየው ለማየት የፈለገውን ነው” እንዲሉ፣ እኩል ወደ ሰማይ አንጋጠን አንዳችን “ከፊል ደመናማ” ሌላኛችን “ከፊል ፀሐያማ” ማለታችንን “ብዝኃነት “ ነው ብለን ጉዟችንን በጋራ ከመቀጠል ውጭ ምን ምርጫ አለን ?
በተለይ የመቶ ሚሊየኖች አይን የሚያርፍበት መንግስት የትችት ጭነቶች ማራገፊያ ወደብ ነው። ታዲያ ከሚመራው ህዝብ ትችቶች ሲቀርቡበት ሆደ ሰፊ መሆን እንጂ ተቺዎቹን በጠላትነት ፈርጆ ማሳደድ የለበትም። የኔ የሚሏት አገር እንድትሻሻል በማሰብ ትክክል አይደለም ብለው የሚያምኑት ነገር ሲኖር በቀናነት የሚተቹ ሰዎች ብዙ ናቸው። እንዲህ ላሉ ሰዎቻችን ግልምጫ፣ ተግሳጽና ጅራፍ ደሞዝ መሆን የለበትም። ይህን ካደረግን እንደ አገር የምናጣው ብዙ ነው።
የአንድ ዕድር አባላት በሊቀመንበራቸው ሰብሳቢነት በአካባቢያቸው ስላሉ ስራ አጥ ወጣቶች ውይይት ይዘዋል። አንድ አባት “እነዚህ ወጣቶች ስራ አጥ ስለሆኑ ነው ሱሰኛ የሆኑት። ስለዚህ ባለን አቅም ከመንግስት ጋር ተባብረን የስራ ዕድል ብንፈጥርላቸው ከተዘፈቁበት ሱስ ይወጣሉ” ሲሉ፣ ሰብሳቢው “አፌ ቁርጥ ይበልሎት የኔ ጌታ ልክ ብለዋል” አሏቸው።
ሌላ ሃሳብ ሰጪ ደግሞ “እነዚህ ወጣቶች ሱሳቸውን ለማስታገስ አላፊ አግዳሚውን መዝረፍ ደረጃ ደርሰዋል። ስራ ለመስራትም ዝግጁ አይደሉም። ከዚህ ቀደም ተደራጅተው ወረዳችን ድረስ መጥተው ገጠር ሄደን ጫት መትከል ስለምንፈልግ ብድር ይሰጠን ብለው ነበር። ዶሮ ብታልም ጥሬዋን ማለት ይህ አይደለምን ? እነዚህን ለቃቅሞ ማስጠፈር ነው እንጂ ሌላ መፍትሄ የለም !” ሲል ፣ አሁንም ሰብሳቢው “አፌ ቁርጥ ይበልልህ የኔ ጌታ ልክ ብለሃል” አሉ። በዚህ ጊዜ አንድ እናት “ሰዎቹ የሰጡት ሀሳብ ለየቅል ሆኖ እንዴት ይህንንም ያንንም ትክክል ይላሉ ?” ብለው ጠየቁ። ሰብሳቢው ግንባራቸው ላይ የሚንቆረቆረውን ላብ እየጠረጉ “ ተይኝ ልጆቼን በሰላም ላሳድግበት” አሉ።
መንግስት ተቺዎቹን እየለቀመ የሚያስር ከሆነ “ልጆቼን በሰላም ላሳድግ” በሚሉ አድርባዮች ይከበባል። አድርባዮች ውድቀትን የሚያፋጥኑ ስስ ብልቶች እንጂ የዓላማ ጽናት ያላቸው መካቾች አይደሉም። በተጨማሪም ተቺዎቹን በገዛ እጁ ዝሆን ያደርጋቸዋል። አብዛኞቹ የዓለማችን የተቃውሞ ጎራ ፖለቲከኞች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ጋዜጠኞች ገናና ስም የሚያተርፉትና አላማቸውን ለማሳካት ይበልጥ ኃይል የሚያገኙት ህዝብ ውስጥ ሆነው በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሳይሆን ኮሽ ባለ ቁጥር ማሰርን መፍትሔ አድርገው በሚወስዱ መንግስታት ለእስር በመዳረጋቸው ነው።
