ኢትዮጵያ እምቅ የሆነ ያልተካ የምድር ውስጥ በረከት ያላት ሀገር ነች።ይሁን እንጂ ለዘመናት ያህል የተፈጥሮ ፀጋዋን ሳትጠቀምበት ኖራለች።ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ማዕድን ከግብርና ቀጥሎ የኢትዮጵያን ብልጽግና እንደሚያረጋግጥ ታምኖበት በብዙ ተግዳሮቶችም ውስጥ ቢሆን ውጤት ለማምጣት እየተሰራ ነው።
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም የማዕድን ዘርፉ የገጠሙትን ፈተናዎች፣ ፈተናውን ለመሻገር የተሰሩ ሥራዎች፣ ዘርፉ በአሁኑ ወቅት የሚገኝበትን ደረጃ እና ቀጣይ ሥራዎች በተመለከተ ከማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ ጋር ቆይታ አድርጓል። መልካም ንባብ።
አዲስዘመን፤ የማዕድን ዘርፉ እንደ ሀገር ከተመረጡ አምስት ዋና ዋና ዘርፎች ውስጥ አንዱ መሆኑ ይታወቃል። የዘርፉ አስተዋጽኦ እንዴት ይገለጻል? እስካሁን ዘርፉ እንደሀገር ያመጣውን አበርክቶ ቢያብራሩልን።
አቶ ሚሊዮን፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለረጅም አመታት በአንድ ዘርፍ ላይ ተንጠልጥሎ የቆየ መሆኑ ይታወሳል። አሁን ላይ ግን የብዝሐ ዘርፍ ኢኮኖሚ እንደሚያስፈልግ በመንግሥት በኩል እምነት በመያዙ ካለፉት አራትና አምስት አመታት ጀምሮ የተለያዩ የኢኮኖሚ ሴክተሮችን ለማልማት ጥረት በመደረግ ላይ ነው።
ከዚህ በፊት ትኩረት ያላገኙ ዘርፎች ትኩረት እንዲያገኙ ተደርጎ ብዝሐ ዘርፍ የኢኮኖሚ ልማትን እየተከተልን እንገኛለን። ከዚህ አንፃር ከአምስቱ ዘርፎች አንዱ የማዕድን ዘርፍ ይጠቀሳል። በሚቀጥሉት አስር አመታትም ኢትዮጵያ ለምታስበው አጠቃላይ የልማትና የብልጽግና ጉዞ ዘርፉ ሀብት በመፍጠርና ለሌሎች የልማት ዘርፎችም ሀብት በማመንጨት እንዲያገለግል ነው የሚጠበቀው።
ኢትዮጵያ በጣም ትልቅ ሀገር ናት። አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ስኩዌር ካሬ ሜትር የቆዳ ስፋት አላት። እስካሁን ባለው መረጃ በብዙ ሀገሮች አንድ ወይንም ሁለት አይነት የአለት መአድን ነው የሚገኘው። እንደ መታደል ሆኖ ግን ኢትዮጵያ ሶስቱም አይነቶች ነው ያሏት። ከሳተጎመራ የሚፈጠረው ቮልካኒክ፣ በመሸርሸር ሂደት ደግሞ ከብዙ ሚሊዮን አመታት በኋላ እንደገና ሴዲመንታሪ ወይንም ንብርብር የሚባለው አለት አይነት ይፈጠራል።
ሌላው ደግሞ በሙቀት ግፊት የሚፈጠረው ሞታሞርፊክ የሚባለው አለት ነው። በዚህ መነሻም ኢትዮጵያ ከከበሩ ማዕድናት ጀምሮ ለግንባታ፣ለኤሌክትሪክ ኃይል፣ ለግብርና፣ ለኢንደስትሪ፣ ለተለያዩ አገልግሎቶች ግብአት ሆነው የሚያገለግሉ ከጋዝ እስከ ጂኦተርማል ድረስ ለሀገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ የተለያዩ የማዕድን ሀብቶች ያላት ሀገር ናት። ከዚህ አንጻር ለሀገር ተጨማሪ ሀብት ለመፍጠር የማዕድን ዘርፉ ወደፊት እንዲመጣ መደረጉ ትክክለኛ እይታ ነው።
በሚቀጥሉት አመታትም ብዙ ተግባራትን ማከናወን ይጠበቃል። ዘርፉ የፍለጋና የልማት ምዕራፎች አሉት። የፍለጋ ምዕራፍ ረዘም ያለ ጊዜ ይወስዳል። የሚወስደው ጊዜም አስር አመትና ከዚያም በላይ ሊሆን ይችላል። በፍለጋው የሥራ ሂደት የኢኮኖሚ አዋጭነቱ ከተረጋገጠ በኃላ ነው ሥራው ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ የሚሸጋገረው።
