በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ አምስት ነዋሪ ወጣት ዳንኤል ደምሴ ተወልዶ ያደገው በዚሁ ወረዳ የቤት ቁጥር 280 ውስጥ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ቤቱም በ1967 ዓ.ም በአዋጅ የተወረሰ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ በወቅቱ እነ ገብሩ ንስራነ በሚል ስም 12 ሰዎች ተመዝግበው ይኖሩ ነበር፡፡ አቶ ገብሩ አጎታቸው እንደሆኑ የሚናገረው ወጣቱ፤ አባታቸው በ1995 ዓ.ም ማረፋቸውን ተከትሎ በዓመቱ ለአጎታቸው ባለቤት ወይዘሮ አስካለ ፍቅሩ ስም ዝውውሩ ተደርጎላቸዋል፡፡ በ1996 ዓ.ም እንዴትና ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባልታወቀ ሁኔታ የተደረገው ስም ዝውውርም ምላሽ ሳያገኝ ሲንከባለል ይቆያል።
ወጣት ዳንኤል፤ ድርጊቱ ሲፈፀም ያሳወቃቸው አካል እንዳልነበር ነው የሚናገረው፡፡ ለ12 ሰዎች በሚል የተሰጠው የመንግሥት መኖሪያ ቤት በአንድ ግለሰብ ስም ያውም ግለሰቡ በሕይወት እንዳሉ እየታወቀ እንዴት ሊዛወር ቻለ? የሚለውን ጥያቄ ግን ፍቺ ሊያገኙለት አልቻሉም፡፡ በዚህም 2000 ዓ.ም ላይ አቤቱታቸውን ለወረዳውና ለክፍለ ከተማ አስተዳደር ያቀርባሉ፡፡ ይሁን እንጂ ጉዳዩ ምንም ዓይነት ምላሽ ሳያገኝ፣ መፍትሔ ሳይበጅ ብሎም ሕገወጥ ድርጊት የፈፀሙ አካላት ተጠያቂ ሳይደረጉ እነሆ ድፍን 10 ዓመት ያስቆጥራል።ተገቢው ፍትሕ ባለመስፈኑም በአሁኑ ወቅት ሕገወጡ ሕጋዊ ሆኖ ጭራሽ መብታቸው እንደተጣሰና ከአስተዳደሩ ቤቱን የሚመለከተው ማሕደር በመጥፋቱ ጎዳና ሊወድቁ እንደሆነም ይናገራል፡፡
ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ለጥያቄያቸው ምላሽ በጊዜው ላለማግኘታቸው ምክንያቱ ግለሰቧ እስከ ክፍለ ከተማ ድረስ የሚያውቋቸው የቤተሰብ አባላት መኖራቸው እንደሆነ እንደ ምክንያት አድርጎ ያነሳል፡፡ ቀድሞ መንግሥት ለጋራ የሠጣቸው ቤት እንደነበር በማወስ፤ ውሃና መብራት እንዲሁም የተለያዩ አገልግሎቶቹን ያገኙና ይጠቀሙ ነበር፡፡ የቤቱን ኪራይም በጋራ ይከፍሉ እንደነበር ነው የሚያስታውሰው፡፡ ሆኖም በአሁኑ ወቅት የቤቱ ዋና ማሕደር ሰነድ የጠፋ በመሆኑ እኩል ባለመብት በነበሩበት ቤታቸው ባይተዋር ተደርገው ውሃ፣ መብራትም ሆነ መፀዳጃ ቤት መጠቀም እንዳይችሉ አድርጓቸዋል፡፡ «የአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ መሀል መገናኛ ላይ እየኖርን ለሰው ልጅ መሠረታዊ የሚባሉ አገልግሎቶችን እንኳ ማግኘት አልቻልንም» ሲል የዕለት ተዕለት ኑሯቸውን ለመግፋት ምን ያክል ከባድ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ያስረዳል፡፡
መንግሥት ዝቅተኛ የአኗኗር ሁኔታ ውስጥ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል በማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ ይሠራል፡፡ በዚህም በማሕበራዊ ሕይወታቸው የተጎሳቆሉና ኢኮኖሚያቸውም ዝቅተኛ የሆኑ ዜጎችን ከጎዳና እያነሳ መልሶ ለማቋቋም ቢሠራም «እኛ ግን ተወልደን ካደግንበት ቤት ወደ ጎዳና ልንወጣ ነው» በማለት ችግሩን በምሬት ይገልፃል፡፡ እርሱን ጨምሮ ሁለት እህቶቹና አንዲት የስድስት ዓመት ሕፃን የእህቱ ልጅ አስተዳደሩ ሊያስተካክለው ባልቻለው ሕገወጥ ድርጊት ገፈት ቀማሽ ሆነዋል፡፡
