የሰው ልጅ በፍጥረቱ የብዙ አቅሞች /ክፍሎቶች ባለቤት ነው ። ይህ ደግሞ በግላዊም ሆነ በማኅበራዊ ሕይወቱ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን አሸንፎ መሻገር የሚያስችለው፤ በዘመናት መካከል ያጋጠሙትን ፈተናዎች አልፎ አሁን ላይ ላይ ለደረሰበት ሁለንተናዊ ዕድገት ትልቅ አቅም ነው።
እነዚህ አቅሞቹ በየዘመኑ የይቻላል መንፈስን በመፍጠር ፣ ዓለም ዛሬ ላይ ለደረሰችበት ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ሕይወት ፤ ከዚያም አልፎ የቴክኖሎጂ ምጥቀት ትልቅ ድርሻ አበርክቷል። በመጪዎቹ የሕይወት ዘመኑ ሊያሳካቸው የሚያስባቸው የላቁ ፍላጎቶቹም እውን የሚሆኑት በዚሁ የይቻላል መንፈስ ነው።
እንድ ማኅበረሰብ/ ሕዝብ እንደ ማኅበረሰብ ዛሬ ላይ የሚያጋጥሙትን ችግሮች ተሻግሮ ነገዎችን የተሻሉ እና ብሩህ ማድረግ የሚችለው ፤ በሠብዓዊ ማንነቱ ውስጥ ያሉ ክሒሎቶቹን አቀናጅቶ በይቻላል መንፈስ መንቀሳቀስ ሲችል እንደሆነም ይታመናል። ስለዚህ ነገር ሰፋፊ ዓለም አቀፍ ትርክቶችን በማሳያነት ማቅረብ ይቻላል።
ዓለምን በዋነኛነት የለወጡ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እሳቤዎችም ሆኑ የቴክኖሎጂ እና የምርምር ግኝቶች መነሻቸው በግለሰቦች ውስጥ ያሉ ክሒሎቶች በይቻላል መንፈስ ተነቃቅተው እንደሆነ የታሪክ ማህደራት ይመሰክራሉ። እነዚህ እሳቤዎች እና ግኝቶች ጅማሬያቸው ግለሰባዊ ቢሆንም ፍጻሜያቸው ግን ማኅበረሰብን ከአንድ የታሪክ ምዕራፍ ወደ ሌላ ማሻገር ያስቻለ ነው።
በአንደኛውም ሆነ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በብዙ አስቸጋሪ ተስፋ አስቆራጭ መፈራረስ/ የልብ ስብራት ውስጥ የነበሩ ሀገራት እና ሕዝቦች ፤ ከጦርነት ፍርስራሽ ውስጥ ወጥተው ዛሬ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የደረሱበት ልዕልና ላይ መድረስ የቻሉት የይቻላል መንፈስ በፈጠረው ማኅበረሰባዊ መነቃቃት ስለመሆኑ ብዙም ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም።
እኛም ብንሆን እንደ አንድ ትልቅ ማኅበረሰብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሞገስና ክብር ያጎናጸፈን የዓድዋ ጦርነት ፤ በዘመኑ በነበረው የኃይል አሰላለፍ ሆነ ማኅበረሰባዊ የአቅም ልኬት ባለድል የመሆናችን እውነታ ለመላው ዓለም የሚታሰብ አልነበረም። እንደ ማኅበረሰብ ከኃይል አሰላለፋችን በላይ በእኛ ውስጥ የነበረው የይቻላል መንፈስ ክስተቱን አስገራሚ፣ አስደማሚ እና ታሪካዊ አድርጎታል።
አሁን ላይ ትውልዱ ወደ ፍጻሜ እያደረሰው ያለው የታላቁ ህዳሴ /የዓባይ ግድብ እውነታም ከዚህ የተለየ አይደለም ፣ የይቻላል መንፈስ በፈጠረው መነቃቃት ተጀምሮ እየተጓዘ ያለ ፣ ከአይቻልም ቁዘማ ወጥቶ ይቻላል ብሎ የማሰብና በቁርጠኝነት የመንቀሳቀስ ማኅበረሰባዊ ንቅናቄ ትሩፋታችን ነው።
ዛሬም እንደ አንድ በታሪክ ቄጭት ውስጥ እንዳለ ማኅበረሰብ ከፍ ባለ ድምጽ ድህነትን ታሪክ እናደርጋለን ፤ ወደ ቀደመው የታሪክ ከፍተታችን እንመለሳለን ስንል ፣ በውስጣችን በዘመናት ሂደት ውስጥ አድጎ ዛሬ ላይ የደረሰው ማኅበረሰባዊ የይቻላል መንፈስ በፈጠረው መነቃቃት ፤ መነቃቃቱ በፈጠረው መሻት ነው። ድንገት የተከሰተ ፤የሁኔታዎች መገጣጠም የፈጠረው አይደለም።
እኛ ኢትዮጵያውያን የብዙ ታሪክ ፤የብዙ ባህል እና ሥልጣኔ ባለቤት የሆንን ሕዝቦች ነን። የቀደሙት ሥልጣኔዎቻችን ዛሬም ዓለምን የሚስደምሙት እና የሚያስደንቁት ፤ ለእኛም ሞገስ እና ክብር የሆኑት የአባቶቻችን ከፍ ያለ የይቻላል መንፈስ እና ቁርጠኝነት በፈጠረው ድካም እና ልፋት ነው።
ወቅቱ /ዘመኑ በአይቻልም መንፈስ ፤ መንፈሱ በሚፈጥረው ቁዘማ ያስበላናቸውን ዘመናት የምንክስበት ፤ ማህበረሰባዊ የይቻላል መንፈሳችንን የምናድስበት ፤ በታደሰ መንፈስ በርግጥም ያሰብነውን ፤ ያቀድነውን እና ተስፋ ያደረግነውን ተጨባጭ አድርገን ፤ የመሆን መሻታችንን እውን የምናደርግበት ነው።
ለዚህ ደግሞ በአይቻልም መንፈስ አቧራ የሸፈናቸውን ግለሰባዊ እና ማኅበረሰባዊ ክሒሎቶችን፤ በይቻላል መንፈስ ማደስና ሀገራዊ ሞገስ የሆኑንን የቀደሙ እና አሁናዊ ትርክቶቻችንን ለትውልዱ የይቻላል መንፈስ አቅም እንዲሆኑ መቀመር እና መሥራት ፤ ይጠበቅብናል !
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 22 ቀን 2016 ዓ.ም