
በቅርቡ ወደ ሙሉ ትግበራ የገባው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያና እሱን ተከትሎ ብሄራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓት ላይ ያወጣው ማሻሻያ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸው ስለመሆናቸው መንግሥትም የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችም አስታውቀዋል። ሊያጋጥሙ ይችላሉ የተባሉ ስጋቶችን ከወዲሁ በመቆጣጠር የሚተገበር ከሆነ ውጤታማ ሊሆን እንደሚችልም እየተገለጸ ነው።
ሕገወጥ ንግድ ተግዳሮት እንደሚሆን አስቀድሞም እንደተጠቆመው ሁሉ ማሻሻያው መተግበር እንደጀመረ ሕገወጥ ነጋዴዎች በሸቀጦችና በግብርና ምርቶች ዋጋ ላይ ያልተገባ ጭማሪ አድርገዋል። መንግሥትም በማሻሻያው ላይ ለንግዱ ማህበረሰብ ከሚያደርገው ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ ጎን ለጎን በሕገወጥ ተግባሩ በተሠማሩት በእነዚህ ስግብግብ ነጋዴዎች ርምጃዎች እየወሰደ ይገኛል።
በርምጃውም ለሕገወጦቹ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል፤ መደብሮች ታሽገዋል፤ ምርቶችን ደብቀው በተገኙ ላይም እንዲሁ ምርቶቹን ወርሶ በሸማቾች ማህበራት በኩል ለህብረተሰቡ እንዲሸጡ እስከ ማድረግ የደርሰ ርምጃ የተወሰደበት ሁኔታም ታይቷል። እነዚህ ርምጃዎች ስለመወሰዳቸውም በመገናኛ ብዙሃን በማሳወቅ ሌሎች በሕገወጥ ተግባሩ እንዳይሳተፉ ማድረግ የሚረዳ ሥራም እየተሠራ ነው።
መንግሥት ወደዚህ ርምጃ የገባው በመገናኛ ብዙሃን እና በተለያዩ መድረኮች ማሻሻያውን ተከትሎ የግንዛቤ ማሳጨበጥ ሥራ ሠርቶም ነው። በዚህ ሥራም በአሁኑ ወቅት ሊደረግ የሚገባው ምንም አይነት የዋጋ ጭማሪ መኖር እንደሌለበትና ዋጋ ጨምረው በሚገኙ ላይም ጥብቅ ርምጃ እንደሚወሰድ ግንዛቤዎችን በበቂ ሁኔታ ሰጥቷል።
መንግሥት በየቀኑ በሚያወጣው መረጃ ይህን ሕገወጥ ተግባር ለመቆጣጠር ትኩረት አድርጎ እየሠራ ስለመሆኑ እያስገነዘበ ይገኛል። ከመረጃዎቹ መረዳት እንደሚቻለውም የምርት እጥረት እንዲፈጠር በማድረግ የንግድ አሻጥር እየሠሩ ባሉ ሕገወጦች ላይ ርምጃ መውሰዱን ቀጥሏል። ይህ ብቻ አይደለም፤ በየደረጃው የሚገኙ የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች እየታየ ያለውን ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በፍጥነት ለመቆጣጠር በቅንጅት መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም እያስገነዘበ ነው።
የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራው በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮችም እየተሰጠ ይገኛል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅርቡ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ያላቸውን አካላት በሙሉ በመሰብሰብ ስለማሻሻያው ግንዛቤ የመፍጠር ሠርቷል። በወቅቱ ከንቲባ አዳነች አበቤን ጨምሮ የኢኮኖሚ ዘርፉን የሚመሩት አመራሮች ተገኝተው ማብራሪያ ሠጥተዋል።
