የሕግ ዕድሜ ከሰው ፍጥረት እኩል ነው ቢባል ያለ አዋቂ ንግግር አይሆንም። ምክንያቱም ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ከፈጣሪ የሰማው ቃል መብትና ግዴታን የሚገልጽ ሕግ መሆኑን በቅዱሳን መጻሕፍት ተጽፎ እናገኛለን። በሃይማኖት ትምህርት መንፈሳዊ ሕግጋት አሉ። በምድር አስገዳጅ የሕግ አስፈጻሚ አካል ባይኖራቸውም ሰው በመንፈስ እንዲገዛ አድርገውታል። በከፍተኛ ደረጃ የሚያከብራቸው እና የሚኖርላቸውም ሆነው እናገኛቸዋለን።
ሳይንስ ሳይቀር የተፈጥሮ ሕግጋት በማለት የሚጠራቸው የሕጎቹን ኃያልነት በደንብ ስለሚረዳው ነው። የትኛውም የፊዚክስ ፈጠራ መሰረት እነርሱ እንደሆኑም ይታመናል። ለምሳሌ፡- የመሬት የስበት ሕግ ባይኖር ወይም የሚቀያየር ወይም የሚለዋወጥ ቢሆን ኖሮ ሰው በአይሮፕላን መብረር ባልቻለ ነበር። ፕላኔቶች በፀሐይ ዙሪያ ሲሽከረከሩ ምህዋራቸውን(ገደባቸውን) ጠብቀው ባይሆን ኖሮ ፀንተው ባልኖሩ ነበር። ሌሎችም እንዲሁ!
ሰው በምድር በጋራ መኖር ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ ደግሞ በተለያየ ቅርጽ ለራሱ ሕግ ሰርቶ መኖር እንደጀመረ የሕግ ታሪክ ትምህርት ያሳያል። በሂደትም ቅርፅ የያዙ እና የተጻፉ ሕጎችን ሰርቶ በመተግበር ዛሬ ላይ ደርሷል። ከቀደምት ስልጣኔዎች መካከል ‘የሜሶፖታሚያ’ ስልጣኔ መሪ የነበረው ንጉስ ሀሙራቢ የሰራው የሀሙራቢ ሕግ የመጀመሪያው ቅርፅ የያዘ ወይም የተጻፈ ሕግ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
በዚህ ሕግ ዘመን ሰው “የገደለ ሰው እንዲገደል፣ ዓይን ያጠፋ ሰው ዓይኑ እንዲጠፋ፣ የሰረቀ ሰው እጁ እንዲቆረጥ፣ የተበላሸ ሕንፃ የሰራ ሰው ልጁ እንዲገደል…ወዘተ” ሕጉ ይደነግጋል። ከዚህ አንጻርም ኢትዮጵያም የምትመራባቸው ክብረ-ነገሥት፣ ፍትሐ-ነገሥት እና ፈውሰ- መንፈሳዊ የተባሉ ጥንታዊ ሕግጋት ነበሯት። በእንደዚህ ሂደት እያደገ መጥቶም ዛሬ ላይ የአንድ ሀገር መሠረታዊ መገለጫ እስከመሆን ደርሷል።
