የ19 ዓመቷ አና ድንገት በመውደቋ ምክንያት በጣም ኃይለኛ የወገብ ሕመም የጀመራት አኖሬክሲያ ነርቮሳ ከተባለ የአመጋገብ ችግር እንዳገገመች ነበር። የአከርካሪዋ ሁለት አጥንቶች የተሰበሩ ሲሆን ይህም ቁመቷ በ5 ሴንቲ ሜትር እንዲያጥር አድርጓል። ለዚህ መንስኤው ኦስቲዮፖሮሲስ ወይም የአጥንት መሳሳት ነበር።
“ኦስቲዮፖሮሲስ” ቃል በቃል ሲተረጎም “የተበሳሳ አጥንት” የሚል ፍቺ አለው። ይህ ሕመም ድምፅ አልባ ተብሎ የተጠራው አጥንት በድንገተኛ ጭነት፣ ግጭት ወይም መውደቅ ምክንያት እስኪሰበር ድረስ መሳሳቱን የሚጠቁም ምልክት ስለማይታይ ነው። ስብራቱ በአብዛኛው የሚከሰተው ዳሌ፣ ጎድን፣ አከርካሪ ወይም የእጅ አንጓ ላይ ነው። አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ኦስቲዮፖሮሲስን የሚያያይዙት አቅመ ደካማ ከሆኑና በዕድሜ ጠና ካሉ ሴቶች ጋር ነው። ይሁን እንጂ ከአና ሁኔታ ማየት እንደሚቻለው ኦስቲዮፖሮሲስ ወጣቶችንም ሊያጠቃ ይችላል።
ከባድ የጤና ችግር
ዓለም አቀፍ የኦስቲዮፖሮሲስ ማኅበር እንደዘገበው “በአውሮፓ ኅብረት አገሮች በየ30 ሴኮንዱ አንድ ሰው በኦስቲዮፖሮሲስ ምክንያት አጥንቱ ይሰበራል።” በዩናይትድ ስቴትስ 10 ሚሊዮን የሚያህሉ ሰዎች ኦስቲዮፖሮሲስ ያለባቸው ሲሆን 34 ሚሊዮን የሚያህሉ ሰዎች ደግሞ አጥንታቸው በመሳሳቱ ምክንያት ለዚህ በሽታ ይጋለጣሉ የሚል ስጋት አለ። ከዚህም በላይ የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የጤና ተቋም እንደገለጸው “50 ዓመት ወይም ከዚያ በላይ ከሆናቸው ሁለት ሴቶች መካከል አንዷ አሊያም ከአራት ወንዶች መካከል አንዱ በሕይወት ዘመናቸው ውስጥ ከኦስቲዮፖሮሲስ ጋር ተያያዥነት ያለው የአጥንት መሰበር ያጋጥማቸዋል።” ለወደፊቱም ቢሆን ሁኔታው እንደሚሻሻል የሚያሳይ አዝማሚያ አይታይም።
የዓለም ጤና ድርጅት ዜና መጽሔት በኦስቲዮፖሮሲስ ምክንያት የሚደርስ ስብራት በመላው ዓለም በቀጣዮቹ 50 ዓመታት በእጥፍ እንደሚጨምር ገልጿል። ይህ ትንበያ፣ እየጨመረ ይመጣል ተብሎ የሚታሰበውን የአረጋውያንን ቁጥር መሠረት ያደረገ ሳይሆን አይቀርም። ያም ሆኖ የሚያስከትላቸው ውጤቶች በጣም የሚያስፈሩ ናቸው። ኦስቲዮፖሮሲስ ለአካል ጉዳት ወይም ለሞት የመዳረጉ አጋጣሚ በጣም ሰፊ ነው። ሃምሳ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ ሆኗቸው የዳሌ አጥንት ስብራት ካጋጠማቸው ሰዎች መካከል ወደ 25 በመቶ የሚሆኑት በሚደርስባቸው የጤና ችግር ምክንያት በቀጣዩ ዓመት ይሞታሉ።
አንተንስ ያሰጋህ ይሆን?
