ትላንት በወጣትነትና ጉልምስና እድሜያቸው ላይ አገራቸውን በብዙ ያገለገሉ ናቸው። ዛሬ ቀን ዘምበል ሲልባቸው፤ ጎንበስ ቀና ይሉላቸው የነበሩ ሁሉ የት እንዳሉ እንኳን በውል ማስታወስ አይፈልጉም።
ጊዜ እራሱ አድሎ የሚፈጽም እስከሚመስል ድረስ ለአገር ለወገን ብዙ የዋሉ ወጣትነታቸውን የገበሩ ሰዎች ሳይታዩ ሳይከበሩ መከበሩ ቀርቶ ለኑሯቸው እንኳን አስፈላጊ ነገር ሳይሟላላቸው በአሳዛኝ ሁኔታ እድሜያቸውን እንዲጨርሱ በለፉባት አገርና ሕዝብ ዘንድ ዋጋ ቢስ ሆነው ተስፋ ሲቆርጡ መመልከት የተለመደ እየሆነ ነው።
የዛሬ የሕይወት ገጽታ ዓምዳችን ባለታሪክ የ 50 አለቃ ወይንሸት ደምሴ ይባላሉ ። የቀድሞ የክቡር ዘበኛ ሙዚቀኛ አባል ናቸው። ሮጠው መስራት አገራቸውን በውትድርናው እንዲሁም በጥበቡ ዘርፍ ብዙ ማገልገል በስራቸው ያሉትንም በሚገባ መምራትና አርዓያ መሆን በሚችሉበት ቁመናና የጤና ሁኔታ ላይ ሆነው አገራቸውን በብዙ አገልግለዋል። ደከመኝ ይሉትን ነገር ሳያውቁ ሴት ነኝ ቆይ ይህንን አልችልም ቤተሰቤ ይፈልገኛል፤ ይጠብቀኛልም፤ ሳይሉ በበዓል በአዘቦቱ መላ አገሪቱን ተዘዋውረው ብዙ የሰሩ ጀግና ናቸው። ምን ዋጋ አለው ሰርተው ሳይጠግቡ አገርም በቅጡ ሳትጠቀምባቸው ጤና ይሉት ገበያ ዘንበል ብሎባቸው ቤት ከዋሉ ዓመታት ተቆጥረዋል።
የጤናቸው ችግር ከስራቸው ጋር ተያይዞ በተፈጠረ የመኪና አደጋ በየመጣ ቢሆንም ከወቅታዊ ሕክምና የዘለለ ዘለቄታዊ መፍትሔን የሰጣቸው አሰሪ አላገኙም ።
የ50 አለቃ ወይንሸት ደምሴ የተወለዱት አዲስ አበባ ከተማ ተክለሃይማኖት አካባቢ ጎላ ሚካኤል ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ሲሆን እድገታቸው ደግሞ ሽሮሜዳ ቀበሌ 03/04 ስለመሆኑ ይናገራሉ።
“……… ያደኩበት ሰፈር አባቶቻችን ኮርያ ኮንጎ ዘምተው ሲመጡ የሰፈሩበት የጀግኖች መንደር ነው። እኔም የኮንጎ ሰፈር ልጅ ነኝ” ይላሉ።
አባቴ ወታደር ነው የሚሉት ሀምሳ አለቃ ወይንሸት እናቴ እኛን በማሳደግ ቤት ውስጥ ብትሆንም እንደምንፈልገው ግን አልኖርንም። እንደውም እኔ ተፈሪ መኮንን እማር ስለነበርና ልጆቹ ደግሞ በጣም ዘናጭ ስለነበሩ በትምህርቴ ጎበዝ ብሆንም ይህንን ነገር ግን መቋቋም ባለመቻሌ ወታደር ለመሆን ወሰንኩ ይላሉ።
እሳቸው በ1972 ዓ.ም ውትድርና ሲቀላቀሉ አባታቸው ግዳጅ ላይ ነበሩ። ነገር ግን ከቤተሰብ ደብዳቤ ተጽፎ ወታደር መሆናቸው ሲነገራቸው የእኔ መች አነሰናነው እሷ ደግሞ ወታደር የምትሆነው በማለት ቅሬታ ማቅረባቸውን ያስታውሳሉ።
“………በነገራችን ላይ በወቅቱ ቤት ውስጥ እኔ ብቻ ሳልሆን ወታደር የሆንኩት ታናሽ ወንድሜም አስመራ ላይ በሙዚቀኛው ክፍለ ጦር ውስጥ ተቀጥሮ ነበር። እኔም አባቴ ወደነበረበት ባሌ አካባቢ ለስራ ስሄድ አባቴን የማግኘት እድል አግኝቼም ወታደር መሆኔን አረጋግጦ ብሎም ማዕረጋችንም ተመሳሳይ ሆኖ ተገርመን ነው የተለያየነው” በማለት ያስታውሳሉ።
