
ጦርነት –መቅሰፍት
የመጋቢት ወር ከገባ አምስት ቀናት ተቆጥረዋል:: ሙቀት ከንፋስ ቀላቅሎ የዋለው ቀን መልከ ብዙ ሆኖ አልፏል:: እየመሸ ነው:: ሰላም ከራቀው አምባ የሚሰማው የከባድ መሳሪያ ድምጽ በዋዛ ይበርድ አይመስልም:: ሰማዩ ደም ለብሷል:: ምድር ቀውጢ ሆናለች:: ጦርነት ያጠላበት አካባቢ ዛሬም በጤና ውሎ አላደረም:: ከነሥጋቱ ቀጥሏል::
በጦርነቱ በርካታ ወታደሮች ከውጊያ ገብተዋል:: በእዚህ ቦታ የእያንዳንዱ ወኔና ጀግንነት ልዩ ነው:: ሁሉም በተሰጠው ድርሻ ግዴታውን መወጣት ይዟል:: ጨለማው እያየለ ፣ ምሽቱ እየገፋ ነው:: የሕይወት መስዋዕትነቱ፣ ደም መፋሰሱ ቀጥሏል:: የጥይቱ ድምጽ፣ የመድፍና ታንክ ትርምሱ አልቆመም:: እዚህም እዚያም በጀግንነት የሚወድቁ ወታደሮች ቁጥር እየጨመረ ነው::
የመጋቢት አቦ …
መጋቢት 5 ቀን 1983:: በደርግ መንግሥትና በሕወሓት ሃይሎች መሀል የትጥቅ ትግሉ ቀጥሏል:: በየቀኑ የሞት ሽረት ትግል ፣ የሕይወት መሥዋዕትነት ይመዘገባል:: በአይበገሬነት የቆሙት ተዋጊዎች ሁሌም ድል ከእጃቸው እንዲያልፍ አይሹም:: በየቀኑ በቆራጥነት ይወድቃሉ:: በየእለቱ አካል ነፍሳቸውን ይሰዋሉ::
የደርግ ወታደር ዓለም ደስታ ምሽቱን በተሰለፈበት የመንደፈራው ራማ ግንባር የተሰጠውን ግዳጅ በብቃት እየተወጣ ነው:: አፍላነቱ ከሀገር ፍቅር ተዳምሮ ወኔውን አግሎታል:: አስራሁለት ሰአት ሲሆን ከአምስት ጓዶቹ ጋር ለቅኝት ዓላማ መውጣት አለበት:: የቅኝት ሥራ ጥልቅ ጥንቃቄን ይሻል:: የጠላትን መውጫ መግቢያ፣ የሰው ሃይልና የመሣሪያ ብዛት፣ አይነት ሰልሎ በቂ መረጃ ለመስጠት ድፍረት፣ ከብልሃት ይጠይቃል::
ስድስቱ የቃኝ ቡድን አባላት ተልዕኳቸውን ሊወጡ ከጠላት ቀጣና ደርሰዋል:: የእነሱ በሥፍራው መገኘት ለብዙሃን ህልውና ወሳኝነት አለው:: ንቁ ዓይኖች፣ በርቀት እያነጣጠሩ፣ በጥልቅ እየቃኙ ነው:: ቀልጣፎቹ ሰላዮች ዓላማቸውን አልሳቱም:: በመጡበት ሥልት ወደፊት ገፍተው ከጫፍ ሊደርሱ ተቃርበዋል::
በአጋጣሚ ግን በቆሙበት የኤርትራ ድንበር አንድ አስደንጋጭ ነገር ተፈጠረ:: በድንገት እንደነሱ ለቅኝት ከወጣ የጠላት ቡድን ዓይኖች ውስጥ ወደቁ:: ቡድኑ ለአፍታ ጊዜ አልሰጣቸውም:: ሳይቀድሙት ቀድሞ የጥይት ናዳ አወረደባቸው::
ወጣቱን ወታደር ተነጣጥረው የተተኮሱ ሁለት ጥይቶች የጀርባ አከርካሪውን አገኙት:: አብረውት ከወጡት ጓዶቹ መሀልም ገሚሶቹ ወዲያውኑ ተሰዉ:: ዓለም በወቅቱ እግሩን የመደንዘዝ ስሜት ያዘው:: ይህ ሲገባው ከወደቀበት ተነስቶ ለመቆም ሞከረ:: እንዳሰበው ሆኖ መራመድ አልሆነለትም:: ለሌቱን ሙሉ በወደቀበት በደም ተነክሮ በህመም አሳለፈ::
