ሴት ልጅ በእናት፤ ሴት ልጅ በሚስት፤ ሴት ልጅ በልጅ፤ ሴት ልጅ በእህት፤… ተመስላ የምትገለጽባቸው በርካታ ሁነቶች አሉ፡፡ እነዚህ ምስለ ገለጻዎች የሴት ልጅን ቅርበት፤ የሴት ልጅን ሁለንተናዊ ክሱትነት፤ የሴት ልጅን ክብርና ፍቅር ተለጋሽነት፤… ከፍ አድርገው የሚናገሩ ናቸው፡፡
ለምሳሌ፣ ሴት ልጅ እናት ናት፤ የሚለው ገለጻ፣ ሴት ልጅ የሁሉ ነገር መነሻ፤ የነገሮች መከሰቻ ዓውድ መሆኗን አመላካች ነው፡፡ ምክንያቱም፣ እናትነት ፍቅር ነው፤ እናትነት ትኅትና ነው፤ እናትነት ፈጣሪነት ነው፤ እናትነት ሠላም ነው፤ እናትነት የሁሉ ሆኖ መገለጥ ነው፤ እናትነት ሰውን ሠርቶ ሰው የማድረግ ኃላፊነት ነው፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ እናትን በሀገር እንመስላታለን፡፡ ይሄ ደግሞ ኢትዮጵያውያን እንደ ሕዝብ ለሀገራቸው ካላቸው ክብርና ፍቅር ይመነጫል፡፡ ስለ ሀገራቸው ፍቅር በቃል ይናገራሉ፤ ስለ ሀገራቸው ክብርና ሉዓላዊነት አንድያ ነፍሳቸውን ሳይቀር አሳልፈው ይሰጣሉ፡፡
እናም እናትን በሀገር ሲመስሉ፤ በወል ለሀገራቸው ያላቸውን ከፍ ያለ ዋጋ ሁሉም ስለሚገነዘበው፤ ለእናትም ክብርና ፍቅር ያን ያህል ዋጋ የሚሰጡ መሆኑን ለመግለጽ ነው፡፡ ኢትዮጵያን በፍቅር ቃል “አንቺ” ብሎ በሴት መስሎ የሚጠራት ኢትዮጵያዊም፤ በሀገሩ ስያሜ ውስጥ የእናቱን/የሴትን ክብርና ፍቅር በአደባባይ እያወሳና እየገለጠ መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም፡፡
ዛሬ ላይ የዓለማችን ግማሽ ያህል ሕዝብ ሴቶች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያም ወደ 49 በመቶ የሚሆነው የሕዝብ ቁጥር በሴቶች የተያዘ ነው፡፡ እናም እነዚህ ሴቶች ናቸው በኢትዮጵያውያን ዘንድ በኢትዮጵያ ተመስለው ያሉት፡፡ እነዚህ የሀገር አምሳያ ሴቶች ናቸው፡፡ እናት፣ ሚስት፣ እህትና ልጅ ተብለው የሚገለጹት፡፡
ይሄ ገለጻ እና የማመሳሰያ ሁኔታ ሲታሰብ፣ ሴትነት በእጅጉ ከፍ ይላል፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ ገለጻና ምስያ ከፍታ ባሻገር ሊታሰቡም፣ ሊታረሙም የሚገባቸው አያሌ ጉዳዮች አሉ፡፡ ሴቶች በተመሰሉበት ገጽ፣ በተነገሩበት ልክ እንዳይታዩ የሚያደርጉ በርካታ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሌሎችም ጫናዎች በዙሪያቸው ተብትበው ይዘዋቸዋል፡፡
በዚህ ረገድ እኛ ኢትዮጵያውያን ከታሪክና ሁነት አኳያ የተሻለ የሴቶችን ከፍታ መግለጽ እንችል ይሆናል፡፡ ዓለም ዛሬ ላይ ለሴቶች መብትና ጥቅም እያወራ የዘለቀበትን 113ኛ ዓመት ሲዘክር፤ እኛ ግን ሴቶቻችን በአመራርም በተመሪም ደረጃ ሆነው ወራሪን ድል የነሱበትን 128ኛ ዓመት አክብረናል፡፡ ይሄ ደግሞ የዓለም ኃያላን እንኳን ስለ ሴቶች መብትና ጥቅም ይሁንታን ከመስጠታቸው በፊት፤ ኢትዮጵያ በሴት ልጆቿ መሪነት፣ በሴት ልጆቿ ብልሃት፣ በሴት ልጆቿ አቅምና ብርታት ታግዛ በዓለም ፊት ደምቆ የሚታይ ታሪክና ገድል ባለቤት መሆን ስለመቻሏ ሕያው ምስክር ነው፡፡