የቅርብ ጊዜ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሰዎች በአብዛኛው በዚህ በሽታ የሚያዙት በዘር ውርስ ነው። ወላጆች የዳሌ አጥንት ስብራት አጋጥሟቸው ከነበረ ተመሳሳይ የሆነ ስብራት በልጆች ላይ የመድረሱ አጋጣሚ በእጥፍ ይጨምራል። ሌላው መንስኤ አንድ ልጅ በእናቱ ማህፀን እያለ የተመጣጠነ ምግብ ባለማግኘቱ የተነሳ ከልጅነቱ ጀምሮ የአጥንት መሳሳት የሚያጋጥመው መሆኑ ነው። የዕድሜ መግፋት ደግሞ በኦስቲዮፖሮሲስ የመጋለጥን አጋጣሚ ይጨምራል። በአብዛኛው በዕድሜ የገፉ ሰዎች አጥንታቸው እየደከመ ይሄዳል። እንደ ኩሺንግ ዲዚዝ፣ የስኳር በሽታና እንቅርት የመሰሉ የጤና ችግሮችም ለኦስቲዮፖሮሲስ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ።
ሴቶች በሚያርጡበት ጊዜ አጥንት እንዳይሳሳ የሚከላከለው ኤስትሮጅን የተባለው ሆርሞን ይቀንሳል። በኦስቲዮፖሮሲስ የሚሠቃዩ ሴቶች ቁጥር ከወንዶቹ በአራት እጥፍ ያህል የሚበልጠው በዚህ ምክንያት ነው። የአንዲት ሴት ዘር አመንጭ አካል (ኦቫሪ) በቀዶ ሕክምና በመወገዱ ምክንያት የኤስትሮጅን ማነስ ስለሚፈጠር ከዕድሜ በፊት ማረጥ ሊያጋጥም ይችላል።
አንድ ሰው የአመጋገብና የአኗኗር ዘይቤውን በመለወጥ ለኦስቲዮፖሮሲስ የመጋለጥ አደጋን ሊቀንስ ይችላል። ካልሲየምና ቫይታሚን ዲ ያነሰው አመጋገብ ለአጥንት መሳሳት አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ ሁኔታዎች አንዱ ነው። ብዙ ጨው መመገብም ሰውነት ብዙ ካልሲየም እንዲያስወጣ ስለሚያደርግ ለአጥንት መሳሳት መንስኤ ይሆናል። ከመጠን በላይ አልኮል መጠጣት የአመጋገብ ሥርዓት ስለሚያዛባ ለአጥንት መሳሳት አስተዋጽኦ ያደርጋል።
በመግቢያው ላይ የተጠቀሰችው አና በኦስቲዮፖሮሲስ የተጠቃችው የአመጋገቧ ሥርዓት ስለተዛባ ነው። ይህ የአመጋገብ ልማዷ የአልሚ ንጥረ ነገሮች እጥረት፣ ከመጠን ያለፈ የክብደት መቀነስና የወር አበባ መጥፋት አስከትሎባታል። በዚህም የተነሳ ሰውነቷ ኤስትሮጅን የተባለውን ሆርሞን ማመንጨት ስላቆመ አጥንቷ ሊሳሳ ችሏል።
አንድ ሰው በኦስቲዮፖሮሲስ እንዲጠቃ የሚያደርገው ሌላው ምክንያት በቂ አካላዊ እንቅስቃሴ እንዳያደርግ እንቅፋት የሚሆን የአኗኗር ዘይቤ መከተሉ ነው። በተጨማሪም ማጨስ በአጥንት ውስጥ የሚገኙ ማዕድናትን ስለሚሸረሽር ለአጥንት መሳሳት ችግር ከሚያጋልጡት ዋነኛ መንስኤዎች መካከል አንዱ ነው። የዓለም ጤና ድርጅት እንደገለጸው የዳሌ አጥንት ስብራት ከሚደርስባቸው ስምንት ሰዎች አንዱ ይህ አደጋ የሚያጋጥመው በማጨስ ምክንያት ነው። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ማጨስ ሲያቆም አጥንቱ የመሸርሸሩና ለስብራት የመጋለጥ ዕድሉ እንደሚቀንስ ጥናቶች ያመለክታሉ።
ኦስቲዮፖሮሲስን መከላከል
ኦስቲዮፖሮሲስን ለመከላከል የሚያስችል የመጀመሪያው እርምጃ መወሰድ ያለበት በልጅነትና በጉርምስና ዕድሜ ነው። ምክንያቱም የአንድ ሰው አጥንት 90 በመቶ የሚገነባው በዚህ ዕድሜ ላይ ነው። ለአጥንት ጥንካሬ ወሳኝ የሆነው ካልሲየም በዋነኝነት የሚከማቸው በአጥንት ውስጥ ነው። የካልሲየም ዋነኛ ምንጭ ከሆኑት የምግብ ዓይነቶች መካከል ወተት እንዲሁም እንደ እርጎና አይብ ያሉ የወተት ተዋጽኦዎች፣ የታሸገ ሰርዲንና ሳልመን (ከነአጥንቱ ሲበላ)፣ አልሞንድ የተባለው የለውዝ ዝርያ፣ ኦትሚል (ሲናር)፣ ሰሊጥ፣ የአኩሪ አተር ቺዝ (ቶፉ) እና ጠቆር ያሉ አረንጓዴ ቅጠላ ቅጠሎች ይገኙበታል።
