አዲስ አበባ፡– የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ለቦርዱ የቀረበው የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ህዝበ ውሳኔ ለማከናወን የመጀመሪያ ደረጃ ዝግጅት ላይ መሆኑን አስታወቀ።
ቦርዱ የሲዳማ ዞን ክልል የመሆን ጥያቄን ህዝበ ውሳኔ አስመልክቶ በተሰጠው መግለጫ፣ የሲዳማ ዞን የክልልነት ህዝበ ውሳኔ የማደራጀት ጥያቄ ከክልሉ ምክር ቤት ለቦርዱ የደረሰው ህዳር 12/2011 ዓ.ም መሆኑና በህገ መንግስቱ አንቀጽ 47/3/ለ/ ለክልሉ የተሰጠው “ጥያቄው ከደረሰበት ቀን ጀምሮ በአንድ አመት” የሚለው የማደራጀት ጊዜ ገደብ በቦርዱም ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን አስታውቋል።
በዚሁ መሰረትም በህገ መንግስቱ የተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ በቀሩት አምስት ወራት ጊዜ ውስጥ ህዝበ ውሳኔውን ለማከናወን የመጀመሪያ ደረጃ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አመልክቷል። በህገ መንግስቱና በምርጫ አዋጁ የተሰጠውን ሃላፊነት ዓለም አቀፍ የምርጫ መሰረታዊ መርሆዎች ጋር በማጣመር ሃላፊነቱን ለመወጣት ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግም ገልጿል።
ቦርዱ በመግለጫው ህዝበ ውሳኔ የሚከናወነው የህዝብን ፍላጐትና ውሳኔ ህጋዊ እና ነፃ በሆነ አግባብ መሰጠቱን ለማረጋገጥ እንደሆነና ቦርዱ ተገቢና በቂ ዝግጅት አድርጐ ህዝበ ውሳኔውን ማካሄድ የሚያስችለውን ዝግጅትም እንደሚያደርግ ጠቅሶ፣ ከዝግጅቶቹም የህዝበ ውሳኔ አካሄድ የሚመራበት የሥነሥርዓት መመሪያ፣ የህዝበ ውሳኔ አጠቃላይ ጊዜ ሰሌዳና በጀት ማመቻቸት፣ በህዝበ ውሳኔ ዝግጅትና ድምፅ መስጠት ሂደት ስለሚኖረው የፀጥታ አጠባበቅ ሁኔታ ግብረ ሃይል ማደራጀትና ዕቅድ ማፅደቅ እንደሚጠቀሱ አስረድቷል።
ቦርዱ ተሟልቶ ስራ በጀመረበት ባለፈው አንድ ወር በእንጥልጥል የሚገኙ እና አስቸኳይ ናቸው ያላቸው ጉዳዮች ላይ ውሳኔ በመስጠት ላይ እንደሆነ በመግለጫው ጠቁሞ፣ ስራ ከጀመረ አንስቶ የሲዳማ ዞን ክልልነትን የሚመለከቱ በተለያዩ ጊዜያት የቀረቡትን ጥያቄዎች ከመመልከቱም በላይ ከክልሉና የዞን መስተዳድር አመራሮች ጋር በጉዳዩ ላይ ውይይት ማድረጉን እንዲሁም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 06 ቀን 2011 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ተጨማሪ አራት የቦርድ አባላት ሹመት ተከናውኖ ቦርዱ አባላት ተሟልተውለት ስራውን እንደጀመረ አስታውሷል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2011
በጋዜጣው ሪፖርተር