ለሌቱን በደፈጣ ያሳለፉ ወታደሮች ማለዳውን የሞቱትን መቅበር፣ የቆሰሉትን ማንሳት ጀመሩ:: ዓለም ያለመቋረጥ ደም ሲፈሰው አድሯል:: በቃሬዛ ተነስቶ ወደ ሆስፒታል እስኪሄድ የደረሰበት ጉዳት የከፋ አልመሰለውም:: ቁስለኛው ወታደር አስራዘጠኝ ቀናትን በአስመራ ቃኘው ሆስፒታል አሳለፈ:: ቆሞ መራመድ ባይጀምርም በእግሮቹ ላይ የተለየ ህመም እየተሰማው አይደለም::
ከቀናት በአንዱ በቅርብ ሲከታተለው የነበረ ሀኪም በዊልቸር ተቀምጦ እንቅስቃሴ እንዲጀምር ምክር ለገሰው:: ዓለም የዶክተሩን ቃል አላስጨረሰውም:: በተለየ መተማመን ተሞልቶ ስሜቱን ሊገልጽ ሞከረ:: ዊልቸሩ እንደማያስፈልግና በቅርቡ ቆሞ መሄድ እንደሚችል በእርግጠኝነት ተናገረ::
ልጅነትን ወደ ኋላ …‹‹ሰገኔት››
ትንሹ ዓለም ደስታ ኤርትራ ‹‹ሰገኔት›› ከምትባል ሥፍራ ልጅነቱን አሳልፏል:: የእሱ ማንነትና መሠረት ሁሌም ከኤርትራዊ ምድር ፣ ከሰገኔት መሬት ይነሳል:: ማንም ስለልጅነቱ ቢጠይቀው ከአንደበቱ የሚወጣው የመጀመሪያ ፊደል ‹‹ሰገኔት›› በሚለው ቃል የተዋዛ ነው:: ዓለም በሰገኔት ውብ ልጅነቱ ታስሯል፣ የክፉ ደግ ትዝታው ተዋቅሯል:: ሁሌም ይህን ሥፍራ ሲያነሳ የክፉ ደግ አይረሴ ትዝታዎች በአእምሮው መስኮት ብቅ ይላሉ:: እነዚህ ታሪኮች የማንነቱ ቀለም፣ የሕይወቱ ስር መሠረት ናቸው:: ባሰባቸው ቁጥር በሳቅ ፈገግታ፣ በኀዘንና ደስታ ይዋጣል::
ዓለም ሰገኔትን እንዲህ ቢያስብም የትውልድ ሥፍራው ግን ከትግራይ ክልል ይነሳል:: ዓለም ገና በጠዋቱ ትግራይን ትቶ ሰገኔት በገባ ጊዜ ኑሮውን ለመግፋት ያልሞከረው የለም:: የልጅነት ትከሻው ከከብት እረኝነት እስከ ሰው ቤት ቅጥር አድርሶታል::
ከጊዜያት በኋላ ግን የወታደር ሚስት የነበረችው ታላቅ እህቱ ስለ ወንድሟ ጉዳት ብዙ ታስብ ያዘች:: ሃሳቧ ዕቅዱን አልሳተም:: ከሰው ቤት እንክርት አውጥታ ትምህርት ቤት አስመዘገበችው:: ዓለም እንደእኩዮቹ ደብተርና እርሳስ ይዞ ቀለም መቁጠር፣ ፊደል መለየት ጀመረ:: ትምህርት ቤት ገብቶ ዕውቀት መቅሰሙ ከዕድሜው መብሰል ጋር መልካም ሆነለት::
ውትድርና…
ዕድሜው ከፍ እያለ ሲሄድ ከዘመኑ የወጣቶች ማህበር አ.ኢ.ወ.ማ ቡድን ጋር ቅንጅት ጀመረ:: በኪነት ተሳትፎው የልቡን ለመሙላት አልተቸገረም:: ዋል አደር ሲል ሃሳቡ ከሌላ መንገድ አደረሰው:: የውትድርናን ዓለም ከልቡ ተመኘው:: ምኞቱ ለቀናት አልዘገየም:: ምዝገባውን አጠናቆ እዛው አስመራ ‹‹አንበሳ ግቢ›› ከተባለ ማሰልጠኛ ቆይታውን አጠናቆ ተመረቀ::
አሁን ዓለም ለሀገር ዘብ የሚቆም፣ ለባንዲራው ፍቅር የሚታገል ቆፍጣና ወታደር ሆኗል:: ወዶና ፈቅዶ በገባበት የውትድርና ሕይወት ተገቢውን ግዴታ ለመወጣት ዝግጁ ነው:: 1982 ዓ.ም :: ዓለም ከውትድርና ሥልጠና በኋላ ዳግም ወደሰገኔት የተመለሰበት ጊዜ ሆነ::