በፍለጋው ሥራ ላለፉት አመታት በተከናወኑት ሥራዎች ወደ ልማት ምዕራፍ የተሸጋገሩ አሉ። ወደልማት ሊቀየሩ የሚችሉ እድሎች እንዳሉም ማረጋገጥ ተችሏል። ከዚህ አንጻር በወርቅ፣ በጂኦተርማል፣ በፖታሽ፣ ጭምር ወደሀብትነት የሚቀየሩ ትልልቅ እድሎች ናቸው በእጃችን የሚገኙት።
የማዕድን ዘርፉ ወደፊት ሲመጣ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ላይ የሚያስከትለው ተግዳሮት ደግሞ አለ። መንግሥት ጠንከር ብሎ ሰላምና ፀጥታን ማስከበር ካልቻለ ዘርፉ ለፀጥታ ስጋት ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ይሄን ተቋቁመው ያላቸውን የማዕድን ሀብት ተጠቅመው የለሙ ሀገራት አሉ።
በኢትዮጵያ በኩልም ቢሆን ከሚኒስቴር መሥሪያቤቱ ጀምሮ የአስፈጻሚ ተቋማትን መዋቅራዊ አቅም በመፈተሽ፤ እስከ ክልል ድረስ ሊደግፍ የሚችል አሰራር ተዘርግቶ ሥራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ።
በአሁኑ ጊዜም በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈትቤት ብሄራዊ የማዕድን ልማት ምክርቤት ተቋቁሞ እየሰራ ይገኛል። ይህ ከፌዴራልና ከክልሎች የተውጣጡ አካላት የተካተቱበት ምክርቤትም በየወሩ በመገናኘት ሥራዎችን ይገመግማል። ከፀጥታ በተያያዘ እና እንደ መብራት፣ መንገድ የቴሌኮም አገልግሎት ያሉ መሠረተልማትን ከማሟላት እንዲሁም የፋይናንስና የማትጊያ ሥርዓትን ምቹ ከማድረግ አንጻር፣ ያሉትን ችግሮች በመፍታት ለልማቱ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የሚያግዝ ምክር ቤት ተቋቁሞ ስራዎች በመሰራት ላይ ናቸው።
የዘርፉን ልማት ለማፋጠንም ሆነ ለልማቱ እንቅፋት የሚሆኑትን ለመፍታት የማዕድን ሚኒስቴር ከሚደርገው ጥረት ጎን ለጎን በርካራ አካላትም አጋዥ ሆነው እየሰሩ ነው።ችግሮችን መፍታት የሚቻለው በቅንጅት መስራት ሲቻል በመሆኑ በፌዴራል የሚፈታውን በፌዴራል፤ ክልሎችም የየራሳቸውን ሚና በመውሰድ የበኩላቸውን ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።በመወጣት ድርሻቸውን ይወስዳሉ። ይህም በመሆኑ ጠንከር ያለ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ በመሆኑ በኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፉ አዲስ እድል እና ተጨማሪ ሀብት ይዞ እየመጣ ነው።
በአሁኑ ጊዜም የወርቅ ማዕድን ልማቱን የሚያፋጥኑ የትላልቅ ኩባንያዎች ግንባታም በመከናወን ላይ ይገኛል። ለምሳሌ፤ የፋይናንስ ድጋፍ አግኝተው ወደ ግንባታ ሥራ ከገቡት መካከልም በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ቱሉካፔ አካባቢ የተጀመረው ግንባታ ይጠቀሳል። ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኩሙሩክ የግንባታ ቁሳቁስ እየተጓጓዘ ነው። በኩሙሩክ የሚገነባው በኢትዮጵያ ትልቁ የወርቅ ፋብሪካ ሲሆን፣ በየአመቱም ዘጠኝ ቶን ወርቅ የማምረት አቅም ይኖረዋል። ይህ ፋብሪካ ኢትዮጵያ እስከዛሬ በባህላዊም ሆነ በተለያየ መልክ ስታመርት የነበረውን ወርቅ አንድ ፋብሪካ ብቻውን ያመርታል ማለት ነው።
