ስምና ግብር ለየቅል እንደሚባለው አዲስ አበባ ስሟን በማይመጥን ሁኔታ ለዘመናት ኖራለች። እንደ ስሟ አዲስ ሳትሆን ከእርጅናም በታች ወርዳ ተጎሳቁላ እና ነትባ ዘመናትን ተሻግራለች።
130 ዓመታትን ባስቆጠረው ቆይታዋ ወደ ፊት ከመጓዝ ይልቅ የኋሊት እየተጓዘች የከተሞች ጭራ ለመሆን በቅታለች። በተለይም መሃልኛው የአዲስ አበባ ክፍል ችምችም ብለው በተሰሩ ቤቶች የታጨቀ፤ ከዘመኑ ጋር ያልዘመነ፤ከ130 ዓመታት በፊት በነበረው የቀጠለ እና በአሁኑ ወቅት ያለውን የአኗኗር ሁኔታ የማይመጥን ነው። አብዛኞቹ ቤቶች አንድ መጸዳጃ ቤትን ለሰላሳ ፤ለአርባ የሚጠቀሙ ብዙዎችም መጸዳጃ ቤት የሌላቸውና በየጥጋጥጉ ለመጠቀም የተገደዱ ዜጎች ያሉባቸው አካባቢዎች ናቸው።
እነዚህ አካባቢዎች የአዲስ አበባን የኋሊት ጉዞ የሚያሳዩና የከተማዋ የድህነት መገለጫዎችም ናቸው። ጎዳና ተዳዳሪነት፤ሴተኛ አዳሪነት ፤ማጅራት መቺነት የመሳሰሉት ኢሞራላዊ እና ወንጀል ነክ ድርጊቶች የሚፈጸምባቸው ናቸው። ቁማር ቤቶች፤ጫት ቤቶች፤ሺሻ ቤቶችና አረቄ ቤቶች የእነዚህ አካባቢዎች መገለጫዎች ናቸው።
ፒያሳን የመሳሰሉ አካባቢዎች ስማቸው ገናና ቢሆንም በገቢር ግን ስማቸውን የሚመጥን ገጽታ የላቸውም። ምንም አይነት ዘመናዊነት የማይታይባቸው ኋላቀር አካባቢዎች ከመሆናቸውም በላይ በስመ አራዳ ለዘመናት ድህነት ተጭኗቸው የቆዩ ናቸው።
ስምና ግብር በተራራቀበት በእነዚህ አካባቢዎች ሰዎች በአንዲት ክፍል ውስጥ ቆጥና ምድር ሰርተው ፤መጸዳጃ ቤት ተጋርተው ፤በአንዲት ክፍል አስር፤ አስራ አምስት ሆነው ተደራርበውና ተነባብረው የሚኖሩባቸው የድህነት ጥግ የሚታይባቸው የከተማችን አካል ናቸው።
ይህ አልበቃ ብሎ አካባቢዎቹ በመሰረተ ልማት እጥረት የተጎዱ ናቸው። ለስሙ መሃል አካባቢ ይባል እንጂ የአሌክትሪክ ዝርጋታው እጅግ ኋላቀር ከመሆኑ በላይ እጅግ የተወሳሰበና ለአደጋም የተጋለጠ ነው። በዚህ ላይ ዝናብና የንፋስ ሽውታ ሲያገኘው በቀላሉ የሚበጠስና መብራትም በየአጋጣሚው የሚጠፋበት አካባቢ ነው።
ከሁሉም የከፋው ደግሞ በእነዚህ አካባቢዎች ሲኖሩ የቆዩ ነዋሪዎች በቂ መጸዳጃ ቤቶች ሌላቸው፤በአንዲት ጠባብ ክፍል ተቆራምደው ለመኖር ተፈረደባቸውና ከሰው ልጅ አኗኗር ባፈነገጠ መልኩ በአንዲት ጠበብ ክፍል አባወራና እማ ወራ፤ልጆችና አለፍ ሲልም ዘመድ አዝማድ ታጉረው እንዲኖሩ የተፈረደባቸው ናቸው።
ይህ ከሰው በታች የሆነ ኑሮ አንድ ቦታ ማብቃት ስላለበት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመቀናጀት የከተማ መልሶ ማደስና ኮሪደር ልማት ፕሮጀክትን ይፋ አድርጓል። ይህ የመልሶ ማልማትና ኮሪደር ልማት ፕሮጀክት በአይነቱ አዲስ ሆነና ከፍተኛ ስፋት ያለውን ቦታ የሚሸፍን ነው።
