አካባቢው
ደመና የለበሰው ሰማይ የፀሐይ ብርሃን ሙቀቱን ሊያግድ አልተቻለውም። በቆላማው መሬት ሰዎች ወዲህ ወዲያ ይወራጫሉ። ሁሉም በየፊናው የኑሮ ቀዳዳን ለመድፈን ደፋ ቀና በሚልበት በዚያ ሃሩር ከጭንቅላቷ ላይ የጠመጠመችው ጨርቅ እንደ ሳር ቤት ጉልላት ቆለል አሳምራ ጠፍራዋለች። ወገቧን በመቀነት ሁለት ዙር አገልድማበት ጠበቅ አድርጋ ታጥቃለች። እንደ አራስ ነብር ወዲህ ወዲያ ዓይኗን ጣል እያደረገች አረሙን ስትመነግለው ከኑሮ ጋር ግብግብ ስለመግጠሟ ምስክር አይሻም። እንደ ተወርዋሪ ኮኮብ ብድግ ብላ በዶማዋ መሬቱን ጫር! ጫር! ስታደርግ ከጠላት ለመግጠም ምሽግ የምትቆፍር እንጂ ማሳውን የምትኮተኩት አይመስልም።
ይህች እንስት ዛሬ ኑሮዋን በማሸነፍ ስለነገ ብዙ ማለም ትፈልጋለች። ትናንት እጅግ መራር ቀናቶችን አሳልፋለች፤ ዛሬም በመራር ሕይወት ውስጥ እየተጓዘች ነው። ምንም እንኳን እንደ ትናንትናው እጅግ የመረረ ባይሆንም። ታዲያ ትናንት፣ ከትናት ወዲያ ያለፈችባቸውን ቀናቶች ስታስታውስ ሁኔታዎች ፈፅሞ ከህሊናዋ አይጠፉም፤ ፈጽሞ ዳግም ማየትም አትፈልግም።
ወይዘሮ እመቤት መኮንን ትባላለች። በአንኮበር ወረዳ ሞሄ አምባ በሚባል አካባቢ ነው የተወለደችው። በ40ዎቹ መጀመሪያ የምትገኘው ይህች እናት ለወላጆቿ የመጨረሻ ልጅ ናት። እናት እና አባቷ በልጅነቷ ስለሞቱ ኑሮ እንደ ገብስ ቆሎ ፍትግ አድርጎ መጫወቻ አድርጓታል። እርሷም ላለመሸነፍ ብዙ ትፍጨረጨራለች።
ወድቆ ማመስገን
በሕይወቷ ውስጥ ከባድ የውድቀት ጊዜ ምትለው አላት። ከዓመት ዓመት የምትለብሰው፤ የምትቀምሰው ነገር ባጣች ጊዜ ከገበያ ገበያ እየኳተነች የልጆቿንና መላ ቤተሰቧን ሕይወት ለመታደግ ብዙ ለፍታለች፤ ረጅም መንገድ በእግር እየተጓዘች ለመነገድ ፈግታለች። በተለይም ደግሞ ልጆቿ ከትምህርት ዓለም እንዳይሰናከሉባት አቅሟን አሟጣ ተጠቅማለች። በዚህ የውድቀት ጊዜ እርሷ በበጎ ወስደዋለች። በኑሮ ክፉኛ መፈተኔ የጥንካሬ ምንጭ ሆኖኛል ስትል ውድቀትን ታመሰግናለች። ምንም እንኳን ዛሬም በፈታኝ ሕይወት ውስጥ ብትሆንም ካለፉት ዓመታት አኳያ ግን ለውጡ ሰፊ እንደሆነ ትናገራለች። የሆነው ሆኖ ውድቀትን አሜን ብላ ያለመቀበሏ ዛሬም ጠንካራ አድርጓታል። ግን ደግሞ አንዳንዴ ውድቀትን ማመሰገን ጥሩ ነው ትላለች።
ያላለቀ ዕዳ
ወይዘሮ እመቤት መኮንን የሕይወት ውጣ ውረድን ለማሸነፍ ብዙ ታግላለች። መሬቷ አንድ ቀጠላ (አንድ ገመድ) ብቻ በመሆኑ የዕለት ጉርስ ለመሸፈን ተቸግራለች። ታዲያ ኑሮዋን ለመደጎምና የልጆቿን ሕይወት ለመታደግ ስትል ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ድርጅቶች ብር ተበድራ ሸምታ በልታለች። ከአማራ ብድር ቁጠባ ተቋም (አብቁተ) 16ሺ ተበድራለች። ወለዱ እየጨመረ ሄዶ 20ሺ ብር ደርሶ ነበር። በወቅቱ እርሷ ያደረገችው በ16ሺ ብር በሬ ገዝታ ነበር። ግን እዳውን መክፈል ስለነበረባት በሬውን ሸጣው 10ሺህ ብር ከፈለች። ግን አሁንም 10ሺ ብር ዕዳው አልተከፈለም። ወለዱ እንዳለ እየጨመረ ነው። ወለዱ እና ገቢዋ ባለመመጣጠኑ ፈተና ሆኖባታል። ታዲያ በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ አንዳች ተዓምር ካልተፈጠረ በደካማዋ ጎጆ ውስጥ ሆና ምንም አድርጋ እዳውን እንደማትከፍል ትገነዘባለች። ወይዘሮ እመቤት እናትና አባቷ በልጅነቷ በመሞታቸው የሚያግዛት አላገኘችም። ታዲያ አሁን እናትና አባት የሆናት በአካባቢው ያለችው ‹‹አፋጀሽኝ›› የምትባለው ውሃ ናት።
ትዳር የታደገ ፕሮጀክት
ወይዘሮ እመቤት ትምህርት አልተማረችም፤ ባለቤቷም እንዲሁ ከአስኳላ ጋር አይተዋወቅም። ኑሮ ከብዷቸውና ከባለቤቷ ጋር መስማት አቅቷት ፍቺ ጠይቃ ነበር። የትዳር አጋሯም በኑሮው ደስተኛ ባለመሆኑ ትዳሩን ለማፍረስ መወሰኑን ታስታውሳለች። ሌት ተቀን ቢለፉም ምንም ለውጥ የለም። መሬቱ ጠባብ ከመሆኑ የተነሳ በዓመት ከሦስት ጭነት በላይ ሊያገኙ አልቻሉም። ታዲያ ይህ ነገር ሁለቱንም አታካተቸው። ‹‹ያማረ፤ የከበረ ትዳር ይሁንላችሁ›› ተብለው ተመርቀው፤ የመረረ ትዳር ሆነባቸው። ምርቃቱ ርግማን ይመስል ሁለቱም ተሰለቻቹ። በመጨረሻም ሊፋቱ ከዳር ደረሱ።
በአጋጣሚ ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የክርስቲያናዊ ልማት ተራድኦ ኮሚሽን በአካባቢው የልማት ሥራዎችን ለማገዝ ሲንቀሳቀስ እርሷ ከተጠቃሚዎች አንዷ ሆነች። ኮሚሽኑም በአካባቢው ‹‹አፋጀሽኝ›› የምትባለውን ውሃ ወደ መስኖ ሥራ እንድትገባ አደረጓት። ከዚያም ይህ ፕሮጀክት ሊፈርስ የተቃረበውን ትዳር ለመታደግ ደረሰ።
በአንድ ቀጣላ መሬት
በአሁኑ ወቅት በአንድ ቀጠላ መሬት ሦስት እና አራት ጊዜ እያመረተች ነው። ባለፉት ስድስት ወራት በዚህች መሬት ላይ ጎመን እና ሽንኩርት አምርታ በጥሩ ዋጋ ሸጣለች። ላለፉት ሦስት ዓመታት ከዚህ መሬት ላይ ባገኘችው ገቢ ቆርቆሮ ቤት ሠርታለች፤ ቀድሞ የነበራትን ሳር ቤት ደግሞ ወደ ማዕድ ቤት ቀይራዋለች። አሁንም በዚህች መሬት ላይ ያገኘችው እያንፈጫፈጨች ልጆቿን ታስተምራለች። በተጨማሪም በሳምንት 100 ብር እቁብ እየጣለች 10ሺ ብር ወጥቶላታል። ከዚያም ሦስት ሺህ ብር ጨምራ በ13 ሺ ብር በሬ ገዝታለች። ታዲያ ለዚህ ሁሉ ጥረቷ ታክሎበት የ‹‹አፋጀሽኝ›› ውሃ በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋሉ አንዷ የበረከት ምንጭ ነው ትላለች።
365 ቀን ያለዕረፍት