በውትድርና ቆይታው የሰለጠነበት ሙያ በሰርጎገብነት ቅኝት በማካሄድ መረጃዎችን መያዝ ላይ ያተኩራል:: ይህን ግዴታ በአሸናፊነት ለማለፍ ደግሞ ልዩ ጥንቃቄ ይጠይቃል:: ዓለም በግዳጅ ሥምሪቱ ሃላፊነቱን በብቃት መወጣት ችሏል:: አንድ ዓመት ያስቆጠረው ቆይታም ከጦርሜዳ አውሎ ከሚስጥራዊ መረጃዎች አድርሶታል::
ይህ የአንድ ዓመት ውትድርና ከጀግንነቱ የተዘገነ፣ ከማንነቱ ውስጠት የተዋዛ ዕውነታ ነው:: ዓለም ደስታ በፍላጎት በገባበት ሙያ ለአንድም ቀን አዝኖና ተጸጽቶ አያውቅም:: የቆመለት ድንቅ ዓላማ ለሀገር ፍቅርና ፣ ለወገን ክብር መሆኑን ጠንቅቆ ያውቃል::
መጋቢት 5 ቀን 1982 ዓ.ም:: ዓለም አሁን የጦር ቁስለኛ ሆኗል:: በጦርሜዳ ውሎ አከርካሪው ላይ ያገኙት ሁለት ጥይቶች ስለነገ ማንነቱ እያያሰቡት ነው:: አስመራ ላይ ከተኛበት ሆስፒታል ውስጥ ያገኘው ሀኪምም ይህን እውነት ደጋግሞ ይነግረው ይዟል::
ከዶክተሩ ጋር..
በዛን ቀን ጠዋት ዓለም ከዶክተሩ ጋር የጀመረው ውይይት ፈጽሞ ልቡ አልገባም:: ሀኪሙ ያለበትን ደረጃ ስለሚያውቅ ከዚህ በኋላ ዊልቸር መጠቀም ግድ እንደሚል ነግሮታል:: ዓለም ጥይቶቹ ያረፉት በጀርባው እንጂ እግሮቹ ላይ አለመሆኑን ያውቃል:: ህክምናው ሲጠናቀቅም እንደቀድሞው እንደሚቆምና መራመድ እንደሚጀምር እርግጠኛ ነው::
በዕለቱ እንዲቀመጥበት የቀረበለትን ዊልቸር ማየት ያልፈለገው ወጣት በቻለው ሁሉ ዶክተሩን ሊያስረዳው እየሞከረ ነው:: ማዳን ከቻለ ጊዜ ወስዶ እንዲሞክርለትም ይወተውት ይዟል:: ዶክተሩ ግን ቁርጡን ከመናገር አልተመለሰም:: ከዚህ በኋላ የዓለም እግሮች ፈጽሞ እንደማይታዘዙለት ያውቃል:: እናም ‹‹ፓራላይዝድ›› እንደሆነ በግልጽ ነገረው::
ዓለም በወቅቱ ከዶክተሩ የሰማውን እውነታ በቀላሉ ለመቀበል አልቻለም:: በውትድርና ዓለም መቁሰል፣ መድማት ያለ ነው:: ወድቆ መነሳት፣ ሕይወትን ማጣትም ብርቅ አይደለም:: እንዲህ አይነቱ በዊልቸር የመቀመጥ አጋጣሚ ግን ለእሱ ነገን ብዙ ለሚያልመው ወጣት ከአእምሮ በላይ ሆኗል::
ዓለም የወደፊት ዕጣ ፈንታውን ከሀኪሙ አንደበት ከሰማ በኋላ በአስመራ ሆስፒታል ብዙ አልቆየም:: የእሱ ጉዳት ከፍ ያለ በመሆኑ ደብረዘይት ወደሚገኘው የጀግኖች አምባ ሊዛወር ግድ አለው:: ጀግኖች አምባ ሲደርስ በዓይኖቹ የሚያስተውለው እውነታ ውስጡን ሊቀይረው ግድ ሆነ::
ጀግኖች አምባ…
ለጥቂት ጊዜያት ከራሱ ሲታገል፣ ከውስጡ ሲነጋገር የቆየው ዓለም ውሎ አድሮ አእምሮውን አሳመነው:: በጀግኖች አምባ ከእሱ በባሰ እጅና እግሩን ያጣ፣ ሁለት ዓይኖቹ የጠፋ፣ ህሊናውን የሳተ ጉዳተኛ መኖሩን ተመለከተ:: ዓይኖቹ ያሳዩትን ሀቅ ከራሱ አወዳድሮም ማንነቱን ፈተሸ:: እሱ ሁለቱም ዓይኖቹ እጆቹና ጤነኛ ህሊናው ከቦታው አልጎደሉም::