ይሄ ለኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ ነው። አዲስ ሀብትም ይዞ ነው የመጣው። የወርቅ ፋብሪካውን ግንባታ በአንድ አመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ነው የታቀደው። ጋምቤላ ክልል ከሁለት ወር በኋላ ሥራ የሚጀምር ፋብሪካ ግንባታ ተጠናቅቋል። ትግራይ ክልልም ወደ ግንባታ ለመግባት ቅድመ ሁኔታዎች እየተመቻቹ ነው።
በሌሎች የማዕድን ዘርፎች ላይም እንዲሁ እየተሰራ ነው። በጥቂት ወራት የሚመረቀው ሰሜንሸዋ በለሚ አካባቢ የተገነባው ሲሚንቶ ፋብሪካ ከ30 እስከ 40 በመቶ የሲሚንቶ አቅርቦት ፍላጎትን ለመሸፈን የሚያስችል ነው። በአጠቃላይ እየተከናወነ ያለው ሥራ የኢትዮጵያን ኢንዱስትሪና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚወስኑ ትላልቅ አቅሞች ናቸው። ለግብርናው ግብአት የሚውል ማዳበሪያም እንዲሁ የማዕድን ዘርፉ አበርክቶ እንዲኖረው እየተሰራ ነው።
በማዕድን ዘርፉ የሚያጓጉ እድሎች ናቸው ያሉት። የማዕድን ፍለጋው ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድና ከፍተኛ ካፒታልም የሚጠይቅ ቢሆንም፤ በፍለጋ ሂደት ሀብቱ ተገኝቶ ወደ ምርት ሊሸጋገሩ ያሉ ትልልቅ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ሊወስኑ የሚችሉ የልማት አውታሮችን ለመገንባት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።በዚህ ሁኔታ ተጠናክሮ የማዕድን ልማቱ ከቀጠለ ከአስር አመቱ የልማት እቅድ በፊት ቀድሞ ለኢንደስትሪውም ሆነ ለግብርናው ዘርፍ የሚሆን ሀብት ማመንጨት ይቻላል። ይህን ለማሳካትም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈትቤት የተቋቋመው ብሄራዊ የማዕድን ምክርቤት ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው።
በአስር ወራት ከአጠቃላይ የማዕድን ልማት ዘርፍ ወደ አራት መቶ ሃያስምንት ሚሊዮን ዶላር (428ሚሊዮን ዶላር) ገቢ ለማግኘት አቅደን እየተንቀሳቀስን ነው። ከዚህ ውስጥም ወደ 3ሚሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት ተችሏል።ይህ በመቶኛ ሲሰላ 75 በመቶ ይደርሳል። ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻፀርም ብልጫ ያለው አፈፃፀም ነው የተመዘገበው።
ይሄ ውጤት የተገኘው በአንድ ሚኒስቴር መስሪያቤት ብቻ ሳይሆን፣ ደጋፊ አደረጃጀት በመፈጠሩና ሥራዎችም በየወሩ በመገምገማቸው ጭምር ነው። ስለዚህ ትክክለኛውን መስመር ይዘን ነው እየተጓዝን ያለነው። የበለጠ ውጤታማ ለመሆን የመሠረተልማት አቅርቦት ወሳኝ ነው።በዚህ ረገድም በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የማዕድን ዘርፉ ባለፉት ጥቂት አመታት በህገወጥ አዘዋዋሪዎች፣ በግብይት ችግር ፣ በፀጥታና ተያያዥ ጉዳዮች ፈተና ውስጥ እንደነበር ይታወቃል። ፈተናዎቹን እንዴት መሻገር ተቻለ?
