ቡሳ ጎኖፋ- የመረዳዳትና ፈጥኖ የመድረስ ባህላዊ እሴት

በመስከረም 25 እና 26 ቀን 2017 ዓ.ም የተከበረውን የኢሬቻ ባህላዊ በዓል አስመልክቶ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን በስካይ ላይት ሆቴል የኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንት ኤግዚቢሽን ለሦስት ቀናት ማካሄዱ ይታወሳል። በኤግዚቢሽኑ ላይ የክልሉ የቱሪዝም መስህቦች፣ የቱሪዝም ዘርፍን የሚያሳዩ ተግባራትና በርካታ የክልሉ ባህላዊ እሴቶች ቀርበው ተዋውቀዋል፡፡ ባንኮችና የቴክኖሎጂ ተቋማትም በኢግዚቢሽኑ ተሳትፈዋል፡፡

የገዳ ስርዓት አንዱ እሴት የሆነው የቡሳ ጎኖፋ የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴትም በአውደ ርዕይው ቀርቦ ለታዳሚያኑ ቀርቦ እንዲተዋወቅ ተደርጓል። የዝግጅት ክፍላችን የዚህን አገር በቀል ባህላዊ ስርዓት ምንነት፣ ጠቀሜታና አጠቃላይ እሴቶቹን በዛሬው ›ሀገርኛ› አምድ ላይ ይዞ ቀርቧል፡፡

ወይዘሮ ኤልዳና ሱሌማን በቡሳ ጎኖፋ የኦሮሚያ የኮሙኒኬሽንና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምክትል ኃላፊ ነች። እሷ እንደምትለው፤ ቡሳ ጎኖፋ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እንደ አንድ የአደጋ መከላከል ተቋም የሚሰራ ሲሆን፣ ከዚያም ያለፉ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ማእቀፎች በመያዝ የተቋቋመ ድርጅት ነው።

ቡሳ ጎኖፋ የሚለውን ስያሜ ያገኘው ከኦሮሞ የገዳ ስርዓት ነው። በገዳ ስርዓት ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እንዲሁም ባህላዊ ጉዳዮች የሚፈፀሙባቸው እሴቶች አሉ። ከእነዚህ ወስጥ ቡሳ ጎኖፋ የሚል ስያሜ ያለው የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሳቤም አንዱ ነው።

የኦሮሞ ብሄረሰብ የተፈጥሮ፣ የሰው ሰራሽና ሌሎችም በሕይወት ኡደት ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮች ሲያጋጥሙት አንደ ሕዝብ መልሶ እንዲያገግምና ወደ ቀድሞው (ከዚያም በተሻለ ሁኔታ) ይዞታው እንዲመለስ የሚያደርግበት ስርዓት ቡሳ ጎኖፋ ይባላል። በዚህ እሳቤ (በቡሳ ጎኖፋ ስርዓት) በማህበረሰቡ ውስጥ ጉዳት የደረሰባቸው፣ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ዜጎች በድንገተኛ ድጋፍ የማገዝ፣ የጠፋው ሀብት ንብረታቸውን መልሰው እንዲያገኙ የመርዳት፣ በስነ ልቦናና በጤና ጉዳይ ከሚገጥማቸው እክል ድነው መልሰው እንዲቋቋሙ የማድረግ ተግባር ይፈፀማል።

እንደ ምክትል ኮሙኒኬሽን ኃላፊዋ ገለፃ፤ ቡሳ ጎኖፋ በገዳ ስርዓት ውስጥ ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ሁነቶችን በአንድ ላይ አቅፎ የያዘ ነው። ከእነዚህ ወስጥ ደግሞ የማህበራዊና የኢኮኖሚ ጉዳዮችን በስፋት ይዳስሳል።

