የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የአየር ብክለት ቁጥጥርና ክትትል ከፍተኛ ባለሙያ አቶ መሠረት አብዲሳ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ወደ ሰባት ሚሊዮን ሕዝብ በአየር ብክለት እንደሚሞት ይጠቅሳሉ።
በውጪ አየር ብክለት 4ነጥብ2 ሚሊዮን ሰዎች በየዓመቱ እንደሚሞቱ የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣውን መረጃ ጠቅሰው ያስረዳሉ። 3ነጥብ 8 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ በቤት ውስጥ በሚፈጠረው ብክለት ሕይወታቸውን እያጡ መሆናቸውንም ይጠቅሳሉ።
የአየር ብክለትን ለየት የሚያደርገው ድንበር የሌለው መሆኑ ላይ ነው የሚሉት አቶ መሠረት፣ «በአንድ ቦታ የተከሰተ ብክለት በተለያየ ቦታ ስለሚዳረስ ችግሩ በጣም ከፍተኛ ነው እንደ ውሃና ሌሎች ብክለቶች አይደለም»ሲሉ ያብራራሉ።
ለምግብ ማብሰያነት የሚያገለግለው ኤሌክትሪክ እንደሚፈለገው አለመዳረሱም የቤት ውስጥ የአየር ብክለት ችግር እንዲባባስ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው፣ ኮሚሽኑ በፀሐይ የሚሠሩ ኃይል ቆጣቢ ምድጃዎችን እስከታች ለማውረድ እየሠራ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
አንዱ ብክለት የመቀነሻ መንገድ አትክልት ማልማት መሆኑን የሚናገሩት አቶ መሠረት፣ አትክልቶች እነዚህ በካይ ጋዞችን ወደ ራሳቸው ይወስዱና ለእኛ ደግሞ እኛ የምንፈልገውንና የምንተነፍሰውን አየር ይሰጡናል ይላሉ። ለዚህም ሲባል በርካታ የዛፍ ችግኞች ተከላ እየተካሄደ መሆኑን ያመለክታሉ። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢ ሳይንስ ረዳት ፕሮፌሰር አንዱዓለም መኮንን ሰሞኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የአየር ብክለትን አስመልክቶ በተካሄደ ጉባዔ ላይ ባቀረቡት ጥናት እንዳሉት፤ የአየር ብክለት በሁለት ይከፈላል፡፡ አንደኛው በመኖሪያ ቤት ውስጥ የአየር ብክለት ሲሆን፤ ሌላው በውጪ የሚከሰት የአየር ብክለት ነው፡፡ በቤት ውስጥ አየር ብክለት ዙሪያ የተሠሩ ሥራዎች ሁሉም የሚያሳዩት በካይ ነገር ለጤና ከተወሰነው በላይ በከፍተኛ ሁኔታ እንዳለ ነው።
ሀገራችን ብዙ ኢንዱስትሪ ስለሌላት የአየር ብክለት አያሰጋትም የሚለው አንፃራዊ ነው የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር አንዱዓለም፣ የቤት ውስጥ ብክለትን ስንመለከት ችግሩ ከእኛ ይመነጫል ሲሉ ይናገራሉ። በቤት ውስጥ የምንጠቀማቸው ሙቀት አማቂ ጋዝ የሚለቁ ኩበት፣ እንጨትና የመሳሰሉት ተረፈ ምርቶችን መሆናቸውን ይገልጻሉ።
እንደ አዲስ አበባ ያሉ ከተሞች ደግሞ ከአሮጌ መኪናዎች ጋር ተያይዞ ከቤት ውጪ የአየር ብክለት እንደሚከሰት ጠቅሰው፣ አንዳንድ ጥናቶችም ይህንኑ እንደሚያመለክቱ ይጠቁማሉ። በሀገሪቱ ካሉት አሮጌ መኪናዎች ከስድሳ በመቶ በላይ የሚሆኑት ያሉት አዲስ አበባ ውስጥ መሆኑን ጠቅሰው፣ መኪናዎቹ በኃይል አጠቃቀማቸው ችግር እንዳለባቸው ከዚህ ጋር ተያይዞም የተበከለ አየር ልቀት ይኖራል ይላሉ።
