ሕገወጥ ግንባታን በተገቢው መንገድ እንከላከል!

እንደ ሀገር ሕግ እና ሕጋዊነትን ለማስፈን በመንግሥት ደረጃ ከፍተኛ ጥረቶች እየተደረጉ ነው። በዚህም እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶች ተስፋ ሰጪ ቢሆኑም፣ በተለያዩ መንገዶች እና ሁኔዎች የሚፈጠሩ ሕገ ወጥነቶች ግን አሁንም ሀገር እና ሕዝብን ብዙ ዋጋ እያስከፈሉ ናቸው።

በተለይም በከተሞች አካባቢ ከሚካሄዱ ከግንባታ ጋር በተያያዘ እየተስተዋሉ ያሉ ሕገወጥነቶች ፣በሀገር ሀብት ላይ እያስከተሉት ያለው ጥፋት ከፍተኛ ነው ።በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ባለው ግንኙኑነት ላይም እየፈጠሩ ያለው አሉታዊ ተጽዕኖም በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

በየትኛውም ዓለም መንግሥት ሕግ እና ሥርዓትን የማስጠበቅ ትልቅ ኃላፊነት አለበት፤ ይህንን ኃላፊነቱን ለመወጣት አስፈላጊ ሕጎችን በማርቀቅ በሚመለከታቸው አካላት አጸድቆ ወደ ሥራ የሚገቡበትን አግባብ ያመቻቻል ።ለሕጎቹ ተፈጻሚነትን ሙሉ ኃላፊነቱን ወስዶ ባለው አቅም ይሠራል።

በተለይም በከተሞች አካባቢ የሚደረጉ የግንባታ ሥራዎች ፣ አጠቃላይ የሆነውን ቀጣይ ሀገራዊ የከተሞች ልማት ታሳቢ ባደረገ መንገድ በፕላን የሚመሩበትን የሕግ እና የአሠራር ሥርዓት ያስቀምጣል፣በተጨባጭ ተግባራዊ መሆናቸውንም በጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት ይከታተላል።

የከተሞች ልማት በጊዜ ሂደት ውስጥ የሚከናወን ከፍተኛ ሀብት የሚጠይቅ፣ ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገዎችንም ታሳቢ የሚያደርግ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን የሚያካትት ነው። በተለይም እንደኛ ባሉ ከተሞችን በሚፈልጉበት መንገድ ለመገንባት የሀብት ውስንነት ያላቸው ሀገራት ያላቸውን ውስን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም የከተሞች ልማትን በከፍተኛ ጥንቃቄ ለ መምራት ይገደዳሉ ።

በተለይም ዜጎች ባላቸው አቅም በከተሞች ልማት ውስጥ የሚሳተፉበትን ፤ለከተሞች እድገት አቅም ሆነው የሚያገለግሉበትን እድል በመፍጠር ሂደት ውስጥ የመንግሥት ኃላፊነት ከፍተኛ ነው። ይህ ኃላፊነቱ የከተሞችን ልማት ግልጽ በሆነ ፖሊሲ ከመምራት ጀምሮ፤ዜጎች የከተሞች ልማት ስትራቴጂክ አቅም የሚሆኑበትን አስቻይ ሁኔታ መፍጠርን ያካትታል።

በሀገራችን ረጅም ዘመናትን ያስቆጠሩ ብዛት ያላቸው ከተሞች ቢኖሩም ፤ለከተሞች ልማት ተገቢውን ትኩረት ባለመሰጠቱ የእድሜያቸውን ያህል ዘመናዊነት ተላብሰው ለነዋሪዎቻቸው የተሻሉ የመኖሪያ ስፍራ መሆን የቻሉ አይደሉም። ይህ እውነታ በአፍሪካ መዲናነቷ በምትታወቀው የሀገሪቱ ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባም በግልፅ የሚስተዋል ነው።