አቶ ሚሊዮን፤ በጣም መሠረታዊ ጥያቄ ነው። በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ባለፉት አመታት በዘርፉ ላይ ያጋጠሙት ተግዳሮቶች በሌሎች አፍሪካ ሀገራትም በተመሳሳይ የሚያጋጥሙ ናቸው። የወርቅ ልማቱ ለዘመናት በባህላዊ መንገድ ነው ሲመረት የቆየው። የአመራረት ሥርዓቱን ለማዘመን ጥረቶች እየተደረጉና የተሻለ ገቢም እየተገኘ ባለበት በዚህ ወቅት ልማቱ ላይ የመሰማራት ፍላጎቱ እየጨመረ መጥቷል። በህገወጥ ድርጊት ውስጥ የታጠቁ ኃይሎች ጭምር ናቸው ሲሳተፉ የነበረው። ህገወጥነት በመስፋፋቱ ይሄን የማስተካከል ሥራ ለመሥራት ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። እስካሁን ድረስ በፋብሪካ ደረጃ ወርቅ እያመረተ ያለው ሜድሮክ ኩባንያ ብቻ ነው። ብሄራዊ የማዕድን ምክርቤት ለማቋቋም ምክንያት የሆነውም አንዱ እንዲህ ያለውን የህገወጥ ተግባርን ለመከላከል ነው።
ሌላው ችግሩን ለመሻገር የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ ምን ይመስላል የሚለውን ማየት ነበር። ችግሮቹን ነቅሶ በመለየት ወደ መፍትሄ መግባትም አቅጣጫ ተወስዷል።የማዕድን ዘርፉ በጣም ሩቅ በሆነ አካባቢ የሚገኝ በመሆኑ ከፍተኛ የፀጥታ ኃይሎችን ማሰማራት ይጠይቃል። የፖለቲካ አመራሩንና ማህበረሰቡን ማሳተፍ የግድ ይላል። ይህን ሁሉ ግምት ውስጥ በማስገባት በየጊዜው ያልተቆራረጠ ድጋፍ እንደሚያስፈልግና ሥርዓት ውስጥም መግባት እንዳለበት ታሳቢ ተደርጎ ነው እየተሰራ ያለው። በዚህ መልኩ ነው ያጋጠሙትንም ሆነ የሚያጋጥሙትን ችግሮች ለመቀልበስ ጥረት ሲያደረገት ቆይቷል። ይህ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
አዲስ ዘመን፡- ብሄራዊ የማዕድን ምክርቤቱ እስካሁን ባከናወናቸው ተግባራት በተጨባጭ ምን ውጤቶች አስገኘ?
