ነገረ “የገንዘብ ልውውጥ”

(Currency Swap)

ዲዶላራይዜሽን ወይም “De-dollarization” የአሜሪካን ዶላር በዓለም አቀፍ ንግድ፣ ፋይናንስ እና ክምችት ላይ ያለውን የበላይነት የመቀነስ ሂደት ነው። በዓለም ላይ ያሉ ሀገራት በመጠባበቂያ ክምችት ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው የአሜሪካ ዶላር ይይዛሉ። ከፍተኛውን የዓለም አቀፍ ንግዳቸውን በዶላር ያካሂዳሉ። የቻይና የሕንድና የሌሎች በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ኢኮኖሚ በፍጥነት እያደገ ሲመጣ ግን ከዶላር ጥገኝነት ነፃ መሆን የግድ እየሆነ መጣ።

የጂኦፖለቲካል ጉዳይ ሌላው ምክንያት ነው። ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ባለው የፖለቲካ ውጥረት ወይም የአሜሪካ ማዕቀብ ሊያስከትል በሚችል ስጋት ምክንያት ሀገራት በዶላር ላይ ያላቸውን ጥገኝነት መቀነስ ይፈልጋሉ። ሌላው በዶላር ላይ በእጅጉ መመካት ሀገሮችን ለወጪ ምንዛሪ ስጋት እና ለአሜሪካ ፌዴራል ሪዘርቭ ፖሊሲዎች ባርነት ያጋልጣል። የመጠባበቂያ ክምችት እና የንግድ ልውውጥ በሌሎች ገንዘቦች ማድረግ ግን ይህንን አደጋ ሊቀንስ ይችላል።

እንዲሁም የገንዘብ ሉዓላዊነት ፍላጎት ተጨማሪ መግፍኤ ነው። ሀገሮች በገንዘብ ፖሊሲያቸው ላይ የበለጠ ባለመብት ለመሆን፣ ነፃ የገንዘብ ፖሊሲ እንዲኖራቸው እና አሜሪካ በኢኮኖሚያቸው ላይ የምታሳድረውን ተጽዕኖ ለመቀነስ ከዶላር ውጭ ለመገበያየት እየወሰኑ ይገኛል። ሀገራችን ይሄን ይበል የሚያስብል ርምጃ ሰሞኑን ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር አሀዱ ብላ ጀምራለች።

ኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በራሳቸው ገንዘብ ለመገበያየት የሚያስችል የሁለትዮሽ የገንዘብ ልውውጥ(Currency Swap) ስምምነት ያደረጉ ሲሆን፤ ባለፈው ማክሰኞ ሐምሌ 9 ቀን 2016 ዓ.ም በተደረገው በገንዘብ ልውውጥ ስምምነቱ መሠረት፣ ኢትዮጵያ 46 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ የንግድና ኢንቨስትመንት ሥራን ያለ ዶላር አስፈላጊነት ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ጋር መገበያየት ወይም መለዋወጥ ያስችላታል። ይህም ዋጋ ከሦስት ቢሊዮን ድርሃም ወይም 800 ሚሊዮን ዶላር ጋር ተመጣጣኝ ነው።

የገንዘብ ልውውጥ ስምምነት ማለት ዋጋቸው እኩል የሆኑ ምርቶችን መለዋወጥ (In Kind Trade) ሲሆን፣ ከምርቶቹ ዋጋ በላይ የሆነውን ትርፍ ዋጋ ብቻ በገንዘብ ያወራርዳሉ። ይህም ማለት ኢትዮጵያ ከዱባይ በብር መግዛት የምትችል ሲሆን፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶችም በድርሃም ከኢትዮጵያ መግዛት ትችላለች።

በተጨማሪ ኢትዮጵያ ለምሳሌ ለተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ላቀረበችው ዕቃ ክፍያውን በድርሃም ከተቀበለች ወይም የክፍያው ትርፍ ወደ ኢትዮጵያ ሆኖ በብር ለተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ከከፈለች፣ ሁለቱ ሀገሮች ገንዘቦቹን ከሚጠቀሙ ሌሎች ሀገሮች ጋር እንዲገበያዩበት ያስችላል።

