የታላቁ ቅናሽ- ታላቅ ኪሳራ

አንዳንዴ ለሁኔታዎች ትኩረት ሰጥተን ቆም ብለን ካላሰብን ብዙ ነገሮች ሊበላሹ ይችላሉ። ‹‹ልብ ካለየ ዓይን ብቻውን ዋጋ የለውም›› እንዲሉ ልቦናችን ከእኛ ባልሆነ ወቅት የእጃችንን የምንጥልባቸው አጋጣሚዎች መበርከታቸው አይቀርም።

እኛ በተለምዶ አባባል ‹‹የጅብ ችኩል›› በምንሆን ጊዜ ከትርፋችን ኪሳራችን ያመዝናል። ማግኘት ሲገባን ማጣታችን ይበዛል። ሁሌም ማስተዋላችን ሲነጠቅ ውሏችን በችኩልነት ይነጠቃል። ይህ ተሞክሮ የሚደጋገም ከሆነ ደግሞ በጤናማ መንገድ የመኖራችን ሀቅ የከሰመ፣ አልያም የጠፋ ይሆናል።

ሰሞኑን በአንዳንድ የከተማችን መሀል ቦታዎች ድንገቴ የሚባል የንግድ ሂደት ሲካሄድ ተመልክተናል። ይህ አጋጣሚ በኮሪደሩ ልማት ምክንያት የንግድ ሱቆቻቸው እንዲነሳ ትዕዛዝ በደረሳቸው ነጋዴዎችና ገበያተኞች መካከል የተስተዋለ እውነታ ነው።

ከሰሞኑ በአንዳንድ ሥፍራዎች የነበረው ክስተት ነጋዴዎቹ ሥፍራውን ለመልቅቀ የሚያደርጉት ውክቢያ ብቻ አልነበረም። ከሱቆቹ ወጥተው ለሽያጭ በቀረቡ ዕቃዎች ላይ የነበረው መራኮትም በእጅጉ ያስደንቅ ነበር።

አስገራሚው ጉዳይ የገዢና ሻጮቹ ተለምዷዊው ግብይት አይደለም። በነዚህ ሥፍራዎች ከተፈጠረው ድንገቴ የሱቆች መነሳት ጋር ነጋዴዎቹ ዕቃዎቻቸውን አውጥተው መሸጣቸው ፈጽሞ አያስደንቅም። ነጋዴዎቹ በቦታዎቹ የቆዩ ናቸውና ዕቃዎቹን ወደቤት ላለመውሰድ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ‹‹ታላቅ ቅናሽ ›› እያሉ ገበያቸውን ይቀጥላሉ።

ጥሪያቸው ፈጣንና አስቸኳይ መሆኑን ያስተዋሉ አብዛኞቹ መንገደኞች ታዲያ የጎንዮሽ አይተዋቸው ብቻ አያልፉም። ከጊዜያቸው ጊዜ ነጥቀው፣ ከሌሎች እየተጋፉ፣ ወደእነሱ ጎራ ይላሉ። ከነዚህ መሀል አንዳንዶቹ የሰዎችን ብዛት አይተው ብቻ ከበባውን የተቀላቀሉ ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ ቢገዙም ባይገዙም ዕቃዎቹን አንስተው፣ አገላብጠው ለመጣል የሚያህላቸው የለም።

ገሚሶቹ ለሽያጭ የቀረቡትን በእጃቸው ጨብጠው ዋጋ በተቆረጠላቸው ልብሶች ላይ መከራከር መለያቸው ነው። እንደውም አንዳንዴ ሂሳብ እንዲቀነስላቸው ልመናቸው የለቅሶ ያህል የሚከብድና የሚያስጨንቅ ይሆናል።

ከሁሉም የሚያስገርሙት ግን ‹‹ታላቅ ቅናሽ የሚለውን ጥሪ ሰምተው ብቻ ልብሶቹን ለመግዛት የሚሻሙት መንገደኞች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ወደሥፍራው የሚያጣድፋቸው ‹‹ቅናሽ›› የምትለው ቃል ‹‹ታላቅ›› በሚል ማባበያ መጠራቷ ብቻ ነው።