ቤቱ ሲወረስ መጀመሪያ ስድስት ክፍል ብቻ እንደነበር የሚያስታውሰው ወጣት ዳንኤል፤ በወቅቱ የከብቶች ማደሪያ የነበሩትን ክፍሎች በመደባለቅ በአሁኑ ወቅት እስከ 10 ክፍል የሚደርስ ቤት በግቢው ውስጥ እንደሚገኝ ይጠቁማል፡፡ ከዚህም በአንዱ ክፍል ውስጥ እነርሱ ይኑሩ እንጂ በርካታው ግን ለግለሰቦች ኪራይ የሚውል ነው፡፡ ምንም እንኳ ቤቱ የመንግሥት ቢሆንም ግለሰቧ ግን እንደ ግል ንብረታቸው እየተገለገሉበት በየወሩ ጠቀም ያለ ገቢ ከኪራይ ያገኛሉ፡፡ የእርሱን አባት ጨምሮ ሰባት ሰዎች በአሁኑ ወቅት በሕይወት እንደሌሉ በማንሳት፤ አስተዳደሩ ማህደሩ ቢጠፋም የተለያዩ ማስረጃዎችን ለምን አገላብጦ መመልከት እንዳልቻለ እንደማይታወቅና ምናልባትም ችግሩ ባለበት እንዲቀጥል የሚፈልግ አካል ስለመኖሩም ያለውን ጥርጣሬ ያመለክታል፡፡
መጀመሪያ ሲጠይቁ የነበረው መሠረታዊ ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ውሃ፣ የመፀዳጃ ቤት እንዲሁም መብራት ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን ጭራሽ ቤቱን በተመለከተ የሚያስረዳው በአስተዳደሩ የሚገኘው ዋናው ማሕደር ባለመኖሩ የመኖር ሕልውናቸውም አደጋ ላይ እንደወደቀ ወጣት ዳንኤል ይናገራል፡፡
ሌላኛው ወገን
የቅሬታ አቅራቢዎቹን አቤቱታ ይዘን ወደ ወይዘሮ አስካለ ጉዟችንን አደረግን፡፡ ቤቱን አስመልክቶ ለረጅም ዓመታት ሲከራከሩ መቆየታቸውን ነው ወይዘሮ አስካለ የሚናገሩት፡፡ በአዋጅ ከቀድሞ ባለቤታቸው አቶ ገብሩ አጎት የተወረሰ መሆኑንም ያስታውሳሉ።ቤቱ ልጆች ያፈሩበት ኑሯቸውን ለማቅናትም የደከሙበት ነው።ከትዳር አጋራቸው ጋር የነበራቸው የጋራ ሕይወትም ሲያበቃ ቤቱን በተመለከተ ክርክሩ ፍርድ ቤት ድረስ አምርቶ ነበር፡፡
በወቅቱ ቤቱ መንግሥት የወረሰው እንደሆነ እየታወቀ አቶ ገብሩ እና በሕይወት የሌሉት የእነ ዳንኤል አባት የአጎታቸው እንደሆነ ይሞግቷቸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር አድምጦና የሰነድ ማስረጃዎችን ተመልክቶ ለእርሳቸው መወሰኑን ያስረዳሉ፡፡ የቤቱ ወርሃዊ ክፍያ ሒሳብ 70 ብር ቢሆንም ለረጅም ዓመታት ከ1985 እስከ 1996 ዓ.ም ድረስ ሳይከፈል በመቆየቱም ውዝፍ መክፈል አቅቷቸው ከዘመድ አዝማድ ባገኙት ድጋፍ ድጋሚ ቤቱን እንደያዙትና ስሙም በእርሳቸው እንዲዞር የተደረገበት ምክንያት ይኸው መሆኑን ያብራራሉ፡፡
ቤቱ በአዋጅ እንደተወረሰና በወቅቱ የሚኖሩ በሚል አቶ ገብሩ ንስራነ እንደሆኑ የሚያሳይ የሰነድ ማስረጃም አውጥተው አሳዩን። በተያያዘ ቤቱ በ«እነ» የተመዘገበ እንዳልሆነና ደባል እንዳልሆኑም በተደጋጋሚ ይናገራሉ፡፡ ልጆቹን ጎዳና ከሚወድቁ በሚል ቢሰበስቧቸውም አላስኖር እንዳሏቸውና ፍርድ ቤት ድረስ ከሰዋቸውም መብት እንደሌላቸው ተገልፆ ለእርሳቸው እንደተፈረደላቸው ይናገራሉ፡፡ ቤቱም አራት ልጆችን ያለ አባት ለማሳደግ ደፋ ቀና ብለው ያቀኑት በመሆኑና ማንም ሲቸገሩ ዞር ብሎ ሳያያቸው የቤት ኪራይም ሳይከፍል የመብት ጥያቄ ቢያነሳም አሳልፈው እንደማይሰጡና ለመብታቸው እስከመጨረሻው እንደሚታገሉም ይናገራሉ፡፡
ሰነዶች