እንዲህ ዓይነት ስምምነት የብሪክስ (BRICS) ሀገሮች በተለይ በብዛት እየጀመሩት ሲሆን፣ ይህም በዋናነት ዶላር እንዲዳከም ለማድረግ ያለመ ነው። ኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በቅርቡ የብሪክስ አባል ሀገሮች ሲሆኑ፣ ይህም ስምምነት የዚሁ አካል ነው ሲሉ ተንታኞች ይገልጻሉ። በተለይ አሜሪካ በብዙ ሀገሮች ላይ የምትጥለው ማዕቀብ ተፅዕኖ እንዳያርፍባቸው ብዙ ታዳጊ ሀገሮች ዶላርን ላለመጠቀም እየወሰኑ ነው። ቻይና፣ ሩሲያ፣ እንዲሁም ህንድ በብሪክስ ሥር ተመሳሳይ ስምምነት በማድረግ ያለ ዶላር በየራሳቸው ገንዘቦች መነገድ ከጀመሩ ሰንብተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምሕረቱና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ካሊድ መሐመድ በፊርማቸው የደረሱበት ስምምነት ይህንኑ ያጠናክራል እየተባለ ነው። ሁለተኛው የመግባቢያ ስምምነት የሁለቱ ሀገሮች የንግድና ኢንቨስትመንት፣ እንዲሁም ማናቸውም ሽያጮች በራሳቸው ገንዘቦች እንዲደረጉ ያስችላል። ለዚህም የሁለቱ ሀገሮች የንግድ ባንኮች እንዴት የክፍያ ሥርዓቶቻቸውን ማቀላጠፍና የጽሑፍ መልዕክቶችን መላላክ እንደሚችሉ ያትታል።

‹‹ስምምነቱ ሁለቱ ሀገሮች በየራሳቸው ገንዘቦች ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲያካሂዱ ያስችላል። የኤሌክትሮኒክ ክፍያ ሥርዓቶቻችንም እንዴት ተዋህደው ሊሠሩ እንደሚችሉ ከስምምነት ደርሰናል። ይህ ስምምነት ሁለቱ ሀገሮች የጋራ ፍላጎቶቻቸውን ከግብ ለማድረስ ጠቃሚ ነው፤›› ሲሉ አቶ ማሞ ተናግረዋል። የኤምሬትስ ብሔራዊ ባንክ ገዥ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከዓረብ ኤምሬትስ የምገዛቸው ምርቶች በርካታ መሆናቸውን ገልጸው፣ በተለይ ደግሞ የኤምሬትስ ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ በብዛት እንዲመጡ እንደሚያደርግ አስረድተዋል።

አቶ ዋሲሁን በላይ የተባሉ የኢኮኖሚ ባለሙያና ተንታኝ “The Ethiopian Economist View” በሚለው የቴሌግራም ገጻቸው የገንዘብ ልውውጥን በተመለከተ ሰፊ ትንታኔ አቅርበዋል። የዓለም አቀፍ ሁኔታ የኃይል ሚዛን ፍላጎት መቀያየር እና የአሜሪካ እና የአጋሮቿ ተደጋጋሚ የኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ማዕቀብ በርካታ የዓለም ሀገራት በተለይ በፍጥነት እያደጉ ያሉት ሀገራት ዶላርን በሀገራቱ መካከል እንደ ማዕከላዊ የመገበያያ ገንዘብነት የመምረጣቸው ፍላጎት እየቀነሰ ነው።

ስለዚህ በርካታ ሀገራት ከሌሎች ሀገራት ጋር የሚኖራቸው የንግድ ግንኙነት ዶላር ላይ ያለውን ጥገኝነት በመቀነስ ወደ አማራጭ የክፍያ ስልቶችን መፈለግ ጀምረዋል። በተለይ ሀገራት ከንግድ አጋሮቻቸው ጋር በሚያደርጉት ስምምነት የንግድ እና የኢንቨስትመንት ክፍያዎቻቸውን በየራሳቸው ገንዘብ ለማድረግ (Bilateral Currency Swap Lines) በየማዕከላዊ ባንኮቻቸው በኩል ስምምነት እየፈጸሙ ነው። የዚህ ዋነኛ አቀንቃኞች ቻይና፤ ራሽያ እና ህንድ ሲሆኑ ብዙ ሀገራት እየተቀላቀሉት ነው።

በተናጥል በሚያደርጉት የክፍያ ስምምነት ለተለያዩ ሀገራት የተለያያ የገንዘብ ዓይነት ይጠቀማሉ በየራሳቸው ገንዘብ ለመገበያየት ከወሰኑት ሀገራት ጋር በየራሳቸው ገንዘብ ነገር ግን ስምምነት ካልፈጠሩባቸው ሀገራት ጋር በተመረጡ የምንዛሬ ዓይነቶች ሊገበያዩ ይችላሉ።

