ሰው ስለ ሰው …

አንዳንዴ ‹‹ውሃን ቢወቅጡት እንቦጭ›› ይሉት ሆኖ እንጂ የነገሮች መደጋገም ከአቅም በላይ ሲሆን ያሰለቻል። ምክንያት መነሻው ባይታወቅም አሁን ዘመን ላይ ሰው ስለራሱ ብቻ መኖርን ትቷል ቢባል ውሸት አይሆንም። ዘንድሮ ሰው ስለሰው ያሻውን ይላል፣ የራሱን ትቶ ከሌላው ቤት ያድራል። ሰው ስለሰው ሕይወት አያገባው ገብቶ ይዳኛል፣ ስም ያጠፋል፡፡

ወዳጆቼ! ይህ ልማድ ድሮም አልነበረም እያልኩ አይደለም። ቀድሞም ቢሆን ሐሜትና ስም ማጥፋቱ አሳምሮ ይከወናል። ነባሩ ተለምዶ ግን ወግ ልማዱ ከአሁኑ የተለየ ነው። ሰዎች ሰዎችን ማማት ቢፈልጉ ፊታቸውን ዞር አድርገው አፋቸውን በዘዴ ሸብበው ነው። እንዲህ በሆነ ጊዜ ምንም እንኳን ጉዳዩ ነውር ቢሆንም ድምፅ ጎልቶ አይሰማም። በሹክሹክታና በዓይን እይታ ብቻ የታሰበው ሁሉ ይሆናል፡፡

እንዲህ መደረጉ ሐሜት ይሉት ልማድ በጎነት ስሌለው ድብቅ እንዲሆን በመፈለጉ ነው። ነውርነት ሁሌም እውቅና አይኖረውምና ነገሮች በአደባባይ እንዳይወጡ ሽሽግ፣ ድብቅ ማድረጉ ተለምዷል። ምንአልባትም ‹‹ምስጢር የባቄላ ወፍጮ አይደለም›› ይባል ምሳሌ መነሻው ይህ ዓይነቱ ልማድ ሊሆን ይችላል። ባቄላ ከወፍጮና መጅ ሲገናኝ ሊሰማ የሚችለውን ጉልህ ድምፅ በመገመት፡፡

የዘንድሮው ሐሜት ግን የአደባባይ እውቅና ከተሰጠው ቆየ። ማንም ስለማንም ማውራትና ማማት ቢፈልግ ስለሚያወራው ጉዳይ አስቦና ተዘጋጅቶ ነው። ሐሜተኛው በፈለገ ጊዜ ብቅ ብሎ ያሻውን ሰው በአደባባይ ቁምስቅሉን ያሳየዋል። እንደ አስፈላጊነቱ ሐሜቱን የሚያጅቡና የሚያዳምቁ ቡድኖች ሊኖሩ ይችላሉ። ከእነሱ የሚጠበቀው ስለሚታማው ሰው ምንነትና ስለሚነሳው ጉዳይ ርዕሱን ማወቅ ብቻ ነው፡፡

አሁን የምንገኝበት ዘመን ዓለም በቴክኖሎጂ ከአንድ ሳሎን የሚውልበት ነውና ኮሽታዋ ሁሉ ሳትሰማ አታልፍም። ይህ ዓይነቱ አጋጣሚ በበጎ ሲተረጎምና ለመልካም ግብዓት ውሎ ሲገኝ ‹‹እሰዬው›› ያስብላል። በፈጣን መረጃ ፈጣን ግልጋሎትና ዕውቀት ሲገኝ ይጠቅማልና። በሌላ መልኩ ማኅበራዊ ሚዲያን የመሰሉ መገናኛዎች ቴክኖሎጂውን ለነውርነት ዓላማ ሲጠቀሙበት ደግሞ ጉዳቱ ያመዝናል። የትውልድ ዝቅጠትን ይጠቁማልና ከምርቱ ግርዱ ማየሉ ሁሌም አሳሳቢ ነው ።

ዘንድሮ አንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያው ጓዳዎች ብዙ ነገሮችን እያሳዩ፣ እያሳቀቁን ነው። አስቀድሜ እንዳልኩት በተለይ ሰዎችን ማማትና ስም ማጥፋት ሲፈለግ የፎቶና ቪዲዮ ምስላቸውን በግልጽ እያሣዩ፣ ያሻውን ቃልና ስድብ እየሸለሙ ሆኗል፡፡

