በአንድ ፖለቲካዊ ውይይት ላይ አቶ ልደቱ አያሌው ለአቶ ሌንጮ ለታ ምላሽ ሲሰጡ፤ ‹‹አንዱ ችግራችን የውይይት ጥራት ችግር ነው›› ብለው ነበር፡፡ ይህን ማለት የፈለጉበት ምክንያት ደግሞ በዚያው ውይይት ላይ አቶ ሌንጮ ለታ የተናገሩት ነገር ነው። አቶ ሌንጮ ስለፌዴራሊዝም ሥርዓት ሲናገሩ፤ የአንድ ሃይማኖት፣ የአንድ ቋንቋ፣ የአንድ ባህል የበላይነት የሚል እሳቤ ያላቸው ሃይሎች ለኢትዮጵያ እንደማይሆኑ አብራሩ፡፡ አቶ ልደቱ ደግሞ በመገረም፤ ‹‹ውይይታችንን ጥራት ያሳጣው ባልተባለ ነገር ላይ መከራከር ነው›› አሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ፤ አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ቋንቋ፣ አንድ ባህል… የሚል የተደራጀ ሃይል በፍጹም እንደሌለ አጽንዖት ሰጥተው ተናገሩ፡፡ ምናልባት ከተባለም በግለሰብ ደረጃ እንጂ እንዲህ የሚል የተደራጀ የፖለቲካ ሃይል የለም፤ ‹‹ለምን በሌለ ነገር እንከራከራለን?›› ሲሉ ነበር፡፡
የፖለቲከኞችን ክርክር እንደመነሻ ከተጠቀምኩ ወደራሴ ትዝብት ልግባ፡፡
እንግዲህ በምናነበውም ሆነ በምን ሰማው አቶ ልደቱ እንዳሉት፤ አንድ ቋንቋ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ባህል… ብሎ የተደራጀ ሃይል የለም፤ ትልቁ የፖለቲከኞችና የፓርቲዎች መከራከሪያ የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ላይ ነው፤ ለዚያውም አተገባበሩ ላይ ነው፡፡ የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ፈጽሞ መፍረስ አለበት የሚሉትም ቢሆን አንድ ቋንቋና አንድ ሃይማኖት መሆን አለበት አይሉም፤ ለምሳሌ ራሳቸው ልደቱ አያሌው የብሄር ፌዴራሊዝም ለአገሪቱ አይበጅም የሚሉ ናቸው፤ ግን አንድ ቋንቋ አንድ ሃይማኖት በፍጹም ሊሆን እንደማይችል ያምናሉ፡፡
እንግዲህ ደፈር ብለን እንናገር ከተባለ ይሄ አንድ ቋንቋ፣ አንድ ሃይማኖት የሚባል ነገር የሚያርፈው አማራው ላይ ነው፡፡ አማራው ላይ ከሆነ ደግሞ አንድ ነገር ልብ እንበል! ይሄ አንድ ቋንቋ፣ አንድ ሃይማኖት የሚባል ነገር በአጼው ሥርዓት የነበረ ነው፤ ግን የአጼውን ሥርዓት የገረሰሰው ማነው? የአጼው ሥርዓት የጨቆነው ማንን ነበር? የአጼው ሥርዓት ፍጻሜ የሆነው የቀዳማዊ አጼ ሃይለሥላሴ ሥርዓት ሲወድቅ አማራ እጁ አልነበረበትም? የጎጃም ገበሬዎች እኮ ያመጹት በዚያ ሥርዓት ላይ ነበር አይደል? ያ ሥርዓት እነርሱን የሚጠቅም ከነበር ለምን አመጹ ታዲያ?
