ዛሬ ከአዲስ አበባ ወጣ እንላለን፡፡ ለነገሩ ከአዲስ አበባ ብንወጣም ከተማዋ አምሳለ አዲስ አበባ ነች፤ ልክ እንደ አዲስ አበባ ሁሉ የከተማ አስተዳደር ናት፡፡ ማን እንደሆነች አወቃችሁ አይደል? በቃ ወደ ድሬዳዋ ሄደናል፡፡
ድሬዳዋ ከተማ ውስጥ ሁለት ሰፈሮችን ለምን እንደተባሉ እንነግራችኋለን፤ ‹‹እናስተዋውቃችኋለን›› ያላልነው ስለነዚህ ቦታዎች ያልዘፈነ ታዋቂ ዘፋኝ ስለሌለ ነው፡፡
ከዚራ
‹‹ከዚራ›› የሚለውን ቃል ‹‹ገዚራ፣ ኸዲራ እና ቀሲራ›› ብለው የሚጠሩትም አሉ፡፡ ቢሆንም በብዙዎቻችን አፍ የተለመደው ከዚራ ነው፡፡ ሁሉንም የሚያመሳስላቸው ግን ቃሉ የአረብኛ ነው የሚለው ነው፡፡ ገዚራ ማለት በአረብኛ ደሴት ማለት ነው፡፡ ይህም ከዚራ በከተማዋ እምብርት ላይ የሚገኝ በመሆኑ የተሰጠው ስያሜ ነው፡፡
በሌላ በኩል ቀሲራ ከሚል የአረብኛ ቃል የመጣ ነው ተብሎም ይነገራል፤ ቀሲራ ማለት በአረብኛ የተደረደሩ ቤቶች ማለት ነው፡፡
ኸዲራ ማለት ደግሞ በአረብኛ አረንጓዴ፣ ለምለም እንደማለት ነው፡፡ በጥላዎች የተሸፈነ ስለሆነ ይህኛው ስያሜ የሚገልጸው ይመስላል፡፡
ሦስቱንም ትርጉም እንጠቀመው ከተባለ፤ ከዚራ ማለት ደሴት የሆነች፣ የተደረደሩ መንደሮች ያሉባት፣ አረንጓዴ ዛፎች እና ጥላዎች የበዙባት ናት ማለት ነው፡፡
ሼመንደፈር
ሼመንደፈር ማለት የፈረንሳይኛ ቃል ነው፤ ትርጉሙም የባቡር መንገድ፣ የባቡር መስመር፣ የባቡር መሄጃ ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ድሬዳዋና ባቡር ምንና ምን እንደሆኑ ለቀባሪ ማርዳት ነው፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሀምሌ 13/2011