በየካ ወረዳ አስተዳደር የሕብረት ሥራ ማኅበር ጽሕፈት ቤት በቀን 7/5/1969 ዓ.ም በእጅ የተፃፈና ሕጋዊቱን ማረጋገጫ ማሕተሞች ያረፉበት ሰነድ በቀዳሚነት ከተመለከትናቸው ማስረጃዎች ውስጥ ይገኝበታል፡፡ በሰነዱ የፍርድ ሸንጎው በከሳሽ በቀበሌው ጽሕፈት ቤትና በተከሳሽ አቶ ገብሩ ንስራነ መካከል ስላለው ክስ ተመልክቶ የሰጠውን ውሳኔ ያስረዳል፡፡ ውሳኔውም ቤቱ በአጠቃላይ ስድስት ክፍሎች እንዳሉት ያረጋግጣል፡፡ ቤቱም በአዋጅ 47/67 በትርፍነት ለመንግሥት ከመዘዋወሩ አስቀድሞ የቤቱ ባለቤት ጋ ይኖሩ የነበሩ የቤቱ ባለቤት ዘመዶች ማለትም አቶ ገብሩ ንስራነና ደባሎቻቸው መቆየታቸው እንደተረጋገጠ የአኗኗር ሁኔታቸውን በዝርዝር ያትታል፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን የተመለከትን ሲሆን፤ ከነዚህ መካከል የመንግሥት ቤቶች የመኖሪያ ቤት የኪራይ ውሎች ይጠቀሳሉ፡፡ ከውሎቹ መካከል በ2002 ዓ.ም በአንድ ዓመት ውስጥ ቤቱ 70 ብር የሚከፈልበት ከመሆኑና ከሚገኝበት አድራሻ በስተቀር የመኖሪያ ቤቱ ክፍል ብዛት ግን ጥቅምት 24 ቀን 2002 ዓ.ም በተደረገው ውል ላይ ሰባት ሲል ነሐሴ 20 ቀን 2002 በዚያው ዓመት የተደረገ ውል ላይ ደግሞ 10 የመኖሪያ ክፍሎች እንዳሉት ያሳያል። መረጃዎቹን መመልከታችንን በመቀጠል ያገኘነው በ2011 ዓ.ም የተደረገ ውል ላይ ደግሞ የመኖሪያ ቤቱ ክፍል ብዛት ስምንት በሚል የተለያየ ማስረጃዎችን ያሳያሉ፡፡
በየካ ክፍለ ከተማ የወረዳ አምስት የቤቶች ልማት እና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በቀን 11/6/2010 ዓ.ም በመዝገብ ቁጥር የካ/ክ/ከ/
ወ/05/ቤ/ል/አስ/ጽ/ቤት 247/10 ወጪ ሆኖ ለክፍለ ከተማው ቤቶች አስተዳደር ጽሕፈት ቤት የላከው ደብዳቤ ሌላኛው ሰነድ ነው፡፡ በደብዳቤው በቀን 02/06/2010 ዓ.ም በደብዳቤ ቁጥር የካ/ቤ/አስ/ጽ/ቤት/1885/2010 የእነ ዳንኤል በወረዳው የቀድሞ ቀበሌ 07 የቤት ቁጥር 280 እየኖሩ እንደሆነ በመጥቀስ በፊት «በእነ ገብሩ ንስራነ» የነበረው በአሁኑ ወቅት በወይዘሮ አስካለ ፍቅሩ ስም መደረጉን ተጠቅሶ የተፃፈ ደብዳቤ እንደነበር ያትታል፡፡ በዚህም የመብራት፣ የውሃ እና መሠል አገልግሎቶችን ማግኘት አለመቻላቸውን በመጥቀስ በወረዳው በኩል መፍትሔ እንዲሰጣቸው መጠየቁን ያስረዳል፡፡
ጥያቄውን መሠረት አድርጎ ወረዳው ባደረገው የማጥራት ሥራም ሕጋዊ ተከራይ ሆነው ውል ያላቸውና የቤት ኪራይ እየከፈሉ የሚገኙት ወይዘሮ አስካለ መሆናቸውን እንዲሁም ቤቱ በእነ ገብሩ ንስራነ የነበረው በ1996 ዓ.ም በወይዘሮ አስካለ ስም ዝውውር የተደረገበት አባሪ አያይዘው ይልካሉ፡፡ በዚህም እነ ዳንኤል በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም ቤቱን በተመለከተ ላቀረቡት ጥያቄ ግን መፍትሔ ለመስጠት በወረዳው በኩል ምንም ዓይነት ሕጋዊ የሆነ መረጃ የሌላቸው መሆኑንም በደብዳቤው ያሳውቃል፡፡
የወረዳው የቤቶች ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ለወረዳው ፍትሕ ጽሕፈት ቤት በመዝገብ በቁጥር የካ/ክ/ከ/ወ/05/ቤ/ል/ጽ/ቤት 448/2011 ደብዳቤ ልኳል፡፡ ደብዳቤው በቀን 26/03/2011 ዓ.ም በከሳሽ ወይዘሮ አስካለ ፍቅሩና በተከሳሾች እነ ዳንኤል ደምሰው መካከል ስላለው የፍትሐብሔር ክስ የወረዳው ቤቶች ጽሕፈት ቤት ጣልቃ እንዲገባ መታዘዙን ያስነብባል፡፡ በዚህም ቤቱ በፊት በአቶ ገብሩ ስም ይጠራ እንደነበርና ኪራይም በሳቸው ስም ይከፈል እንደነበር ያረጋግጣል፡፡ ሆኖም በቁጥር የካ ክ/ከ/ቀ/15/2573/96 ዓ.ም በቀን 6/8/1996 ዓ.ም ግለሰቡም ማለትም አቶ ገብሩ በሕይወት እያሉ ስም የዞረበትን ወረቀት አያይዘው መላካቸውን ያስረዳል፡፡