ሰዎች ባልተባለ ነገር ላይ የሚከራከሩት የራሳቸውን ሀሳብ ትኩረት ለማሰጠት ነው፡፡ ለምሳሌ በፌዴራሊዝም ሥርዓቱ የሚያምኑ ሰዎች ‹‹ችግር አለበት›› የሚሉትን ሲተቹ፤ ‹‹አንድ ቋንቋ፣ አንድ ሃይማኖት›› ያሉ በማስመሰል ነው፡፡ የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ችግር አለበት የሚሉት ደግሞ እነዚያኞችን ሲተቹ፤ የአገሪቱ ችግር ሁሉ በፌዴራሊዝም ሥርዓት የመጣ፣ በአጼው ሥርዓት ጊዜ አገሪቱ ውስጥ ምንም ችግር ያልነበረ፣ መገዳደል የተፈጠረው ከ27 ዓመት ወዲህ… በማስመሰል ነው፡፡ የሁለቱም ሀሳብ ግን ትክክል አይደለም። ሁሉም የየራሳቸውን እምነት ትኩረት ለማሰጠት እንጂ ችግሩ የየራሳቸው ነው፡። የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ነው ችግር ያመጣ ለሚሉት ከዚያ በፊትም የግፍ አገዛዝ እንደነበር ራሳቸው ያውቁታል፤ ከፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ወዲህ ነው አገሪቱ አገር የሆነች ለሚሉትም እነዚህ የሚሏቸው ቋንቋዎችና ባህሎች አሁን እንዳልተፈጠሩ ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡
ቆይ ግን የሚገርመኝ ነገር! እንዴት ቢንቁን ነው ግን? እነርሱ እንጂ እኛ ከታች ያለን ተራ ሰዎች ታሪክ የማናውቅ ይመስላቸዋል? ድሮ ምን እንደነበር፤ አሁን ምን እየሆነ እንዳለ ሕዝብ ይታዘበናል አይባልም? ለነገሩ ሕዝቡን እንኳን ታዝበውታል፤ ከመጣ ከሄደው ጋር ነው ግራ የሚጋባው!
አሁን ከምንም በላይ አስቸጋሪ የሆነብን የራስን ሀሳብ ትክክል ለማስመሰል የሌሎችን አጣሞ መተርጎም ነው፤ የራስን ትኩረት ለማሰጠት የሌሎችን እንከኑን ማጋነን ነው። ለነገሩ ይሄ እንኳን በግለሰብና በፖለቲካ ፓርቲዎች፤ በገዥዎችም የለመድነው ልማድ ሆኗል፡ ፡ አንድ መንግስት ሲመጣ ያለፈው መንግስት የሠራቸውን በማፍረስ ነው፡፡
በፖለቲከኞች ውስጥ ይሄ የተለመደ ነው፤ ሚዛናዊ አድርጎ መቀበል ያለበት ህዝቡ ነው፡፡ መግቢያ ላይ የተጠቀምኩትን መደምደሚያ ምላድርገው፡፡ ለምሳሌ አንድ ፖለቲከኛ የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ እንከን የለበትም ቢል፤ ሌላኛው የችግሮች ሁሉ ምክንያት የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ነው ቢል፡፡ ፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ችግር አለበት የሚሉትን የአንድ ቋንቋና ሃይማኖት አቀንቃኞች ቢል፤ ይህን ሁሉ ማመዛዘን ያለበት ህዝቡ ነው፡፡ ማን አለ? ለምን አለ? የሚለውን ማመዛዘን ነው፡፡
ፖለቲከኞች የሌሎችን ሀሳብ እያጣ መሙ የሚተረጉሙት አልገባቸው ብሎ ሳይሆን አለመፈለግ ነው፡፡ የፌዴ ራሊዝም ሥርዓት ጥላቻ ያለበት ሰው የችግሮች ሁሉ ምክንያት ያደርገዋል፤ ፌዴራሊዝም ላይ የሙጥኝ ያለ ሰው ሥርዓቱን የተቸውን ሁሉ ‹‹የአንድ ቋንቋ፣ የአንድ ሃይማኖት አቀንቃኝ›› እያለያላለውን በማስተጋባት እንዲ ጠላ ያስደርገዋል፡፡ ይህንንም አመ ዛዝኖ መረዳት የህዝቡ ነው፤ፖለቲ ከኞች ያለመግባባት ብቻ ሳይሆን ያለመፈለግም ነው፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሀምሌ 13/2011
ዋለልኝ አየለ