ሐሜተኞቹ ይህን ሲያደርጉ ‹‹እረፉ፣ ተጠንቀቁ›› የሚላቸው፣ ድርጊታቸውን የሚቃወማቸው የለም። በአንድም ይሁን በሌላ ሀሳባቸውን የሚጋራ፣ ጅማሬያቸውን የሚያጠናቅቅ አጋር አያጡም። ‹‹የወደቀ ዛፍ ምሳር ይበዛበታል›› እንዲሉ በርዕሰ ሀሳቡና ስሙ እየተገሸለጠ በሚብጠለጥለው ሰው ላይ ዱላ የሚያነሳው ይበረክታል፡፡

አሁን ላይ በማኅበራዊ ሚዲያው እየሆነ ያለው ይኸው ነው። በሆነ አጋጣሚ ስህተት ሠርቷል፣ በንግግሩ ስቷል የሚባል ሰው ከአፍታ ሰከንድ በኋላ ከብዙኃን አፍ ገብቶ ይላመጣል፣ ይታኘካል። ማግስቱን ደግሞ የተደራጁ የወሬኛ ቡድኖች ኃይላቸውን አጠናክረው ይጠብቁታል። ያሻው የልቡን ነውር አውጥቶ እንደፈለገ አድርጎ ይሰድበዋል። ሌላው በአስተያየቱ ተመርኩዞ መርዝ ይረጭበታል። ተመልካች አድማጩም አጥንት በሚሰብር ቃላት ሞራል ስሜቱን ያደቀዋል፡፡

ይህ ሁሉ የሚሆነው የሚነሳው ርዕስ ለብዙኃኑ ስሜት የቀረበ አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኖ አይደለም። እንደተለመደው ለማኅበራዊ ሚዲያው ፍጆታና እውቅና ሲባል እንጂ። የአጋጣሚ ጉዳይ ሆኖ የነውርነቱ ሁሉ መነሻና መድረሻ የእኛ ሀገር ሆኖ እንጂ በሌሎች ዓለማት ቢሆን አንድ እርምጃ ማለፍ ባልተቻለ ነበር፡

ባደጉት ሀገራት አንድ ሰው ያለአንዳች መረጃና ማስረጃ ስሙ በአደባባይ ቢብጠለጠል ሳይውል ሳያድር ሕግን መከታ ማድረጉ አይቀሬ ነው። በእሱ ማንነት ላይ ተመርኩዘው መረጃ የሚደርቱትም ይህን ድፍረት አይሞክሩትም። ቢሞክሩትም ስለሚያወሩት ጉዳይ እርግጠኞች ሆነው ነው፡፡

ወደእኛው ልማድ ስንመለስ ግን የሰዎችን ስም እንደፈለጉ ማብጠልጠል በሕግ የተፈቀደ ያህል እየተለመደ ነው። እንደውም አንዳንዶች ስም ሳታጠፉ ውላችሁ እንዳታድሩ የተባሉ ይመስላል። መነሻ መድረሻቸው ሁሉ የሰው ስምና ስም ብቻ ሆኗል። ሰውን ያነሳሉ፣ ይጥላሉ፣ ስሙን ያጠፋሉ፣ ታሪኩን ያጠለሻሉ፡፡

በጣም የሚገርመው ደግሞ የተከታዮቻቸው ብዛት። ከቁምነገር ይልቅ ሁሌም ለዚህ ጉዳይ የሚሳብ የሚማረከው ይበረክታል። ከቅርብ ግዜ ወዲህ የጋርዮሽ ስድድብና ብሽሽቅ ገሐድ መሆን ጀምሯል። ሁሉም ከያለበት በአንድ መስኮት ተገናኝቶ መለፋለፉን ሲቀጥል መነሻው የሰዎች ስምና ያልተገባ ሐሜት ነው፡፡

አጋጣሚ አግኝቶ ይህን መሰሉን ቆይታ መታዘብ የቻለ ተመልካች ጆሮው የማይሰማው ጉድ አይኖርም። ተናጋሪዎቹ ሲሻቸው ተራ በተራ አልያም ተገፋፍተው ይገቡና ነውራቸውን ያወርዱታል። በዚህ መሐል የሚወረወሩ የስድብ ቃላቶችና የሚሰነዘሩ ሀሳቦች ፍጹም ከጨዋነት የተጣሉ፣ የተጣረሱ ናቸው፡፡