ከምንም በላይ ደግሞ የዛሬዋን ጀንበር ለማየት ያልታደሉ የትግል ጓዶቹን አሰባቸው:: እሱ ዛሬን በሕይወት ቆሟል:: ይህ ሁሉ ሲገባው አምላኩን በምስጋና አከበረ:: የሆነበትን ጉዳትም አምኖ ተቀበለ::
ዓለም የጀግኖች አምባ ቆይታው ብዙ አስተማረው፣ ቆሞ የሚሮጠውን ሳይመለከት ከእሱ በታች የተጎዱትን እየቃኘ ራሱን በጥንካሬ ገነባ:: ይህን ማድረግ ሲጀምር ሰላምና እፎይታ ተሰማው:: ውስጡ ያቀበለው ፈገግታም በፊቱ መፈንጠቅ ጀመረ:: ዓለም ስለአዲስ ሕይወት፣ እያሰበ ራሱን ለበጎ ዓላማ አዘጋጀ ::
ደብረዘይት ለእሱ ካሰበው በላይ መልካም ሆነለት:: አካባቢው ለጦር ጉዳተኞች በጎ እሳቤ አለው:: በግቢው በርካታ ሙያዎችን መማር፣ ልምድ መቅሰም ይቻላል:: በቀለም ትምህርት ልቆ ለመሄድም ሁኔታቸው ምቹ ናቸው:: ይህ ሁሉ እይታ ለዓለም የአዲስ መንገድ ጅማሬ፣ የበጎነት ምልክት ነው :: አሁን ውስጠቱ የደስታ ማረፊያ ሆኗል::
ከለውጥ ማግስት…
ይህን ስሜት እያጣጠመ ሳለ ግን ሁኔታዎች በድንገት ተቀየሩ:: ጊዜው የመንግሥት ለውጥ የተካሄደበት ማግስት ነበር:: የቀድሞው ጀግኖች አምባ በነበረበት እንዳይቀጥል የሚያስገደድ አጋጣሚ ሊከሰት ግድ ብሏል:: ይህ አጋጣሚ እነዓለምን ከነበሩበት አንስቶ ወደሌላ ሥፍራ አሸጋግሯል:: ወደ አዲስአበባ የአካልጉዳተኞች ተሀድሶ ልማት ማዕከል::
ሕይወት በድንገት ከሰፊው ዓለም ወደ ጠባቡ አጸድ ተቀየረ:: ይህ ጊቢ እንደ ጀግኖች አምባ አይደለም:: ቢሆንም ግን በርካታ የጦር ጉዳተኞችን አሳባስቦ ይዟል:: በዚህ ሥፍራ ከንጉሡ ዘመን እስከ ሶማሌ ወረራ ፣ ከደርግ ውጊያ እስከ ኢትዮ – ኤርትራ ጦርነት በተጋድሎ የቆዩ ጀግኖች አርፈውበታል:: ሁሉም በተለያዩ የአካል ጉዳት ውስጥ የሚገኙና በመንግሥት ድጋፍ የሚታገዙ ናቸው::
ዓለም በዚህ ሥፍራ ለሃያ ስድስት ዓመታት ቆይቷል:: እነዚህ ዓመታት በኑሮ ውጣረድ ብዙ ተምሮባቸዋል:: ሕይወት በክፉና ደግ ሚዛን ብታስቀምጠውም ረጅሙ የዕድሜው ዘመን የተቆጠረው ከአካል ጉዳቱ በኋላ ባለው ጊዜ ሆኗል:: ይህ አጋጣሚም ማንነቱን በያዘው አቅጣጫ እንዲቃኝ አስችሎታል::
ቀደም ሲል በተሀድሶ ማዕከሉ ሁለት መቶ ሰባ የሚጠጉ የጦር ጉዳተኞች ይኖሩ ነበር:: በዕድሜ ብዛትና በህመም፣ ያለፉትን ጨምሮ በራሳቸው በግል ምክንያት ተቀናንሰው አሁን አንድ መቶ ሃምሳ ያህል ቀርተዋል:: ሁሉንም ፡‹‹እህ!›› ብሎ ሰማቸው በእያንዳንዳቸው ውስጠት ድንቅ ታሪክ ተከትቧል:: ከተጎዳው አካላቸው ጀርባም አይረሴ የሀገር ታሪክ ተጽፏል::
ከሃያ ስድስት ዓመታት በኋላ