1.ቻይና ከንግድ አጋሮቿ ጋር በየራሳቸው ገንዘብ ለመገበያየት Network of Bilateral Currency Swap Agreements ቀዳሚዋ እና ትልቋ ሀገር ናት። የቻይና ማዕከላዊ ባንክ People’s Bank of China ከ41 የተለያዩ ሀገራት ብሔራዊ ባንኮች ጋር ስምምነት አድርጓል። ይህም ከ3.5 ትሪሊየን ዩሃን ወይም ከ480 ቢሊየን ዶላር በላይ አቻ ነው። ቻይና ከአሜሪካ ዶላር ቀጥሎ ከፍተኛ የዓለም አቀፍ የንግድ ግንኙነት ገቢ ያገኘችው ስምምነት ካደረገችባቸው ሀገራት ነው።

በIMF ጥናት ከቻይና ጋር ስምምነት ያደረጉ ሀገራት የክፍያ መጠናቸው በ2014 ከነበረበት ዜሮ ከመቶ በ2021 ድርሻው 20በመቶ ደርሷል። የተወሰኑ ሀገራት ከቻይና በቻይና ገንዘብ መገበያየት ከመቻላቸው በተጨማሪ ከሌላ ሶስተኛ ሀገር የቻይናን ገንዘብ ተጠቅመው ክፍያ መፈጸም ይችላሉ። ለምሳሌ ህንድ ከራሽያ በቻይና ገንዘብ ነዳጅ ትሸምታለች። ቻይና፤ ሆንግ ኮንግ፤ ታይላንድ እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ በማዕከላዊ ባንኮቻቸው በኩል የራሳቸው ዲጂታል የክፍያ ዘዴ ፈጥረው ግብይት ለመለዋወጥ ሥራ ጀምረዋል (mBridge)።

  1. ህንድ ስምምነት ከምታደርግባቸው ሀገራት ጋር በራሷ ገንዘብ (ሩፒ) ለመገበያየት ወስናለች። እስካሁን ከ22 ሀገራት ጋር ስምምነት ደርሳለች። ህንድ የዛሬ ዓመት ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ጋር በሩፒ ለመገበያየት ስምምነት አድርጋለች። በርግጥ ህንድ ከመካከለኛው ሀገራት ጋር በሩፒ የመገበያየት ነባር ልምድ ነበራት። ኢራን እና ማይናማር ተመሳሳይ ፍላጎት አላቸው።

ምን ማለት ነው? ስምምነት ያደረጉ ሀገራት በህንድ ባንኮች አካውንት ከፍተው ወይም Special Vostro Rupee Accounts ሩፒ ይቆጥባሉ። ከዚያ ለሚያደርጉት ሸመታ ክፍያ ከአካውንታቸው ይፈጽማሉ። በተመሳሳይ የህንድ ድርጅቶች ስምምነት ባለባቸው ሀገራት ሂሳብ ከፍተው የየሀገራቱን ገንዘብ ይቆጥባሉ ለሸመታቸው ክፍያ ይፈጽማሉ ማለት ነው። ህንድ በዓለም አቀፉ ንግድ ውስጥ ያላት ድርሻ ከ1.8 በመቶ ባይበልጥም በቻይና ከሚመራው የ15 በመቶ ንግድ ጋር ሲደመር ተጽዕኖው ቀላል አይደለም።

  1. ራሽያ በተደጋጋሚ የማዕቀብ ሰለባ በመሆኗ የቻይናን ገንዘብ መገበያያ አድርጎ ወደ መቀበል አዘንብላለች። በተለይ ከ2022 ጀምሮ ከዩክሬን ጋር ጦርነት ውስጥ መግባቷን ተከትሎ በውጭ ሀገራት የነበሯት የመጠባበቂያ አካውንቶች መዘጋት እና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ዝውውር ዘዴ SWIFT መታገዷ በሀገራት ጋር በተናጥል ገንዘቦች ለመገበያየት ገፊ ምክንያት ሆኗታል። ራሽያ ከቻይና ጋር ሁለት ሶስተኛ የሚሆነውን የንግድ ልውውጥ እያከናወነች ያለችው በሩብል እና በዩሃን ነው።