የወረዳው የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በመዝገብ ቁጥር የካ/ክ/ከ/ወ/05/ወ/ኩ/ም/ቅ/ጽ/ቤት 0164/2011 ዓ.ም በቀን 12/02/2011 ዓ.ም ለወረዳው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽሕፈት ቤት ጉዳዩን አስመልክቶ የላከው ደብዳቤንም መመልከት ችለናል፡፡ በሰነዱ እንደተገለፀው፤ በቁጥር የካ/ክ/ወ/05/አስ/809/2011 ዓ.ም በቀን 12/02/2011 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ ቤቱን አስመልክቶ የተመዘገቡትን የቤተሰብ ዝርዝር፤ እንዲሁም ከመቼ ጀምሮ እንደተመዘገበ እንዲጣራ መጠየቁን ያስታውሳል፡፡ በተደረገው ማጥራት ሥራም ከቀን 26/01/1996 ዓ.ም ጀምሮ በወይዘሮ አስካለ የቤተሰብ ተጠሪነት የተከፈተ መሆኑን ያስረዳል፡፡ በቤቱ የተመዘገቡ ነዋሪዎች ብዛትም በመጀመሪያ 18 ሲሆን፤ ወይዘሮ አስካለ ባስገቡት ማመልከቻ መሠረት የተመዘገቡትን ነዋሪዎች በማሰረዝ ስድስት ቤተሰብ ብቻ መመዝገቡን በደብዳቤው ላይ ያመላክታሉ፡፡
የወረዳው ቤቶች ልማት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ለወረዳው ዋና ሥራ አስፈፃሚ በቀን 30/01/2011 ዓ.ም በቁጥር የካ/ክ/ከ/ወ/05/ቤ/ል/ጽ/ቤት/201/2011 ወጪ በሆነ ደብዳቤ ቤቱን አስመልክቶ መረጃ መላኩን የሚያሳይ ደብዳቤ ይገኛል፡፡ በዚህም ጉዳዩን አስመልክቶ ተጣርቶ እንዲቀርብ ከዋና ሥራ አስፈፃሚ በተሰጠ ትዕዛዝ መሠረት ቦታው ላይ በመውረድ እንደተጣራ ተጽፏል፡፡ በዚህም ቤቱ አንድ ሲሆን፤ ቅሬታ አቅራቢዎች በአንድ ክፍል እንደሚኖሩና በአጠቃላይ በውል ላይ ያለ የመኖሪያ ቤት ክፍል ብዛት ስምንት ክፍል ቢሆንም በአካል ጉዳዩን ሲያጣሩ ግን በቦታው 11 ቤቶችን እንደተመለከቱም ለዋና ሥራ አስፈፃሚው በተላከው ደብዳቤ ላይ ይነበባል፡፡
እንዴት ተፈፀመ?
በወረዳው የመንግሥት ቤቶች አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ጌጤነው ደምሌ፤ ጉዳዩ የቆየ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ቤቱ የቀድሞ ቀበሌ 07 የሚገኝ ሲሆን፤ ሕጋዊ ተከራይም ወይዘሮ አስካለ ፍቅሩ ናቸው። ቤቱ «በእነ» ሆኖ የአባታቸው ሕይወት ከማለፉ በፊት «እነ ገብሩ ንስራነ» በሚል ይኖሩ እንደነበር ቅሬታ አቅራቢዎቹ ይናገራሉ ፡፡ ይህንን መነሻ በማድረግ ሲታይ የነበረው ውል በአቶ ገብሩ ንስራነ ነው ይላሉ፡፡ ነገር ግን አቶ ገብሩ በሕይወት እያሉ ወደ ግለሰቧ ስም እንዲዞር ተደርጓል ይላሉ፡፡
ባል ወይም ሚስት በሕይወት እያለ ስም ማዞር በመመሪያው መሠረት እንደማይቻልም ቡድን መሪው ያስረዳሉ፡፡ ታዲያ ይህ ከሆነ ስሙ እንዴት ሊዞር ቻለ? ያቀረብንላቸው ጥያቄ ነበር፡፡ ሆኖም «ጥያቄው የእኛም ነው» ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተውናል፡፡ ስም ዝውውሩ ከተደረገ ቢቆይም የታወቀው ግን በቅሬታ አቅራቢዎቹ አማካኝነት በዘንድሮ ዓመት ነው፡፡ ድርጊቱ እንዴት ተፈፀመ? የሚል ጥያቄ ሲነሳም በወቅቱ የነበረው አመራር ተሰብስቦ ስም መዞር አለበት የሚል ቃለ ጉባዔ ተይዞ ነው የሚል ምላሽ ቢገኝም ይህ ቃለጉባዔ ግን ሊገኝ እንዳልቻለ ይናገራሉ፡፡ ወይዘሮ አስካለ ሲጠየቁም በቃለጉባዔ እንደዞረ ይናገራሉ፡፡ ጉዳዩን በጥልቀት ለማጥራት ቢሞከረም ለዚህ የሚረዳ ማብራሪያ የሚሆን ሰነድ ግን ሊገኝ አልቻለም፡፡
ምን መፍትሔስ ተወሰደ?