ይሁን እንጂ ይሄ የሴቶች መሪነት፣ ብልሃትና አቅም በሚፈለገው ልክ እንዳይወጣ፤ ሀገርም ከሴት ልጆቿ ልታገኝ የሚገባትን ሁሉ በሙላት እንዳታገኝ የመሆኗን ሐቅ የምንክደው አይደለም፡፡ ይሄ ደግሞ ዓለም የወንዶች ብቻ መስላ እንድትገለጽ ያደረገ፤ ስለ መብትና ዴሞክራሲ በኩራት የሚናገሩ ኃያላን ሳይቀር ሴቶችን በመሪነት ዙፋን ላይ መሰየም የቋጥኝ ያህል ከብዷቸው ሳይሞክሩት ዛሬም ድረስ እንዲዘልቁ ያደረጋቸው ነው፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያንም ከትናንት እስከዛሬ ሴቶችን ወደፊት የማምጣቱ ልምድ ያለ ቢሆንም፣ አንድም ከቁጥራቸው አኳያ በሚገባቸው ልክ፤ ሁለተኛም ከአቅማቸው አኳያ የሚገባቸውን ቦታ አግኝተዋል ብሎ አፍን ሞልቶ ሊያናግር የሚችል አይደለም፡፡ ከዚህም በላይ ሴት ልጅን እናት አልያም ሀገር ብለን የመሰየማችንን ያህል፤ እናት አልያም ሀገር ሊገባት የሚችለውን ነገር አላደርግንላቸውም፡፡
ምክንያቱም እናት ሠላም ትፈልጋለች፤ እናት ልጆቿን ያለ ልዩነት አቅፋ ማኖር ትሻለች፤ እናት ለልጆቿ የምታጎርሰው አጥታ እጅ እንዳያጥራት፣ የልጆቿንም ሕመምና ስቃይ ያለማየት፤… ከፍ ያለ ሕልምና ፍላጎት አላት፡፡ ልጆቿ ሲራቡ፣ ሲሰደዱ፣ ሲጣሉና ሲዋጉ፣ ሲነጣጠሉና በቂም በቀል ሲገዳደሉ ማየትን ፈጽማ አትሻም፡፡ ይሄ የሴት ልጅ ፍላጎት፤ የእናትነት ፀጋ መገለጫ ነው፡፡
ሴት ልጅ እንደ እናት እነዚህን ሕልምና ምኞቶቿን ስታጣ ታዝናለች፤ ጥልቅ ቁዘማና ድባቴ ውስጥ ትገባለች፤ ትጎሳቆልና የሰቀቀን ኑሮን ትኖራለች፡፡ ስለ ሠላም መስፈን፤ ስለ ልጆቿ ፍቅርና አብሮነት፤ ስለ ልጆቿ በልቶ ማደርና ማደግ፤… አብዝታ ትሰቃያለች፡፡ የልጆቿን በሠላም ወጥቶ መግባት፤ ወንድማማችነትና አብሮነት፤ መተባበርና በጋራ መቆም፤… እውን መሆን በጭንቅ ውስጥ ሆና ትጠባበቃለች፡፡
እነዚህ ጭንቀትና ተስፋዎች፤ ስጋትና መሻቶች፣… የእናትነት ተፈጥሯዊ ባሕሪ፣ የሴትነት መገለጫዎች፤ በጥቅሉም ስብዕናዋ ናቸው፡፡ ታዲያ ሴት እንደ ሴት፤ እናትም እንደ ሀገር ምሳሌነት ይሄ ጭንቀትና ስጋቷ ተቀርፎ፤ ተስፋና መሻቷ ሞልቶ ማየት የሁሉም ኃላፊነት መሆን ይኖርበታል፡፡ የማርች ስምንትም እሳቤውም ይሄው ነው፡፡ ሴቶችን የማክበር፣ ሴቶችን የማገዝና የማብቃት፤ ሴቶችን ወደሚገባቸው ቦታና ክብር ማድረስ፤… ነው፡፡
በመሆኑም የሴቶች ቀንን ስናከብር፣ ሀገር ያልናትን እናት፤ እናት ያልናትን ሴት ሕልም እውን ለማድረግ፤ መሻቷን ለመፈጸም በመነሳሳት ውስጥ ሊሆን ይገባል፡፡ በሠላም እጦት፣ በስደትና ጦርነት፣ በኢኮኖሚ ችግርና ሌሎችም ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ሥነልቡናዊ ጫናዎች ውስጥ የምትከፍላቸውን ያልተገቡ ዋጋዎች ለማስቀረት፤ ዓለምንም ለሴቶች ቦታ ያላትና የተመቸች ለማድረግ ሁላችንም ቃል በመግባት ውስጥ ሊሆን ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 30 ቀን 2016 ዓ.ም