አዲስ አበባ፡– ለኅብረተሰቡ ቅሬታ ምንጭ የሆኑ የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ በመንግሥት ተቋማት ሪፎርም እየተከናወነ መሆኑን የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ ጳጉሜን 2 ቀን 2016 ዓ.ም “ሪፎርም ለላቀ አገልግሎት” በሚል መሪ ሃሳብ የሚከበረውን የሪፎርም ቀን ምክንያት በማድረግ ትናንትና መግለጫ ሰጥቷል።
የተቋሙ ምክትል ኮሚሽነር ስመኝ ውቤ እንደገለጹት፤ ኅብረተሰቡ ቅሬታ የሚያነሳበትን የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግር ለመቅረፍ መንግሥት ሰፊ የሪፎርም ሥራ ሠርቷል፡፡
በኮሚሽኑ አቅራቢነት የፀደቀው የመንግሥት አስተዳደርና አገልግሎት ፖሊስ በየደረጃው የሚገኙ አካላት ውይይት አድርገውበት ሥራ ላይ መዋሉን አስረድተዋል፡፡
ፖሊሲውን ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎች እየተዘጋጁ መሆኑን ጠቅሰው፤ ፖሊሲው በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚስተዋለውን የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግር ይቀርፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።
ከዚህ ቀደም በሲቪል ሰርቪሱ ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ለሚሆኑት የመንግሥት ሠራተኞች ግልጽ አቅጣጫ የሚሰጥ እንዳልነበር አስታውሰው፤ አሁን የተዘጋጀው ፖሊሲ አደረጃጀትን፣ ብቃትን፣ አገልግሎትንና ዲጂታላይዜሽንን የተመለከቱ ጉዳዮችን በውስጡ ማካተቱን አስታውቀዋል።
ሪፎርሙ ሁሉም ተቋማት በአንድ ጊዜ የሚተገበሩት ሳይሆን በሦስት ምዕራፍ ተከፋፍሎ እንደሚተገበር ጠቁመው፤ በመጀመሪያው ምዕራፍ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንን ጨምሮ ስምንት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ወደ ተግባር መግባታቸውን ተናግረዋል።
ትምህርት ሚኒስቴር፣ ገንዘብ ሚኒስቴር፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ፕላን ልማት ሚኒስቴር፣ ግብርና ሚኒስቴር ፣ የጤና ሚኒስቴርና ገቢዎች ሚኒስቴር በመጀመሪያው ዙር የሪፎርም ሥራ ከተካተቱ ተቋማት መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይ ደግሞ በሁለተኛው ዙር የሪፎርም ሥራ ተጨማሪ የመንግሥት ተቋማት እንደሚካተቱ አንስተው፤ ቀልጣፋ አገልግሎት ለሕዝቡ መስጠት እንዲችሉ መንግሥት ጠንካራ የሪፎርም ሥራዎችን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የፌዴራል ተቋማት ፖሊሲያቸውን መፈተሽ፣ ሥራዎቻቸውን ከወረቀት ወደ ዲጂታል የመቀየርና ዘመናዊ አገልግሎት ሥርዓትን መዘርጋት በሪፎርሙ የሚተገበሩ ሥራዎች መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ላይ ከመሬት አስተዳደር ጋር በተገናኘ እንዲሁም የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ጋር በተገናኘ የሪፎርም ሥራዎች ተሠርተው ተግባራዊ ለውጥ እያመጡ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የሪፎርም ሥራ በአንድ ወቅት ተጀምሮ የሚያልቅ ሥራ አለመሆኑን የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሯ፤ ቀጣይነት ያለውና በየጊዜው እየተገመገመ ወደተለያዩ ዘርፎች የሚስፋፋ ሥራ እንደሚሠራ አመላክተዋል።
በሌላ በኩል ጷጉሜን ሁለት ቀን 2016 ዓ.ም “ሪፎርም ለላቀ አገልግሎት” በሚል መሪ ሃሳብ የሚከበረውን የአገልጋይነትና የሪፎርም ቀን በማስመልከት ሁሉም የመንግሥት ሠራተኞች ቅዳሜ ሙሉ ቀን ለማኅበረሰቡ አገልግሎት በመስጠት እንደሚያከብሩ ጠቁመዋል።
ዕለቱን ለማክበር ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን፤ በዕለቱ ባለፉት አምስት ዓመታት የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች ውጤታማነት በተመለከተ የፓናል ውይይት እንደሚካሄዱ ተናግረዋል።
አማን ረሺድ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 30 ቀን 2016 ዓ.ም