በመድረኩ ከንቲበ አዳነች አበቤ እንዳስታወቁት፤ ማሻሻያው ዘላቂ ልማትንና አካታችነትን የሚያረጋግጥ፣ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርግ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት፣ የመንግሥትን የእዳ ጫና ለመቀነስ፣ የተረጋጋ፣ ተወዳዳሪ እና የዋጋ ግሽበትን መቀነስ የሚያስችል የገበያ ሁኔታን ለመፍጠር፣ ተኪ ምርቶችን በማምረትና ለውጭ ገበያ የሚላከውን ምርት ለማሳደግ እንዲሁም ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ በመፍጠር የውጭ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ እድል ይፈጥራል።
ማሻሻያው ተግዳሮቶች ሊያጋጥሙት እንደሚችሉ ጠቁመው፣ ተግዳሮቶቹን ለመፍታትም በመንግሥት ደረጃ ታችኛው ክፍል ድረስ በመዋቅር በመደራጀት የክትትልና ቁጥጥር ሥራ ይሠራል ሲሉም አስገንዝበዋል።
ከዚህ ጎን ለጎንም ከአምራቾች እና አስመጪዎች ጋር በቅርበት በመሥራትና ገበያውን የሚያዛቡ፣ በተለይም ምንም ከውጭ ምንዛሪ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ምርቶች ላይ አላግባብ ዋጋ በሚጨምሩ እና ምርት በሚሰውሩ አካላት ላይ ጠንካራ የሆነ ቁጥጥር እና ሕግ የማስከበር ሥራ እንደሚሠራም ተጠቀሟል። በተደረገ ቁጥጥርና ክትትል / እስከ አለፈው ሳምንት ድረስ/ በአዚህ ሕገወጥ ንግድ ላይ ተሠማርተው በተገኙ 769 የንግድ ድርጅቶች ላይ ርምጃ ተወስዷል። ከእነዚህም ውስጥም 346ቱ ያለአግባብ ዋጋ በመጨመር በመያዛቸው ታሽገዋል፤ 423 የሚደርሱት ደግሞ ምርት በመሸሸግና ዋጋ ዝርዝር ባለመለጠፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ናቸው ተብሏል።
እንደ እኔ ደግሞ ከተማ አስተዳደሩ ያከናወነው ተግባር ወቅታዊና ተገቢነት ያለው ሆኖ፣ ማሻሻያው ይዞት ከመጣው ቱሩፋት አኳያ ግንዛቤ የማስጨበጡ ሥራ ተከታታይነት ባለው መልኩ በስፋት መካሄድ ይኖርበታል።
መንግሥት ማሻሻያውን ወደ ሥራ ሲያስገባ ብዙ ማሳሰቢያዎችን ሰጥቶ እያለ ፣ የማሻሻያው ሀገራዊ ፋይዳ በሚገባ ተገልጾ እያለ ሕገወጦቹ ለምን በእዚህ አይነት ተግባር ውስጥ በእዚህ ልክ ተሠማሩ ብሎ መጠየቅም ይገባል።
በመሠረቱ ሕገወጦቹ በምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ እያደረጉ ያሉት ከሁለት ምክንያት በመነጨ ነው ማለት ይቻላል። የመጀመሪያው የግንዛቤ እጥረት ሲሆን፣ ሁለተኛው በእዚህ አይነቱ ሕገወጥ ተግባር መከበር የለመዱ ስግብግቦች እየተበራከቱ በመምጣቸው ነው። ስለዚህም ሁለቱንም ተግባሮች እንደየመልካቸው እያዩ ሕገወጥ ድርጊቱን ለመቆጣጠር መሥራት ያስፈልጋል።
ሕገወጥ ድርጊቱ ከግንዛቤ እጥረት ጋር በተያያዘ ሊከሰት እንደሚችል ይችላል፤ ለእዚህም ነው ከየትኛውም ርምጃ በፊት ግንዛቤ ለማስጨበጥ ሥራ ቅድሚያ የሚሰጠው። መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ትግበራ ሲጀምርም ይህንኑ አድርጓል፤ የተሠራው ግን ምን ያህል ለውጥ ማምጣት ያስችላል የሚለውን መመልከት ይገባል፤ በሸቀጦች በተለይ ደግሞ በግብርና ምርቶች ላይ የተደረገው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪም ይህን መመልከት የግድ ይላል።
ለእነዚህ ወገኖች በዚህ ሕገወጥ ድርጊት መግባት አንዱ ምክንያት እስከ አሁን የመጡበት መንገድ ነው ብዬ አስባለሁ። መንግሥት አንድ ለውጥ ሲያደርግ/ የነዳጅ ዋጋ ሲጨምር፣ የትራስፖርት ዋጋ ሲጨምር /፣ የተለያዩ ችግሮች ሲፈጠሩ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት በሌለበት ሁኔታ ዋጋ ሲጨምሩ ኖረዋል፤ ዝናብ ጣለ ብለው የታክሲ ታሪፍ የሚጨምሩ ያሉበት ሀገር ውስጥ ነው ያለነው።