አቶሚሊዮን፡- የክልል ምክትል ፕሬዚዳንቶች የምክርቤቱ አባላት ናቸው። ምክርቤቱ የሚገመግማቸው ሁሉ በክልሎችም አጀንዳ ሆነው ይነሳሉ። በመሆኑም ተመሳሳይ መድረኮችን ፈጥረው ሥራው እስከታች እንዲወርድ በማድረግ ህገወጦችን የመከላከሉንና ሥርዓት የማስያዙን ተልዕኮ ይወጣሉ።
ሥርዓት ማስያዝ ያስፈልጋል የሚል አቋም በመንግሥት ደረጃ ከላይ እስከታች እየተያዘ ሲመጣ ተጠያቂነትን የሚያስከትል መሆኑ፤ በየደረጃው ችግሮች እየተስተካከሉ መጥተዋል። ሚኒስቴር መስሪያቤቱ በአንድ ክልል ላይ ከሚያሳድረው ተጽዕኖ ይልቅ ምክቤቱ በተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኙ አካላትን ያቀፈ በመሆኑ አንድ ላይ መጥተው የሚያስፈጽሙት የተሻለ ይሆናል። እያንዳንዱ የሰራውን ሥራ በተጠያቂነት ነው የሚፈጽመው። በዚህ መልኩ እየተከናወነ ያለው ሥራ ለማዕድን ዘርፉ ትልቅ አቅም መፍጠር ችሏል ።
አዲስዘመን፡- በአጠቃላይ አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ከማዕድን ዘርፉ ምን እንጠብቅ?
አቶ ሚሊዮን፤ ቤንሻንጉል፣ ወለጋ፣ ጉጂ፣ ጋምቤላ፣ ትግራይ፣ አማራ ውስጥ በርካታ የማዕድን ሃብቶች አሉ። ትላልቅ የሚባሉ ባለሀብቶችንም ወደ ዘርፉ ለመሳብ እየተሞከረ ነው። አስቸጋሪ የሚባሉ ምዕራፎች አልፈን አስተማማኝ የሆነ ምፍ ላይ ነው የምንገኘው። እነዚህን ምቹ ሁኔታዎች በመጠቀም አምስት ስድስት ፋብሪካዎች ላይ ብቻ ጠንከር ያለ ሥራ መሥራት ከተቻለ፤ ውጤታማ መሆን ይቻላል። ኢትዮጵያ እንደ ኦፓል ያሉ በዓለም ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የሚፈለጉ የማዕድን ሀብት ያላት ናት። ከዓለም የኢነርጂ ፍላጎት ሽግግር ጋርም ጋር በማስተሳሰር ሥራዎች እየተሰሩ በመሆኑ ውጤቱ ለሀገር የሚበቃ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ በዘርፉ ፍላጎት እያሳዩ ያሉት ኩባንያዎች የትኞቹ ናቸው? በምን ያህል መጠንስ መሳብ ተችሏል? የኩባንያዎቹ ፍላጎት ልማቱ ላይ ወይንስ ፍለጋው ላይ የሚለውንም አክለው ቢገልጹልን?
አቶ ሚሊዮን፡- የካናዳ፣ የአሜሪካን፣ የእንግሊዝ፣ የኖርዌይ፣ አውስትራሊያ፣ ቻይና፣ህንድ፣ በአጠቃላይ ከምዕራብም ከምሥራቅም ትላልቅ የሚባሉ ኩባንያዎች ናቸው በኢትዮጵያ ማዕድን በማልማት ላይ የተሰማሩት። ኩባንያዎቹ ከፍለጋ አልፈው ወደ ግንባታ ምዕራፍ የተሸጋገሩ ናቸው።
የአብዛኞቹ ኩባንያዎች ፍላጎት በፍለጋ የተረጋገጠ ሀብት ላይ መሰማራት ነው። በርካቶቹ እየተሰማሩ ያሉት ከሶስት አመት እስከ 15 አመት የፍለጋ ምዕራፋቸው ተጠናቅቆ የመጨረሻ ደረጃ የደረሱትን የማዕድን ዘርፎች ላይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በማዕድን ዘርፍ በተግዳሮት ከሚነሱት አንዱ ለአካባቢ ጥበቃና የአካባቢ ማህበረሰብን ተጠቃሚ ከማድረግ ጋር ያለው ክፍተት ነው። በዚህ በኩል ያለውን ሁኔታ ቢገልጹልን?