በአሁኑ ወቅት ‹‹አፋጀሽኝ›› አካባቢ ያለው መሬት ሆነ ሰው በዓመቱ 365 ቀን ዕረፍት የለውም። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የክርስቲያናዊ ልማት ተራድዖ ኮሚሽን ወደ አካባቢው ከመጣ በኋላ አዲስ የሥራ ባህል ተለምዷል ትላለች። አካባቢውም ከደረቅ ወደ ልምላሜ ተቀይሮ የበርካቶች ዓይን ማረፊያ ሆኗል። ጥላችሁት ጥፉ! ብረሩ! ብረሩ! ያሰኝ የነበረው አካባቢ፤ ዛሬ ልምላሜው ይጣራል። እኔም ይህን ልምላሜ ስመለከተው የሰው ልጅ ከሠራ እንደሚለወጥ ተገነዝቤያለሁ፤ ትዳሬንም ከመፍረስ ታድጌያለሁ። የልማት ድርጅቱ ወደ አካባቢው ከመጣ ጀምሮ የዘመሙ ቤቶችም ሆኑ ሊፈርሱ የተቃረቡ ትዳሮች ተቃንተዋል ትላለች የራሷን ተሞክሮ እንደ አብነት በማንሳት።
አዲስ አበባ ታዘብኩሽ
ወይዘሮ እመቤት አዲስ አበባ ተመላልሳ ዘመድ ጠይቃለች፤ እንዲያውም በአዲስ አበባ ለመከተም አስባም ነበር። አዲስ አበባ ከአራዳ አካባቢ የቁልቁለት እያየሁ ታዘብኩት ትለላች። ስፍር ቁጥር የሌለው ሰው እንዲያ ሲርመሰመስ ለእኔ ለባላገሯ ግርምት ፈጠረብኝ በማለት ትገልፃለች። ‹‹ከሰው ብዛት ያልተናነሳ የመሂናው ብዛት ግራ ያጋባል። ድምጡ ሁሉ ይረብሻል፤ ህንጣ እንጂ አንድም ቤት ደስ የሚል ነገር የለውም። ኋላ ሳስበው እዚሁ እዱር መዋል ይሻላል ብዬ ወደ አንኮበር አገሬ ተመለስኩ›› ስትል የአዲስ አበባ ትዝብቷን ትናገራለች።
አዲስ አበባ የተማረ ሰው የሚውልባት፤ የሚኖርባት እንጂ ለእኔ ቦታ የላትም የምትለው እመቤት፤ ልጆቿ ግን ትምህርታቸውን ጨርሰው በዚህች ከተማ ጥሩ ሥራ እንዲኖራቸው ትመኛለች።
እቅዶች
እመቤት ኑሮ አሸንፏት ሳይሆን፤ እርሷ ኑሮን አሸንፋ ለበርካታ ሰዎች ተምሳሌት የመሆን ትልቅ ህልም አላት። እርሷ ከፊደል ጋር ሳትተዋወቅ መሃይም መሆኗ ያበሳጫታል፤ ታዲያ ይህን ህልም በልጆቿ ዕውን ማድረግ ትፈልጋለች። ለዚህም ያገኘችውን ሁሉ ለልጆቿ ትምህርት ቅድሚያ ትሰጣለች። እርሷ አዲስ አበባ ሂዳ ደማቅ ከተማ አይታ በሁኔታዋ እንደተገረመች አካባቢዋ ከተማ ሆኖ ማየት ትፈልጋለች፤ ወደ ከተማም ጠጋ ብላ ቤት ለመሥራት ታስባለች።
እመቤትና መሰሎቿ ባለመማራቸው ብድር ተበድረው ለረጅም ዘመናት በእዳ ውስጥ እንዲዳክሩ ያደረጋቸውን አሠራር ተሻሽሎ ማየት ትመኛለች፤ ይህንንም አንድ ቀን ልጆቻቸው እንዲያስተካክሉ አሊያም ደግሞ ብድር ሲበደሩ ምን እንደሚሠሩበት ቀድመው እንዲገነዘቡ ትሻለች። ለዚህ መድሃኒቱ ደግሞ ትምህርት ስለሆነ ልጆቿን ታስተምራለች። እመቤት ከዚህም ሌላ ብዙ ነገር ታስባለች። ሰፊ እርሻ ኖሯት ትርፍ ምርት ማምረት። መንግሥትም እንዲህ ጥረት ለሚያደርጉ ሴቶች የራሱን ድጋፍ ማድረግ እንዳለበትም ትጠቁማለች። እመቤት በኑሮ ውጣ ውረዷ ውስጥ ያየቸውን ነገር ሁሉ ወደ መልካም የመቀየር ህልም አላት።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሀምሌ 13/2011
ክፍለዮሃንስ አንበርብር