ሀሳብ የማይዳሰስና የማይጨበጥ ነገር ግን ደግሞ የማንኛውም እምነትና ነገረ-ክዋኔ መነሻና መሰረት በመሆኑ የማንኛውንም ግለሰብ፣ ማህበረሰብ እንዲሁም ሀገር መነሻ ብቻ ሳይሆን መድረሻም ጭምር የሚወስን ታላቅ የለውጥ ሀይል ነው፡፡ ብዙም ይሁን ጥቂት ትንሽም ይሁን ትልቅ እያንዳንዱ የሰው ልጅ ልቦና ውስጥ ቢያንስ አንድ ሀሳብ አለ።
ይሁን እንጂ ለማንኛውም ሰው የተቸረና ሁሉም የታደለውን ይህን ሀይል የማየት፣ የመገንዘብና ተግብሮ ጥቅም ላይ የማዋል ፀጋ ታድለው ከራሳቸውና ቤተሰባቸው አልፈው ለወገንና ሀገር የተረፈ ተግባር መፈፀም የቻሉት ውስጣቸውን በአንክሮ የማዳመጥ፣ ዙሪያቸውን በጥልቀት የማስተዋል፣ ነገሮችን በሰከነ መንፈስ የመመርመርና አቀናጅቶ የማጤን ልምድ ያላቸው ጥቂት ሰዎች ናቸው፡፡
ይህን ፀጋ ስለመታደላቸው የሚመ ሰክር ህይወት ተሞክሮ ካላቸው ውስጥ አንዱ የዛሬው ሲራራ አምድ እንግዳዬ ደግሞ አቶ ነጋሲ አርአያ ይባላል። የተወለደው በታሪካዊቷ ዓድዋ ሲሆን ከቤተሰቦቹ ጋር በመሆን የመናገሻይቱ አዲስ አበባን አፈር የረገጠው ገና በጨቅላ ዕድሜው ነው፡፡ ታዲያ ከዚህ ዕድሜው ጀምሮ የሚያሳየው ዝንባሌ ያላማራቸው ቤተሰቦቹ ትምህርት ላይ ብቻ እንዲያተኩር ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም፡፡
እሱ ግን ውስጡን ለገዙት እግር ኳስና ፈጠራ ሥራ የነበረው ብርቱ ፍቅር እያደር በመባሱ አባቱ የሚወዱትን አዲስ ዘመን ጋዜጣ ርዕሰ-አንቀፅ በእጁ ገልብጦ እንዲፅፍና ማታ ማታ እንዲያሳያቸው ጥብቅ መመሪያ አስተላለፉ፡፡ ነገር ግን በዚህ እርምጃ ምክንያት ነጋሲ ቤት ቢውልም ቅሉ ይበልጥ ከቴክኖሎጂና ፈጠራ ነክ መፅሀፍት ጋር አቀራረቡትና ልቡ ውስጥ ተደብቆ ከቆየው ፈጠራ ወዳድነቱ ጋር የእውቂያ በር ከፈተ፡፡
ትምህርት ብቸኛው የህይወት መንገድ እንደሆነ በፅኑ በሚያምን ቤተሰብና ማህበረሰብ ውስጥ ማደግ በልጅነቱ እሳቤው ላይ ከፍተኛ ጫና እንዳሳደረበት ይጠቅሳል፡፡ በሙያ ላይ ነቀፌታና ማጥላላት እንዲሁም አዳዲስና የተሻሉ ነገሮችን ከመቀበል ይልቅ በነባር ነገሮች ላይ የሙጥኝ ማለት የመሳሰሉት ማህበራዊ ትችቶች በንግድ እንቅስቃሴውን አጣብቂኝ ውስጥ የከተቱ ፈተናዎች መካከል ተጠቃሾቹ ናቸው።
ዳሩ ግን እነዚህ ችግሮች በማርሻል አርት፣ በሴቶች እግር ኳስ ውድድር ማዘጋጀት እንዲሁም ሌሎች በርካታ በሮችን ሳይታክት እንዲያንኳኳ እንጂ ከዓላማው ወደ ኋላ እንዲንሸራተት አላደረጉትም፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ለዓላማው መሳካት የሚደግፉንና መልካም አጋጣሚ የሚፈጥሩልን ሰዎችና ሁኔታዎች የመኖራቸውን ያህል የሚነቅፉት መኖራቸውን በእኩል ደረጃ ማሰብ መቻሉ እንደሆነ ያስረዳል፡፡
ባልተሳኩለት የሥራ መስኮች ተስፋ ሳይቆርጥም ከጓደኞቹ ጋር በመሆን “ሁለገብ የሥልጠና እና ፈጠራ ማዕከል” የተባለ ተቋም መሰረተ፡፡ ይህ ተቋም ካስገኘው ጥቅም ባልተናነሰ መልኩ ማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ ችግሮችን አጥንቶ መፍትሔ የሚሆኑ አዳዲስ የቴክኖሎጂና ፈጠራ ውጤቶችን እንዲሁም ቅጂ (ተኪ አምሳያ) ግብዓቶችን አምርቶ የማቅረብ የተቋቋመው የብረታ-ብረት ቴክኖሎጂና ፈጠራ ሥራ ድርጅት ከፈቱ፡፡ በዚህም ሳይወሰን ኦክስፎርድ ኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩትና ሌሎች የማስ ታወቂያና ፕሮሞሽን የተሰኘ ድርጅት መሰረተ፡፡