“…….አባቴ ወታደር ይሁን እንጂ እናቴ ደግሞ አርበኛ ነበረች። ከእናትና አባቶቿ ጋር ጣልያንና እንግሊዝ አገር ሄዳ ተዋግታ የመጣች ናት። ወታደር መሆኔንም ስትቃወም አንቺ ለጣሊያን ተዋግተሽ የለ እንዴ እላት ነበር” በማለት ይናገራሉ።
የ50 አለቃ ወይንሸት እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በቀጥታ ያመሩት ወደ አምሃ ደስታ ትምህርት ቤት ነው ። በዛም የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሚገባና በጥሩ ሁኔታ ከተከታተሉ በኋላ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመጀመር ያቀኑት በቀድሞው ተፈሪ መኮንን አሁን ደግሞ እንጦጦ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት ወደሚባለው ነው።
በወቅቱ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ሲማሩ ጎበዝ ለትምህርታቸው ልዩ ፍቅር የነበራቸው እንደነበሩ የሚገልጹት ባለታሪካችን ነገር ግን የኑሮ ሁኔታ ከትምህርት ቤት እኩዮቻቸው እኩል ሊያደርጋቸው አልቻለም ነበር። ኑሯቸው እኩል አለመሆኑ ብቻም ሳይሆን መሰረታዊ የሚባሉት ነገሮች እንኳን በአግባቡ ሊሟሉላቸው የሚችሉበት ሁኔታም አልነበረም። ይህ ለወጣቷ ወይንሸት ከባድ ነበርና ኑሮን በሚፈልጉት መንገድ ለመምራት ብሎም መሰረታዊ ነገሮቻቸውን ለማሟላት የሚያስችል መንገድን ማማተራቸው አልቀረም።
“……..በወቅቱ ቤተሰቦቼ ሊያበሉኝ ሊያጠጡኝ ይችላሉ፤ ነገር ግን እንደ አንድ ወጣት የሚያስፈልጉኝን ነገሮች ማሟላት የሚያስችል አቅም አልነበራቸውም። ይህ ደግሞ በእኔ ላይ ከፍ ያለ ተጽዕኖን በማሳደሩ ራሴን አወጣለሁ በሚል ትምህርቴን አቋርጬ የውትድርናውን ዓለም ተቀላቀልኩ”ይላሉ።
ገና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን ሃ ብለው ሲጀምሩት ሁኔታውን መቋቋም ያቃታቸው 50 አለቃ ወይንሸት ቶሎ ብለው የተቀላቀሉት ውትድርና ስልጠናው ከባድና አስቸጋሪ ቢሆንም በእንጥልጥል ያስቀሩትን ትምህርት ግን እንዲሁ ሊተውት ስላልፈለጉ በማታው ክፍለ ጊዜ ተምረው የቀድሞውን 12 ተኛ ክፍልን ስለማጠናቀቃቸው ይናገራሉ።
“…….የሚገርምሽ ነገር ወታደር እሆናለሁ የሚል ምንም ሃሳቡ አልነበረኝም፤ በወቅቱ ግን የቀበሌ ኪነት ላይ ከጓደኞቼ ጋር በመሆን የነቃ ተሳትፎን እናደርግ ነበር፤ ጓደኞቼም ከእኔ ቀድመው ሄደው ውትድርና ውስጥ በተወዛዋዥነት ለመስራት ተመዝግበው መጡ” የሚሉት የ 50 አለቃ ወይንሸት ወቅቱ እኔ ልቅደም እኔ የሚባልበት ስላልነበር አንዱ ላንዱ መተሳሰቡና ፍቅሩ ልዩ ስለሆነ ጓደኞቻቸው ያዩትን ይነግሯቸዋል እንደውም እሳቸው ቢመዘገቡ ከመልክና ቁመናቸው አንጻር ውጤታማ እንደሚሆኑም አልደበቋቸውም።