አዲስ አበባ ከመቶ ዓመት የበለጠ የእድሜ ባለጸጋ ብትሆንም ፤ከተቆረቆረችበት ጊዜ አንስቶ በተከሰቱ እና ዛሬም ድረስ በሚከሰቱ፤ እድገቷን በሚፈታተኑ ችግሮች ስትጠላለፍ ቆይታለች።

ከነዚህም ውስጥ በዋንኛነት የሚጠቀሰው የሕገ ወጥ ግንባታ ነው ። ባልተገባ መንገድ የከተማዋን ፕላን እና ነገዎች በሚፈታተን መንገድ የሚከናወኑ እነዚህ ሕገወጥ ግንባታዎች ፤ የከተማዋን ገጽታ ከማበላሸት በተጨማሪ የከተማ ውስጥ መሠረተ ልማት ግንባታዎችን በቀላሉ ለማከናወን የሚደረጉ ጥረቶችን በፈተና የተሞሉ አድርጓቸዋል።

ችግሩን ለዘለቄታው ለመቅረፍ በሚል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማ ደረጃ የደንብ ማስከበር ቢሮ ቢደራጅም፤ ቢሮው በራሱ በተለያዩ ሕገወጥ አሠራሮች ተጠላልፎ ለችግሩ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሆነበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

ያለ ከልካይ በጠራራ ፀሐይ ብዙ ሀብት ፈሶባቸው የተገነቡ ሕገወጥ ግንባታዎች ፤በጠራራ ፀሐይ ሕገወጥ ተብለው የሚፈርሱበት ሁኔታ የብዙዎችን ልብ የሰበረ፤ እንደ ሀገር የፖለቲካ አጀንዳ ሆኖ፤ ሀገርን ላልተገባ ብዙ ጥፋት የዳረገ ነው።

ሰፊ ሀብትና የሰው ኃይል እየተሳተፈበት ባለው ሕገወጥ ግንባታን የመቆጣጠር የመንግሥት ጥረት፤ በራሱ በተቆጣጣሪው ተቋም ውስጥ ባለ የተበላሸ አሠራር የተጠበቀውን ውጤት ማምጣት አልቻለም። እንዲያውም ለውጡን ለሚጻረሩ ኃይሎች የፖለቲካ አጀንዳ በመሆን በለውጡ መንፈስ ላይ ያልተገባ ጥላ እንዲያጠላ አድርጓል።

ችግሩን ዛሬም ሙሉ በሙሉ የተፈታ/የተሻገርነው አይደለም ።አሁንም በየጥጋጥጉ እና በየመንደሩ ሕገወጥ ግንባታ በእጅ መንሻ እየተካሄዱ ነው። ለዚህ ደግሞ ጠዋት ፈርሰው ማታ ላይ ተመልሰው የሚገነቡ ሕገወጥ ግንባታዎችን መመልከት በቂ ነው።

ለዘለቄታው ችግር ለመፍታት ከሁሉም በፊት፤ ደንብ አስከባሪ በስፋት ከማሰማራት እና ችግሩን ለመከላከል ከመሞከር በፊት ግልጽ እና ቀልጣፋ የግንባታ ፍቃድ አሰጣጥ መመሪያ ማውጣት እና በመመሪያው ዙሪያ ሕዝቡ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ማስቻል ያስፈልጋል።

ከዚህ ጎን ለጎን ለተሰጠው ኃላፊነት ታማኝ የሆነ ባለሙያ ማፍራት ፤ተጠያቂነትን ማስፈን የሚያስችል ጠንካራ አሠራር ማስፈን ያስፈልጋል ።ከዚህ ውጪ በራሱ ሕገወጥ የሆነ ኃይል አሰልፎ ሕገ ወጥነትን መከላከል አይቻልም። በዚህ መልኩ ሕገወጥነትን ለመከላከል የሚደረግ ጥረት እንደቀደመው ጊዜ የሕዝብን ሀብት ለጥፋት ከመዳረግ፤ በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት ከማበላሸት ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም።

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You