በኦሮምኛ ቋንቋ ቡሳ ማለት በፍጥነት የሚለውን የአማርኛ ፍቺ ይወክላል። ይህም ማለት በኦሮሞ ማህበረሰብ ውስጥ አንድ ተፈጥሯዊም ይሁን ሰው ሰራሽ አደጋ ሲከሰት በስርዓቱ አማካኝነት የድጋፍ ማሰባሰብ አድርጎ ምላሽ መስጠት ላይ የሚያተኩር ነው።

ጎኖፋ የሚለው የኦሮምኛ ቃል ደግሞ በድንገተኛ አደጋ ንብረቱን አሊያም ሌሎች ሀብቶቹን ያጣ ሰው በጊዜያዊነት ከተደረገለት ድጋፍ ባሻገር በቋሚነት የሚቋቋምበት መንገድን የሚወክል ነው። በጥቅሉ ቡሳ ጎኖፋ በማህበረሰቡ ውስጥ የደረሰን አደጋ በአጭር ጊዜም ሆነ በዘላቂነት በመመከት መፍትሄ መስጠት ላይ ትኩረቱን ያደርጋል።

‹‹ሰዎች ደንገተኛ አደጋ ገጥሟቸው ሀብት ንብረታቸውን ሊያጡ ይችላሉ›› የምትለው የኮሙኒኬሽን ምክትል ኃላፊዋ ወይዘሮ ኤልዳና፤ አደጋውም ከኢኮኖሚ ጫና ያለፈ የሞራል ስብራት፣ የቤተሰብ መበተን ሊያስከትል እንደሚችል ትገልፃለች። ለምሳሌ ያህል በኦሮሞ ብሄረሰብ ውስጥ አንድ መቶ ከብቶች ያሉትና ኑሮውን በጥሩ ሁኔታ ሲመራ የነበረ የአንድ አካባቢ ነዋሪ በድንገተኛ አደጋ ሁሉንም ከብቶች ቢያጣ በቡሳ ጎኖፋ የገዳ ባህላዊ ስርዓት እያንዳንዱ ጎረቤትና የመንደሩ ነዋሪዎች ካላቸው ከብቶች አንድ አንድ በማዋጣት 99 የሚሆኑትን በመተካት ተጎጂውን ወደነበረበት የኑሮ ደረጃ የመመለስ ግዴታ እንዳለባቸው ትናገራለች።

ይሁን እንጂ ይህ ስርዓት ከ100 ከብቶች ውስጥ 99 የሚሆኑትን በመተካት አንዷን ከብት በመጨመር 100 የማይደፍንበት ምክንያት ‹‹አንዷ የእግዚአብሄር ነች፤ ወይም በእግዚአብሄር የምትተካ ነች›› የሚል እሳቤ ስላለው እንደሆነም ታብራራለች። ይህን መሰል የመተጋገዝና የመተባበር እሴት በኦሮሞ ብሄረሰብ የገዳ ስርዓት ውስጥ ከጥንት ጀምሮ የነበረና አሁንም ድረስ ተጠብቆ የቆየ መሆኑን ታነሳለች። በዚህ ምክንያት የተፈጥሮም ይሁን የሰው ሰራሽ አደጋ በሚከሰትበት ወቅት የማህበረሰቡ አባላት ከሀብት ንብረታቸው እንዳይጎሉ፤ ስነ ልቦናቸው እንዳይጎዳና ተስፋ እንዳይቆርጡ ከለላ የሚሆን ባህላዊ እሴት መሆኑን ትገልፃለች።

በኦሮሞ ባህል ውስጥ ልመና ነውር መሆኑን የምትናገረው ምክትል ኃላፊዋ፤ አንድ ሰው ተቸግሮ ጎረቤቱ የተደላደለ ኑሮ መኖሩና ለማገዝ ፍላጎት አለማሳየቱም እንዲሁ የተወገዘና ነውር የሆነ ተግባር እንደሆነ ትናገራለች። በመሆኑም የተቸገረው ሰው በሁለት እግሩ እንዲቆምና ኑሮውን፣ ቤተሰቡን መምራት እንዲችል ማድረግ በገዳ ስርዓት ቡሳ ጎኖፋ እንደሚበረታታ አመልክታ፤ ማህበረሰባዊ ግዴታም ተደርጎ እንደሚቆጠርም ትናገራለች።