አቶ ሚሊዮን፡– ልማቱ የአካባቢን ማህበረሰብ ካላቀፈና ተጠቃሚ ካላደረገ ዘላቂነት አይኖረውም። ይሄ በህግም ጭምር የተደነገገ ነው። የማህበረሰብ ልማት ፈንድ አለ። ከአካባቢውም ሮያሊቲ ይሰበሰባል። ለክልል ነው ፈሰስ የሚደረገው። የማዕድን ፍለጋም ሲከናወን የመሬት ግብር ክፍያ ይፈፀማል። ወደ ማልማት ሥራ ሲገባ ደግሞ ከፍተኛ ግብር ነው የሚከፈለው።
በአጠቃላይ የአካባቢውን ማህበረሰብ ሊደግፉ የሚችሉ ግብር፣ የአካባቢ ማህበረሰብ ፈንድ፣ ሮያሊቲ ክፍያዎች አሉ ማለት ነው። በአካባቢው ላይ የሚሰማራው አልሚ ወይንም ኩባንያ ለማህበረሰቡ ትምህርት፣ ውሃና ሌሎችንም አገልግሎት በማቅረብ ያግዛል። የአካባቢ ጥበቃን በተመለከተ በተገኘ የመቆፈሪያ መሣሪያ የመጠቀም ሁኔታ ይስተዋላል። በባለሙያም የታገዘ ባለመሆኑ ጉዳቱ ያመዝናል። የሚፈለገውን ማዕድን ለማግኘትም አላስፈላጊ የሆነ ኬሚካል የመጠቀም ሁኔታም ይኖራል። ስለዚህም እነዚህ ችግሮች በቀጣይ እየተቀረፉ ይሄዳሉ።
የማህበረሰብ ተጠቃሚነት፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ በዘርፉ የተሰማሩት ያሉባቸው የክህሎት ማነስ፣ የገበያ ትስስርና ሌሎች ክፍተቶች ተለይተው መፍትሄ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ ነው። አነስተኛ ማዕድን አምራቾችን አቅም ለማሳደግና ተጠቃሚነታቸውን ሊጨምር የሚችል ሥራ ለመሥራት ፕሮጀክት ተቀርጿል። በተጨማሪም የጌጣጌጥ ማዕድንን በተመለከተ ስትራተጅክ ዶክመንት ተዘጋጅቷል።
አዲስ ዘመን፡- ሀገሪቱ የሚያስፍልጋትን የብረት ግብዓት በሀገር ውስጥ ለመተካት እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ እንደሆነ ይታወቃል። ከዚህ አንጻር የብረት ማዕድን ክምችት ባለባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን ቢገልጹልን?
አቶ ሚሊዮን፡- የብረት ማዕድን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተለያየ መልኩ ነው የሚገኘው። ትግራት ክልል ሽሬ፣ አማራ ክልል ሰቆጣ፣ መካነሰላም፣ ወለጋ ቢቅላል፣ ጋምቤላ ጉጂ አካባቢዎች ከፍተኛ የሆነ የብረት ክምችት አለ።
የብረት ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ ባለሀባቶቹ ባይሰሩ እንኳን በራስ አቅም እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚያስፈልግ እምነት ተይዟል። በሚኒስቴሩ ሥር ያለው የጂኦሎጂ ኢኒስቲትዩት ጉጂ አካባቢ የጥናት ሥራ አከናውኗል። በጥናት በተከናወነው የመለየት ሥራም አካባቢው ላይ ጥራት ያለው የብረት ክምችት መኖሩ ተረጋግጧል። በጋምቤላ ክልልም በተመሳሳይ የብረት ማዕድን ክምችት ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- የማዕድን ፍለጋ ሥራ ጊዜን የሚወስድና ከፍተኛ የገንዘብ አቅምም ይጠይቃል። እንዲህ ያለውን ችግር ለመፍታት ምን አይነት የመፍትሄ እርምጃዎች ናቸው እየተወሰዱ ያሉት?
