በመከባበር መተባበር

ሀገር ሰሪ ትውልድ አናጭ ከሆኑ የማህበረሰብ እሴቶች ውስጥ መከባበር ቀዳሚው ነው። ሀገራችን ኢትዮጵያ በዚህ የማህበረሰብ ባህልና ወግ ጥንተ መሰረቷን የማገረች የመቻቻል ደሴት ስለመሆኗ ብዙዎች ይመሰክራሉ። ብዝሀነትን በህብረ-ብሔራዊነት አቅፋ ይዛ፤ በአንድነትና በአብሮነት ወንድማማችነትን ያጸናችበት እልፍ ገጸ ውበት አላት። ክብርና አንቱታን ሰጥተው በፊተኝነት ያቆሙን እኚህ የሀገር ካስማ እሴቶቻችን ባለፈውና ባለው፤ በመጪውም እኛነታችን ውስጥ የጎላ ድርሻ አላቸው።

በባህልና በሥርዓት በአብሮነትም የተማገሩት የመከባበር እሴቶቻችን ሀገር ሰጥተውን፣ ታሪክ አውርሰውን፣ በነፃነትና በክብር በሉዓላዊነትም አጽንተውናል። በዓለም አደባባይ በኢ-ፍትሃዊነት የተረገጠውን የሰው ልጅ ክብር በማስመለስ፣ ዘረኝነትንና የነጮችን የበላይነት ሰው በሚሉት የፍትህ ልኬት የመዘንን፣ የነፃነትን መንፈስ በብዙ መከራና የግፍ አገዛዝ ውስጥ ለነበሩ ወንድማቾችን ያጋባን ነን።

እኚህ የክብር ጸጋዎቻችን ከየት ተነሱ? ብለን ብንጠይቅ መልስ ሊሆን የሚችለው በመከባበር የበለጸገ አብሮነታችን ነው። መከባበር የእኛ የኢትዮጵያውያን ስምና መገለጫ ሆኖ ከዘመን ዘመን ተሻግሯል። ይሄ የማንነት መልክ እኔን ከእናንተ እናንተንም ከኔና ከሌላው የደባለቀ፣ የፍቅር፣ የክብር፣ የፍትህና የሚዛናዊነት ሰው የመሆንም ውርስ ነው። እንደ ሀገር ገዝፈንና ተንሰራፍተን ብኩርናን ስንቸር በመተባበር በኩል አልፈን ነው።

የእኛ ከሆኑ የድልና የገድል ስሞቻችን መሀል በመከባበር መተባበር የሚለው ቀዳሚው ነው። በፍቅር የተቀለሙ ብዙ ወርቃማ ስሞች ቢኖሩንም እንደ መከባበርና መተባበር መሳይ ብዙሀነታችንን የሚያገዝፍ ስም ግን የለንም። ጸንተንና በርትተን ዛሬ ላይ የቆምነው የአንተ የእኔ በሌለው በዚህ ስም ነው።

የስልጣኔ ቀዳማይ የተባልነው በዚህ የጋራ ቀለማችን በኩል ነው። ይሄ የጋራ ስም የጋራ ታሪክ፣ የጋራ ሀገር፣ የጋራ እሴት፣ የጋራ ማንነት፣ የጋራ ሥርዓት፣ የጋራ ወግና ባህል ሰጥቶን ኢትዮጵያዊ አስብሎናል። እንደሀገር በአብሮነታችን ስር የተንጸባረቁ፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎሉ እልፍ ሥነ ቃሎች ያሉን ሕዝቦች ነን።

ለአብነት ያክል ብናነሳ እንኳን ከአንድነታችን የተወለዱ እንደ ‹ድር ቢያብር አንበሳን ያስር፣ ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ› ዓይነት ሥነ ቃሎችን መጥቀስ እንችላለን። ሌላው ከዚህ ውህድና ድብልቅ ሕዝባዊነት ተነስቶ ማንነታችን እስከመሆን የደረሰ፣ ኢትዮጵያና አንድነት ሲነሳ ቀድሞ የሚነሳ በታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰ ‹ኢትዮጵያዊነት መልኩን ነብር ዥንጉርጉርነቱን ይቀይራልን? የሚል ትርክት ባለቤት መሆናችን ነው ።

እኚህ ከላይና ከታች የተገለጹ ዓለማዊና መንፈሳዊ አብሮነትን ገላጭ ቃሎች በአብሮነት ምን ያህል እንደጀገንንና እንደበረታን ከመጠቆማቸውም በላይ አንድ ሆኖ ከመቀጠል ሌላ አማራጭ እንደሌለንም የሚያወሱ ናቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ስሟ ከአርባ በላይ የተጠቀሰው ሀገራችን ለፈጣሪ ምን ያህል ቅርብ የሆነ ጥንተ መሠረት እንዳላት የሚጠቁም ነው።