ቅሬታ አቅራቢዎቹም የሕጋዊነትና በቤቱ የመኖር ጥያቄ አንስተዋል፡፡ አስተዳደሩ ደግሞ ጥያቄውን ተቀብሎ እንዳያስተናግድ ቤቱ በወይዘሮ አስካለ ስም የሚገኝ መሆኑ ከሕግ አንፃር የማይቻል አድርጎታል፡፡ ልጆቹም መነሻ የሚሆን ማስረጃ እንዲያቀርቡ ቢጠየቁም ተጨባጭ የሆነ ማስረጃ እንደሌለ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን 12 የሚጠጉ ሰዎች የያዙት ቃለጉባዔ ቢቀርብም ይህን የሚደግፍ ሕጋዊና አሳማኝ ሰነድ ግን ሊገኝ አልቻለም፡፡ አስተዳደሩም ዝም ከማለት ይልቅ ለሚመለከተው አካል ምን መደረግ እንዳለበት ውይይት አድርጎበታል። ሆኖም ግን ቅሬታ አቅራቢዎቹን ባለመብት ለማድረግ አልተቻለም፡፡ ሕጋዊ ተከራይዋም በተደጋጋሚ ውሳኔ እንደተሰጣቸው የገለጹ በመሆኑ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አስተዳደሩ እንደተቀበለ አቶ ጌጤነው ችግሩን ለማቃለል የሄዱበትን ርቀት በሰጡት ማብራሪያ ያስረዳሉ፡፡
የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ዳንኤልና ቤተሰቡ እንደማይመለከታቸው ለግለሰቧ እንደወሰነም ቡድን መሪው ያስታውሳሉ፡፡ በዚህም ማዕድ ቤት፣ መፀዳጃ ቤትም ሆነ ሌሎች ግልጋሎቶችን መጠቀም እንደማይችሉም ከውሳኔው ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ የልጆቹን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ካሉት ማስረጃዎች አንፃር አስተዳደሩን መመሪያ ቢይዘውም ችግሩን ግን ካመናችሁበት ለምን መቀልበስ አልቻላችሁም? ሌላኛው ጥያቄያችን ነበር፡፡ ይህንን ለማስተካከል ምንም ማስረጃ ባለመገኘቱ ድርጊቱ ስህተት መሆኑ ቢታወቅም መቀልበስና ማረም ግን እንዳልቻሉም ነው አቶ ጌጤነው በምላሻቸው የነገሩን፡፡
ሌላኛው የቅሬታ አቅራቢዎቹ ጥያቄ የእናት ማሕደሩ መጥፋቱ ነው፡፡ ሰነዱ በተደጋጋሚ ቢፈለግም እንደጠፋ ይናገራሉ፡፡ የአስተዳደሩ ሕንፃ ግንባታ ሲፈፀም የነበረው የሰነዶች አቀማመጥ ትክክል ስላልነበር ይህ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል በመግለጽ፤ በአሁኑ ወቅት ኮሚቴ ተዋቅሮ ችግሩን ለማስተካከል እየተሠራ መሆኑን አቶ ጌጤነው ይጠቁማሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ማሕደር ሲደራጅ ከዓመት በፊት እንደነበር የአስተዳደሩ ሠራተኛ መስክሯል፡፡ ይህንን መነሻ በማድረግ ቢፈለግም ግን ሊገኝ አልቻለም፡፡ ነገር ግን ጠፍቷል ወይም ከሌሎች ሰነዶች ጋር ተደባልቆ ነው የሚለው ጥያቄ ምላሽ ማግኘት የሚችለው ማሕደሮችን መልሶ የማደራጀት ሥራው ሲጠናቀቅ እንደሆነ ይገልፃሉ።
ኃላፊው ምን ይላሉ?