ይህን የሰሙት ወጣቷና ቆንጆዋ ቁመተ መለሎዋ ወይንሸት የተሰጣቸውን አድራሻ ይዘው በተነገራቸው ምልክት መሰረት ወደቦታው ሄደው ምዝገባውን አካሄዱ።
” ……በወቅቱ በጣም የሚያማምሩ ሴትና ወንዶች በቦታው ላይ ነበሩ። እኔም ከእነሱ መካከል አንዷ ሆኜ ተመረጥኩኝ ። በሚገርምሽ ሁኔታ መራጮቼ አሁን እንኳን በሕይወት የሉም ነገር ግን ታሪክ ያላቸው እንደ እነ ኮሎኔል ሳህሌ ደጋጎ፣ ኮሎኔል ሀይሉ ወልደማርያም ፣ አቶ አየለ ማሞ፣ የተፈራ ካሳ እናት ወይዘሮ አረጋሽ ኩንቴሳና ሌሎችም ነበሩ፣ በዚህም ከሶስት መቶ ሴት አስሮቻችን ከወንዶችም 40 ተመርጠን ክቡር ዘበኛ የሙዚቃ ቡድንን ተቀላቀልን ” በማለት በትዝታ ወደኋላ ሄደው ይናገራሉ።
1 ሜትር ከ70 ሳንቲ ሜትር ቁመት፣ቀጥ ብሎ የወረደ አፍንጫ የሚያምር ጸይም ቆንጆ ኢትዮጵያዊ ቀለም ያለው ፊት የያዙት 50 አለቃ ወይንሸት በጓደኞቻቸው እንደተመረጡት ሁሉ በአንጋፋ ባለ ሙያዎችም ዘንድ በጣም ተፈላጊ መሆን አላቃታቸውም።
ከኮንጎ ሰፈር እሳቸውን ጨምሮ 6 ሴቶች ሆነው ክቡር ዘበኛን ተቀላቀሉ። ዛሬ ላይ ሶስቱ በሕይወት የሉም ። አሁን ወደ ስልጠና ፣
የውትድርና ስልጠና
አስር ሴቶችና አርባ ወንዶች በሚገባ ተጣርተው ከተመረጡ በኋላ ቅድሚያ እንዲያውቁት የተፈለገው ነገር መሰረታዊ ወታደራዊ ትምህርት ነበር። በዚህም ጠዋት ጠዋት ወታደራዊ ሰልፍ አለ። ኢላማ ተኩስ በሚገባ መማር ግዴታ ሲሆን ከምሳ በኋላ ደግሞ የተቀጠሩበትን የሙዚቃ ዘርፍ ውዝዋዜና ድምጽ መማር ስራቸው ሆነ።
“……..አሁን ላይ ሆኜ ራሱ ሳስበው ግርም የሚለኝ በወቅቱ አሰልጣኞቻችንንና መላውን የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ አስገርሞ የነበረው ነገር ሌሎች በዓመትና ከዛ በላይ ሰልጥነው የማይጨርሱትን ትምህርት እኛ በሶስት ወር ሙሉ ስልጠናችንን አጠናቀን ሰልፈኛውም ባንዱም ኦርኬስትራ ክፍል ድምጻውያንና ተወዛዋዦችም ዝግጁ ሆኖ ሲታይ በጣም ነበር ጉድ ያሰኘው”በማለት በወቅቱ ለሙያው የተከፈለውን ዋጋና የነበረውን ተነሳሽነት ያስታውሳሉ።
በዚህ መልኩ ስልጠናቸውን ካጠናቀቁ በኋላም ፊታቸው ዘመን መለወጫ (አዲስ ዓመት ) ነበርና ለእዛ የሚሆን ስራን ይዘው ቀረቡ። በወቅቱ ሲቪል ሚሊተሪ ማለትም ፖሊስና ምድር ጦር አብረዋቸው ነበሩ ብሔራዊ አገር ፍቅር ራስ ቲያትር አብረው ስለነበሩ ፉክክሩ በጣም የሚገርም እንደነበር ያስታውሳሉ።
“…….ሁሌም በየዓመቱ ዘመን መለወጫ ሲመጣ በጣም ይከፋኛል። ምክንያቱም ውዝዋዜ ላይ አራት ዓመት ከሰራሁ በኋላ ማርሽ ባንድ ላይ ከፊት ሆነው ዱላ የሚያሽከረክሩት ሴቶች ይማርኩኝ ስለነበር ወደ ሰልፈኛ ባንድ ገባሁ። እዛ ከገባሁ በኋላም መስከረም አንድ በየዓመቱ ትልቅ ትርዒት ይታይ ነበርና እኔም በዛ ላይ ብዙ ጊዜ ተሳትፌያለሁ፡፡ የሚገርመሽ እኮ እስከ መስቀል ድረስ ቤታችን አንገባም ነበር ብቻ ምን ያደርጋል ጊዜውም ስራውም ሁሉም ጥሩ ነበር ምን ዋጋ አለው” በማለት ሀምሳ አለቃ ወይንሸት እዝን ክፍት ብለው ትዝታቸውን ይናገራሉ።