ይህንን የማስታወቂያ ድርጅት ለመክፈት ምክንያት የሆነው ከጥቂት ዓመታት በፊት ከአምስት መቶ የሚልቁ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የሠራተኛ እጥረት ሲገጥማቸው ተቀጣሪ ባለ ሙያ ፈልገው የቅጥር ማስታወቂያ የሚለጥፉበት ስፍራ ማጣታቸውን ማስተዋሉ ነው።
«ድርጅቶቹ በራሳቸው ላይ ያለውን ማስታወቂያ ቦርድ ብቻ የሚጠቀሙ በመሆኑ በቂ ተወዳዳሪ ባለማግኘት ማስታወቂያቸውን በተደጋ ጋሚ ለማውጣት ከመገደዳቸው ባሻገር በአማራጭም ረገድ ብዙ ባለሙያ ባለማግኘት ይቸገሩ ነበር» ይላል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ሥራ ወይም መስሪያ ቤት ለመቀየርና የተሻለ ቦታ ተወዳድሮ ለመቀጠር የሚፈልግ በርካታ ሠራተኞች ቢኖርም በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙት መስሪያ ቤቶች ስላወጡት መረጃ ለማግኘት ይቸገር እንደነበር ያስታውሳል፡፡ «አጋጥሞት የሚመዘገበውም ማስታወቂያ ያወጣው ተቋም ውስጥ ዘመድ ወይ ጓደኛ ያለው ብቻ በመሆኑ የዜጎችን ዕኩል የመሳተፍ ዕድል የማያረጋግጥበት ሁኔታ ነበር» በማለትም አቶ ነጋሲ ይናገራል፡፡
ከዚህም ባሻገር ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የተለመደው በየጎዳናና በየመንገዱ ማስታወቂያ መለጠፍ ተግባር የከተማዋን ገፅታ እያጠፋ የነበረ ከመሆኑም በላይ ጠቃሚ ማስታወቂያዎች ተገቢው ሰው ሳያነባቸው ተቀደው የሚነሱበት ሁኔታ መኖሩን ተረዳ፡፡
እነዚህ ሁኔታዎችም በመጀመሪያ ላይ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀስ ማስታወቂያ ቦርድ በመስራት አገልግሎት እየሰጡ ቆየ። ዛሬ ላይ ግን ያ ተሽከርካሪ የማስታወቂያ ሰሌዳ አድርጎ አራት ኪሎ ጆሊ ባር አካባቢና ፒያሳ አደባባይ ያለውን ጨምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አስር የህዝብ ማስታወቂያ ቦርዶች ማዘጋጀት ቻለ፡፡ እነዚህ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች ታዲያ ለድርጅቱ የገቢ ምንጭ ከመፍጠራቸው ባሻገር የከተማዋንም ችግር በተወሰነ መልኩ የቀረፈ ምስጉን ተግባር መፈፀሙን ብዙዎች እንደሚመሰክሩለት አጫው ቶናል፡፡
እንደ አቶ ነጋሲ ማብራሪያ፤ ቦርዶቹን የተጠቀሙ ተቋማት በቂ የተወዳዳሪ አማራጮችን እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ ድርጅቱ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት መሠረትም ቦርዶቹ ከቆሙ ጀምሮ በተለያዩ ተቋማት ለተቀጠሩ ከ1ነጥብ5 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ሥራ ፈላጊዎች የመረጃ ምንጭ በመሆን የሰጡት ማህበራዊ አገልግሎት ቦርዶቹ ለእርሳቸውና ለድርጅታቸው ከሚያስገኙት ገቢ አንፃር ብዙ እጥፍ የበለጠ ነው፡፡