በየካ ክፍለ ከተማ የወረዳ አምስት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አብርሃም ኪዳነማርያም፤ ምንም እንኳ አስተዳደሩ ቅሬታቸውን ሊፈታው ባይችልም ትክክለኛ መሆኑን ግን ያምናሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ቅሬታ አቅራቢዎቹ ውሃም ሆነ መብራት መጠቀም እንደማይችሉ በመግለጽ፤ ወረዳውም የቅሬታቸውን ትክክለኛነት አምኖበት ከእነርሱ ጎን እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በአንድ ወቅት በፍርድ ቤት በነበራቸው ክርክር ላይም ወረዳው ጣልቃ ገብቶ ፤እነርሱን ደግፎ ሲከራከር መቆየቱን ያስታውሳሉ፡፡
በ2011 ዓ.ም መጀመሪያ ወርሃ መስከረም ላይ ወደ ወረዳው መምጣታቸውን የሚናገሩት አቶ አብርሃም፤ ወጣት ዳንኤልና ቤተሰቦቹ ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ እንደቆዩ ይገልፃሉ፡፡ ይህን ያህል በደል የደረሰባቸውም ግለሰቧ የሚረዳቸው ሰው በመኖሩ እንደሆነ ነግረዋቸዋል፡፡ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ግለሰቧ ክፍለ ከተማ ድረስ ሰው እንዳላቸው ቢያነሱም ለዚህ መሠል ጣልቃ ገብነት ግን አስተዳደሩ ክፍት ስላልሆነ በዚህ መልኩ የሚፈጠር ክፍተት እንደማይኖርም ያረጋግጣሉ፡፡ ጉዳዩን ለማረጋገጥ ብዙ ርቀት እንደተጓዙ የሚገልጹት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ ለወረዳው የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት እንዲሁም ለቤቶች ጽሕፈት ቤት በደብዳቤ መጠየቃቸውን ነው የሚናገሩት፡፡ ስም ዝውውሩ እንዴት እንደተደረገ? በአሁኑ ወቅት ቤቱ በማን ስም ተመዝግቦ እንዳለ? እንዲሁም ማንና እንዴት እንዳዞረው ግልጽ ተደርጎ መረጃው እንዲላክላቸው ለጽሕፈት ቤቶቹ ለጠየቁት ጥያቄም ማን እንዳዞረውም ሆነ ድርጊቱ እንዴት እንደተፈፀመ የሚታወቅ ነገር እንደሌለ ምላሽ እንደተሰጣቸው ያስታውሳሉ፡፡ ድርጊቱ ሆነ ተብሎ የተፈፀመ እንደሚሆንም ያምናሉ፡፡
ውሉ በአሁኑ ወቅት የሚገኘውና ሕጋዊ ተከራይ ሆነው ስማቸው የሰፈረውም የወይዘሮ አስካለ ሲሆን፤ በየጊዜው የሚመዘገበው የመኖሪያ ቤቱ የክፍል ብዛትም ይለያያል፡፡ ድርጊቱ ከተፈፀመ ዓመታት ስለተቆጠረ በአሁኑ ወቅት ይህንን ሊያስረዳ የሚችል ፈፃሚ ባለሙያም ሆነ ሰነድ ሊቀርብ አለመቻሉንም ይገልፃሉ፡፡ አቶ ገብሩ ባለቤታቸው ከነበሩት ከወይዘሮ አስካለ ጋር ፍቺ ሲፈፅሙ እንዴት እንደሆነ ባልታወቀ መንገድ ስም ዝውውሩ ቢደረግም፤ ቅሬታ አቅራቢዎቹ በቤቱ ከ20 ዓመታት በላይ እንደኖሩ ግን የአካባቢው ሕብረተሰብ ሕያው ምስክር እንደሆነ ትዝብታቸውን ይናገራሉ፡፡
በመመሪያ ደረጃ ስም ዝውውር ማድረግ የሚቻለው ቤቱ ይጠራበት የነበረው ግለሰብ በሕይወት ከሌለ ነው የሚሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ በዚህም በቤቱ ለረጅም ዓመታት መኖሩ የተረጋገጠ፣ እንደ ልጅ ሆኖ ለረጅም ዓመት የቆየ አልያም የሟች ሚስት ወይንም ባል ሊዛወርላቸው እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡ መመሪያው የሚያስቀምጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች እንዳሉ በመግለጽም ግለሰቡ በሕይወት እያለ ግን ስም ዝውውር ማድረግ አይቻልም ይላሉ፡፡ ይሁን እንጂ በወረዳው የቤት ቁጥር 280 መመሪያው በማይፈቅደውና እንዴት እንደሆነ ባልታወቀ ሁኔታ አቶ ገብሩ በሕይወት እያሉ ስም ዝውውር ተደርጓል። ድርጊቱን በተመለከተ ቃለጉባዔ ተይዞ እንደተለወጠ ቢነሳም፤ ይህን ሊያስረዳ የሚችል ማስረጃ ግን ማግኘት አልተቻለም፡፡ ቅሬታ አቅራቢዎቹም ሆነ ተብሎ የተፈፀመ ድርጊት እንደሆነና በስምም ከኃላፊ እስከ ባለሙያ የሚያነሷቸው ግለሰቦች እንዳሉ አቶ አብርሃም ይናገራሉ፡፡ ሆነ ተብሎ የተፈፀመ ከሆነም ግለሰቦቹ በሕይወት ያሉ በመሆናቸው መክሰስ ይቻላል የሚሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ በድርጊቱ ተሣታፊ የሆኑ አካላትን ተጠያቂ ማድረግ እንደሚቻል ያረጋግጣሉ፡፡