በዚህ ልማት የሚካተቱት አካባቢዎች ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ፣ ከአራት ኪሎ እስከ ቦሌ ድልድይ፣ ከቦሌ ድልድይ በመገናኛ ወደ ሲኤምሲ፣ ከቦሌ ተርሚናል ወደ ጎሮ፣ ከሜክሲኮ ወደ ወሎ ሠፈር፣ እንዲሁም ከእንግሊዝ ኤምባሲ ወደ አራት ኪሎ የሚወስዱ ኮሪደሮች መሆናቸው ታውቋል። ስራውም በስድስት ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅም የከተማዋ አስተዳደር ኃላፊዎች እየተናገሩ ነው።
እነዚህ ሥራዎች ሲከናወኑም ከተለያዩ ቦታዎች ለሚነሱ ግለሰቦች ምትክ ቦታ እየተሰጠ ነው። ቀደም ሲል በቀበሌ ቤት ውስጥ ለሚኖሩ ነዋሪዎች ከቦታው በመነሳታቸው ምክንያት ለችግር እንዳይጋለጡ ምትክ የቀበሌ ቤት ወይም ኮንዶሚኒየም እንደ ምርጫቸው እየተሰጣቸው ነው። በተመሳሳይም የግል ይዞታ የነበራቸው ነዋሪዎች ምትክ ቦታና ካሳ እንደሚሰጣቸው ተነግሯል። ይህም ተግባራዊ እየሆነ ነው።
የኮሪደር ልማቱ ገና በጥንስስ ላይ እያለ እና መተግበር ከጀመረ በኋላም የሚነዙ በርካታ አሉባልታዎች ነበሩ። በተለይም ድሃውን ከኖረበት ለማቀፈናቀል የተሸረበ ሴራ ነው፤የአዲስ አበባን ባህልና ተውፊት ለማጥፋት የታለመ ነው፤ ድሃዎችን ለማፈናቀል ነው ወዘተ የሚሉ አሉባልታዎች በስፋት ይነዙ ነበር። ሆኖም እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል እንዲሉ ሳይውል ሳያድር ልማቱ በተቃራኒው በርካታ ትሩፋቶችን ይዞ መምጣቱን እያስመሰከረ ነው።
ለዘመናት በአንዲት ጠባብ ክፍል ይኖሩ የነበሩ ዜጎች ዛሬ ቀን ወጥቶላቸው ባለሁለትና ባለሦስት ክፍል ቤት አግኝተው እንደ ልባቸው መኖር ጀምረዋል። ቀደም ሲል ሻወር መውሰድ፤ንጹህ መጸዳጃ ቤት ማግኘት፤ንጹህ ማዕድ ቤት ማብሰል ቅንጦት ይመስል የነበረው ዛሬ ሁሉም በሚባል ደረጃ የዚህ እድል ተጠቃሚ ሆነዋል።
በተለይም በመልሶ ማልማቱ የተነሳው የፒያሳ አካባቢ ጎዳና ተዳዳሪነት፤ሴተኛ አዳሪነት ፤ማጅራት መቺነትና የመሳሰሉት ኢሞራላዊ እና ወንጀል ነክ ድርጊቶች የሚፈጸምባቸው የአዲስ አበባ አካባቢዎች ግንባር ቀደሙ ነው። ቁማር ቤቶች፤ጫት ቤቶች፤ሺሻ ቤቶችና አረቄ ቤቶች የእነዚህ አካባቢዎች መገለጫዎች ናቸው።
በእነዚህ አካባቢዎች መሸት ሲል በቀላሉ ወጥቶ መግባት አይቻልም። ማጅራት መመታት፤መሰረቅ፤መደፈርና የመሳሰሉት ድርጊቶች ሰርክ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ናቸው። እንኳን አዲስ ሆኖ እግር ለጣለው ሰው ቀርቶ ዘመናትን ለኖረ ሰው በእነዚህ አካባቢዎች በሰላም ወጥቶ መግባት ብርቅ ነው።
