የባሌ ጎባ ልጅ ነች፡፡ ያለ አባት የምታሳድገውን የአራት ዓመት ልጇን ለመርዳት ወደ አዲስ አበባ ከመጣች ሦስት ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡ እናት፣ አባት፣ እህት እና ወንድም የላትም፡፡ ብቸኛዋ እናት ሠላም ጌታቸው ትባላለች (ስሟ የተቀየረ)፡፡ ልጇን ለአክስቷ ሰጥታ ነው ወደ አዲስ አበባ የመጣችው፡፡ በአንድ ሆቴል ጽዳት መሥራት ጀመረች፡፡ በሆቴሉ ምንም የሚቸግራት ነገር የለም፡፡ የሚሰጣት የወር ደመወዝ በየወሩ ለልጇ ትልካለች፡፡ በሂደት ወደ ሆቴሉ ጎኑን ለማሳረፍ ከሚመጣ ሰው ጋር ተዋወቀች፡፡ ትውውቃቸው አድጎ በፍቅር ለሁለት ዓመት ያህል ቆዩ፡፡
ይህ ሰው ለሠላም በጣም ጥሩ የሚባል ዓይነት ሰው ነበር፡፡ ‹‹አይዞሽ!›› ይላታል፡፡ ልጇን እንድታሳድግ ያበረታታል፡፡ ሠላም በጥቂቱም ቢሆን አይዞሽ የሚል ሰው በማግኘቷ ልቧ ያረፈ ይመስላል። ሰውነቷም ጨመርመር አለ፡፡ ነገር ግን የእርሷ መወፈር በተለየ መንገድ የታያት ጓደኛዋ ‹‹ምንድ ነው በጣም እየወፈርሽ እኮ ነው? የተፈጠረ ነገር አለ እንዴ?›› ብላ ብትጠይቃት ምንም የተፈጠረ ነገር እንደሌለ በልበ ሙሉነት መለሰችላት፡፡ መልሷ ያልተዋጠላት ጓደኛዋ ግን ወደ ሕክምና ተቋም ሄዳ ምርምራ እንድታደርግ አሳሰበቻት፡፡
ሠላም ሃሳብ ያዛት፡፡ ወደ ሕክምና ተቋም አቀናች። ስትመረመር ለእርሷ መርዶ የሆነ ነገር ተነገራት። ነፍሰጡር ናት፡፡ ለሁለት ዓመት በፍቅር ቆይተናል ላለችው ሰው ነገረችው፡፡ እርሱም ‹‹ታዲያ ምን ችግር አለው? እናሳድገዋለና›› አላት፡፡ በፍጥነት ክትትሏን እንድትጀምር ነገራት፡፡
እናት ለልጇ ያላትን ሁሉ ብር ስለምትልክ እጇ ላይ ምንም አይኖራትም፡፡ ‹‹በዚህ ብር ተመርመሪ›› ብሎ በሰጣት ብር አልትራሳውንድ ታየች፡፡ እርግዝናዋን ብታውቀውም ያላሰበችው ሆነ- መንታ መጸነሷ ተነገራት። ተደናገጠች፡፡ የምትሆነው ጠፋት፡፡ ዶክተሩ ዕድለኛ መሆኗን ቢነግራትም እርሷ ግን መውለድ እንደማትፈልግ ነገረችው። አሁን ምንም ማድረግ እንደማትችል እና ጊዜው እንዳለፈ ቢነግራትም ማሳቧን አላቆመችም ነበር፡፡ በተደጋጋሚ ‹‹መንታ መሆኑን ሲያውቅ ቢክደኝስ?›› ብላ ፈራ ተባ እያለች ነገረችው፡፡ ‹‹ያስብልኛል፡፡ ይረዳኛል›› ያለችው ፍቅረኛዋ ይህንን ከሰማ በኋላ እንደፈራችው ጥሏት ጠፋ፡፡ ‹‹አለ›› የተባለበት ቦታ ሁሉ ቢፈልግ ዱካውን ማግኘት አልተቻለም፡፡
አማራጭ አልነበራትምና ሥራዋን ቀጠለች፡፡ በሥራ ቦታዋ ሰዎች እግርዝናዋን በተለይም አለቃዋ እንዳታውቅባት ጥንቃቄ ታደርግ ነበር፡፡ አንድ ቀን ሥራዋን ጨርሳ ባለችበት ወቅት ድንገት ንፋሱ ልብሷን አነሳው፡፡ ሆዷን የተመለከተችው አሰሪም ተጠራጥራ ጠየቀቻት፡፡ እርሷም የተፈጠረውን ነገር በዝርዝር ተናዘዘች፡፡ ግራ የተጋባችው አሰሪዋ ‹‹በቃ ልጁን አዝለሽም ቢሆን ሥራሽን ትሠሪያለሽ፡፡ ››ብላ ብትነግራትም መንታ መጸነሷን ስትነግራት ምን መመለስ እንዳለባት ግራ ተጋባች፡፡