ሃምሳ አለቃ ወይንሸት ዛሬ ላይ ቆመው ሲያስቡት ብዙ የሚቆጫቸው ነገር አለ። በወቅቱ የሙዚቃና የስራ ፍቅር ብቻ ይዞን ወይ በትምህርታችን አልገፋን አልያም መጦሪያ የሚሆነንን ሃብት አልያዝን ብቻ መስራት ነው። የኛ ፍላጎት ዛሬ ላይ ቢሆን ስንት ነገር ነበር በማለትም ቁጭታቸውን ይናገራሉ።
“……አንድ ቤት የሚኖሩ የእናትና አባት ልጆች ሁለት ሶስት ሆነው ባለመግባባት ይጋጫሉ፤ እኛ ግን ከ 80 በላይ ሆነን አንድ ቀን በመካከላችን ጸብ ሳይገባ አብረን ውለን እናድራለን። ዛሬም ድረስ በሕይወት ካሉት ጋር ወንድሜ እህቴ ተባብለን እንጠያየቃለን”በማለት የነበረውን ፍቅርና መተሳሰብ ያስታውሳሉ።
ሃምሳ አለቃ ወይንሸት በክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ ውስጥ ባገለገሉባቸው ዘመናት ከበርካታ አንጋፋና ዛሬም ድረስ በሙዚቃው ውስጥ አንቱታን ካተረፉ ብዙ አይረሴ ስራን በመስራት በሰዎች ልብ ውስጥ ነግሰው እየኖሩ ካሉት ከእነ ጥላሁን ገሰሰ፣ብዙነሽ በቀለ ፣ ሂሩት በቀለ፣ ተዘራ ሀይለሚካኤል፣ ተፈራ ካሳና ከሌሎችም ጋር የማይረሱ ሙዚቃዎችን በውዝዋዜ አጅበው ሰርተዋል።
ሀምሳ አለቃ ወይንሸት እነዚህን የሙዚቃ ባለሙያዎች በውዝዋዜ ከማጀብ ባሻገር የሙዚቃ ቡድኑን በበትር አሽከርካሪነት እንዲሁም ድራም (ከበሮ) በመምታት አገልግለዋል።
ማሕበራዊ ሕይወትና ሙዚቃ
ሀምሳ አለቃ ወይንሸት እንደ አጋጣሚም ሆኖ ባለቤታቸውም በተመሳሳይ የሙዚቃ ሕይወት ውስጥ ያሉ በመሆናቸው አንዳቸው ለአንዳቸው ድጋፍ መሆናቸው አልቀረም፤ ነገር ግን ከስራቸው ባሻገር የልጆችም ሆነ ማሕበራዊ ኃላፊነቶችን መወጣት ላይ እምብዛም እንዳልነበሩ ይናገራሉ።
” ……ቤታችን ይችው የምታያት ናት 40 ዓመት በላይ ኖረንባታል፤ በወቅቱ ልጆች ብንወልደም በተለይም የዓመት በዓል ወቅቶች ላይ ስራዎች ስለሚኖሩ በዓልን በቤታችን ውለን አናውቅም፡፡ በመሰረቱ እኔም እናቴ ልጆቼን ትይዝልኝ ስለነበር ያን ያህል አልቸገርም ነበር።ኋላ ላይ ስራው ሲቀርና ከሕብረተሰቡ ጋር ስንቀላቀል ግን ሁኔታው በጣም ከብዶን ነበር” በማለት ይናገራሉ።
የአካል ጉዳታቸው መንስኤ
የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ብሔራዊ ውትድርና ዘማቾችን ለማስመረቅ ደዴሳ ወደሚባል አገር እየተጓዙ ባሉበት ወቅት በተነሳ እሳት ምክንያት እሳቸውንና የስራ ባልደረቦቻቸውን ጭኖ ይጓዝ የነበረው “ኦራል “ትልቅ የወታደር መኪና ወደኋላው ይንሸራተታል በዚህ ጊዜ የካሜራ ማቆሚያ ስታንድ ይወድቃል ሀምሳ አለቃ ወይንሸትም እየወደቀ ያለውን ስታንድ ለማትረፍ ባደረጉት ጥረት ከመኪናው ተፈናጥረው ወደመሬት በመውደቃቸው ምክንያት አከርካሪ አጥንታቸው ላይ ጉዳት እንደደረሰባቸው ይናገራሉ።