አቶ ሚሊዮን፡– በራስ አቅም ለመንቀሳቀስ ፍላጎቱና ጥረቱ አለ። ካለው የቆዳ ስፋትና ከፍተኛ የሀብት ክምችት አንጻር ግን በመንግሥት አቅም ለማከናወን ከፍተኛ መዋዕለነዋይ ይጠይቃል። ሀብቱ ያለበትን ማመላከት ይቻላል። ሆኖም ግን ኢኮኖሚያዊ አዋጭ መሆኑን ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ሰፊ ሥራና የገንዘብ አቅም ያስፈልጋል። በመንግሥት አቅም ለይቶ ማቅረብ ቢቻል ግን የተሻለ እንደሆነ ይታመናል። እስካሁን ግን የኩባንያዎችን ብቃት መሰረት አድርገን ነው ፍለጋው እየተከናወነ ያለው ።
አዲስ ዘመን፡- የከበሩ የጌጣጌጥ ማዕድናት ገበያ ላይ አዋጭ የሚሆኑት እሴት ተጨምሮባቸው ሲቀርቡ እንደሆነ ተደጋግሞ ይነሳል።እሴት በመጨመር በኩል እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ካሉ ቢነግሩን ?
አቶ ሚሊዮን፡– እሴት ጨምሮ ለገበያ ለማቅረብ በተቻለ መጠን ጥረት እየተደረገ ነው። ግን አሁንም ገና ነው። የተጠናከረ ሥራ ያስፈልጋል። ከዩኒቨርስቲዎችና ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛዎች እንዲሁም በግላቸው ልምድ ካካበቱት ጋር በቅርበት እየሰራን እንገኛለን። እንዲህ ያለው ሥራ ህግ በማውጣትና ጫና በማሳደር ብቻ ሳይሆን፤ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራም ጎን ለጎን በማስኬድ የሚሰራ ነው። ማህበረሰቡ በቂ ግንዛቤ ሲኖረው የሚፈለገው ውጤት ላይ መድረስ ይቻላል።
አዲስ ዘመን ፡- የወርቅ ሃብታችን በበርካታ ተግዳሮቶች ውስጥ መቆቱ የሚታወስ ነው።በአሁኑ ወቅት ያለው ለውጥ ምን ይመስላል?
አቶ ሚሊዮን፡- ባለፉት ጊዜያት በወርቅ ልማቱ ላይ ከፍተኛ ፈተናዎች ነበሩ። ኮንትሮባንድ ከፍተኛው የዘርፉ ፈተና ነው የነበረው። ፍቃድ የሚሰጡት ክልሎች በመሆናቸው ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ጋር የማስተሳሰር ችግሮች ነበሩባቸው። አንዳንድ አካባቢዎች የባንክ አገልግሎት አለመኖር እንደቅሬታ የሚነሳበት ሁኔታም ነበር።እነዚህን ሁሉ ችግሮች ማስተካከል የግድ ይል ነበር።በዚህ ረገድ ቤንሻንጉል ጉሙዝ እና ጉጂ ላይ ተጨማሪ የባንክ ቅርጫፎች እንዲከፈቱ ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ እስከ አምስት ኪሎግራም ወርቅ ለሚያስገባ አልሚ 60 በመቶ ክፍያ ይፈጽማል። እየፈፀመ ያለው ክፍያ ከዓለም ገበያ ከፍ ያለ ነው። ጉድለቱን መንግሥት ነው እየሸፈነ ያለው። ይህም ሆኖ በሚፈለገው መጠን ወርቅ ወደ ባንክ እየገባ አይደለም። ህገወጥ ግብይቱም አልቆመም። ይሄን ማረም የሚቻለው፤ ቁጥጥሩን በማጠናከር ነው። ሥራም እየተሰራ ነው።ውጤቶች ይመጣሉም ብለን እናስባለን።
አዲስዘመን፤ የማዕድን ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት መቅረቡ ይታወሳል። አዋጁ አሁን በምን ደረጃ ላይ እንደሆነና አጠቃላይ የአዋጁን ይዘት ቢገልጹልን?