ሕግ የሚለው ቃል በብዙ መመዘኛዎች ከተለያዩ ምልከታዎች አንፃር በተለያየ መንገድ ሊገለፅ እና ሊተረጎም ይችላል። የእኛ ትኩረት ሀገር ላይ ያነጻጸረ በመሆኑ ይህንን ስንመለከተው ሕግ ማለት የአንድ ሀገር ነዋሪዎች የጋራ መግባቢያ፤ የእድገት እና ስልጣኔ መሰረት፤ የሀገረ-መንግሥት ሥርዓት መዘርጊያ መሳሪያ፤ ጠንካራው ደካማውን፣ ባለጠጋው ደሃውን፣ ባለሥልጣኑ ሕዝቡን እንዳይበድለው የሚቀረጽ ዋስትና ነው። በጥቅሉ ሕግ ሀገርን የማፅኛ፤ መርሆዎችን የማሰሪያ ገመድ ነው ሊባል ይችላል።
ሕግ የታለመለትን ዓላማ የሚያሳካ ስለመሆኑ የተለያዩ መስፈርቶችን በማስቀመጥ መመዘን የሚቻል ሲሆን፤ ለመረዳትና ቀለል ባለ መልኩ ለመግለጽ ሕግ ዓላማውን በአግባቡ የሚመታው አንድም በይዘቱ ከተፈጥሮ ሕግጋት እና ከሰዎች ልቦና ጋር የተዋደደ ሲሆን፤ በአተገባበሩ ደግሞ የተገዥውም የገዥውም የበላይ ሆኖ ሲቀመጥ እና ሲተገበር ወይም በሙያው አገላለጽ የሕግ የበላይነት እውነተኛ መሰረት ሲይዝ ነው።
የሕግ ይዘትን በተመለከተ በ1952 የፍትሐብሔር ሕጉ መግቢያ ላይ የተፃፈው ሃሳብ እጅግ ጠንካራ የሕግ ፍልስፍና ሆኖ እናገኛዋለን። ሃሳቡም “ማናቸውም ሕግ የሰዎችን መብትና ግዴታ ለመግለፅ እንዲሁም በመካከላቸው ያሉት ግንኙነቶች የሚተዳደሩበትን መሠረታዊያን ሃሳቦች ለመግለጽ የወጣ ሲሆን ሕጉ ከወጣላቸው ሰዎች ልብ የሚደርስ ፍላጎታቸውን ልምዳቸውን ወይም የተፈጥሮ ፍትሕን የሚጠብቅ ካልሆነ በቀር ዋጋ ሊኖረው አይችልም” የሚል ነው። ይህ አገላለጽ ሕግ ሊኖረው ይገባል ከሚባለው ባህሪው አንዱ የሆነውን ከተፈጥሮ ፍትህ ጋር የመጣጣምን መስፈርት የሚያሳይ ነው። ስለዚህ ሕግ በሚወጣበት ጊዜ ይዘቱን በውል መመርመር ሁልጊዜም አስፈላጊ ነው።
አተገባበሩን በተመለከተ ደግሞ በአንድ ሀገር ሕግ እና ፍትህ አለ ሊባል የሚችለው ሕጉ ብቻ ስላለ ሳይሆን ሕጉ ከሁሉም በላይ ሆኖ በአግባቡ መተግበር ሲቻል ነው። በዓለም ላይ እጅግ ሰልጥነዋል የምንላቸው ሀገራት በተለይም የምዕራቡ ዓለም ስልጣኔ ቀዳሚ መለያው የሕግ በጥብቅ መተግበር ነው። የሕግ የበላይነት ወይም የሕግ አተገባበር የፖለቲካ ምህዳርን ጨምሮ በሌሎች ማለትም በሰዎች የሕግ ግንዛቤ ሁኔታ፣ በኢኮኖሚ ሁኔታ፤ በሕግ አስፈፃሚ እና ተርጓሚ አካላት አደረጃጀት እና ብቃት ሁኔታ፣ በሕግ ባለሙያዎች የሥነ-ምግባር ሁኔታ፣ በዴሞክራሲ ተቋማት አይነት እና ጥንካሬ ሁኔታ …ወዘተ ሊወሰን የሚችል ነው።
የሕግ ሥርዓት ምንድነው?