አሠሪዋ አንድ ሃሳብ አመጣች ‹‹ልጆቹ ከተወለዱ በኋላ ለምን ለመንግሥት አንሰጥም ?›› አለቻት ሠላምም በዚህ ሃሳብ ተስማማች፡፡ አለቃዋ ድጋሚ ሌላ ሀሳብ አመጣች። ልጆቹ ከተወለደ በኋላ የሚወስዱ ሰዎች መገኘታቸውን ነገረቻት፡፡ ልጆቹን ለመውሰድ አንዲት ሴት ከአለቃዋ ጋር ብዙ ንግሮችን ታደርጋለች፡፡ ሠላምን ግን አንድም ቀን አውርታት አታውቅም፡፡ ሁለቱ የማይተዋወቁ ሰዎች ስምምነት አደረጉ፡፡ ሠላም ልጆቿን ስለምትወስድላት ሴት ምንም መረጃ እንዳይኖራት እና ልጆቹም ከተወለዱ በኋላ ማን እንደሚወስዳቸው ዝርዝር መረጃ መጠየቅ እንደሌለባት ጭምር ተስማሙ፡፡
ሠላም ‹‹ልጆቼን ይዤ ጎዳና ከምወጣ ብትወስዳቸው ይሻላል›› ብላ የወለደች ቀን ልጆቿን ልትሰጥ ቃል ተግባቡ። የማይደርስ የለምና ሠላም ለወሊድ ወደ ዘውዲቱ ሆስፒታል ሄደች፡፡ ወንድ እና ሴት ልጆችን በሠላም ተገላገለች፡፡ ልጆቿን ለማታውቃት ሴት ለመስጠት ፈራ ተባ እያለች የአሰሪዋን የቅርብ ሰው መጠባበቅ ጀመረች፡፡
ሠላምን የስድስት ወር ነፍሰ ጡር ከሆነችበት ጀምሮ እስክትወልድ ድረስ የምትከታተላት ሴት ሃሳቧን ቀየረች። ልጆቹን እንደማትወስዳቸው አስረግጣ ተናገረች፡፡ ይህ ዜና ለሠላም እና ለአሠሪዋ መጥፎ ዜና ነበር፡፡ አራሷ እናት ይህንን ስትሰማ ቀኑ ጨለመባት፡፡ ምን እንደምታደርግ ግራ ገባት። ከወለደች ሰዓት ጀምሮ ሥራዋ ለቅሶ ብቻ ሆነ፡፡ መሄጃ የላትምና ዕድሏን ረገመች፡፡
በዚሁ ሁሉ ሂደት ግን አንዲት ዶክተር የሠላም ሁኔታ ትከታተል ነበርና ወደ መፍትሄው እንዲያመሩ አነጋገረቻት፡፡ እስከ ስድስት ወር የሚያርሳት ድርጅት መኖሩን አበሰረቻት፡፡ የዚህችን ሴት እና የልጆቿን ሕይወት የታደገው በጎ አድራጎት ድርጅት ‹‹የአምላክ ልጆች ፋውንዴሽን›› ይባላል፡፡
አዲስ ሕይወት
ሠላም ዛሬ በአራስ ቤት ጥሩ ቆይታ እያደረገች ነው። ልጆቿን እስከ ስድስት ወር ታቆያለች፡፡ እንዲሁም የእጅ ሥራ ስልጠና እየወሰደች ትገኛለች። ሠላም በትናንት ሃሳቧ ትጸጸታለች፡፡ ዛሬ ጠንካራ ሆናለች፡፡ አራት ወራትን በአራስ ቤት በጥሩ ሁኔታ እያሰለፈች ሲሆን፤ በአራስ ቤቱ ያሉ ሁሉ እያደረጉት ስላለው በጎ ነገር ምስጋናዋን ታቀርባለች፡፡ ከአራስ ቤት ወጥታ የተለያዩ የእጅ ሥራዎችን እየሠራች ልጆችን ለማሳደግ አስባለች፡፡
ደግሞ ሌላ ታሪክ