አንድ ወቅት ላይ የነበሩን፣ ለሌሎች ሰጥተን ያካፈልናቸው የሰላም፣ የአንድነት፣ የመከባበር እሴቶቻችን አሁን ላይ ተሸርሽረዋል። እንኮራባቸው የነበሩ የፍቅርና የወንድማማችነት መንፈሶቻችን በነጣጣይ ትርክቶች ተቀይረው አስጊ ደረጃ ላይ ደርሰናል። ሰላም ፈላጊ ከሆንን ቆይተናል።

አንድነት ርቆን በዘርና በብሔር ከተቧደንን ሰንበትበት ብለናል። መተሳሰባችን ወደስጋትና ወደእርስ በርስ መፈራራት ተቀይሮ ከወንድሞቻችን ጋር የማንኖር እስኪመስለን ድረስ በስጋት ውስጥ ነን። ኢትዮጵያዊነትን ከማስቀጠል ይልቅ የአንድ ወገንን የበላይነት ለማስፈን የሚታትሩ ፖለቲከኞችም ተፈጥረው ፈተና ሆነውብናል።

ተነጋግሮ ከመግባባት ይልቅ ጦርነትን እንደመፍትሔ በመውሰድ ዛሬም እንደ ትውልድ ያልተገባ ዋጋ እየከፈልን ነው። የአባቶች የማስታረቅ፣ የሃይማኖት መሬዎች የግሳጼ ሚናቸው ደብዝዞ ትውልዱ ሀይ ባይ እያጣ ነው። ከአንድ ቦይ መንጭተን እየፈሰስን የእኔ የአንተ መባባል ጀምረናል። በአንድ ቅርንጫፍ ላይ አብበን መገፋፋታችን ልቋል። በብሔርተኝነትና በጎጠኝነት ሰብዓዊነታችን እየሸሸን ነው።

ባለመደማመጥና ባለመነጋገር በትንሽ ቅራኔ ትልቅ ቤታችንን ስጋት/አደጋ ውስጥ ከትተን አልፈናል። በአንድ እንብላ፣ በአንድ እንጠጣ የነበርን ሕዝቦች ገበታ ለያይተናል። ለዚህም የመጀመሪያው ተጠያቂዎች ፖለቲካውና ፖለቲከኞቻችን ናቸው። የፖለቲካ አስተሳሰብ በአንድ ሀገር ላይ የሥርዓት፣ የብዙሃነት፣ የተሀድሶ፣ የለውጥና የነውጥ መሠረት መሆን ይችላል።

የትኛውም ፖለቲከኛ በሃሳቡ በኩል ሀገርን እንደፈለገ አድርጎ መፍጠር ይቻለዋል። ትውልድም የዚህ አስተሳሰብ ውጤት የመሆን እድሉ የሰፋ ነው። እንደአለመታደል ሆኖ የእኛ ሀገር ፖለቲካ ከለውጥ ይልቅ ነውጥ ላይ ያተኮረ ነው። የሕዝብን ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ የራስን ፍላጎት በሕዝብ ላይ በመጫን ተወዳዳሪ የሌለው ነው።

በሃሳብ እና በኢትዮጵያዊነት የበሰለ ሳይሆን በእልህና በቂም በቀል ያረረ ነው። ያ ያደረና የዋለ እልህና በቀል በብሔርና በራስ ወዳድነት ቀርቶ ከኢትዮጵያዊነት ሸሽጎናል። መሸሸግ ብቻ አይደለም የብሔር ካባ ለብሰን እርስ በርስ እንድንፈራራም አድርጎናል። ዛሬ ላይ የተፈጠሩብን ይሄን መሰል አጓጉል ነገሮች ከፖለቲካው ምህዳር የተፈናጠሩ ነውሮች ናቸው።

ፖለቲካው ሃሳብ በሌለው ልብና አእምሮ ከመጣንበት የኢትዮጵያዊነት ሥነልቦና አሽሽቶ የዘረኝነት እድፍ ላይ ጥሎናል። ተያይዘን ካቆምነው ሰንድ ታሪክ ውስጥ አጉድሎና ጨምሮ የመጣንበትን እንድንፈራ አድርጎናል። በአንድ የበላንባቸው ፎሌና ሽክናዎቻችን ተወርውረው፣ በአንድ የተቀመጥንባቸው ጥላዎቻችን ተመንጥረው የሃሩር ሲሳይ እየሆኑ ነው። ግጥምጥም ኮቴዎቻችን መለያየት ገብቶባቸው እዚያ እና እዚህ ተሰምረዋል።