የሕግ ሥርዓት የሚለውን ሐረግ በሕግ ሳይንስ ዕይታ ስንመለከተው የሕግ ሥርዓት ማለት ሕጉ፣ ሥርዓቱ፣ የሕግ-ሥርዓቱ መርሆዎች፣ የሕግ አመለካከት እና እምነቶች ድምር ወይም ውህደት ነው ልንል እንችላለን። ከዚህ አንፃር በዓለም ላይ የሚታወቁ ሁለት ዋና ዋና የሕግ ሥርዓቶች ያሉ ሲሆን፤ እነዚህም የተፃፈ የሕግ ሥርዓት እና ያልተፃፈ የሕግ ሥርዓት የሚባሉት ናቸው። በተግባር የሀገራትን የሕግ ሥርዓት ስንመለከተው ግን የሕግ ሥርዓቶቹ የሁለቱም ቅይጥ ሆነው እናገኛቸዋለን። ጉዳዩን በቀላሉ ለመገንዘብ በሀገራት ደረጃ መመልከት ጠቃሚ ነው።
ከላይ የጠቀስነው መነሻ ሃሳብ እንደተጠበቀ ሆኖ በየሀገሩ ያለው አጠቃላይ የሕግ እና የፍትህ ጉዳይ ተጠቃሎ ሲጠራ የሕግ ሥርዓት ወይም በእንግሊዝኛው አጠራር “Legal system” ይባላል። ታዲያ አንድ ሀገር ሕግጋት እና ሥርዓቶች ቢኖሯትም እነዚህ ሕግጋት እና ሥርዓቶች ተሰናስነው እና ተናበው የራሳቸውን ጠንካራ መልክ እስካልፈጠሩ ድረስ አንድ ሀገር የራሷ የሆነ የሕግ ሥርዓት አላት ለማለት አይቻልም። ኢትዮጵያም የራሷ የሆነ የሕግ ሥርዓት አላት/የላትም የሚለው ክርክር አሁንም በባለሙያዎች ዘንድ መደምደሚያ የተሰጠው አይደለም። ለዚህ ጽሑፍ ዓላማ ግን ለአረዳድ ይመች ዘንድ ኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት አላት የሚለውን ይዘን እንቀጥል።
በአንድ የሕግ ሥርዓት ውስጥ ሦስት ዋና ዋና የፍትህ አስተዳደር ሥርዓቶች አሉ። እነዚህም የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ሥርዓት፣ የፍትሐብሔር ፍትህ አስተዳደር ሥርዓት እና የአስተዳደር ፍትህ ናቸው። በኢትየጵያ ውስጥም እነዚህ ሥርዓቶች ይገኛሉ። በወንጀልና በአስተዳደር ፍትህ ውስጥ ከሦስቱ የመንግሥት ክንዶች መካከል አስፈፃሚው አካል ዋነኛ ተዋናይ ሆኖ የሚገኝ ሲሆን፤ በፍትሐብሔር ፍትህ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ደግሞ ዋነኛ ተዋንያኖች ሰዎች (የተፈጥሮ እና የሕግ ሰዎች) ናቸው። በሦስቱም የፍትህ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ዋናውና ወሳኙ አካል ደግሞ ሦስተኛው የመንግሥት ክንድ የሆነው ሕግ ተርጓሚው ፍርድ ቤት ነው።
የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ሥርዓት
ከሦስቱ የፍትህ አስተዳደር ሥርዓቶች ውስጥ እጅግ መሠረታዊ እና አንዱ የሆነው የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ሥርዓት ከዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጋር በእጅጉ የሚቆራኝ፤ አፈፃፀሙ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው የፍትህ ሥርዓት አይነት ነው። በዚህ ሥርዓት ውስጥ ካሉ የሕግ ተግባራት መካከል ወንጀል መከላከል፣ ወንጀል መመርመር፤ የወንጀል ፍርድ ሂደት እና ጥፋተኞችን ማረም ከዛም ወደ ህብረተሰቡ መመለስ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