አንዳንዶች ደግሞ ነገሬ ብለው የሚቦጭቁትን ሰው ተራ በማስያዝ በዕቅድ የሚንቀሳቀሱ ናቸው። ስሙ የሚብጠለጠለውን ሰው አስቀድመው የሚያውቁት ይመስላል። ከእነሱ የሚጠበቀው ስለግለሰቡ ጥቂት መረጃዎችና የመነሻ ሀሳብ ብቻ ነው። ፎቶግራፉን በግልጽ ለጥፈው አጥንቱ እስኪራቆት ሥጋውን ታናሽ ከታላቅ እያሉ ያወራርዱታል፡፡

በዚህ ትዕይንት ላይ እንደልማድ ሆኖ አስተያየት የሚሰጠው ተመልካች ብዙ ነው። አንዳንዱ የሐሜተኞቹን ነውርነት በግልጽ ይቃወማል። ሌላው ለንግግራቸው የ‹‹ወድጄዋለሁ›› ምልክትን ይነካል። የእነሱ ቢጤ ስም አጥፊው ደግሞ በእሳት ላይ ቤንዚን እንደመጨመር ነገሩን እያቀጣጠለ ያሟሙቃል፡፡

አንዳንዴ እንዲህ ዓይነቱን ልማድ ከሚያራምዱት ቡድኖች መሐል አንደኛው ተረኛ ሆኖ ሊብጠለጠል የሚችልበት ዕድል ይከሰታል። እርስ በርስ የመተማማት፣ የመሰዳደቡ ጉዳይ በሚኖር ጊዜ ለሐሜት ተራ የተያዘለት ሰው አረፍ ይልና የራሳቸው ትዕይንት ይቀጥላል። ይህኔ ታዲያ ጉድን በየዓይነቱ ማየትና መስማት ነው። አዕምሮ ያፈለቀው የማይመስል ቃላት የጦርነቱ ጥይት ይሆናል። ሥነምግባር ይሉት እውነት በአደባባይ ይዋረዳል። ነውርነትን የሚገልጹ ማገዣዎች ሁሉ ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡

በንግግራቸው መሐል ዕድሜ፣ ሴትነት፣ እናትነት፣ ክብርና፣ ታላቅነት የሚባሉ እውነታዎች አፈር ከድሜ ሲበሉ ማየት ብርቅ አይሆንም። ሁሉም የተሻለ፣ የተሻሻለ፣ የሚለውን ዘመነኛ ነውሩን በአደባባይ ሲያሰማ ከፊቱ አንዳች መሳቀቅ አይታይበትም። ይህ አይነቱ ሐቅ ዘመናችን እያሳየን ካለው ክፋት ጥቂቱ መገለጫ ነው፡፡

ማንም ቢሆን በተሻለ ቴክኖሎጂ ዘመናዊነትን ቢለማመድ አይጠላም። ኋላቀርነትን ወደ ኋላ አሸቀንጥሮ ዓለም ከሚገኝበት የሥልጣኔ ጥግ ቢደርስ ይወዳል። የዘመናዊነት አጠቃቀሙ ጤናማ ሆኖ ካልዘለቀ ግን ለእርሱም ሆነ ለሌላው ውጤቱ ሕመም መሆኑ አይቀርም። ይህ አይነቱ አይድኔ ሕመም በወቅቱ መታከም ካልቻለ ደግሞ ጉዳቱ በቀላሉ አይቋጭም፤ ከራስ አልፎ ትውልድ እስከመግደል ይቀጥላል፡፡

መልካም ይሏቸው ሰዎች ለትውልድና ለሀገር የሚበጀውን ታሪክ አውርሰው በክብር መዝገብ ስማቸውን በወርቅ ብዕር አጽፈው ያልፋሉ። አንዳንዶች ደግሞ ሕይወታቸውን በአልባሌ ታሪክ አዋዝተው፣ በአሳፋሪ ማንነት ተገልጠው የሞት ጽዋን ይጎነጫሉ፡፡

ዘመናት አልፈው ዘመናት ቢተኩ የሰው ልጆች ክፉ ደግ ታሪክ በማንነታቸው ልክ ሊነሳ ግድ ይለዋል። ይህ እውነት ከራስ አልፎ ለትውልድ በተሻገረ ጊዜም የኩራትና እፍረት ንቅሳት ደምቆ ይወጣል። አበው ሲተርቱ ‹‹ሰው ለሰው መድኃኒቱ ነው›› ይላሉ። ሰው ስለ ሰው ጠላቱ ሲሆን ደግሞ እነሆ! ማንነት እንዲህ ሆኖ ይገለጣል። በክፋት፣ በተንኮልና ስም ማጥፋት። አበቃሁ!

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You