የአፍሪካ ሕብረት ርዕሰ ብሔሮችና መንግስታት በናይጄሪያ ርዕሰ መዲና ኒያሚ ባካሄዱት ሙሉ ቀን የዘለቀ 12ኛው ልዩ መደበኛ ስብሰባ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ተግባራዊ ስራ እንዲጀምር መወሰኑን የአፍሪካ ሕብረት በድረ ገፁ አስነብቧል።
የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና የሚመራው ተግባራዊ በሚያደርጉት አምስት ክፍሎች ነው። እነዚህም የምስረታው ሕጎች፤ የኦንላይን ድርድር ፎረም፤ የቁጥጥርና የታሪፍ እገዳዎችን የሚያስወግድ፤ የዲጂታል ክፍያ ዘዴና እንዲሁም የአፍሪካ ንግድ ተቆጣጣሪ ናቸው፡፡
እያንዳንዱ ክፍል የሚከፈተው በተለያዩ ርዕሰ ብሄሮችና የመንግስት መሪዎች ሲሆን የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራምፖሳ፤ የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር የሆኑት የግብጹ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አልሲሲ፤ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሚ/ር ሙሳ ፋኪ ማሀማት እንዲሁም የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ሻምፒዮን የሆኑትን የናይጄሩን ፕሬዚዳንት መሀመዱ ኢሱፉን ያካትታል፡፡
በመክፈቻው ስነ ስርዓት ላይ ነጻ የንግድ ቀጣናውን መመስረት ያጸደቁት 27 ሀገራት ስም በክብር ይጠራል። የፈረሙ ግን ደግሞ ያላጸደቁትም ይጠቀሳሉ፡፡ የፊርማ ስነ ስርዓቱ ለማስታወሻነት ይዘከራል፡፡ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት የተደረሰውና የተፈረመው ማርች 21 ቀን 2018 ኪጋሊ የነበረ ሲሆን ወደስራ የሚገባው ከሜይ 30 ቀን 2019 ጀምሮ ነው። የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሚ/ር ሙሳ ፋኪ መሀመት ‹‹የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና በፍጥነት ወደስራ መግባት ለሁላችንም የኩራት ምንጭ ነው›› ብለዋል፡፡
በአቡጃው ስምምነት መሰረት ነጻ የንግድ ቀጣና መመስረቱ የአፍሪካን 2063 አጀንዳ ለማሳካት ለአሕጉራዊ ውሕደቱ መፈጠር አንድ መሳሪያ በመሆን ያገለግላል ያሉት ሙሳ ፋኪ በአህጉሩ የሰላምና ደሕንነት ግንባታን አስፈላጊነት አጉልተው በመግለጽ ሰላምና ደህንነት ከሌለ ስለንግድና ልማት ማውራት ቅዠት ነው ብለዋል። የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ውጤታማ እንዲሆን ለሌሎች አፍሪካውያን ድንበሮችን መክፈት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ፕሬዚዳንት መሀሙዱ ኢሱፉ በበኩላቸው ነጻ የንግድ ቀጣናው መመስረትና ወደስራ መግባት በቀደመው የአፍሪካ ቅኝ ግዛት ዘመን የተቀመጠውን ድንበር በመበጣጠስ ሙሉ አሕጉራዊ ውሕድነትን ያረጋግጣል ብለዋል፡፡
የግብጹ ፕሬዚዳንት አብደል ፈታህ አልሲሲ ከግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ፤ ከንግድና ኢንቨስትመንት ማሕበረሰቡ ጋር ትስስር የመፍጠሩን አስፈላጊነት ገልጸው ለልማትና እድገት የተጀመረውን ጉዞ ወደፊት የሚያስቀጥለው ወጣቱ ትውልድ ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ አድርገዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሀፊ ሚስ አሚና መሀመድ ነጻ የንግድ ቀጣናው በአፍሪካ እድገትና ፈጠራን ለማምጣት መሳሪያ ሲሆን በተጨማሪም እድሎችን በመፍጠር በማስፋት ቀጣይነት ያለው እድገት ለማስመዝገብ እንዲሁም አጀንዳ 2063ን እውን ለማድረግ ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡
የአለም ንግድ ድርጅት ከተመሰረተ በኋላ የተመ ሰረተው የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና የአለማችን አንደኛው ግዙፍ ቀጣና ነው፡፡ አሁን ያለው 1.2 ቢሊዮን የአፍሪካ ሕዝብ በ2050 ወደ 2.5 ቢሊዮን እንደሚያድግ ይጠበቃል፡፡ ይህም ግዙፍ እድሎችና ገበያን ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ርዕሰ ብሔሮችና የመንግስት ተወካዮች በተገኙበት የአፍሪካ ሕብረት ልዩ መደበኛ ስብሰባ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣናን መመስረት ተከትሎ በአስተናጋጅነት ለመቀበል ከስድስት ሀገራት በላይ ፍላጎት ያሣዩ ቢሆንም ጋና የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ሴክሪታሪያት ዋና ጽ/ቤት እንድትሆን ወስነዋል፡፡
ናይጄሪያ በአፍሪካውያን መካከል ነጻ የንግድ ቀጠና ምስረታውን በመፈረሟ የበለጠ ተጠቃሚ ትሆናለች ሲል የቻይና ዜና ወኪል ዥንዋ ዘግቧል። ኦላቱንጂ ሳሊዩ ከአቡጃ ባስተላለፈው ዜና ትንተና የአፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ የሆነችው ናይጄሪያ የአፍሪካን ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት ፈርማለች። ይህ ስምምነት በአፍሪካውያን መካከል ያለውን ንግድ የበለጠ እንደሚያሻሽለው የኢኮኖሚ ቀጣይነት ያለው እድገት እንደሚያመጣ ይጠበቃል ብሏል ዥንዋ፡፡
በናይጀር ዋና ከተማ ኒያሚ በተካሄደው የአፍሪካ ሕብረት ልዩ ስብሰባ ናይጄሪያ ከቤኒን ጋር በመሆን የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣናው ምስረታ ይፋ ሲደረግ ነው ተገኝተው የፈረሙት፡፡ ከስብሰባው በፊት ማለትም የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣናን የናይጄሪያ መንግስት በይፋ ፈርሞ ከመቀላቀሉ በፊት ከባለድርሻ አካላት ጋር ከፍተኛ ምክክር አድርጓል፡፡ በፕሬዚዳንቱ የተቋቋመው ኮሚቴ ሪፖርቱን አጠናቆ ችግሮቹንም በመዳሰስ ናይጄሪያ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠናን ለመቀላቀል ዝግጁ መሆኗን አረጋግጧል፡፡
የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት በአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 መሰረት አንዱ የባንዲራ (የማንነት መለያ) ፕሮጀክት ሲሆን አላማው ለንግድ ሰዎችና ለኢንቨስትመንት ነጻ እንቅስቃሴ እንዲኖር ማድረግ ለሸቀጦችና ለአገልግሎቶችም አንድ አህጉራዊ ገበያ መፍጠር ነው፡፡
የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና መመስረት በአለማችን አንዱ ግዙፍ ነጻ የንግድ ቀጣና እንደሚሆን በማመን 55 የአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገራት በመጋቢት 2018 እንቅስቃሴ የጀመሩ ሲሆን 44 ሀገራት ቀድመው ስምምነቱን ፈርመዋል። በዚያን ወቅት የአፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ የሆነችው ናይጄሪያ ከእነሱ ውስጥ አልነበረችም፡፡
የናይጄሪያ ባለስልጣናት ናይጄሪያ ስምምነቱን ከመፈረም የዘገየችው በሀገር ውስጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር የናይጄሪያ ሌበር ኮንግረስ፤ ከናይጄሪያ ማኒፋክቸረር ማሕበር እና ከሌሎችም የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚዎች ጋር ለመምከርና ለመወያየት ሰፊ ግዜ ስለሚያስፈልግ እንደነበረ ይገልጻሉ፡፡
ሌላው የተጠቀሰው ምክንያት ግልጽነት የሌለው የንግድ ተግባር መጣል ማራገፍ መፈጸሙና የመሳሰሉት አሳሳቢ ችግሮች የነበሩ ሲሆን በኃላ ላይ በተሰጠው ውሳኔ መሰረት የሀገሪቱን የውጭ ንግድ ከምርት ዋጋው ዝቅ ማድረግ የሚል ነው፡፡
ይሄን ጉዳይ በተመለከተ አንዳንድ የሀገር ውስጥ ተንታኞች ናይጄሪያ ስምምነቱን ከፈረመች በኃላ ያልተገባ የገበያ ድርሻ ታገኛለች ይላሉ፡፡ ብዙ ተንታኞች ደግሞ የናይጄሪያ መኖር ንግድ በአህጉሩ እንዲስፋፋ ያደርጋል፡፡ ሀገሪቷም ስምምነቱን በመፈረሟ የበለጠ ታገኛለች ይላሉ፡፡