ራሽያ ከ2022 አጋማሽ ጀምሮ የራሽያ ወዳጅ ያልሆኑ ሀገራት ነዳጅ ከራሽያ ለመሸመት የራሽያ ገንዘብ ማለትም ሩብል ይዘው መገኘት አለባቸው የሚል ውሳኔ አውጥታለች። ለምሳሌ እንግሊዝ ከራሽያ ነዳጅ ለመግዛት ብትፈልግ መክፈል ያለባት በፓውንድ፤ በዩሮ ወይም በዶላር ሳይሆን በሩብል ነው። ከዚህ ውሳኔ በኋላ 54 የውጭ ሀገር ድርጅቶች ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ዝውውር ዘዴ SWIFT ቁጥጥር ውጭ የሆነ Gazprombank የሚባል አካውንት ከፍተው ሩብል በመቆጠብ ይጠቀማሉ።

የእስያ ሀገራት የሆኑት ኢንዶኒዢያ፤ ማልይዥያ፤ ሲንጋፖር እና ታይላንድ (ፊሊፒንስ ትቀላቀላለች ተብሎ ይጠበቃል) እርስ በርስ በየራሳቸው ገንዘብ ለመገበያት ስምምነት አድርገዋል። ስምምነቱ Local Currency Settlement Framework ይባላል። የብሪክስ አባል ሀገራት በየራሳቸው ገንዘብ ለመገበያየት (BRICS Pay) ስምምነት ያደረጉት የዛሬ ዓመት ነው። ኢትዮጰያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በተጨማሪ የብሪክስ አባል ናቸው። ኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በየራሳቸው ገንዘብ ለመገበያየት ስምምነት አድርገዋል፤ ስምምነቶቹ የተፈረሙት በሁለቱ ሀገራት ማዕከላዊ ባንክ ገዢዎች ነው።

የወደፊት ስምምነቱ የክፍያ ሥርዓት (UAESWITCH እና ETHSWITCH ለማስተሳሰር) እና የክፍያ መረጃ የመለዋወጥ ዘዴዎችን የሚጨምር ነው። ነገር ግን በየራሳቸው ገንዘብ ለመገበያየት የወሰኑት Currency Swap የስምምቱ ማዕቀፍ የ3 ቢሊየን ድርሃም እና የ46 ቢሊየን ብር ዋጋ ያለው ነው። ምን ማለት ነው? የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 3 ቢሊየን ድርሃም የምታስቀምጥ ሲሆን ኢትዮጵያም በተመሳሳይ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ማዕከላዊ ባንክ 46 ቢሊየን ብር ታስቀምጣለች ማለት ነው።

ይህንን ያስቀመጡትን ገንዘብ እስኪጨርሱ የሁለቱ ሀገራት ብሔራዊ ባንኮች ከአካውንቶቻቸው ወጪ እያደረጉ ሸመታ እና ኢንቨስትመንት ያከናውናሉ ማለት ነው። ለምሳሌ ኢትዮጵያ የመቶ ሚሊየን ብር ዋጋ ያለው መኪና ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ለመግዛት ብታስብ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ማዕከላዊ ባንክ ካላት 46 ቢሊየን ብር አውጥታ ትገዛለች ማለት ነው። በተመሳሳይ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከኢትዮጵያ የ100 ሚሊየን ድርሃም ዋጋ ያለው ቡና ለመግዛት ብትፈልግ በኢትዮጵያ ማዕከላዊ ባንክ ካላት 3 ቢሊየን ድርሃም ላይ አውጥታ ትገዛለች ማለት ነው። የዋጋ ተመኑ በገንዘቦቹ መካከል ባለው ልዩነት ይሆናል። አንድ ብር አንድ ድርሃም ይሆናል ማለት አይደለም።

በመጀመሪያ ስምምነታቸው ማለትም የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የምታስቀምጠው 3 ቢሊየን ድርሃም እና ኢትዮጵያም በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ማዕከላዊ ባንክ የምታስቀምጠው 46 ቢሊየን ብር እስኪያልቅ ነው። የሁለቱም ሀገራት ብሔራዊ ባንኮች ይህንን ያስቀመጡትን ገንዘብ ለየትኞቹ ዘርፎች እና ምርቶች እንደሚውል እና በምን ያህል ጊዜ እየተጠቀሙ እንደሚጨርሱት በቀጣይ የሚወስኑ ይሆናል። የዚህ ዓይነቱ ስምምነት በጥምረት የሚሰሩ የንግድ አጋርነት ለመፍጠር እና የንግድ ልውውጥ መጠንን ለማስፋት ጠቀሜታ ይኖረዋል፤ የግብይት ወጪን ይቀንሳል፤ ከሶስተኛ ሀገር ማዕቀብ ነፃ ነው።

ሻሎም ! አሜን ።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2016 ዓ.ም

Recommended For You