ከሕዝብ እውነት ይልቅ ለራስ እውነት ፊተኛ በመሆን ብዙሃነትን ወደ ብሔርተኝነት አውርደናል። ኢትዮጵያን በሚያሽር የእርቅና የተግባቦት መድረክ ላይ ከመቆም ይልቅ ቁርሾ በማስቀመጥ ትውልዱ እየተነቋቆረ እንዲኖር ሃሳብ አልባ፣ እርቅ አልባ፣ ምክክር አልባ ምህዳርን ለመፍጠር ሞክረናል።

የፖለቲከኞቻችንም የርዕዮተ ዓለም መነሻ ሀገር፣ ሕዝብ፣ ትውልድ እና የጋራ ትርክት ሳይሆን የራስን ፍላጎት በሕዝብ ላይ መጫን ነው። የብቻ ትርክት ላይ መሠረት ያደረገ ነው። የብቻ ትርክቶች ደግሞ የመጣንበትን፣ ያደግንበትን፣ ባለታሪክ የሆንበትን እና በአንድነት የቆምንበትን የጋራ እውነት ወደ እኔነት የሚለውጥ ነው።

ሁለተኛው በተረት ተረት ሕዝብን ከሕዝብ በማቃረን ትርፍ በሚፈልጉ ግለሰቦችና ቡድኖች የተፈጠረው ተግዳሮት ነው። በእኚህ መሳይ ግለሰቦችና ቡድኖች ብዙ መከራዎችን እንዳለፍን የሚታወቅ ነው። ዳር ቆመው በሚያራግቡት ወሬ፣ እንዲህ ሆነሃል፣ ይሄን ትሆናለህ እያሉ በነጣጣይ ትርክት እንድንፈራራ አድርገውናል። ታሪክ አዛንፈው፣ እውነት አሻፈው ያልኖሩበትን ትላንት እንደትርክት በመውሰድ አንድነታችን ውስጥ መለያየትን ፈጥረዋል፤ አብሮነታችን ውስጥ ጥርጣሬን ነዝተዋል። አንዳንዶች ለአላማቸው ውሸትን እንደእውነት በመውሰድ ጥንተ ብዙሃነታችንን ነቅንቀዋል። አንዳንዶቻችን ሴራቸው ገብቶን በስክነት ኢትዮጵያዊነታችንን አጥብቀናል።

በሶስተኛ ደረጃ የሚነሳው የሚዲያ አሉባልታ ነው። ምንጩ በማይታወቅ፣ የትና ለምን፣ መቼ፣ በማን እንደሆነ በማናውቀው የሚዲያ ወሬ ፍቅራችንን በጥላቻ፣ አብሮነታችንን በመለያየት የቀየርን ብዙ ነን። ከላይ የገለጽኳቸው ሶስቱ መነሻዎች ኢትዮጵያዊነትን አድብዝዘው በእኔነት እንድንቆም አድርገውን እልፍ ዋጋ አስከፍለውናል።

መፍትሔው ሃሳብ አልባ የሆነውን የፖለቲካ ምህዳር ሃሳብ አመንጭ ማድረግ ነው። ፖለቲካችን ሞጋችና በላጭ፣ አንቂና አብቂ ልዕለ ሃሳባውያን የሉትም። ሀገር የፖለቲካ ጽንስ ናት ካልን በኢትዮጵያዊነት እንድናድግ፣ በጋራ ታሪክ ስር እንድንቆም ኢትዮጵያዊ ሃሳብና መልክ ያስፈልገዋል።

ፖለቲከኞቻችን ወደፖለቲከኛ ከመቀየራቸው በፊት ሰው ነበሩ። ሰው ሆነው ሀገር እንዲመሩ፣ ሰው ሆነው ሕዝብ ፊት እንዲቆሙ፣ ሰው ሆነው እንዲሟገቱ፣ ሰው ሆነው ሰው ሰው እንዲሸቱ ልንረዳቸው ይገባል። ለዚህ ደግሞ እኛ ቀድመን የተለወጠ ማንነት ልንገነባ ይገባል።