አቶ ሚሊዮን፡- ረቂቅ አዋጁ በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ማስተካከያ እየተደረገበት ይገኛል። በቅርብ እንደሚፀድቅ ይጠበቃል። የአዋጁ አጠቃላይ ይዘት፤ የማዕድን ሀብት በአይነትም በብዛትም በመጨመር የውጭ ምንዛሪ ግኝትን የማሳደግ ተልዕኮ ያለው ነው። ከዚህ አንጻር አዋጁ ከመንግሥት ምን ይጠበቃል የሚለውን የሚመልስና የተሻለ አቅም ያላቸውን ባለሀብቶች ለመሳብ የሚያስችል ነው።በተጨማሪም የወጭ ንግዱንም የበለጠ ለማሳደግ፣ ተኪ ምርቶችንም በሀገር ውስጥ ለመተካት፣ በአጠቃላይ ስትራቴጂክ የሆኑ ሀብቶችን ለማልማት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የሚያስችል ነው።ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ያሉ ኢንዱስትሪዎች እንዴት እንደሚመሩ፣ የፍለጋ ፍቃድም እንዴት እንደሚያገኙና ወደ ልማት እንዴት እንደሚሸጋገሩ በግልጽ ያሳያል።
አዲስ ዘመን፡- የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ያለባቸውን የኃይል አቅርቦት ችግር ለመፍታት የድንጋይ ከሰል ልማት ላይ ሥራዎች መጀመራቸው ይታወሳል። ሥራው በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አቶ ሚሊዮን፡– የድንጋይ ከሰልን ሲሚንቶ ፋብሪካዎች በስፋት የሚጠቀሙ ቢሆኑም የብረትና ሌሎች ፋብሪካዎችም ይፈልጉታል። ኢትዮጵያ ከአራት እስከ ስድስት መቶ ሚሊዮን ቶን የሚገመት የድንጋይ ከሰል ሀብት አላት። የጥራት ደረጃውን ከፍ ለማድረግ አንድ የስትራተጅክ ዶክመንት ተዘጋጅቷል።
የድንጋይ ከሰል ልማትን ከኢንደስትሪዎች ጋር እንዴት ማስተሳሰር እንደሚቻልም የሌሎች ሀገሮችን ተሞክሮ ለመቀመር ባለሙያዎች ወደ ህንድ ተልከዋል። የድንጋይ ከሰልን በሀገር ውስጥ ለመተካት እየተከናወኑ ባሉት ተግባራት እስከ 60 በመቶ በሀገር ውስጥ መተካት ተችሏል። የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ማሽን ዳውሮ ላይ ግንባታው ተጠናቅቋል። ቤንሻንጉል ጉሙዝ ላይ ቀድሞ ሥራ የጀመረ አለ። ሌሎችም በሥራ ላይ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን፡- በቆይታችን ያላነሳናቸው ነጥቦች ካሉ እድሉን ወስደው በዚሁ ብናበቃ
አቶ ሚሊዮን፡– ኢትዮጵያ በማዕድን ሀብት ፀጋ ያደላት ሀገር ናት። በፍለጋ ምዕራፍ አልፈው ወደ ልማት ምዕራፍ የተሸጋገሩትን በምናይበት ጊዜ ወደተጨባጭ ሀብት መቀየር የሚያስችሉ የልማት ምዕራፎች ላይ ነው የምንገኘው። በነዚህ የልማት ሥራዎች ተጠቃሚው ህብረተሰቡ በመሆኑ ያሉትን እድሎች ተገንዝቦ የበኩሉን ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል። አመራሩም ጠንከር ብሎ መሥራት ይጠበቅበታል በማለት ሃሳን እቋጫለሁ።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2016 ዓ.ም