በወቅቱም በጦር ኃይሎች ሆስፒታል የሕክምና ክትትል የተደረገላቸው ቢሆንም በቀዶ ሕክምና መስተካከል የነበረበት በመሆኑ እሱም ስላልተሰራላቸው ጉዳታቸው እየተባባሰ ሄዶ ዛሬ ላይ በምርኩዝ እንዲንቀሳቀሱ ምክንያት ሆኗቸዋል።
ሀምሳ አለቃ ወይንሸት በግላቸው በጥቁር አንበሳና በሌሎች ሆስፒታሎች እየሄዱ ያደረጉት የሕከምና ሙከራ በአቅም ማነስ ምክንያት ሳይሳካላቸው በመቅረቱ ዛሬም ድረስ በጣም ያዝናሉ። አሁንም የሚያያቸው የሚያሳክማቸው አካል ቢያገኙ ጊዜ አለመርፈዱንም አጫው ተውኛል።
ሃምሳ አለቃ ወይንሸት ጉዳቱ ከደረሰባቸው በኋላ ከሙዚቀኛው ቡድን ጋር አብረው መቀጠል አልቻሉም፤ በምድር ጦር ቴክኒክና ውጊያ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ገብተው ለ9 ወራት ወታደራዊ ሂሳብ አያያዝ የሚል ኮርስ ተምረው በሰርተፍኬት መመረቃቸውን ይናገራሉ። በዚህም በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ወታደሮችን ደመወዝ መስራት ቀለባቸውን በቀን በወር በዓመት ምን ያህል ይበቃል የሚለውን የመማር እድል ማግኘታቸውንም ነው የሚያብራሩት።
ይህንን ትምህርት ተምረው ከወጡ በኋላም መምሪያው ውስጥ ረዳት እንዲሁም ራሳቸውን የቻሉም ጸሃፊ ሆነው አገልግለዋል። ወዲያውም ኮር የሚባል ክፍል በመቋቋሙ እዛ ሄደው ደግሞ መስራት ጀመሩ። ይህ የስራ ክፍል ግን ለሃምሳ አለቃ ወይንሸት ጥሩ እድል ይዞ የመጣ ነበር። ከአስር አለቃነትም ወደ ሃምሳለቅነት ማዕረግ ለማደግም የቻሉት በዚህ ክፍል ነው።
በዚህ ሁኔታ ለሁለት ዓመት ከሰሩ በኋላም የመንግስት ለውጥ በመምጣቱ ምክንያት ሰራዊቱ ሲበተን ክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራም ፈረሰና እሳቸውን ጨምሮ ብዙ ጓደኞቻቸው ከስራ ውጪ ሆኑ።
“……የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ ቡድን በፍጹም መፍረስ ያልነበረበት በታሪክ ስንሰማ እንኳን ስንት ፈረንጆችን የሚያሰለጥን ነበር ⵆ ግን በሚያሳዝን ሁኔታ እጣ ፋንታው መፍረስ ሆኗል። እኛም እድሜያችንን ወጣትነታችንን ለሙያ ክብር ለአገር ፍቅር ሰጥተን አገር ለአገር ተንከራተን መጨረሻችን አሳዛኝ ሆኖ ቀረ” በማለት ቅሬታቸውን ይናገራሉ።
የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ ብዙዎችን ያፈራ ነው፡፡ ዛሬም ድረስ ስመ ጥሩና ገናና የሆኑ የጥበብ ባለሙያዎች በዓለም አደባባይ የራሳቸውንና የአገራቸውን ስም ያስጠሩበታል። በተቃራኒው ደግሞ እንደ ሀምሳ አለቃ ወይንሸት አይነቶቹ ብዙ ቢሰሩም ብዙ ቢለፉም የልፋታቸውን ያህል ማግኘት መከበር ሳይችሉ እንደ ተራ ሰው የትም ወድቀው መገኘታቸው ያሳዝናል። እሳቸውም ይህንኑ ደጋግመው ይናገራሉ። ዛሬ ላይ የሀምሳ አለቃ ወይንሸት ከሕመማቸው ጋር እየታገሉ በመርኩዛቸው እየተደገፉ ቤት ከርመዋል የሰው እጅ ከማየት ብለው በሰፈራቸው ባለ ወጣት ማዕከል ቀን ቀን በጥበቃ ሰራተኝነት እያገለገሉ የሚያገኟትንም የወር ደመወዝ ከእጅ ወደአፍ የሆነውን ኑሯቸውን ይገፉበታል።
