አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች ለኢንቨስትመንት አገልግሎት በሚል ለዓመታት በግል ባለሃብቶች ታጥረው የቆዩ ቦታዎችን ውል በማቋረጥ በጊዜያዊ ውሳኔ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ መጀመሩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ባንክ፣ አስተዳደርና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የጽሕፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ጥላሁን በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ በከተማዋ ውስጥ የሚታየውን የመኪና ማቆሚያ ችግር በጊዜያዊነት ለመፍታትና በፓርኪንግ አገልግሎት የከተማዋን ወጣቶች ተጠቃሚ ለማድረግ በጊዜያዊ ውሳኔ ቦታዎቹ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ ነው፡፡
በከተማዋ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ጥቅም ሳይሰጡ ታጥረው ከተቀመጡ ቦታዎች ውስጥ ሜክሲኮ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ጎን የሚገኘው ቦታ አንዱ መሆኑን የጠቀሱት ሥራ አስኪያጁ፤ ቦታው በከተማዋ ማስተር ፕላን መሰረት በቀጣይ አገልግሎት አስኪሰጥ ድረስ ለሸገር ብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት አውቶብሶች ማቆሚያና ማሳደሪያነት በጊዜያዊ ውሳኔ ጥቅም ላይ እንዲውል መደረጉን ገልፀዋል፡፡ቦታው ለእዚህ አገልግሎት ዝግጁ መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡
በሌሎች የከተማዋ አካባቢዎች በተለይም በአቃቂ ክፍለ ከተማ ለረጅም ጊዜ ታጥረው የቆዩ ሰፋፊ ቦታዎችን ለማስለቀቅ ጥናቶች መጀመራቸውን ሥራ አስኪያጁ ጠቅሰው፣ ተመሳሳይ እርምጃዎችን በመውሰድ የተያዙት ቦታዎች ለጋራ አገልግሎት እንዲውሉ ከክፍለ ከተማው ጋር ውይይቶች እየተካሄዱ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡ አራት ኪሎ ፊት በር አካባቢ (ቤተመንግሥት ፊት ለፊት) ታጥሮ የቆየው ሰፊ ቦታም በመንግሥት አልሚነት ከቤተመንግሥቱ ጋር በሚጣጣም መልኩ ለአረንጓዴ ልማት እንደሚውል አስታውቀዋል፡፡
የሸገር ብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ አዳነ አብደታ በበኩላቸው ድርጅቱ አዲስ በመሆኑና የመኪና ማሳደሪያ እንደሌለው ጠቅሰው፣ በአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ድጋፍ በጊዜያዊነት ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ጎን የሚገኘውን ቦታ ለእዚህ አገልግሎት ማግኘቱን አስታውቀዋል፡፡
ጽሕፈት ቤቱ በቦታው ላይ የመሬት ስር የመኪና ማቆሚያ አገልግሎት ለመገንባት የያዘውን እቅድ እስኪጀመር ቦታው ለአውቶብሶች ማቆሚያና ማሳደሪያነት ጥቅም ላይ እንደሚውል ተናግረዋል፡፡
እንደ ምክትል ሥራ አስኪያጁ ገለፃ ፤ድርጅቱ አውቶብሶችን የሚያቆምበትና የሚያሳድርበት አልነበረውም፡፡በአሁኑ ወቅት በጊዜያዊነት በተፈቀደለት ቦታ ቀለል ያሉ የአውቶብሶች ጥገናዎችንና እጥበቶችን ለማካሄድ ይረዳዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ድርጅቱ ለህዝቡ የሚሰጠው የትራንስፖርት አገልግሎት እንዳይስተጓጎል ትልቅ እገዛ ይኖረዋል፡፡
በቅርቡ በከተማዋ በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ለረጅም ጊዜያት ታጥረው የቆዩ ቦታዎችን ውል በማቋረጥ አጥራቸው እንዲፈርስ መደረጉ ይታወቃል፡፡በቀጣይ ቦታዎቹ የከተማው ማስተር ፕላን በሚያዘው መሰረት ለተለያዩ የህዝብ አገልግሎቶች አስኪውሉ ድረስ በጊዜያዊነት ለተለያዩ አገልግሎቶች እንዲውሉ ይደረግ የሚሉ አስተያየቶች በተለያዩ መድረኮች ላይ ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡
አስናቀ ፀጋዬ