ከዚህ መነሻ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የገዳ አስተዳደር አንድ አካል የሆነውን የቡሳ ጎኖፋ እንዲሁም ሌሎች ማህበራዊና ባህላዊ እሴቶችን በአንድ ላይ በማቀናጀት አንድ ተቋም መመስረቱን የምትናገረው ምክትል ኃላፊዋ፤ ከዋናው የቡሳ ጎኖፋ በተጨማሪ የባህላዊ ፍርድ ቤት የሆነውንና ‹‹ጋቸነ ሲርና›› የሚባለውን፤ ሰላምና ደህንነት የሚጠብቁ ባህላዊ አደረጃጀቶችን እንዲሁም በግለሰቦች ይሁን በቡድኖች መካከል ግጭት በሚፈጠርበት ወቅት የጋራ ሀቅን ለመፈለግ የሚያስችሉ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓቶችን ያካተተውን፤ በሁለተኝነት ደግሞ ጠንካራ ሰላምና ደህንነት አንዲፈጠር የሚያስችለውን አደረጃጀት እንዲሁም በገዳ ስርዓት ውስጥ ተጃጅለ ለሙማ (የዜግነት አገልግሎት) የሚል ስያሜ ያለውን ባህላዊ እሴት በአንድነት በማቀናጀት ለማህበረሰቡ ምቹ በሆነ መንገድ አገልግሎት ለመስጠት ወደ ተግባር መገባቱን አብራርታለች።

ስርዓቱ በመንግስት የተፈጠረ ሳይሆን የማህበረሰቡ ሀብት የሆነ አገር በቀል (Indigenous Knowledge) እውቀት መሆኑን ጠቅሳ፣ ተጃጅለ ለሙማ በሚባለው ባህላዊ ስርዓት አንድ ነዋሪ የማህበረሰቡ አካል በመሆኑ ብቻ በዜግነቱ የሚጣልበት ማህበራዊ ኃላፊነትና ግዴታ እንደሆነ ትገልፃለች። አንድ ሰው የኦሮሞ ብሄር አባል ሲሆን የአካባቢውን ተፈጥሮ መጠበቅ (መንከባከብ)፣ የተጎዱትን ማገዝ፣ አረጋውያንን መርዳት እና ልዩ ልዩ ኃላፊነቶችን መወጣት ከጥንትም የነበረና እንደ ግዴታ የሚቆጠር መሆኑንም ትናገራለች።

እንደ ኮሙኒኬሽን ምክትል ኃላፊዋ ገለፃ፤ በአንድ ድርጅት ውስጥ የተካተቱት ቡሳ ጎኖፋን ጨምሮ ሌሎች ሶስት እሴቶች በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ አነሳሽነት ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ ባህላዊ እሴቶች ናቸው። ድርጅቱም ልማትና ሰላምን እንደሚያረጋግጥ ታምኖበት ሁሉን አቀፍ የሆነ እድገት እንደሚያመጣ ታስቦ የተደራጀ ነው።