በአንድ ሀገር የጋራ እሴት የጋራ ማንነት ያህል ዋጋ ያላቸው ናቸው። የእኔ የአንተ የሌለባቸው፣ የፖለቲካ አስተሳሰብ የማይንጸባረቅባቸው ከኢትዮጵያዊነት መንጭተው ወደ ኢትዮያዊነት የሚፈሱ የጋራ ትውፊቶቻችን ናቸው። በብዙ የተመሳሰልን፣ በብዙ ተቆራኝተን ሀገርና ሕዝብ የሆንን ነን።

ይሄ ማንነት በፖለቲካ ሴራም ሆነ በአሉባልታ አራጋቢዎች እንዳይፈርስ ሆኖ የጸና ማንነት ነው። ስለሆነም በጋራ ከማገርነው ከኢትዮጵያዊነት የሚበልጥ አንዳች እንደሌለ በማሰብ ለአሉባልታና ለወሬኞች ጊዜ ባለመስጠት አብሮነታችንን ማጽናት አለብን።

እንደሀገር አንድነታችንን ለመመለስ፣ በእርቅና በይቅርታ አብሮ ለመጓዝ ኮሚሽን አቋቁመን ነፃና ገለልተኛ ሕዝባዊ ውይይት ለማድረግ እየተሰናዳን ነው። ይሄን መሰሉ አካሄድ ታሪክ በመመለስና አብሮነትን ከማስቀጠል አኳያ እጅግ ዋጋ ያለው፣ ተስፋ ሰጪና መጪውን በበጎ እንድንቃኝ የሚያደርግ ነው። በበጎ ትርክት ዳብረን ቁርሾዎቻችንን ወደ እድል፣ ጥላቻዎቻችንን ወደፍቅር ቀይረን በአዲስ ስም የምንነሳበት ነው።

ብሔራዊ እርቅ ትላንት ዛሬና ነገ የሚዳሰሱበት ከሕዝብ በሕዝብ ለሕዝብ በሆነ ጽንሰ ሃሳብ ነፃ የምንወጣበት የተግባቦት መድረክ ነው። አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ እንደጥሩ አጋጣሚ ተጠቀመንበት ወደኢትዮጵያዊነት ከፍታ የምንመልስበት ነው። ቁርሾዎቻችን ከየትም ይምጡ፣ ለምንም አላማ ማንም ያምጣቸው ከመነሻ እስከመድረሻቸው ድረስ በሕዝባዊ ውይይት እርቅና ተግባቦትን ባስቀደመ አቅጣጫ ታርቀንና ተቃቅፈን የምናልፋቸው ናቸው።

ሃሳብ የዳበረበት፣ ሃሳብ የሚዋጣበት፣ ከምንም በላይ ደግሞ የመፍትሔ ሃሳብ የሚንሸራሸርበት ሀገራዊ ምክክር ያለፈውን አክመን፣ የዛሬን አርመን ነገን የተሻለ ለማድረግ እጃችን ላይ ያለ በጎ እድላችን ነው። በእድላችን ተጠቅመን በአስታራቂ ትርክት አብሮነታችንን የምንመልስበት ወቅታዊ መድረክ ነው።

ሌላው ለችግራችን የመፍትሔ አካል የሚሆነው፤ ለሚዲያ አሉባልታዎች ቦታ አለመስጠት ነው። ማንነቱን ደብቆ ማንም የፈለገውን በሚተፋበት የሚዲያ ዘመን ላይ ነው። ሌሎች የተፉት የሀሰት ወሬ እኛን እንዳያቀያይመን ጨዋና አስተዋይ ሆነን ነገሮችን በእርጋታ መቃኘት ይጠበቅብናል። በገንቢ ትርክት ችግሮቻችንን አክመን ወደፊት ከመሄድ እና አብሮ ከመቆም ሌላ አማራጭ እንደሌለን አያይዘን ልንረዳ ይገባል።

በታሪክ ዳብረን፣ በብዙሃነት አብረን የመጣን ነን። ተሳስረን፣ ተዋልደን፣ በአንድ ገጸ ሰብ ኢትዮጵያዊ የተባልን ነን። በገዘፈ የነፃነት ጥላችን ብዙዎችን በማስጠለል፣ በሰፋ የፍትህ ሚዛናችን ብዙዎችን ባለተስፋ በማድረግ፣ ከወደቁበት በማንሳት፣ ከተናቁበት ቀና በማድረግ ባላደራዎች ነን። በመከባበር መተባበር ምን እንደሆነ ብንጠየቅ የምንመልሰው ብዙ መልስ ያለን ነን። መሀላችን ገብቶ ማንም እንዲያዝለንና እንዲያደነቃቅፈን ባለመፍቀድ አብሮነታችንን እናጽና!።

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10/2016 ዓ.ም

Recommended For You