ሥራ ፈጣሪው ይህ የንግድ ሰው የሥራ ዘርፉን ይበልጥ ያሳድግለት ዘንዳም በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን የመጀመሪያ ዲግሪውን የተማረ ሲሆን የተለያዩ ስልጠናዎችን ወስዷል። በአሁኑ ወቅት ከአራት በላይ የሆኑ የንግድ ስራዎችን ተጓዳኝና ተመጋጋቢ በሆነ መልኩ በአንድ ማዕቀፍ አቋቁሞ ለመምራትና አጣጥሞ ለማስኬድ ደፋ ቀና በማለት ላይ ይገኛል፡፡ በስልጠና ማዕከሉ እና በሌሎች ድርጅቶቹ ሁለት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ካፒታል በማንቀሳቀስ ላይ መሆኑን ይገልጻል።
እሱ እና ጓደኞቹ ይህንን ድርጅት ባቋቁመበት መጀመሪያ ዓመታት ለአዳ ዲስ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ስራዎች ያለው አመለካከት እንደዛሬው የዳበረ ባለመሆኑ ብዙ ወጪ በማፍሰስ የሰሯቸው በርካታ ስራዎች በማህበረሰቡም ሆነ በተጠቃሚዎች ዘንድ ተቀባይነትን አግኝተው ገበያ ውስጥ እንዲገቡ ለማድረግ የገጠማቸው ችግር ከፍተኛ እንደነበርም ያስታውሳል፡፡
በተለይ ተቀማጭ ካፒታል አስቀርተው መንቀ ሳቀስ የሚችሉበት አቅም ሳይኖራቸው ባላ ቸው ዓላማ ፅናት ራሳቸው ኃላፊነት ወስደው የሰሯቸው ስራዎች ካፒታሉን ይዘው እየተቀመጡ ምርቶቹን ማስተ ዋወቅና ገበያ ማፈላለግ ላይ ረጅም ጊዜ እንዲያባክኑ ያስገደዳቸው መሆኑን ያመለክታል፡፡
እንቅስቃሴያቸው ከጅማሬው አንስቶ ተስፋ አስቆራጭ በሆኑና የማይ ታለፉ በሚመስሉ ፈታኝ ሁኔታዎች የተሞላ ነበር፡፡ «እያንዳንዳችን ውስጥ የነበረና በስራ ሂደት ውስጥ በቆየን ቁጥር ሳናውቀው እየጎለበተ የሚሄድ ጥንካሬና በራስ ላይ የሚፈጠር እምነት ማዳበር ቻልን» የሚለው አቶ ነጋሲ ውጣ ውረድ የበዛው ረጅም የንግድ ቆይታ ውስጥ ያገኙት ተሞክሮ በገንዘብ የማይተመን መሆኑን ነው የሚያነሳው።
«ሁሉም ሰው ስለራሱና በዙሪ ያው ስላለው ነገር የሚከተለውና የሚያራምደው አስተሳሰብ ውጤት ይለያየዋል እንጂ ምንም ነገር የሌለው ማንም ሰው የለም” የሚል የህይወት መርህ እንደሚከተል አቶ ነጋሲ ይገልፃል፡፡ የዓላማ ፅናት፣ ሥራ ወዳድ ባህሪ፣ ታታሪነትና ሥራ አለመናቅ በዛሬ ስኬታቸው ላይ የማይናቅ አሻራ እንዳለው የሚያምን መሆኑንና የስኬቱ ቁልፍ ሚስጥር እንደሆነም ያስረዳል።
ይህንንም ሀሳብ ሲያጠናክር ከልጅነቱ ጀምሮ ህይወቱን የተሻለ ከፈጣሪ የተሰጠ ስጦታ እንዳለው መረዳቱም ያጋጠሙን ችግሮች በፅናት እንዲያልፍ አቅም ፈጥሮለታል፡፡ ዛሬ ላይም ባቋቋማቸው ድርጅቶች ውስጥ በቋሚነትና በጊዜያ ዊነት ለሚሰሩት 20 ሠራተኞች አርዓያ በመሆኑን እነሱም የራሳቸውን ድርጅት እንዲከፍቱ ለሌሎችም ዓይን መገለጫ እንዲሆኑ የሚያበረታታቸው መሆኑን ነው ያመለከተው፡፡
ለፈጠራ ሥራ ካለው ጥልቅ ፍቅር የተነሳ ያቋቋማቸው ድርጅቶች ከሚያገኙት ገቢ በላይ ለማህበረሰብና ሀገራዊ ችግሮች መፍትሔ መስጠት ልዩ ደስታ እንደሚሰጠው የሚገልፀው አቶ ነጋሲ፤ በተለይም የሰዎችን መቸገር አይቶ በቀናነት ሰዎችን መርዳትን እንደሚመርጥ ይናገራል፡፡
በዋናነት ደግሞ ሳይማሩም ሆነ ተምረው የህይወት በር አንድ አማራጭ ብቻ አድርገው የሚኖሩ ወጣቶች ካሉበት የቁዘማ ህይወት እንዲላቀቁ የበኩሉን ምክረ ሃሳብ በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 22/2011
አንዳርጋቸው ምንዳ