የአምላክ ፍቅር ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ጀምሮ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ እስከሚወጣ ድረስ ትምህርቱን የተከታተለው በአሜሪካ ነበር፡፡ ከምርቃቱ በኋላ ሀገሩን የማገልገል ራዕይ ነበረው፡፡ ግን አልሆነም። ሞት ቀደመው፡፡ ከተመረቀ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነበር በድንገት ሕይወቱ ያለፈው፡፡ የአምላክ እናት እና አባት ከጎኑ አልነበሩም፡፡ ከተራራቁ ረዥም ጊዜ ነበርና እንደተነፋፈቁ እስከወዲያኛው ተለያዩ፡፡ ያጡት የበኩር ልጃቸውን ነበርና ሀዘናቸው እጅግ በረታ፡፡
አቶ ፈቀደ ተፈራ ‹‹የአምላክ ልጆች ፋውንዴሽን›› ከመሠረቱት አንዱ ናቸው፡፡ በአሁን ወቅት የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ የወላጆቹ የቅርብ ሰውም ናቸው፡፡ እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎች ጎደኞቻቸው ሰብሰብ አሉ፡፡ የአምላክ ወላጆችን ለማጽናናት መምከር ጀመሩ፡፡ የልጃቸውን ስም ሊያስጠራ የሚችል ነገር ለማድረግ ‹‹ምን እናድርግ?›› ብለው ተጨነቁ፡፡ ብቻ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለባቸው ግን ወስነዋል። የአምላክ አባት ለሆኑት ለአቶ ፍቅር አለባቸው የልጃቸውን ስም ሊያስጠራ የሚችል ነገር ለመሥራት እንዳሰቡ ነገሯቸው።አባትም ልጃቸው ገና የ10 ዓመት እና የአራተኛ ክፍል ተማሪ እያለ ጽፎ ያስቀመጠው ራዕይ እንዳለ ተናገሩ፡፡ ልጃቸው ትምህርቱን ሲጨርስ ጎዳና ላይ ያሉ የሀገሩን ልጆች የመርዳት ራዕይ እንዳለው ጽፎ ነበር፡፡ አባትም ራዕዩን እንዲያሳካ የቻሉትን ሁሉ ሊያደርጉለት ቃል ገብተው ነበር፡፡ የአምላክ ባይኖርም አባት ግን ለቃላቸው ታመኑ፡፡
የአምላክ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ተፈጸመ፡፡ እነ አቶ ፈቀደም በቀብሩ ሥነ ሥርዓት ላይ በአምላክ ስም ድርጅት ለማቋቋም እንደታሰበ እና ለእዝን ተብሎ የሚወሰድ ውሃ፣ ቆሎ እና የመሳሰሉትን ከመስጠት ይልቅ ለሚመሠረተው ፋውንዴሽን ድጋፍ እንዲደርጉ የባንክ ሂሳብ ቁጥሩን በመንገር ይፋ አደረጉት፡፡
የአምላክ ሀሳብ
ያሰቡትን ድርጅት ለማቋቋም ብዙ ውይይቶች እና ምክሮችን ማድረግ ጀመሩ፡፡ ‹‹ልጆች ጎዳና መውጣት የለባቸውም፡፡›› የሚለውን የአምላክን ሃሳብ መሠረት በማድረግ ‹‹በአራት ምሰሶዎች ወይም ፒላርሶች ላይ መሥራት አለብን፡፡›› በሚለው ሃሳብ ተስማሙ፡፡ ልጆች ወደ ጎዳና እንዲወጡ ከሚያደርጋቸው ምክንያቶቹ አንዱ ፍቺ ወይም የቤተሰብ መናጋት ነውና እዚህ ላይ መሠራት አለብን አሉ፡፡ ሴቶች በተለይም የኢኮኖሚ ችግር ካለባቸው ለተለያዩ ችግሮች ሲጋለጡ ይስተዋላል፡፡ እነርሱን ባሉበት በገንዘብ በስልጠና እና በሌላ መንገድ መደገፍ ላልተፈለገ እርግዝናም ሆነ ጎዳና ላይ እንዳይወጡ ያግዛል የሚለው ጉዳይ ሁለተኛ ሃሳብ ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ጎዳና የወጡት ልጆች ደግሞ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚገናኙበትን ነገር እንፍጠር የሚል ይገኝበታል፡፡ አሁን አሁን ልጆቻቸውን ታቅፈው የሚለምኑ እናቶች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ እነዚህን እናቶች ‹‹አራስ ቤት›› ብለን እናቋቁማቸው በሚለው ሃሳብ ላይ ተስማሙ። ‹‹አራስ ቤት›› የአምላክ ልጆች ፋውንዴሽን በማለት በ2012 ዓ.ም ፈቃድ አገኝቶ ሥራውን ጀመረ፡፡
ዘመድ አዝማድ ለሌላት እናት ከወለደች በኋላ ለእርሷ እና ለልጇ የሚያስፈልጋትን አልባሳት እና የንጽህና መጠበቂያ በማዘጋጀት ለጤና ጣቢያ በመስጠት በጎ ሥራውን ጀመረ፡፡ እንዲሁም ሆኖ አንዳንዶቹ ልጆቻቸውን ሆስፒታል ጥለው ይሄዳሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ መጸዳጃ ቤት ይጥላሉ፡፡ የሚያርፉበት ቦታ አስፈልጎ ነበርና ቤት ተከራይተው ‹‹አራስ ቤት›› ለብቸኛዋ እናት መጽናኛ ሆነ። አራሶች በቤታቸው እስከ ስድስት ወር ድረስ እንዲቆዩ ይደረጋል፡፡ እንደ ገንፎ፣ አጥሚት እና ሌሎች ምግቦችን እየወሰደች ራሷን እና ልጇን እንድትንከባከብ ትደረጋለች፡፡
ወደ አራስ ቤት የመጣች እናት ጎኗ ጠንከር እስኪል ለአንድ ወር ምንም አይነት ሥራ አትሠራም፡፡አንድ ወር ከሞላት በኋላ ግን ወደ ማእድ ቤት በመውጣት በፕሮግራሟ መሠረት ሥራዎችን ትሠራለች፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ አራስ ቤት ያሉ እናቶች የነገ ሕይወታቸውን ምንም መምሰል እንዳለበት ይታሰብበታል፡፡ አራሶቹም ፍላጎታቸው ተጠይቆ በፍላጎታቸው መሠረት ስልጠና ይሰጣቸዋል፡፡ በአራስ ቤት ሁሉም ነገር የሚከወነው በፕሮግራም ነው፡፡ ለጨዋታ፣ ለሥራ፣ ለስልጠና እና ምግባቸውን የሚያበስሉት በፕሮግራማቸው መሠረት ነው፡፡ በየሳምንቱ ከሚመጡ በጎ ፈቃደኛ የሆኑ የሕክምና ባለሞያዎችም ‹‹እናት ደህና ልጅም ጤና›› እንዲሆኑ የጤና ክትትል ይደረግላቸዋል፡፡
በተጨማሪም እናቶች ከአራስ ቤት የመውጫ ጊዜያቸው ሲደርስ ልጆቻቸው የቤተሰብ ፍቅር አግኝተው እንዲያድጉ ከልጃቸው አባት ጋር እርቅ እንዲወርድ ፋውንዴሽኑ የቻለውን ሁሉ ያርጋል። በተመሳሳይ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲታረቁ በማድረግ እና ወደ መጡበት አካባቢ የመቋቋሚያ እና የቀለብ ገንዘብ በመስጠት ሽኝት ይደረግላቸዋል።