የትዳር ሁኔታ
ሀምሳ አለቃ ወይንሸት ከሀምሳ አለቃ ጌታቸው ዘለቀ ጋር ትውውቃቸው እዛው ክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ ውስጥ ነው። እንደነገሩኝም ባለቤታቸው አገር ያደነቃቸው የትንፋሽ መሳሪያ (ሳክስፎን) ተጫዋች ነበሩ። ግን ምን ያደርጋል ባልና ሚስት አብረው ተቀናሽ ሰራዊት ሆኑ፡፡ ከዛ በኋላ ያለው ኑሮ ከባድ በሚባለው ቃል መገለጽ የማይችል ሆነ። በተለይም ለባለቤታቸው ሁኔታው ከባድ እንደነበር ይናገራሉ።
“……ከመሰረቱም የደሃ ልጆች ነበርን፤ ስራ ስራችንን ስንል ደግሞ በትምህርቱም መግፋት አልቻልንም። ባላሰብነው ሁኔታ ከስራ ስንፈናቀል ደግሞ ዙሪያው ገደል ሆነብን”ይላሉ። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ባለቤታቸው ባጋጠማቸው ሕመም ምክንያት ሆስፒታል ቢገቡም እሳቸው እንደሚሉት በሕክምና ስህተት ምክንያት ከዛሬ 9 ዓመት በፊት ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
ከ41 ዓመት በላይ በኖሩባት አንዲት ክፍል ደሳሳ ጎጆ ውስጥ ሆነው ነገን በተስፋ እየጠበቁ ዛሬን በትግላቸው ለማሳለፍ ደፋ ቀና ይላሉ። የወለዷቸው ሁለት ወንድ ልጆችን በትምህርቱ የመግፋት እድልን ስላላገኙ ኑሯቸው ከራሳቸው አልፎ እናትን ለመደገፍ የሚያበቃ አለመሆኑንም ይናገራሉ።
ድሮና ዘንድሮ
ሙዚቃ ድሮ ቀረ ከሚሉት ወገን አይደለሁም፤ ሁሉም በዘመኑ ጥሩ ነው። ያን ጊዜ ሙዚቃ በፍቅር በጉጉት በከፍተኛ ጥንቃቄና ጥናት ይሰራ ነበር። አሁን ደግሞ ቴክኖሎጂውም ያግዛል፡፡ ከዛም ልጆቹ በጣም ጥበበኞች ናቸው። በዚህ በዛም ብለው ይሰራሉ። ድሮ ገንዘብ የለም ለጆሮ የሚስብ መልዕከት ያለው እስከ አሁን ድረስም ዘመን የተሻገረ ስራ ተሰርቷል። ዛሬ ላይ ወቅታዊ አንዳንዱም ምንም መልዕክት የሌለው ብቻ ዝም ብሎ ጩኸት ሆኖ ይወጣል ግን ደግሞ በቀላሉ ባለገንዘብ ያደርጋል ይላሉ።
“……ድምጻዊ ጥላሁን ገሰሰ 13 ሙዚቃን በሸክላ አስቀርጾ ለሕዝብ ጆሮ ሲያደርስ የተከፈለው ገንዘብ ዛሬ ለአንድ ጉዞ የኮንትራት ትራንስፖርት የማይበቃ ነው። በእርግጥ ገንዘቡም ዋጋ ነበረው። ነገር ግን ከገንዘቡ ባሻገር የሙዚቃው መልዕክት ለዛው ቃናው የሚገርም ነው። እኔ ዛሬ ሲከፋኝ የነ ጥላሁንን ብዙዬን ዜማ ነው የምሰማው የማንጎራጉረው ሌላውም አንደ እኔው ነው የሚሆነው፤ ምክንያቱም ምግብ ማለት ነው” ይላሉ።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን መስከረም 7/2017 ዓ.ም