ዓለም ላለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት በማዕከሉ እሱን ከመሳሰሉት ወገኖቹ ጋር ተመሳሳይ ሕይወትን ሲጋራ ቆይቷል:: ኑሮና የወደፊት ዓላማውን ግን በግቢው ውስጥ ብቻ ተወስኖ እንዲቀር አልፈቀደም:: ዓለም ጎበዝ ስፖርተኛ ነው:: ዘወትር ክብደት ያነሳል፣ የጠረጴዛ ቴኒስ ይጫወታል::
አካል ጉዳቱን አሳቦ ተቀምጦ መዋል፣ መቆዘምን አይሻም:: ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ የቅርጫት ኳስ ሥልጠና እየሰጠ ሌሎችን ያበረታል:: የማዕከሉ የውሎ አዳር ኑሮ በአንድ ሥፍራ መወሰን ብቻ አይደለም:: ከግቢው መውጣትና ፣ ቤተሰብ መጠየቅን ፣ መዝናናትን ይፈቅዳል:: አጋጣሚውን ተጠቅመው ብቸኝነታቸውን የረሱ ፣ በትዳር የተጣመሩ በርካቶች ናቸው::
ጎልማሳው ዓለም ሁሌም ማዘን፣ መከፋት ከፊቱ አይነበብም:: በቻለው አቅም ከሕይወት ጣዕም ጣፋጯን ለይቶ ለመቅሠም ይሞክራል:: ይህ ጥንካሬው ደግሞ የኑሮውን መልክ አስውቦለታል:: ከዓመታት በፊት መንግሥት በሰጠው ዕድል በዕጣ የጋራ መኖሪያቤት አግኝቶ የቤት ባለቤት ሆኗል::
ከአስር ዓመታት በላይ አብራው በትዳር የቆየችው ባለቤቱ ለእሱ መልካም ወይዘሮ ነች:: አካል ጉዳተኛ የዊልቸር ተጠቃሚ ነው ብላ አልተወችውም:: ባሏን አክባሪ፣ ለቃሉ ተገዢ ሆና በፍቅር ዓመታትን ዘልቃለች:: ዓለም ስለ ባለቤቱ ትዕግስት ፋና መልካምነት ለመናገር ቃላት አይበቃውም:: በእሷ መኖር የእሱ ማንነት ተቃንቷል:: የሕይወት መንገዱ ሰ ምሯል::
ዛሬን …
ዓለም ማንም ከጉዳቱ በኋላ ተሰብሮና አንገቱን ደፍቶ መኖር እንደሌለበት ከሚያምኑት ወገን ነው:: ይህ የሕይወት መርህም ከስፖርተኝነቱ አልፎ ሀብት ንብረት እንዲያፈራ ፣ በራሱ አቅም እንዲፈጥን ምክንያት ሆኗል:: ዛሬ ዓለም የሁለት እግሮቹ አለመስራት መኪና ከማሽከርከር፣ ሌሎችን ከማገዝ አላገደውም:: ከቀረጥ ነጻ ባስገባው አውቶማቲክ መኪና ባሻው ጊዜ የዕለት ገቢውን ሰርቶ ይውላል::
በተሀድሶ ማዕከሉ አብሮ ከመኖር ባለፈ እውነተኛ ኢትዮጵያዊነት ይንጸባረቃል:: የአንዱ ሕመም ለሌላው እየተጋራ ስሜትን በእኩል መካፈልም የተለመደ ባህል ነው:: በዚህ ግቢ ያሉ ነፍሶች በተመሳሳይ መንገድና ዓላማ ተያይዘው አልፈዋል:: እነሱን የመሰሉ ብርቱዎች ደግሞ ትናንትን ተሻግረው ዛሬ ላይ ሲቆሙ በብዙ አይታመኔ ማሳያዎች ተሸጋግረው ነው::
አይታለፍ ይመስለውን የሕይወት ሸካራ መንገድ በፈተና ሞርደው ስለነገ ሲያስቡም ያለፉበትን ማንነት ለሌሎች ሕይወት መስታወት በማድረግ ነው:: ልክ እንደ ዓለም ደስታ የጥንካሬ መንገዶች::
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 22 ቀን 2017 ዓ.ም