እነዚህ ሕገወጦች በእዚህና በመሳሰሉት ድርጊታቸው የንግዱን ማህበረሰብ በአጠቃላይ ሲያሳስቱ፣ ሸማቹን ሲጎዱ ኖረዋል። ይህን ያህል ጥፋት ሠርተው ይወሰድባቸው የነበረው ርምጃም እጃቸውን እንዲሰበስቡ የሚያደርግ ነበረ ብሎ መናገር ያስችግራል። ሕገወጦቹ አሁንም ያን አይነት አመላካከት ይዘው በሕገወጥ ተግባሩ ተጠምደው መታየታቸውም ይህንኑ ያረጋግጣል።
ይህ ድርጊታቸው በዚህ ወሳኝ ወቅት እንዳይቀጥል ለማድረግ የንግዱ ማህበረሰብ በማሻሻያው ላይ ጥልቅ ግንዛቤ እንዲጨብጥ ማድረግ ላይ መሥራትን ይጠይቃል። ለእዚህ ደግሞ የንግድ ሥራውን የሚመራው መንግሥታዊ ተቋም ብቻ ሳይሆን ለንግዱ ማህበረሰብ ቅርብ ነው የሚባለው የንግድ ምክር ቤትም ሃላፊነት አለበት።
ኢኮኖሚያዊ ምክንያት በሌለበት ሁኔታ ሰው ሰራሽ የምርት እጥረት በመፍጠር / ምርቶችን በመደበቅ/ መበልጸግን የሀብት ማግኛ መንገድ ያደረጉ ጥቂት የማይባሉ ነጋዴዎች አሉ፤ በተለይ ጅምላ ነጋዴዎች። እነዚህ ሕገወጦች ነበሩ አሁንም አሉ።
ሕገወጦቹ የሀገሪቱ የንግድ ሥርዓት ነጻ ገበያን የማያበረታታ በመሆኑ ነው እስከ አሁን የቀጠሉት። ወደፊት የውጭ ጅምላና ችርቻሮ ነጋዴዎች ሲመጡ ይህ የኖሩበት ድርጊት የማይቀጥልበት ሁኔታ ይፈጠራል ብሎ ከወዲሁ መገመት ይችላል። እዚያው ድረስ ግን የእነዚህንም አካላት ግንዛቤ መቀየር ላይ መሠራት ይኖርበታል።
በአሁኑ ወቅት ለተፈጠረው የዋጋ ጭማሪ፣ ምርት መደበቅና ለመሳሰለው ችግር አንዱ መፍትሄም ይሄው ሊሆን ይገባል። በአጠቃላይ መንግሥት በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው እየተገበረ ያለው ሀገርንና ሕዝብን ሊለወጥ የሚችል ተግባር መሆኑን ለንግዱ ማህበረሰብ ማስገንዘብ ያስፈልጋል፤ መንግሥት በዚህ ትግበራ ወቅት አስቀድሞም ይህን መሰሉ ሕገወጥ ድርጊት ተግዳሮት ሊሆን እንደሚችል በመጥቀስ፣ በሕገወጥ ድርጊቱ የሚሰማሩ አካላት ርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚችል ሲያሳስብ እንደቆየው ሁሉ አሁንም ይህን ማድረጉን መቀጠል ይኖርበታል።
አውቀው የሚያጠፉ ጥቂት አይደሉም፤ እነዚህ ላይ ግንዛቤ ለማስረጽ በሚል ጊዜ ማጥፋት ላያስፈልግም ይችላል። ‹‹አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይነቃም›› እንደሚባለው ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራም ተሠርቶ የማይለወጡ ሊኖሩ ይችላሉ፤ ይኖራሉ። በእነዚህ ላይ ደግሞ ማስረጃ አደራጅቶ የማያዳግም ርምጃ የተባለውን መውሰድ ያስፈልጋል፤ ለዘርፉ አንዱ የማያዳግም የሚባለው ርምጀ ፈቃድ መንጠቅ ሊሆን ይችላል፤ በሕግ መጠየቀም ሌላው ሊሆን ይችላል።
ለሀገርና ሕዝብ ልማት ሲባል ይህን እስከ ማድረግ መድረስ ያስፈልጋል። በዚህ ምክንያት ማሻሻያው መንገራገጭ ሊያጋጥመው አይገባምና በእነደዚህ አይነቶቹ ሕገወጦች ላይ የማያዳግም ርምጃ መውሰድ ተገቢም ወቅታዊም ነው።
አሁን ባለው ሁኔታ ከጉዳዩ አሳሳቢነት አኳያ ከግንዛቤ ማስጨበጡ ጎን ለጎን ተመጣጣኝ ርምጃዎች ለመውሰድ እየተከናወነ ያለው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። መንግሥት ርምጃውን ትኩረት ያደረገው ደግሞ በሸቀጣሸቀጥ ሱቆች ላይ ነው። ጭማሬው ያልገባበት የለም። ዘርፈ ብዙ መልክ ያለው ነውና ግብርና ምርቶች በሚነግዱ ላይ ጨምሮ ጥብቅ ቁጥጥር መደረግ ይኖርበታል፤ ሕገወጥ ተግባር ፈጽመው በተገኙት ላይም ርምጃ መወሰድ ይኖርበታል። ሰላም!!
ክብረ መንግሥት
አዲስ ዘመን ዓርብ ነሐሴ 10 ቀን 2016 ዓ.ም