በወጣትነት ዕድሜያቸው በርካታ ፋብሪካዎችን በማስተዳደር የብልህ አዕምሮ ባለቤት መሆናቸውን አሳይተዋል። ከምግብ እህሎች የወጪ ንግድ ጀምሮ እስከ ከረጢት አምራች ፋብሪካ ባለቤትነት የዘለቀ የኢንቨስትመንት ህይወትን እያሳለፉ ይገኛል። ዘለግ ካለው ቁመናቸው ጋር ጨዋ አነጋገራቸው ተጨምሮበት ተግባቢ የንግድ ሰው እንዳደረጋቸው ብዙዎች ይናገራሉ። ከአዲስ አበባ- አዳማ በየጊዜው እየተመላለሱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችን የያዙ ፋብሪካዎቻቸውን በመቆጣጠር ወደትርፋማነት እያሸጋገሩ ይገኛል።
የትውልድ ቦታቸው በስምጥ ሸለቆዋ የስብሰባ ቱሪዝም መዳረሻ ከተማ አዳማ ነው። የዛሬው እንግዳችን አህመድ ዓሊ አብዱልቃድር ይባላሉ ሙሉ ስማቸው። በልጅነታቸው አዳማ ቁጥር ሰባት የተባለው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እና አዳማ ቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት ሁለተኛ ደረጃን ተከታትለዋል። በልጅነታቸው የኢትዮጵያን ምርቶች በውጭ አገራት እያስተዋወቁ በስማቸው መሸጥ ህልማቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
ያደጉት አያታቸው ጋር ነበር። አያታቸው ደግሞ 15 ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ ነጋዴ ነበሩ። በደርግ ዘመን ግን ለንግድ አመቺ ባለመሆኑ የአያታቸው ንብረት ተወርሶ መጋዘናቸው ብቻ እንዲገለገሉበት ይሰጣቸዋል። እናም አያታቸው የመጋዘኖቹን የቤት ኪራይ እየተቀበሉ ቤተሰባቸውን ያኖሩበት ነበር። አቶ አህመድም የአያታቸውን ሙያ ታሪክ ከመስማት ውጪ ይሄ ነው የሚባል የንግድ ልምድ ባይኖረውም ዘርፉን ተቀላቅሎ የቤተሰቡን ንግድ በተሻለ ሁኔታ ለማስኬድ አስበዋል።
እናም አፍላ የወጣትነት ዕድሜ ላይ እያሉ የልጅነት ህልማቸውን የሚያሳኩበትን መንገድ የጠረገ አንድ አጋጣሚ ተፈጠረ። በወጣትነት አዕምሯቸው ካወጡ እና ካወረዱ በኋላ በእህል ንግድ ላይ መሰማራት እንዳለባቸው ወስነው ከቤተሰባቸው ብር ለመቀበል ያቅዳሉ። ቤተሰብም ፈቅዶላቸው 19 ሺ ብር ለንግድ መነሻ እንዲሆናቸው ተሰጣቸው። በ1988 ዓ.ም ላይ 19 ሺ ብር ብዙ ቢያሠራም አፍላ የወጣትነት ዕድሜ ላይ በመሆናቸው “ተጠንቀቅ ሥራ ሌላ የምንረዳህ የለም” የሚለው የአያታቸው ምክር ታክሎበት ወደንግዱ እንደገቡ ያስታውሳሉ።
በተሰጣቸው ገንዘብ በመጀመሪያ 200 ኩንታል ጥራጥሬ ከአዳማ ዙሪያ አካባቢዎች ገዝተው መሸጥ ጀመሩ። የሚያገኙትን ትርፍ ወደሥራ በማዋል የእህል ንግዱን አጧጧፉት። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ከሻጮች በዕምነት የሚሰጣቸውን ጥራጥሬ በመሸጥ እና ክፍያውን በመፈጸም በአጭር ጊዜ እስከ 500 ሺ ብር የሚደርሱ ጥራጥሬዎችን ማገበያየቱን ተያያዙት።
በሥራቸው ላይ ታማኝነት ዋነኛው መለያቸው መሆኑን የሚናገሩት አቶ አህመድ በርካታ ሰዎች ‹‹ሸጠህ ትከፍላለህ›› በሚል የሚሰጧቸው ምርት በእራሱ ትልቅ ሀብታቸው እንደነበር አይረሱትም።ይሁንና በመጀመሪያ በዱቤ የተረከቡትን ምርት ገንዘብ በወቅቱ እና በትክክለኛው መጠን ለባለቤቶቹ ስለሚመልሱ ደግሞ የበለጠ ታማኝነትን እያተረፉ ንግዳቸውን እንዲያሻሽሉ መንገድ እንደጠረገላቸው ይረዳሉ።