ድርጊቱ ሕጋዊ አለመሆኑ ቢታወቅም ማስረጃ በመጥፋቱ ግን ድርጊቱን የፈፀሙ ግለሰቦችን ተጠያቂ ለማድረግ እንዳዳገታቸው ይገልፃሉ፡፡ እንዴት እንደዞረና ማን እንዳደረገው ለመጠየቅም ማስረጃ ያስፈልጋል የሚሉት አቶ አብርሃም፤ ሰነድ ማስረጃ ቢኖር ወደነበረበት አልያም ደግሞ ወደ መንግሥት እንዲዞር ይደረግ ነበር፡፡ ነገር ግን ግለሰቧ ሕጋዊ ተከራይ ከሆኑበት 1996 ዓ.ም አስቀድሞ ያለው ማስረጃ የለም፡፡ ከ1996 ዓ.ም በኋላ ደግሞ ያለው መመሪያ ግለሰቧን የሚደግፍ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ኪራይ ከመክፈል ጀምሮ በስማቸው ሕጋዊ የሚያደርጓቸውን ሰነዶች ይዘዋል፡፡ ይህን መሠል ችግር በወረዳው ብቻ ሳይሆን በከተማ ደረጃ የሚስተዋል እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡
መንግሥት የራሱ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ ካላወጣ በስተቀር በቤቶች አስተዳደር ሦስት ክፍል የተዋዋሉ ተከራዮች እስከ 10 እና ከዚያ በላይ ክፍሎችን በግንባታ ያስፋፋሉ፤ አከራይተውም ይጠቀማሉ፡፡ ማከራየት ደግሞ አይቻልም፡፡ ነገር ግን በዚህ ላይ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩ ግለሰቦች ከአስተዳደሩ በላይ እየሆኑ ወረዳውንም እየከሰሱ ጭምር ሲረቱት ይስተዋላል። ከወረዳው ፍላጎት ውጪም የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ ወጥቶላቸው ጭምር ውጡ ተብለው የፍርድ ቤት ዕግድ በማምጣት ተከራክረው ያሸነፉና የሚኖሩ አሉ፡፡ ይህ ተገቢ ባይሆንም የሕግ ክፍተት ያመጣው በመሆኑ መንግሥት ሊያስተካክለው እንደሚገባም ነው የሚገልጹት፡፡
የቅሬታ አቅራቢዎቹን ጉዳይ የሚደግፍና የተበዳዮቹን እንባ ያብሳል ተብሎ የሚታመነው ከወረዳው መገኘት የነበረበት እናት ማሕደር ቢሆንም ይህ ግን በአስተዳደሩ ሊገኝ እንዳልቻለ ይገልፃሉ። ይህም ማሕደሩ ለምንና እንዴት ጠፋ? የሚል ጥያቄን ያጭራል። በአስተዳደሩ የሚገኙ ማሕደሮች አቀማመጥ ተከማችቶ የሚገኝ በመሆኑ ይህን ለማስተካከል እየተሠራ ነው፡፡ ጨረታ በማውጣትም ድጋሚ የማደራጀትና ይህንንም በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩም ዘለቄታዊ መፍትሔ ለመስጠት እየተሠራ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡ ይህም ሙሉ በሙሉ የቤት ቁጥር 280 ማሕደር ጠፍቷል ማለት የማይቻልበትና ሰነዶችን ዳግም በማደራጀት ሒደት ውስጥ ሊገኝ ይችላል የሚል ተስፋ እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ነገር ግን ሆነ ተብሎ እንዲሰወር ከተደረገ ሊገኝ አይችልም፡፡ በዚህም በ«እነ» ካሉ ባለመብት መሆን ቢችሉም በተቃራኒው ሰነዱ ባሌለበት፣ ከወረዳው ጋር የፀና ውል የሌላቸውና የቤት ኪራይ ሳይከፍሉ ግን ባለመብት መሆን አይችሉም ይላሉ፡፡ ስለሆነም ማሕደሩ እንዲገኝ አስተዳደሩ በትኩረት እየሠራ ይገኛል፡፡ ይህም ውጤታማ ከሆነ እንባቸውን ማበስ ይቻላል ሲሉ አቶ አብርሃም ተስፋቸውን ይገልፃሉ፡፡
ምን ታሰበ?