በአጋዥነት ከነልጆቻቸው ተቀብሎ ቅጥር እንዲያገኙ ብሎም ልጆቹ የቤተሰብ ፍቅር እንዲያገኙ የቻለውን ሁሉ እየሠራ ይገኛል፡፡ ከቅጥር አኳያ ስልጠና ወስደው የልጆች ማቆያ ቦታዎች ላይ የተቀጠሩ እናቶች ይገኙበታል፡፡ የንግድ ክህሎት ላላቸው ደግሞ ከስልጠና በሻገር የሦስት ወር የቀለብ እና የኪራይ ይከፍልላቸዋል፡፡ ምንም እንኳን የሥራ ቦታ እጥረት ፈተና ቢሆንም የሚያስፈልጋቸውን ግብአቶችን ይሟላላቸዋል፡፡ ከአራስ ቤት ወጥተው በባልትና፣ ቡና ጠጡ፣ እንጀራ በመጋገር በሌች ሞያዎች ውጤታማ የሆኑ እናቶች አሉ፡፡ ትምህርታቸውን ያቋረጡ እናቶች ካሉም እንዲቀጥሉ ያደርጋል፡፡
የአምላክ ወላጆች ዛሬ ተጽናንተዋል፡፡ ‹‹ፈጣሪ የአምላክን ወስዶ ብዙ ልጆችን ሰጠን፡፡ ›› ይላሉ። የሆነባቸው ሁሉ ለመልካም እንደሆነ በማሰብ ብርታትን አግኝተዋል፡፡ ዛሬ የት ልሂድ ያለች፣ የተጨነቀች፣ ግራ የገባት አራስ እናትን ለማጽናናት ተችሏል፡፡ በአሁን ወቅት 24 እናቶች ከነልጆቻቸው እየታረሱ ይገኛል፡፡
ፋውንዴሽኑ 300 መቶ አባላት አሉት፡፡ ከአባላቱ ከሚገኘው ገንዘብ እና ከደጋፊ አካላት በሚያገኘው የገንዘብም ሆነ የዓይነት ድጋፍ የብዙ እናቶችን አብሷል። በርካታ ልጆችን ከጎዳና ሕይወት ታድጓል፡፡ አራስ ቤቱን ይህንን ሲያደርግ ግን ፈተናዎች አልገጡሙትም ማለት አይደለም፡፡ የቤት ኪራይ ክፍያ እና የኑሮ ውድነቱ ለድርጅቱ ተርፏል፡፡ የስኳር እና መሰል ምርቶችን ለማግኘት አዳጋች ሆኖበታል፡፡ ምሽት ላይ እናት ወይም ልጅ በድንገት ሲታመሙ የሚያወጣው የትራንስፖርት ገንዘብም ሌላኛው ፈተና ነው፡፡
ዛሬም ቢሆን ድጋፍ የሚሹ ብዙ ሴቶች አሉ፡፡ ፍላጎቱ ብዙ ቢሆንም ለሁሉም መድረስ ግን አዳጋች ሆኗል፡፡ እንዲህም ሆኖ እናቶችን ከሆቴሎች እና ከሌሎች ተቋማት ጋር በጋራ ለመሥራት ሙከራ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ አራስ ቤትን ከአዲስ አበባ ውጭ ለመሥራት ፍላጎት እና እቅድ አለ፡፡ ይህ የሚሳካው ግን ደጋፊ አካላት ድርጅቱን ሲደግፉ እና ሲያበረቱ ብቻ ነው፡፡
የዚህ ሁሉ በጎ ሥራ የአምላክ ፍቅር ራዕይ ነውና ከራዕዩ በእርሻ ስራ መሰማራት ዕቅድ አለው፡፡ ከእርሻ ከሚገኝ ገንዘብ ብዙዎችን ለመደገፍ የሚል ይገኝበታል። የእርሻ ቦታው ለማግኘት ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ከትምህርት አኳያም ለእናቶቹ መዋዕለ ሕጻናት በመክፈት ልጆቻቸውን እዛው በማስተማር ኑሯቸውን እንዲያቀኑ አቅዷል፡፡
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2016 ዓ.ም