እህል ከአምራች እና ነጋዴ ተቀብሎ ከመሸጥ ባለፈ ቦሎቄ ለውጭ ገበያ ለሚልኩ ሰዎች በማቅረብ ጠቀም ያለ ገንዘብ ያገኙ ነበር። እንዲሁም ከኢተያ አካባቢ የሚገዙትን ዕህል ለፋብሪካዎች በማቅረብ ሥራቸውን እያሳደጉ መጡ። ጤፍም በመግዛት ወደበረሃማ አካባቢዎች ለሽያጭ ይልኩ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ከዚህ ሁሉ ሥራ በኋላ ግን ለምን እራሴ ወደውጭ አልልክም የሚል ሃሳብ ይመጣላቸውና ዝግጅት ማድረግ ይጀምራሉ። በተለይ አዳማ ከተማ ውስጥ ያገኙትን ህንዳዊ ስለ ወጪ ንግድ ያወሩታል። እርሱም በሀገሩ ያሉ ገበያዎችን አግኝቶላቸው የውጭ ንግዱን ሀ ብለው እንዲጀምሩ ምክንያት ሆናቸው።
በወቅቱ ለግብይት በየሚዞሩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ባለመኖራቸው ሥራው አድካሚ ነበር። እርሳቸው አዳማ ከተማ በሚገኝ ቴሌ ፋክስ ጥያቄ በመላክ እና መልስ በጠዋት በመጠበቅ ነበር ግንኙነቱን የፈጠሩት። ለአንድ ፋክስ ጽሑፍ በወረቀት 17 ብር በመክፈል ደንበኞቻቸው ጋር ተገናኙ። በመጨረሻም በ1992 ዓ.ም ወደ ህንድም ማሾ የተሰኘውን ምርት አንድ ኮንቴይነር እንደላኩ ያስታውሳሉ።
ከሸዋሮቢት ገዝተው ምርቱን ሲልኩ በወቅቱ እስከ ስልሳ ጊዜያዊ እና ሁለት ቋሚ ሠራተኞች እንደነበራቸው አይረሱትም። ከዚያም የመን ወደሚገኙ ዘመዶቻቸው ጋር በመሄድ ገበያውን አጥንተው ይመለሳሉ። ለየመን እና ለፓኪስታን የተለያዩ ጥራጥሬ እና የቅባት እህሎችን በጥራት አዘጋጅተው በእራሳቸው ስም መላኩን ቀጠሉበት። የዱባ ፍሬ፣ ነጭ ቦሎቄ፣ ሽንብራ፣ ምስር እና የተለያዩ ጥራጥሬዎችን በአዳማ አዘጋጅተው ይልኩ ነበር።
በመሀል ግን አንድ ያላሰቡት አጋጣሚ የንግድ ሥራቸው ላይ ፈተና አመጣባቸው። በአንድ የቡልጋሪያ ደንበኛቸው አማካኝነት ለዕርዳታ የሚላክ እህል ለመሸጥ ወደየመን የላኩት ምርት በቦታው ቢደርስም ዋጋው እንደማይከፈላቸው ይነገራቸዋል። ጉዳዩ ደግሞ ምርት ከተላከ በኋላ በተፈጠረ የዋጋ አለመስማማት የተከሰተ ችግር ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በየመን ያለመረጋጋት በመኖሩ በዚያው የነበሩ ዘመዶቻቸው ጭምር ምርቱን ሊያስመልሱ አልቻሉም። እናም ምርቱ እንደታሸገ ለረጅም ጊዜ ቆየ። የምርቱ ዋጋ ደግሞ 400 ሺ የአሜሪካን ዶላር ነበርና አቶ አህመድ ሙሉ አቅማቸውን አሟጠው ገንዘባቸውን ያፈሰሱት የንግድ ሥራ ለኪሳራ ተጋለጠ።
ከብዙ ድርድር እና ይከፈለኝ፣ አይከፈልም ከሚል ክርክር በኋላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባደረገው ጥረት ከአንድ ዓመት በኋላ የተወሰነው ክፍያ ተለቆላቸው በድጋሚ ወደ ንግዱ ሥራ ለመመለስ ቻሉ። ሁል ጊዜም ፈተና ሲያጋጥም በጽናት ጉዳዩን መከታተል እንጂ ተሸንፎ መቀመጥ እንደማይወዱ የሚናገሩት አቶ አህመድ፣ የወቅቱን የገንዘብ ችግር ተቋቁመው ሠራተኞቻቸውን እያበረቱ እንዳለፉት ይገልጻሉ።
ከዚህ በኋላ ወደተለያዩ አገራት የኢትዮጵያ አፈር ያፈራቸውን የሰብል እና ቅባት እህሎች በመላክ ሀብታቸውንም ማካበቱን ተያያዙት። በአዳማ ከተማ የቦሎቄ እና የሰሊጥ ማዘጋጃ ፋብሪካ በመገንባት ምርቶቻቸውን በዘመናዊ መሳሪያ እንዲዘጋጁ በር ከፈቱ። ምርቶቹንም ለተለያዩ ላኪዎች እና ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ግኝቱ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ይናገራሉ። ፋብሪካው ከ400 በላይ ሠራተኞች የያዘ እና ዘመናዊ የወጪ ንግድ ምርት አዘገጃጀቶችን ያቀፈ ነው።