ይህ አባባል ለእነሱ የሚገዙትን ዕቃ ለመለየት እንኳን ጊዜ አይሰጣቸውም። ለሽያጭ የቀረቡ ዕቃዎች በሙሉ ‹‹ታላቅ ቅናሽ›› መባላቸው ብቻ በእነሱ እሳቤ ትክክልና እውነተኛ ነው። ይህን አመኔታ ይዘው ወደ ግዢው የሚቀርቡ ሸማቾች እቃው በሚባለው ልክ ዋጋው ይመጥናል ወይ? የሚለውን ለማጣራት ጊዜ የላቸውም። በተባሉት ሂሳብ ተሻምተውና ከፍለው ዕቃውን በእጃቸው ለማስገባት ይጣደፋሉ።

እንዲህ አይነቶቹ ገዢዎች ሊወስዱት የሚጣደፉት እቃ እንደተባለው ሆኖ ጥራቱን የጠበቀ ሊሆን ይችላል። ምንአልባትም በአብዛኞች ዘንድ ተፈላጊና ተመራጭ መሆኑም አያጠራጥርም። አስደናቂው ጉዳይ ግን ታላቅ ቅናሽ የተባለለት ነገር ዋጋው ከተለመደው ገበያ የማይቀንስ ወይም በእጥፍ የሚጨምር ስለመሆኑ አለማጣራታቸው ነው።

ገዢዎቹ በአጋጣሚና በድንገት አገኘነው ለሚሉት ዕቃ የዋጋ ልዩነት በወጉ የሚረዱት ቤት ከገቡ፣ አልያም ከሌሎች ጋር ካወሩበት በኋላ ሊሆን ይችላል። በርካሽ ዋጋ በታላቅ ቅናሽ ማባበያ ከእጃቸው ያስገቡት ዕቃ ዋጋው እንደተባለው ቅናሽ አለመሆኑን ውሎ አድሮ ይሰሙታል። ይባስ ብሎም ገበያ ላይ ከሚታወቅበት የመሸጫ ዋጋ በእጥፍ መጨመሩን ይረዱና በንዴት ሲጦፉ፣ ሲቃጠሉ ይከርማሉ።

ይህ የመንገድ ላይ ታላቅ ቅናሽ ገበያ ነገር በዚህ ብቻ አያበቃም። አብዛኞቻችን ገና ቃሉን ስንሰማው ወደ ዓእምሯችን የሚመጣው የነጋዴዎቹ ሱቅ በድንገት መዘጋትና ለኪሳራ መዳረጋቸው ብቻ ነው። እንዲህ ማሰብ፣ መጨነቃችን ክፋት የለውም። ይህ ስሜት ገፋፍቶንም የአቅማችንን ልንገዛቸው መተባበራችን ጤናማነት ነው። እኛ እንዲህ ቀናውን ስናስብ ግን በሌላ አጋጣሚ ልንሸወድ የምንችልባቸውን ማጭበርበሪያዎችንም አስቀድመን ብንጠረጥር ክፋት የለውም። እንዲህ ማድረጋችን አንድም ለራሳችን፣ ብሎም ለሌሎች ትምህርት ይሆናልና።

ይህ የሰሞኑ የማጣሪያ ቅናሽ ገበያ ጉዳይ ሌላውንም አቅጣጫ እንድንታዘብ ያደርጋል። ሱቁን ለመልቀቅ የሚጣደፉ አንዳንድ ነጋዴዎች የእጆቻቸውን ዕቃዎች ፈጥነው ለመሸጥ የራሳቸውን ዘዴ ይጠቀማሉ። አብዛኞቹ የተመረጡና ዓይነ ገብ ሱሪዎችን፣ ሸሚዝና ጃኬቶችን በእጃቸው እያውለበለቡ የመጡበትን ሀገር ምንጭ ጭምር አድምቀው ይጠራሉ።

ወጪ ወራጅ መንገደኞች በሚተራመሱበት ጎዳና ውድ ተብዬዎቹ የቡቲክ ልብሶች በታላቅ ቅናሽ ከመንገድ መዘርጋታቸው የብዙዎችን ቀልብ ቢስብ አያስገርምም። ይህን ተከትሎ የቱርክ፣ የጣልያን፣የአሜሪካ ስሪት ናቸው የተባሉ ልብሶች ለገበያ መቅረባቸው ደግሞ ይበልጥ ግዢውን ያሰፋል፣ ገበያውን ያጦፋል።

ወዳጆቼ! አሁንም ልብ እንዲባል የሚያስፈልገው የአስተውሎቱ ጉዳይ ነው። አንዳንድ ሰዎች ከዓይናቸው ይልቅ ጆሯቸውን አበክረው ያምኑታል። በዚህ የታላቅ ቅናሽ ጥድፊያ ላይ እየሆነ ያለውም ይኸው ነው። አብዛኞቹ ችኩል ገዢዎቹ የቱርክ የጣልያን፣ የአሜሪካ የሚባሉትን እቃዎች እንደተባሉት ስለመገኘታቸው ለማጣራት ጊዜ አያገኙም፡ የሰሙትን አምነው ይቀበላሉ። የተጠየቁትን ቆጥረው ይከፍላሉ።

አሁንም ገዢዎቹ ስለእውነታው የሚረዱት ዋል አደር ብለው ሊሆን ይችላል። የገዙትን ሲለብሱትና ለሌሎች ሲያሳዩት። በርካሽ ዋጋ ከታዋቂ ቡቲኮች መደርደሪያ እጃቸው የገባው ድንቅ ልብስ ታዲያ ታሪክና መልኩ የተለያየ ነው። የቱርክ የተባለው፣ የቻይና፣ የጣልያን ተብሎ የተሸጠው ደግሞ እዚሁ በሀገራችን የተመረተ የእጅ ውጤታችን ሆኖ ይገኛል።

ይህ ሁሉ ሆኖ በታላቅ ቅናሽና በማጣሪያ ሽያጭ ሥም ሲቸበቸብ የከረመው ልብስና ጫማ እንደተባለው እውነት አለመሆኑ ቆይቶ ይደረስበታል። ብዙዎች በጥድፊያና ችኮላ የሚፈጽሙት ስህተት ከጥቅም ይልቅ ኪሳራ ላይ ሊጥላቸው ግድ ነው።

እንደ እኔ እምነት እንዲህ አይነቶቹ አጋጣሚዎች የሚከሰቱባቸው እውነታዎች ሁሌም ይኖራሉ ለማለት አልደፍርም። ይህን መሰሉን ድርጊት የሚፈጽሙትም ሁሉም ባለቡቲኮችና ነጋዴዎች አለመሆናቸውም ግልጽ ነው። ምንም ይሁን ምንም ግን ሸማቹ በግዴለሽነት የሚፈፅመው ስህተት መልሶ ለጸጸትና ለንዴት ሊጥለው አይገባም ባይ ነኝ።

አንዳንዴ አተረፍ ባይ አጉዳይነት ብዙዎችን ይጎዳል። አለማስተዋልና ችኩልነትም ከትርፍ ይልቅ ለኪሳራ ይዳርጋል። ይህ እንዳይሆን ደግሞ ልክ እንደ ጆሯችን ሁሉ የእይምሮ አስተውሎታችንና የዓይናችን ትኩረት አብሮን ሊጓዝ ይገባል። ያለዛ የታላቁ ቅናሽ ታላቅ ኪሳራ አይነት አጋጣሚዎች ከእኛው ጋር መሰንበት መቀጠላቸው አይቀሬ ይሆናሉ።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You