ለእዚህ አንዱ ክፍተት እነዚህ ያገለገሉ መኪኖች ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡበት ጊዜ የሚጠየቀው ቀረጥ ዝቅተኛ መሆን እንደሆነም ጠቅሰው፣ ይህን ችግር ለመፍታት ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ ነው መሆኑን ይጠቁማሉ።
የገጠር ማኅበረሰብ ዛፍ የመትከል የመንከባከብ የማልማት ልምድ እንዳለው ጠቅሰው፣ በከተማ ግን በየዓመቱ ከሚተከለው ውጪ ዛፍ የመትከል ባህል እንደሌለ ነው ያመለከቱት፡፡
የገጠሩን ሕዝብ ድጋፍ ከተደረገለት የዛፍ ችግኝ ይተክላል፤ ይንከባከባል፡፡ ያሉት አቶ አንዱአለም፣ የከተማው ሕዝብ የዛፍን ፋይዳ እንዲያውቅ ማድረግ እንደሚገባም ይጠቁማሉ።
«በከተማ እስካሁን በርካታ ችግኞች ቢተከሉም ሄደን እየተንከባከብናቸው ነው ወይ» ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ በደርግ ጊዜ ብዙ ቦታዎች የተተከሉ ደኖች እንዳሉም አስታውሰው፣ እስካሁን ድረስም እነዚህ ደኖች በተለያየ አካባቢ እንደሚታዩ ይጠቅሳሉ። ከዚያ ወዲህ በየዓመቱ የሚተከሉት ችግኞች ጸድቀው ለታለመለት ዓላማ ደርሶ እየታየ ነው የሚለውን መጠየቅ እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ።
የዓለም አካባቢ ቀን 2019 በተለያዩ ቦታዎች እየተከበረ ነው ያለው የሚሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ኮምቲሽናል ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር አዲስዓለም አባትሁን፣ በሀገራችን 20ሺህ አካባቢ ሰዎች በዓመት በአየር ብክለት እንደሚሞቱ ብዙም አይታወቅም ሲሉ ገልጸው፣ ኮሌጁ ችግሮችን ከመቃኘት አንጻር ጥናት ማካሄድ ብቻ ሳይሆን ኅብረተሰቡ፣ አካባቢው እና ጊዜው የሚፈልጋቸው ፕሮግራሞችን እንደሚቀርጽ ይጠቅሳሉ፡፡
በዚህ ዓመት እያንዳንዱ ተመራቂ ተማሪ ከመውጣቱ በፊት 40 ችግኝ እንዲተክል ንቅናቄ እየፈጠርን ነው የሚሉት ዶክተር አዲስዓለም፣ ተማሪዎች አካባቢያችንን ለመጠበቅ ሲሉ ችግኝ መትከል ግዴታቸው መሆኑን ይገልጻሉ።
በዚህ ዓመትም ችግኝ ዕቅድ እንዳለ ተናግረው፣ እያንዳንዱ ተመራቂ ተማሪ ከመውጣቱ በፊት 40 ችግኝ እንዲተክል ንቅናቄ እየፈጠርን ነው ሲሉ ያብራራሉ። በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታትም ፈተና እንደሚሆኑ ተናግረው፣ ቦታዎችንና ችግኞችን በማዘጋጀት በኩል ከሚመለከታቸው ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
የሚቀሩ ተማሪዎች ደግሞ ለተተከሉት ችግኞች እንክብካቤ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ በችግኝ ተከላውና እንክብካቤው ዙሪያ ከተማሪዎችም ጋራ ጠቅላላ ውይይት መደረጉንም ይጠቅሳሉ፡፡ ይህ ሥራ ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2011
ኃይለማርያም ወንድሙ