አቶ አህመድ በተለያዩ ጊዜያት ወደውጭ የሚልኩት ምርት በትራንስፖርት ችግር ምክንያት በጊዜው ሳይደርስ ሲቀር ያስጨንቃቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ለዚህ ደግሞ የዘየዱት መላ የእራሳቸውን የትራንስፖርት አማራጮችን ማስፋት ነው። አንድ ብለው የጀመሩት የተሽከርካሪ ግዥ አሁን ላይ የ50 ተሽከርካሪዎች ባለቤት አድርጓቸዋል። በመሆኑም እያንዳንዱን ምርታቸውን ከመሃል አገር ወደ ወደብ የሚያመላልሱት በእራሳቸው ተሽከርካሪዎች አማካኝነት ሆኗል። የትራንስፖርት አማራጮቻቸው መፍጠራቸው በወቅቱ እና በአስፈላጊው ሰዓት ምርቶችን በተፈለገው ቦታ በማድረስ ከደንበኞቻቸው ጋር ጥሩ የንግድ ግንኙነት እንዲኖራቸው አድርጓል።
የአዳማው ሰው በአንድ ሥራ መወሰን እንደማይወዱ ይናገራሉ። በተወለዱባት ከተማ በ150 ሚሊዮን ብር ወጪ የወረቀት እና የካርቶን ፋብሪካ ገንብተው ጨ ር ሰ ዋ ል ። ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ ሥራ ሲጀምር ለ600 ሰዎች ሥራ መፍጠር የሚችል ነው። በተለይ ሀገር ውስጥ ያለውን የማሸጊያ ምርት እጥረት በመቀነስ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችል ፋብሪካ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል። ከዚህ በተጨማሪ የ እ ራ ሳ ቸ ው ን ምርቶች ማሸጊያ የሚሆን እና ለሌሎችም በሽያጭ መልክ የሚቀርብ የከረጢት ማምረቻ አላቸው።
ቃሊቲ አካባቢ ደግሞ ከፍርድ ቤት ላይ በ160 ሚሊዮን ብር የገዙትን የመኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ወደሥራ ለማስገባት ሰፊ ክንውን እያደረጉ ይገኛል። በዘመናዊ መልክ ቫይታሚን እና ፕሮቲን ንጥረ ነገሮች የታከሉበት የእንስሳት መኖ ለማቀነባበር ጥናት አድርገው መጨረሳቸውን ይናገራሉ። አሁን ደግሞ የፋብሪካውን አሮጌ ማሽኖች በመቀየር በዘመናዊ መሳሪያ ለመተካት ግዥ እያካሄዱ ነው። ፋብሪካው በቀን 200 ሜትሪክ ቶን መኖ የማቅረብ አቅም ያለው እና ለ500 ሠራተኞች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚችል መሆኑን ያስረዳሉ።
ወጣቱ ባለሀብት እቅዳቸው ብዙ ነው። በቀጣይ ደግሞ በእንስሳት እርባታው ዘርፍ ሰፊ ሀብት ማፍሰስ ይፈልጋሉ። ከእርሻው ሥራቸው ጋር ተያይዞ ደግሞ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አንድ ሺ ሄክታር መሬት ላይ ሩዝ እያመረቱ ይገኛል። የሩዝ ምርቱንም ደረጃ በማሳደግ ለውጭ ገበያ በሚያመች ደረጃ ጥራቱን ከፍ አድርገው ለማምረት ፍላጎት አላቸው። ከሁሉም በላይ ግን በአዳማ ከተማ ሊከፍቱ ያቀዱት የምግብ ዘይት ፋብሪካ እውን መሆን ትልቅ ጉጉት አላቸው።
ለፋብሪካው የሚሆን መሬት ከሁለት ዓመት በፊት በአዳማ ከተማ ጥያቄ ቢያቀርቡም እስከአሁን ድረስ ምላሽ አለማግኘታቸው ያስቆጫቸዋል። ‹‹እኔ ፋብሪካ ብገነባ ይዤው አልሄድም ሀብቱ ቀሪ የሚሆነው ለሀገር ነው። ይህን የማይረዱ ሰዎች ግን ቢሮክራሲ በማብዛት ለግንባታው የሚሆን ቦታ መፍቀድ አልቻሉም›› በማለት ፋብሪካው ቢገነባ ጥቅሙ ለእርሳቸው ብቻ ሳይሆን ለሀገር መሆኑንም ይናገራሉ።
ለወጣቱ ባለሀብት ዋናው ቁም ነገር ዓላማ ነው። ወጣቱ ዓላማ ካለው እና በሐቀኝነት ከሠራ ማደግ እንደሚችል ይናገራሉ። በተለይ ጥሩ ምርት በሚሰጡ የኢትዮጵያ መሬቶችን በማረስ እራሱን እና ሀገሩን መለወጥ ይችላል የሚል እምነት አላቸው። ሥራን ማክበር እና ከትንሽ መነሳትን አለመፍራት ለትልቅ ስኬት ያደርሳሉ የሚለው ደግሞ ምክራቸው ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሀምሌ 13/2011
ጌትነት ተስፋማርያም