ማህተመ ጋንዲ ቅኝ ገዢ እንግሊዞችን ከአገሩ ለማስወጣት ሰላማዊ በሆነ የትግል መንገድ የህንድን ህዝብ እያንቀሳቀሰ በመታገሉ ምክንያት እንግሊዞች በተደጋጋሚ ያስሩት ነበር። ጋንዲም አሳሪዎቹን “እናንተ እንግሊዛውያን ወዳጆቼ ሆይ ! የሰው ልጅ እኮ በአራት ግድግዳ የሚታሰር ግኡዝ ነገር ወይም እንስሳ አይደለም። የሰው ልጅ መንፈሳዊ ነው። እናንተ ብታስሩኝም ጽናቴና እምነቴ ህንዳውያን ወገኖቼን ለነጻነታቸው እንዲታገሉ ኃይል ይሰጣቸዋል” ይላቸው ነበር።
መንግስት ላይ ትችት የሚያቀርብ ሁሉ እንዲስተካከል የሚሻ አይደለም፣ እንዲያውም ህዝብ ተፍቶት እንዲሽቀነጠር ፈላጊው ይበረክታል። ተረኛ ለመሆን ያሰፈሰፈ ተቺ ደግሞ ርእሰ ጉዳይ አይመርጥም።
ግራም ነፈሰ ቀኝ መንግስታትን ለመተቸት የሚነሱ ግለሰቦች፣ ቡድኖችና አደረጃጀቶች ቢያንስ የሚተቹትን መንግስት መሰረታዊ ባህሪ ማወቅ ያለባቸው ይመስለኛል። አለዚያ ውጤት ሊያመጣ የሚችል ጫና ማሳደር አይችሉም፤ ያልጠበቁት ዱብዕዳ ሊወርድባቸውም ይችላል።
አገር የመግዛት ዕድል የገጠማቸው በዛ ያሉ ፖለቲከኞች ከ 500 ዓመታት በላይ ዕድሜ ባለው “ቅዱስ መጽሐፍ” የሚመሩ ናቸው። ኒኮሎ ማኪያቬሊ “አንድ መንግስት መጥፎ ውጤት ከሚያስከትሉ ድርጊቶች ቢርቅ ጥሩ ነው። ካልቻለ ግን አገዛዙን ጠብቆ ለማቆየት አስፈላጊ ሆኖ እስካገኘው ድረስ ከውጉዝ ምግባሮች ማፈግፈግ የለበትም። በጎ ምግባር አገዛዙን ሊያናጋበት መጥፎ ምግባር ደግሞ በተቃራኒው በጸና መሰረት ላይ ሊያቆመው ይችላል” ሲል ይመክራል። አያሌ መሰል ምክሮችን የያዘው “ልዑሉ” የተሰኘው “ቅዱስ መጽሐፍ” በሶስተኛው ዓለም ያሉ መንግስታት ጠዋትና ማታ የሚያጣቅሱት ኮምፓሳቸው ነው። ስለዚህ በስልጣናቸው ላይ ለመቆየት ምንም ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ አይሉም።
ትችትን የሚቋቋሙት ወፍራም ቆዳ ያላቸው ሰዎች ናቸው ይባላል። ስስ ቆዳ ያለን ሰዎች ደግሞ የባለሙያ ምክር ያስፈልገናል። “ሳይኮሎጂ ቱደይ” ትችት በሚቀርብበት ወቅት መደረግ ያለበትን አስመልክቶ ባቀረበው ምክረ ሃሳብ መረጋጋት፤ ትችቱን አምኖ መቀበል፤ ለመረዳት ማዳመጥ፤ ይቅርታ መጠየቅ፤ በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ሌላ ቀጠሮ መያዝና የራስን ሀቅ መናገር አስፈላጊ መሆኑን ይገልጻል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 17/2011
የትናየት ፈሩ