ሰነዶችን የማደራጀት ሥራው ከተጀመረ አንድ ሣምንት ያስቆጠረ ሲሆን፤ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። ማሕደር የማስተካከል ሥራው ሲጠናቀቅ ማህደሩ ከተገኘ ችግሩን ለማስተካከል መፍትሔ የሚበጅ ሲሆን ካልተገኘ ደግሞ በወረዳው ቤት ለማግኘት ከተመዘገቡትና ተራ ከሚጠባበቁት 1 ሺህ 200 የሚሆኑ በዝቅተኛና አስከፊ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ካሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተራ ጠብቀው እንዲታዩ ይደረጋል፡፡ ይህ ደግሞ እነ ዳንኤል ችግረኞች እንደሆኑ ቢታመንም እንኳ ወደ ደረጃ ውስጥ ሲገባ ግን የባሰ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ አካላት ቅድሚያ እንደሚሰጥ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ያስረዳሉ፡፡ በቀጣይም መንግሥት መሠል ችግሮችን ለማቃለል የሚደግፍ የሕግ ማዕቀፍ እንዲወጣ ሲያደርግ ድርጊቱን የፈፀሙ ግለሰቦች በሕግ ተጠያቂ እንደሚደረጉ ያመላክታሉ፡፡
ክፍለ ከተማው
ጂ.አይ.ኤስ. ወይንም ጂኦግራፊክ ኢንፎርሜሽን ሲስተም በ1988 ዓ.ም፣ በ997 እንዲሁም 2003 ዓ.ም በአየር በረራ የተነሳ ፎቶ ሲሆን፤ በዚያው ዓመት ቤት ለቤት በመዞር የቤቱ ባለቤት ማነው የሚለውን ማወቅ እንዲቻል የተሰበሰበው መረጃም ሲ.አይ.ኤስ. ይባላል፡፡ በዚህም የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ለመስጠት፣ መብት ለመፍጠር እንዲሁም ባለቤትነትን ለመወሰን እነዚህ መረጃዎች ጠቃሚ ናቸው። መረጃዎቹም አንድ ቤት ከ1988 በፊት እንደተሰራ ማሳያ ነው፡፡ ሲ.አይ.ኤስ. ላይ ደግሞ የማን ቤት እንደሆነ ማረጋገጫ ይሆናል፡፡ ይህ ማለት ግን ባለቤትነትን ባያረጋግጥም ባለቤትነትን ለማረጋገጥ አጋዥ መረጃዎች ናቸው፡፡ እኛም ቤቱን አስመልክቶ ምንም እንኳ የሰነድ ማስረጃዎች እንደጠፉ ቢገለጽልንም በተለያዩ ወቅቶች መንግሥት ይዞታዎችንና ባለቤቶቻቸውን ለማጥራት የሠራቸው የጂ.አይ.ኤስ. እና ሲ.አይ.ኤስ. መረጃዎችን ለመመልከት ወደ የካ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት አመራን፡፡ በጽሕፈት ቤቱ ባገኘነው መረጃም ቤቱም ባለቤትነቱ የቀበሌ ሆኖ ከ1988 ዓ.ም በፊት ያለና ስሙም በአቶ ገብሩ ንስራነ እንደሚገኝ ከጽሕፈት ቤቱ ማረጋገጥ ችለናል፡፡
ማጠቃለያ
መንግሥት በከተማዋ ያለውን ሰፊ የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ለማቃለል የተለያዩ አማራጮችን ይጠቀማል፡፡ ከዚህ ውስጥ አንዱ «የደሃ ደሃ» በሚል የከፋ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የቀበሌ ቤት ባለቤት የሚያደርግበት ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ በቀበሌ ቤቶች ውስጥ በጧሪነት፣ በልጅነት አልያም ለረጅም ዓመታት የኖሩ ዜጎችን ቤቱን ከመንግሥት ጋር ውል ፈፅሞ የሚኖረው ግለሰብ ሕይወት ቢያልፍም በዚያው እንዲቀጥሉ ያደርጋል፡፡ ይሁን እንጂ በዘገባችን እንዳወጣነው ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተወልደው ካደጉበት ቤት ያለአግባብ ሊወጡ መሆኑን ያቀርባሉ፡፡ አስተዳደሩም ችግሩ እንዳለ እያመነ ችግሩን ሊቀለብስ ያልቻለው ግን የሰነድ ማስረጃዎች በማጣቱ እንደሆነ ይገልፃል፡፡
ለጉዳዩ የጠፉትን የሠነድ ማስረጃዎች ማፈላለግና ፈጣን ምላሽ መስጠት አንዱ መፍትሔ ነው፡፡ በተጨማሪም በአገሪቱ ሕጋዊ፣ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ውሳኔዎች እንደሚወሰዱ ይታወቃልን፡፡ በተለይም አስተዳደሩ ራሱ በሚያስተዳድረው ቤቶች ላይ የመወሰን ሥልጣን ያለው በመሆኑ ሕብረተሰቡ እንደሚመሰክር በመግለጹም የሕብረተሰቡን ድምጽ ብሎም የተለያዩ ማረጋገጫ ሊሆኑ የሚችሉ ደጋፊ ማስረጃዎችን አጣምሮ የአስተዳደራዊ ውሳኔ ሊያሳርፍ ይገባል፤ የሚመለከተው አካልም ሊመለከተው ይገባል በሚል እናብቃ፡፡
አዲስ ዘመን ሀምሌ10/2011
ፍዮሪ ተወልደ