ካልሲየም በሰውነት ውስጥ እንዲዋሃድ ቫይታሚን ዲ የግድ አስፈላጊ ነው። ይህ ቫይታሚን ቆዳችን ውስጥ የሚመረተው የፀሐይ ብርሃን ስናገኝ ነው። የውስጥ ደዌ ሐኪምና የሜክሲኮ የአጥንትና የማዕድናት ውህደት ማኅበር አባል የሆኑት ማንዌል ሚራሱ ኦርቴጋ “በየቀኑ ለአሥር ደቂቃ ያህል ፀሐይ መሞቅ 600 ዩኒት የሚያክል ቫይታሚን ዲ ስለሚያስገኝ ኦስቲዮፖሮሲስን ለመከላከል አስተዋጽኦ ያደርጋል” ብለዋል። በተጨማሪም ይህ ቫይታሚን ከእንቁላል አስኳል፣ በጨዋማ ባሕር ውስጥ ከሚኖሩ ዓሣዎች፣ ከጉበትና ከመሳሰሉት የምግብ ዓይነቶች ይገኛል።
ኦስቲዮፖሮሲስን ለመከላከል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ አቅልለን ልንመለከተው አይገባም። አካላዊ እንቅስቃሴ በልጅነትና በጉርምስና ዕድሜ አጥንት እንዲጠነክርና እንዲደነድን ሲያደርግ በእርጅና ዕድሜ ደግሞ አጥንት እንዳይሳሳ ይከላከላል። በአጥንቶችና በመገጣጠሚያዎች ላይ ብዙ ጫና ሳይፈጠር ጡንቻዎች እንዲንቀሳቀሱ የሚያደርጉ እንደ ክብደት ማንሳትና የስበትን ኃይል መቋቋምን የሚጠይቁ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ጥሩ እንደሆነ ይመከራል። በእግር መሄድ፣ ደረጃ መውጣትና መጨፈር ወይም መደነስ ቀላል ሆኖም ውጤታማ የሆኑ የእንቅስቃሴ ዓይነቶች ናቸው።
ይህን ድምፅ አልባ በሽታ ለማሸነፍ አስቀድሞ የመከላከያ እርምጃዎችን መውሰድ ወሳኝ ነው። ይህ ደግሞ ቀደም ብለን እንደተመለከትነው አጥንት እንዳይሳሳ ብሎም ጥንካሬው እንዲጨምር ለማድረግ በአመጋገብና በአኗኗር ዘይቤ ላይ ለውጥ ማድረግን ይጨምራል። ብዙ እንቅስቃሴ የማይጠይቅ የአኗኗር ዘይቤ ያላቸው ሰዎች በዚህ ረገድ ለውጥ ማድረግ ቀላል እንደማይሆንላቸው የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ አስፈላጊውን ጥረት የሚያደርጉ ሰዎች በርካታ ጥቅሞች ያገኛሉ። ከሚያገኟቸው ጥቅሞች መካከል የመጀመሪያው በዓለም ዙሪያ በኦስቲዮፖሮሲስ ከሚሠቃዩ በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ ሰዎች መካከል አንዱ ከመሆን መዳን ነው።
ምንጭ፡– «© BSIP/Photo Researchers, Inhttps»ን ዋቢ በማድረግ ያስነበበን የመጠባበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መፃሃፍት
በማይክሮ እንቅልፍ ወቅት አእምሮ ከውጪ የሚመጣን ድምጽም ሆነ ሌላ ስሜት አያስተናግድም። በአካባቢዎ ለሚፈጠር ነገር ድንዝዝ ነዎት። ማይክሮ እንቅልፍ ሲጀምር አጢኖ ማስቆም ስለሚከብድ በእንቅልፍ ምክንያት የሚፈጠሩ ግጭቶች እየጨመሩ መተዋል።
ታዲያ የእንቅልፍ እጦትን እንዴት መከላከል ይቻላል? ከሁሉም የተሻለው መንገድ ምን ያህል እንቅልፍ እንደሚያስፈልገን አውቀን ሳንቀያይር በየቀኑ ለዛ ሰአት ያክል መተኛት ነው። ቅዳሜ እና እሁድም ሆነ በአመት በአል ግዜ ለተመሳሳይ ሰአት መተኛት ተገቢ ነው። ለእንቅልፍ የሚረዱ የአኗኗር ዘይቤ ለውጦችም ማከናወን ጥሩ ነው። አካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ እና ቡናን አለማዘውተር ሌላ ልናደርጋቸው የምንችላቸው መፍትሄዎች ናቸው።
sweetlouise / Pixabay
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሀምሌ 13/2011