ሰኔ ላይ ናይጄሪያ የተመደቡት የግብጽ አምባሳደር አሰም ሀናፍ በሀገራቸውና በናይጄሪያ መካከል ስላለው ዝቅተኛ የንግድ መጠን የተሰማቸውን ስሜት ገልጸው በጣም የማስፋቱን አስፈላጊነት ገልጸው ነበር፡፡ የእኔ አላማ ይላሉ አምባሳደር አሰም በግብጽና በናይጀሪያ በሁለቱ ግዙፍ እምቅ አቅምና ሕዝብ ባላቸው ትልቅ የአፍሪካ ሀገራት መካከል ንግድና ኢንቨስትመንት የሚስፋፋበትን መንገድ መፈለግና መመልከት ነው ብለዋል፡፡
በናይጄሪያና በግብጽ መካከል ያለው የንግድ መጠን ትልቅ አይደለም፡፡ ይሕ ደግሞ በአፍሪካውያን መካከል ላለው የንግድ ግንኙነት ሌላው አሳዛኝ ታሪክ ነው፡፡ በአፍሪካውያን መካከል ያለው የንግድ ግንኙነት ከአፍሪካ የውጭ ንግድ ጋር ሲነጻጸር 15 በመቶ ብቻ መሆኑን የናይጄሪያ መንግስት መረጃ ያመለክታል። አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት በራሳቸው መካከል ንግድ አያካሂዱም ሲል በአቡጃ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ ሸሪፍ ጋሊ ኢብራሂም ይናገራል፡፡
ናይጄሪያ የአሕጉሪቱ ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት የሚገኝባትና ግዙፏ ኢኮኖሚ በመሆኗ በአፍሪካውያን መካከል ለሚካሄደው ንግድ ዋናው የሞተር ክፍል በመሆን የምትጫወተው ጠቃሚ ሚና አለ ሲል ኢብራሂም ለዥንዋ ገልጿል፡፡
ናይጄሪያ ስምምነቱን ለመፈረም መስማማቷ ለሁሉም አፍሪካውያን ታላቅ ጠቀሜታ አለው። ሁሉም አፍሪካውያን በፖለቲካና በኢኮኖሚ በሚገባ እንዲዋሀዱ መሰረት የሚሆን መልካም እድል አድርጌ ነው የማየው ብሏል ኢብራሂም፡ ፡ ኢብራሂም በዚህ ስምምነት መሰረት የንግድ ገደቡን ማስወገድ ናይጄሪያ በጥቂት የአፍሪካ ሀገራት የሚፈለገውን የራሷን አብዛኛውን ሀብት አጥብቃ እንድትይዝ እድል ይሰጣታል ብሏል፡፡.
በ2017 (እኤአ) ወደሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የተላከው ምርት ከናይጄሪያ አጠቃላይ የውጭ ንግድ 12 በመቶ ሲሆን ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ወደ ናይጄሪያ የገባው ምርት ደግሞ 4 በመቶ ብቻ መሆኑን የናይጄሪያ መንግስት መረጃ ይገልጻል፡፡ ናይጄሪያ በዋነኛነት ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የምትልከው የነዳጅ ዘይት ነው። ደቡብ አፍሪካ በአፍሪካ ውስጥ በገቢና በወጪ ንግድ የናይጄሪያ ዋነኛዋ አጋር ነች፡፡
ናይጄሪያ በዋነኛነት ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የምታስገባው ሸቀጦች፤ ማዳበሪያ፤ የተዘጋጁ ባይንደርስ፤ ፍሮዘን አሳዎችን ሲሆን እነዚህ ሀገራት የምዕራብ አፍሪካ ኢኮኖሚ ማሕበረሰብ አባላት አይደሉም፡፡ ናይጄሪያ ዋነኛዋ አቅም ያላት ሀገር ነች። እነዚህ ምርቶች የገቢ ቀረጥ ግዴታ አለባቸው። በስም ምነቱ መሰረት የንግድ ገደቡን በማንሳት ናይጄሪያ ለምርቶቿ በአዲሱ ገበያ ብዙ ታገኛለች ብሏል ኢብራሂም፡፡
ከዚህ ውጭ ‹‹እኛ በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ ያለ የፋሽን ኢንዱስትሪ አለን›› ይላል ኢብራሂም። ናይጄሪያ ይሄንን ወደሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ማዛወር እንዲሁም በኢንዱስትሪው ዘርፍ የባሕል ልውውጥ ማድረግ ይቻላል፡፡ በአፍሪካ ሀገራት መካከል ብዙ የንግድ ባዛሮች ይኖሩናል፡፡ የናይጄሪያ የፊልም ኢንዱስትሪ እየተስፋፋ ስለሆነ ያለገድብ በመላው አፍሪካ ፊልሞቻችንን በነጻነት መሸጥ እንችላለን፡፡በዚህ ስምምነት የናይጄሪያና የሌሎችም ሀገራት አዘጋጆች ኢኮኖሚ ያድጋል ብሏል ኢብራሂም፡፡
በአጠቃላይ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ሁሉን የአፍሪካ አገራት ገበያ የሚያስተሳስር ነው። ከዚህ ባለፈ የቅኝ ግዛት ድንበሮችን እያመከነ አገራቱ የንግድ ትስስራቸውን በማጠናከር ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚ ሆኑ ይገመታል፤ ተስፋም ተጥሎበታል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2011
ወንድወሰን መኮንን