ከዚህ አሰቃቂ ህይወት የወጡ ሰዎችም ዛሬ ፈጣሪንና መንግሥትን ማመስገን ጀምረዋል። በልማቱ ተነስተው ወደ ሌሎች አካባቢዎች የሄዱ ነዋሪዎች ‹‹ቀን ወጣልን›› ሲሉ ተደምጠዋል። ብዙዎቹ ነዋሪዎች የቀድሞው ኑሯቸውን ከጨለማ ጋር አመሳስለውታል።
በአንዲት ክፍል ለዘመናት ተጨቁነው የኖሩት እነዚህ ምስኪን ዜጎች ዛሬ ገበናቸው ተከቷል። የጋራ መኖሪያ ቤትም ሆነ ተገጣጣሚ ቤቶችን የመረጡ ዜጎች እንደ ሰው መተኛት፤እንደ ሰው በዘመናዊ ሻወር ለመታጠብ፤በሁለት በሦስት ክፍል ውስጥ መምነሽነሽ ፣በንጹህ መጸዳጃ ለመጠቀም በቅተዋል።
ከእነዚህ አካባቢዎች ተነስተው በተለያዩ አካካቢዎች የቤት እድል ባለቤት የሆኑት ዜጎች ዛሬ በሰላም ወጥተው ይገባሉ። ልጆቻቸውን ለተለያዩ ሱሶች ከሚያጋልጡ ድርጊቶች የራቁ ናቸው። ጽዳታቸውም በመልካም ሁኔታ የተጠበቀ ነው።
በአጠቃላይ የኮሪደር ልማቱ ለድሃዎች የመጣ ትሩፋት ነው ማለት ይቻላል። የተጎሳቆለውን አዲስ አበባ ገጽታ ለመቀየር ከማስቻሉም በላይ ለዘመናት በድህነት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቀው የቆዩ ምስኪን ዜጎችን ከጨለማ ወደ ብርሃን ያወጣ ሥራ ነው። በተለይም ቀደም ባለው መንግሥት በመልሶ ማልማት ዙሪያ የነበረውን ኢ-ፍትሐዊ እና ሰብአዊ ድርጊት የሻረ እና የዜጎችም በልማት ላይ ያላቸውን እምነት ያረጋገጠ ነው።
ቀደም ባለው ዘመን አዲስ አበባ ከተማ በነባር መንደሮችና በማስፋፊያ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎችን፣ እንዲሁም አርሶ አደሮችን አፈናቅላለች። በተለይ በቂ ምትክ ቦታና ካሳ ሳይከፈላቸው ተፈናቅለው ለከፋ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር የተጋለጡ በርካቶች ነበሩ። የመልሶ ማልማት ሥራ ነዋሪዎችን የሚያካትትና የሚያሳትፍ አልነበረም።
ዜጎች ፣ ከኖሩበት ጎስቋላ ኑሮ የሚያላቅቅና ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያደርስ ሳይሆን የበለጠ ጉስቁልናን በሚያስከትል መልኩ ለባሰ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር የሚዳርግ ነበር።
ዛሬ ግን ሁኔታዎች ተለውጠው መልሶ ማልማትም ይሁን ኮሪደር ልማቱ በዝቅተኛ ኑሮ ህይወታቸውን ሲገፉ ለቆዩ ነዋሪዎች በርካታ ትሩፋቶችን ይዞ መጥቷል። ሰዎችን ከጨለማ ወደ ብርሃን የሚያወጣና በቀጣይም ዜጎች በመልሶ ማልማቱ እና የኮሪደር ልማቱ ላይ እምነት እንዲጥሉ የሚያደርግ ነው። ይህም ከነዋሪዎቹ ከራሳቸው አንደበት ተደምጧል።
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም