ነገረ ቲክቶክ

የቲክቶክ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሹ ዚ ቺው፤ ቲክቶክን የሚያግደው ረቂቅ ሕግ ለሌሎች የማኅበራዊ ሚዲያዎች ጉልበት የሚሰጥ ከመሆኑ ባሻገር፤ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ አሜሪካውያንን ከሥራ ውጪ ያደርጋል ሲሉ ያስጠንቅቃሉ። በነገራችን ላይ የቻይና መንግስት የማንንም የግል መረጃ ጠይቆን የማያውቅ ቢሆንም የአሜሪካውያን መረጃዎችን በአስተማማኙ የኦራክል ክላውድ ቋት ነው የሚከማቸው ይላሉ ቺው።

ቻይና ቲክቶክን ተጠቅማ ጸረ አሜሪካዊ የሆነ ፕሮፓጋንዳ ልትነዛ ትችላለች ስለሚባለውም ዋና ስራ አስፈጻሚው ሲመልሱ፣ 60 በመቶ የሚሆኑት የቲክቶክ ባለቤቶች እኮ ቻይናዊ አይደሉም። መረጃን ሆን ብሎ ማዛባትም ሆነ ፕሮፓጋንድ ቲክቶክ ላይ ቦታ የለውም ሲሉ ቺው ይገልጻሉ። አሜሪካ በተደጋጋሚ ቲክቶክን ለመግዛት ስላቀረበችው ጥያቄ ዋና ስራ አስፈጻሚው ሲመልሱ ቲክቶክ አይሸጥም አይለወጥም ሲሉ እቅጩን መልሰዋል።

ሆኖም ባይትዳንስ፤ ቲክቶክን መሸጥ ከፈለገ ከቻይና መንግሥት ፈቃድ ማግኘት ይኖርበታል። ነገር ግን ቤይጂንግ ይህን እንደማታደርግ እያስጠነቀቀች ነው። አሜሪካ የሚገኙ አንዳንድ የቲክቶክ ተጠቃሚዎች አዲሱን ረቂቅ አዋጅ እየተቃወሙት ይገኛሉ። ቲክቶክ 170 ሚሊዮን የሚሆኑ በአሜሪካ የሚገኙ ተጠቃሚዎቹ ወደ ግዛቶታቻቸው ተወካዮች ደውለው ረቂቁን ሕጉን ውድቅ እንዲያደርጉት እንዲጠይቁ መክሯል።

ቲክቶክ ሕንድ ውስጥ ታግዷል። ሕንድ የቲክቶክ ትልቋ ገበያ ነበረች። ነገር ግን በአውሮፓውያኑ 2020 መተግበሪያውን አግዳዋለች። እንዲሁም በኢራን፣ በኔፓል፣ በአፍጋኒስታን እና በሶማሊያ ጥቅም ላይ እንዳይውል እግድ ተጥሎበታል። በዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ የመንግሥት ሠራተኞች እና የፓርላማ አባላት በሥራ ስልካቸው ቲክቶክን እንዳይጠቀሙ ባለፈው ዓመት ተነግሯቸዋል። የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽንም በተመሳሳይ በሥራ ስልክ ቲክቶክን መጠቀም አግዷል።

ቢቢሲ በደኅንነት ስጋት ምክንያት ሠራተኞቹ ከድርጅቱ የተሰጣቸውን ስልክ ተጠቅመው ቲክቶክን እንዳይገለገሉ ከልክሏል። የቲክቶክ ዋናው መሣሪያ አልጎሪዝም (ስልተ ቀመር) ነው። ይህ መተግበሪያው የተጠቃሚዎችን ታሪክ ተመልክቶ የትኛውን ዓይነት ይዘት ይወዳሉ የሚለውን የሚለይበት ዘዴ ነው። ወደ ቲክቶክ ሲገቡ ከላይ ሦስት ንዑስ ርዕሶችን ያገኛሉ። ፎሎዊንግ፣ ፍሬንድስ እና ፎር ዩ ይባላሉ። ፎሎዊንግ እና ፍሬንድስ ተጠቃሚዎች ከሚከተሏቸው ሰዎች እና ከጓደኞቻቸው የሚያገኟቸው ይዘቶች ናቸው። ፎር ዩ የተሰኘው ደግሞ ቲክቶክ በራሱ መጥኖ ተጠቃሚዎች ይህን ይዘት ይወዱታል በሚል የሚለቀቅ ነው።

ተቺዎች ቲክቶክ ከሌሎች ማኅበራዊ ሚዲያዎች በላይ የተጠቃሚዎችን መረጃ ይሰበስባል፤ ለዚህም ነው የተመረጡ ይዘቶችን የሚያቀርበው ይላሉ። የተጠቃሚዎች አድራሻ፣ የሚጠቀሙበት ስልክ፣ የሚወዷቸው ይዘቶች እና ሲፅፉ የሚያሳዩት ባሕሪን ይሰበስባል የሚል ትችት ያቀርባሉ። ገር ግን ሌሎች እንደ ፌስቡክ እና ኢንስታግራም ያሉ ማኅበራዊ ሚዲያዎችም ይህን በማድረግ ይታወቃሉ። የዩናይትድ ስቴትስ ፖለቲከኞች አዲስ ረቂቅ ሕግ አውጥተው ቲክቶክ መታገድ አለበት አሊያ ደግሞ ባለቤቱ የቻይናው ኩባንያ ሊሸጠው ይገባል የሚል ክርክር ገጥመዋል።

የቪዲዮ ማጋሪያ የሆነው መተግበሪያ በመላው ዓለም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች አሉት። ነገር ግን የደንበኞቹ የመረጃ ደኅንነትን እየጠበቀ አይደለም፤ ከቻይና መንግሥት ጋር ግንኙነት አለው የሚሉ ክሶች ይቀርቡበታል። ከሁለቱም የአሜሪካ አውራ ፓርቲ የተውጣጡ ፖለቲከኞች አዲስ ያረቀቁት ሕግ የቲክቶክ ባለቤት የሆነው ባይትዳንስ መተግበሪያውን ቻይናዊ ላልሆነ ኩባንያ ካልሸጠ ይዘጋል ይላል።

ሕግ አውጪዎቹ ቲክቶክ በአሜሪካ የሚገኙ 170 ሚሊዮን ደንበኞችን መረጃ ለቻይና መንግሥት አሳልፎ ሊሰጥ ይችላል የሚል ስጋት አላቸው። ቲክቶክ ግን የውጭ ሀገር መረጃ ለቻይና መንግሥት አሳልፌ አልሰጥም ሲል ያስተባብላል። የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይም ኮንግረስ ባለፈው ሳምንት በ352 የድጋፍ ድምፅ እና በ65 ተቃውሞ ሕጉን አፅድቋል። አሁን ረቂቅ አዋጁ ወደ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ወይም ሴኔት ተላልፏል።

ነገር ግን ሴኔቱ እንደ ኮንግረሱ ሕጉን በቀላሉ ያፀድቀዋል የሚል ግምት የለም። አብዛኞቹ የሴኔት አባላት ሕጉን ይደግፉታል ወይ? የሚለው ጥያቄ ግልፅ ምላሽ አላገኘም። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ሕጉ በሴኔቱ ከፀደቀ ፊርማቸውን እንደሚያኖሩ ቃል ገብተዋል። አዋጁ በሴኔቱ ፀድቆ የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ፊርማ ካረፈበት፤ ባይትዳንስ ቲክቶክን ለመሸጥ የስድስት ወራት ዕድሜ ይሰጠዋል፤ ካልሆነ ከአሜሪካ ገበያ ይታገዳል። ቲክቶክ አሜሪካ ውስጥ ታገደ ማለት ተጠቃሚዎች መተግበሪያውን ከሚያወርዱበት የአፕ ስቶር እና የጎግል ፕሌይ ይወገዳል ማለት ነው።

ረቂቅ አዋጁ በውጭ አካላት የሚመሩ መተግበሪያዎችንም አሜሪካ ውስጥ አፕዴት ማድረግ እና መጠገን አይቻልም ይላል። ቲክቶክ በምዕራባውያን ስክሪን መቆየት የሚፈልግ ከሆነ ከእናት ሀገሩ ቻይና ጋር መቆራረጥ አለበት ይለናል የምዕራባውያን ፖለቲካል ኢኮኖሚ ልሳን የሆነው “The Econo­mist” መጽሔት በሰሞነኛ ዕትሙ። በፊት የቲክቶክ ሱስ አስያዥ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ወይም ቪዲዮዎች ዕንቅልፍ የሚነሱት ተጠቃሚዎችን ነበር። ዛሬ ዛሬ ግን ፖለቲከኞችንና የሕዝብ እንደራሲዎችን ጭምር እንቅልፍ እየነሱ ነው።

የአሜሪካ ሴናተሮችም ሆኑ የኮንግረስ አባላት ቲክቶክ ከቻይና ጋር ባለው ግንኙነት የተነሳ ዕንቅልፍ ወይም እረፍት ካጡ ሰነባበቱ። ባለፈው መጋቢት መጀመሪያ የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዱላ ቀረሽ እሰጥ አገባ ካካሄደ በኋላ ቲክቶክ ከቻይና ባለቤቱ “ባይትዳንስ” ጋር ሰማኒያውን ቀዶ ፍች እንዲፈጽም የሚያስገድድ ሕግ አውጥቷል። አዎ ! ከቻይና ውጭ ላለ ዜጋ ወይም ኩባንያ እንዲሸጥ፤ ይህን አሻፈረኝ የሚል ከሆነ ደግሞ በአሜሪካ እንዲታደግ ኮንግረሱ ወስኗል።

“ባይትዳንስ” ለመሸጥ የማይስማማ ከሆነ የአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ ወይም ሴኔት ውሳኔውን አጽድቆ ቲክቶክን ከአሜሪካውያን እስክሪን ያግደዋል። ይህን የአሜሪካ ውሳኔ ፈለግ ደግሞ የአአውሮፓ ሕብረት እንግሊዝ፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ ወዘተረፈ መከተላቸው ስለማይቀር በዓለማችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ተወዳጅነትን ያተረፈው የቲክቶክ አዝጋሚ ግብዓተ መሬት ተጀመረ ማለት ነው።

ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ግን ቲክቶክ ላይ የተፈጠረው ስጋት ሳይጋነን አልቀረም ይላሉ። የተጠቃሚዎቹን መረጃ ለቻይና መንግስት ስለላና ጸረ አሜሪካዊ የሆነ ሀሰተኛ መረጃ ለማሰራጨት ይጠቀማል የሚለው ክስ እስካሁን ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ማስረጃ አልቀረበበትም ይለናል መጽሔቱ። የተጠቃሚዎችን መረጃ እንደነ ፌስቡክ ለገበያ ሽያጭ ወይም ለማርኬቲንግ መጠቀሙ ለቲክቶክ ሲሆን ለምን ሀጢያት ይሆናል በማለት የሚሞግቱም አሉ።

የቻይና ሰላዮች የአሜሪካውያንን መረጃ ለማግኘት የበዛ አማራጭ እንዳላቸው፤ ከፈለጉም በቀላሉ መግዛት የሚያስችል አሰራር መኖሩም እየታወቀ ቲክቶክን እንዲህ ያለ ውዝግብ ውስጥ ማስገባት ውሳኔውን ፖለቲካዊ አንድምታ ይሰጠዋል። ቲክቶክ ተዘጋ ማለት ቻይና በምትወስደው አጸፋዊ እርምጃ አሜሪካና ምዕራባውያን ከቻይና የዲጂታል አገልግሎት ጋር ያላቸው ግንኙነት ክፉኛ ተጎዳ ማለት ነው ሲሉ የሚያስጠነቅቁ የዘርፉ ሊቃውንት አሉ። ይልቁን ቲክቶክ በማህበራዊ ሚዲያው ፉክክር እንዲኖር የተጫወተው ሚና ሌሎች ለፈጠራ እንዲነሳሱ አድርጓል።

ለምሳሌ ባለፈው ዓመት በተጠቃሚዎች በብዛት ዳውንሎድ ከተደረጉ 10 መተግበሪያዎች ስድስቱ የሜታ ወይም የፌስቡክ ባለቤት ማርክ ዙከርበርግ ናቸው። ቲክቶክ ከኋላ ተነስቶ በተጠቃሚዎች ዘንድ ተወዳጅ በመሆኑና ዳውንሎድ በመደረግ ቀዳሚ ስለሆነ ሜታንና ሌሎችን ለፈጠራ አነሳስቷል። በዚህ ደግሞ ተጠቃሚ የሚሆኑት ደንበኞች ወይም ሸማቾች ስለሆኑ ይበል የሚያሰኝ ነው ይለናል The Economist።

ለነገሩ ይለናል መጽሔቱ አሜሪካ ቲክቶክን እንደስጋት ብታየው አይፈረድባትም። በአሜሪካ ብቻ ተጠቃሚዎች 170 ሚሊየን ደርሰዋል። እድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች ከሆኑ ሲሶው ወይም ሶስት እጁ ቲክቶክን ለመዝናኛ ብቻ ሳይሆን እንደ መረጃ ምንጭ ይጠቀሙበታል። ይህ ነው እንግዲህ ቻይና ቲክቶክን ሀሰተኛ መረጃንና ፕሮፓጋንዳን ለማሰራጨት እንደ መሳሪያ ልትጠቀምበት ትችላለች የሚል ስጋት የፈጠረው።

ሀገራችንን ጨምሮ ብዙ ሀገራት የሚዲያ ባለቤትነት በውጭ ዜጎች እንዳይያዝ የሚከለክል ሕግ አላቸው። ታዋቂው የበርካታ ሚዲያዎች ባለቤት ሩፐር መርዶክ “ፎክስ”ን ከመግዛቱ በፊት ዜግነቱን አሜሪካዊ አድርጓል። የዱባይ ንጉሳዊ ቤተሰብ ታዋቂውን የእንግሊዝ ጋዜጣ “ቴሌግራፍ”ን ለመግዛት ያደረገው ጥረት ሳይሳካ የቀረው በዚሁ የዜግነት ጉዳይ ነው። የቲክቶክ ተቀባይነትና ተጽዕኖ ፈጣሪነት ከመደበኛው ሚዲያ በላይ ተዘውታሪና ተመራጭ መሆኑ ምዕራባውያንን ክፉኛ አስግቷቸዋል።

ሀገራት መደበኛ ሚዲያው በውጭ ዜጋና ኩባንያ እንዲያዝ እንደማይፈልጉት ሁሉ በማህበራዊ ሚዲያ ባለቤትነት ላይም ተመሳሳይ አቋም ሊከተሉ ይገባል ይለናል The Economist መጽሔት። ማህበራዊ ሚዲያው ከምንም በላይ ጥንቃቄ ይፈልጋል። የአንድ ጋዜጣ ወይም ቴሌቪዥን አዘጋጆች በግላጭ ሲታወቁ በአንጻሩ ቲክቶክ ግን ለእያንዳንዱ ተጠቃሚ በፍላጎቱ መሠረት የተቀመረን መረጃ ቢያደርስም እንደ መደበኛ ሚዲያው አዘጋጆች ክትትል ሊያደርጉ አይችሉም።

አንዳንድ ጥናቶች ቲክቶክ በጋዛ ላይ ሚዛናዊነት የጎደላቸውን ይዘቶችን አሰራጭቷል ሲሉ ሲከሱት ይደመጣል። ይዘቶቹ ለተጠቃሚዎች እየደረሱ ያሉት ፍላጎታቸውን መነሻ ባደረገ አልጎሪዝም ነው ወይስ በቻይና መንግስት ጣልቃ ገብነት የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም። ለነገሩ ቲክቶክ የቻይናን መንግስት ላለማስቀየም ስለ 1989ኙ እኤአ የታይናሚን አደባባይ ጭፍጨፋ የሚያሳዩ ቪዲዮችን ከገጹ ማውረዱን በአደባባይ አምኗል። ሆኖም በዚህ ውሳኔው ተጸጽቶ አሰራሩን ማሻሻሉን ደጋግሞ ቢገልጽም የፈለገውን ያህል ሰሚ ያገኘ አይመስልም። በነገራችን ላይ ይህ ጭፍጨፋ የቻይናን ኮሚንስታዊ አገዛዝ በመቃወም ሰልፍ የወጡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ወጣቶች ቤጂንግ በሚገኘው የታይናሚን አደባባይ በጦሩ በግፍ የተጨፈጨፉበት መሆኑን ያስታውሷል።

ወደ ቲክቶክ ስንመለስ የምዕራባውያንን አመኔታ ለማግኘት ከፍተኛ ወጭ አውጥቶ የተጠቃሚዎችን መረጃ አሜሪካ በሚገኝ ሰርቨሩ ለብቻ ማስቀመጡንና ከቻይና ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ጓዳውን ከፍቶ ከፈለጋችሁ መጥታችሁ አረጋግጡ ቢልም በጀ ያለው አልተገኘም። አሜሪካና አጋሮቿ ግን ቲክቶክን ሞኝህን ፈልግ። አትድከም። አናምንህም። ይልቅስ በአሜሪካ ያለውን ድርሻህን ሽጠህ ራስህን አድን እያሉት ነው። ቲክቶክ ቢቸግረው ተጠቃሚዎቹን አድኑኝ ሲል ዘመቻ ከፍቷል። ወደ ፍርድ ቤት ለመሔድም እየተሰናዳ ነው። ከዚህ ሁሉ ውዝግብና እሰጥ አገባ በኋላ ቲክቶክ መቀጠል ቢችል ሁሉም ተጠቃሚ ይሆናል። ፈጠራንና ውድድርን ከማበረታታት ባሻገር ዘና ፈታም ያደርጋል ይለናል The Economist። በነገራችን ላይ አሜሪካ ቲክቶክ ላይ ጥርሷን መንከስ የጀመረችው ዛሬ አይደለም።

ሻሎም ! አሜን ።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን  ሚያዝያ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You