ዜጎች እና አስፈፃሚ አካላት በየዕለቱ ሊገናኙ የሚችሉት በዚህ የፍትህ ሥርዓት ውስጥ ነው። ታዲያ ዜጎች እና ሰዎች በእነዚህ እያንዳንዱ ተግባራት ውስጥ ምን ግዴታ አለባቸው፣ ምን መብትስ አላቸው? በዚህ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ የሚሰሩ አስፈፃሚ እና የፍትህ አካላት በተለይም ፖሊስ እና አቃቢ ሕግ ምን ስልጣን አላቸው? የስልጣናቸው ገደብስ የት ድረስ ነው የሚሉት ጉዳዮች እጅግ ጠቃሚ ናቸው።
መብቱንና ግዴታውን የሚያውቅ ዜጋ ግዴታውን ለመወጣት ኃላፊነት ይወስዳል። ለምሳሌ የፍትህ ሥራን መተባበር የሕግ ግዴታ መሆኑን ያወቀ ሰው ምስክር ሆኖ ሲጠራ የዜግነት ግዴታውን ለመወጣት መንገድ መፈለጉ የማይቀር ነው። ለአደጋ የተጋለጠ ሰውን አለመርዳት ወንጀል መሆኑን የሚውቅ ዜጋ ቢያንስ ለፖሊስ ደውሎ ሁኔታውን የማሳወቅ ኃላፊነት እንዳለበት ይገነዘባል፣ ሕጋዊ ሥራውን በመሥራት ላይ የሚገኝን የመንግሥት ሠራተኛ ሕግ የሰጠውን ስልጣን አስመልክቶ በሚሰራበት ጊዜ መቃወምና አለመታዘዝ ወንጀል መሆኑን የሚያውቅ ዜጋ ሕግን ጠብቆ እንዲንቀሳቀስ ግንዛቤው ያግዘዋል። ሰዎች በሕይወት ያሉ ሰዎችን መብት መጣስ ብቻ ሳይሆን የሙታንን ክብር መንካት፣ የሞተን ሰው ስም ማጥፋት… ወዘተ ጭምር በሕግ የሚስጠይቅ መሆኑን ስንገነዘብ የሕግ የበላይነትን ብቻ ሳይሆን የሕግ ልዕልናንም እንማርበታለን።
በሌላ መልኩ ደግሞ የአካል ደህንነቱ የመጠበቅ መብት እንዳለው የሚያወቅ ዜጋ ማንም የአስፈፃሚ አካል ይህንን መብቱን እንዳይገፈው የማስረዳት ድፍረት ይኖረዋል፤ መብቱ ተጥሶ ጥቃት ከደረሰበትም አስፈፃሚውን አካል በሕግ የመጠየቅ እና የመክሰስ መብት እንዳለው ይገነዘባል። የመኖሪያ ቤት ነፃነቱ በሕግ የተጠበቀ መሆኑን የሚያወቅ ዜጋ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ እና በሕግ ከተቀመጡ ልዩ ሁኔታዎች ውጭ ማንም አስፈፃሚ አካል መጥቶ ቤቱን እንዳይበረብር የመቃወም፤ መብቱ ከተጣሰበትም በሕግ የመጠየቅ መብት እንዳለው ይገነዘባል። የሕግ አስፈፃሚ አካላትም ያላቸውን የሕግ ሥልጣን ገደብ በልኩ አውቀው እና የዜጎች መብት ሳይጣስ በጥንቃቄ ሥራቸውን መፈፀም መቻል ለሕግ የበላይነት መሠረት መያዝ እና ስር መስደድ እጅግ መሠረታዊው ጉዳይ በመሆኑ ሁልጊዜም የሕግ ግንዛቤን ለማስፋት መወያያት እና መማማር አስፈላጊ ነው።
ሕግን መገንዘብ በሁሉም የፍትህ አስተዳደር ዘርፎች ውስጥ እጅግ ጠቃሚ ብቻ ሳይሆን የፍትህ አስተዳደር ዘርፎቹም እንዲያድጉ ወሳኝ ነው። በመሆኑም በቀጣይ ጽሑፎች አሁን ከጀመርነው የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ዘርፍ በመጀመር በሌሎች የፍትህ ዘርፍ ውስጥ ስላሉ ሕጎች፤ መብትና ግዴታዎች ዙሪያ የተለያዩ ጽሑፎችን የምናደርስ ይሆናል።
ይግረማቸው ከፈለኝ
/ጠበቃና የሕግ አማካሪ እንዲሁም
በወንጀል ፍትህ አስተዳደር ላይ አሰልጣኝ/
0910037554/yigremachewk@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥቅምት 23/2017 ዓ.ም