ጎረቤት ከጎረቤት ተቀያይሞና ግጭት ፈጥሮ በቅራኔ ውስጥ እንዳይቆይ ችግሩን ባህላዊ ፍርድ ቤት መፍታትና ማስታረቅ፤ ሰላምና ደህንነትን ለመጠበቅ ደግሞ በጋቸነ ሲርና፤ አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን እና ለማህበረሰቡ የሚጠቅሙ ተቋማትን ለማልማት፣ ችግኝ ለመትከል፣ የአፈርና የውሀ ጥበቃ ስራ፣ የበጎ ፍቃደኝነት ስራ ለማከናወን ደግሞ በተጃጅለ ለሙማ አደረጃጀቶች በማከናወን፣ ድንገተኛ አደጋ ሲከሰት ተጎጂዎችን ለማቋቋም፣ ድርቅ ቢከሰት ተጎጂዎችን ለማገዝ በዘላቂነት ችግራቸውን እንዲፈቱ ለማስቻል የቡሳ ጎኖፋ እሴትን ተግባራዊ የሚደረግበት ወጥ ተቋም ተመስርቶ አሁን በክልሉ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ቡሳ ጎኖፋና መሰል የኦሮሞ ማህበረሰብ እሴቶች በሉላዊነት (Globalization) ተፅእኖ ስር በመግባታቸው ባህሉ ቀስ በቀስ የመጥፋትና እሴቶቹም በዘመናዊነት ተፅእኖ ውስጥ የመውደቅ ችግር እያጋጠማቸው መሆኑን የምታነሳው ምክትል ኃላፊዋ፤ በተለይ ከ1960ዎቹ ትውልድ ወደዚህ ያለው ማህበረሰብ በፖለቲካና በልዩ ልዩ ምክንያቶች ወደ ውጪ የማማተርና የራሱን እሴቶች የመዘንጋት እክል እንዳጋጠመው ትናገራለች።

ወይዘሮ ኤልዳና እንዳብራራቸው፤ በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች አገር በቀል እውቀቶች እየተዘነጉና የሚሰጡት ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ችላ እየተባለ ዜጎች የሚገባቸውን ሁሉን አቀፍ ልማት ሳያገኙ ቀርተዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን (በተለይ ፖለቲካዊ ለውጥ ከተደረገበት 2010 እና ከዚያ ቀጥሎ ባሉት ዓመታት) ባህላዊ እሴቶቹ ወይም አገር በቀል እውቀቶቹ ዳግም ማህበረሰቡን የሚያገለግሉበትና ችግር መፍቻ ቁልፍ መሳሪያ የሚሆኑበት መንገድ ተቀይሷል፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የምትከተለው ዘመናዊ የመንግስት አስተዳደር አሊያም የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ነው፤ ይሁንና ቡሳ ጎኖፋን የመሰሉ አገር በቀል እውቀቶች ቀድሞውንም የነበሩ በተለይ የኦሮሞ ማህበረሰብ እሴቶቹን በእለት ተእለት ኑሮ ውስጥ በማካተት ተግባራዊ ሊያደርጋቸው ፍላጎት ያለው ከመሆኑ አንፃር ከዘመናዊው የአስተዳደር እሳቤ ጋር ማዋሃድ አስፈልጓል። ፈጣን እና ሁሉን አቀፍ ለውጥ ለማምጣት በዚህ እሳቤ መሄድ ተመራጭ መሆኑን የክልሉ መንግስት አምኖበት ወደ ተግባር እንዲገባ አርጓል።

‹‹በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከዚህ ቀደም የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የሚባል ተቋም ነበር›› የምትለው ምክትል ኃላፊዋ፤ ይህ ተቋም እርዳታን ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች በመቀበል የማከፋፈል ስራ ይሰራ አንደነበር ትገልፃለች። አሁን ግን በራስ አቅም ችግሮችን መፍታት እና እርስ በእርስ በባህላዊ እሴቶቹ አማካኝነት መደጋገፍ እሳቤን ለማምጣት እየተሰራ መሆኑን ትጠቁማለች።

በእርዳታ እና ድጋፍ የማህበረሰቡን ችግር ሙሉ ለሙሉ መቅረፍ እንደማይቻልም ገልጻ፣ ማህበረሰቡ ችግሮቹን በራሱ አቅም ባህላዊ እሴቶቹን ተጠቅሞ አንዲፈታ ቡሳ ጎኖፋን በመንግስት እውቅናና ድጋፍ ማቋቋም ማስፈለጉን አስታውቃለች። በዚህም ማህበረሰቡ በራሱ አቅም ችግሮቹን የሚፈታበት አደረጃጀት እንዲኖር መደረጉን አመልክታለች።

እንደ ኮሙኒኬሽንና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምክትል ኃላፊዋ ማብራሪያ፤ በቡሳ ጎኖፋ አደረጃጀት አዲሱ ትውልድ ቀደም ያሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እሴቶቹን እንዲሁም ስርዓቶችን እንዲያውቅ እየተሰራ ነው። በእሴቶቹ ላይ ግንዛቤ ከማስጨበጥ ባሻገር በዚህ ስርዓት ወስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊ አንዲሆን በማድረግ ጎረቤቱን፣ የአካባቢውን ማህበረሰብ እንዲደግፍ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

በዚህም በኦሮሚያ ክልል በእያንዳንዱ ወረዳ ውስጥ በሚገኙ 10 በሚደርሱ ትምህርት ቤቶች የቡሳ ጎኖፋ ክበብ እንዲቋቋም ተደርጓል። እስካሁን ድረስም በቡሳ ጎኖፋ አደረጃጀት ውስጥ ለመሳተፍ ፍቃደኛ በመሆን አባል የሆኑ 25 ሚሊዮን የሚደርሱ የማህበረሰቡ አባላት አሉ። በቅርቡ ዝናብ አጠር በሆኑ የክልሉ አካባቢዎች እነዚህን አባላት በማሰባሰብ ለተጎጂ ወገኖች የድንገተኛ አደጋ መከላከል ድጋፍ፣ በዘላቂነት ለማቋቋም መሰረት መጣል፣ የአደጋ ቅነሳ ስልት በመንደፍ የአነስተኛ መስኖ፣ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራና ሌሎችንም መሰል ችግሮቹን ሊፈቱ በሚችሉ ተግባራት ላይ ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል። ከዚህ በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ይሁንታ የተመሰረተው የቡሳ ጎኖፋ ድርጅት በክልሉ እስከ ሰባት ሚሊዮን ለሚደርሱ ተማሪዎች ምገባ እያደረገም ይገኛል።

በቡሳ ጎኖፋ ውስጥ ኢትዮጵያዊ የሆነና በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር ማንኛውም ሰው መሳተፍ ይችላል የምትለው ምክትል ኃላፊዋ፤ ይህ ባህላዊ እሴት ብሄር፣ ቋንቋ ሳይለይ ሁሉንም ያለ ልዩነት የሚቀበል መሆኑን ትገልፃለች። በሰብዓዊነት የሚያምንና የአገር በቀል እውቀት የሆነውን የቡሳ ጎኖፋን ራዕይ የሚጋራ የሰው ልጅ በበጎ ምግባሩ ላይ ተሳታፊ የመሆንና የአደረጃጀቱ አባል የመሆን መብት እንዳለው አመልክታለች።

ቡሳ ጎኖፋ የኦሮሚያ ክልል ውስጥ ብቻ ያለውን ችግር አስወግዶ የሚቀመጥ አለመሆኑን ተናግራለች፤ ከክልሉ ውጪ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች ተመሳሳይ ችግር ቢፈጠር ድጋፍ ለማድረግና ስርዓቱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚሰራ መሆኑንም ገልፃለች። ለዚህ ማሳያ ከዚህ ቀደም በኮንሶ አንዲሁም ጎፋ በመሳሰሉ አካባቢዎች ባጋጠሙ ችግሮች ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ፈጥኖ በመድረስ እና የመረዳዳት ግዴታውን መወጣቱን ተናግራለች። በቀጣይም በክልል ብቻ ሳይሆን በመላው አገሪቱ፤ በዚህም ብቻ ሳይገደብ በመላው ዓለም ለሰው ልጆች መድረስና ሰብዓዊ ድጋፍን የማድረግ ራዕይው እንዳለውም አብራርታለች።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2017 ዓ.ም

Recommended For You