ሰዎች በተለያየ መንገድ የሀብት ባለቤት ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን ሀብታቸውን ለማስተዳደር እውቀት እና ብልሀት ከሌላቸው ያላቸውን ሀብት እንደያዙ ላይቆዩ ይችላሉ። የሥራ ጥንካሬ ፣ ትጋት እና ህልም በውስጣቸው ያሉ ሰዎች ደግሞ በዙርያቸው ያለውን ትንሽ ነገር ተጠቅመው በማሳደግ እና ያልተገደበ ጥረትን በማድረግ የሀብት ባለቤት ይሆናሉ። ሀብታቸውም በሚታየው ቁሳቁስ ብቻ ሳይሆን ይህንን ለማድረግ የለፉባቸው ዓመታት ውስጥ ያሳለፉት ውጣውረድ የሚመነዘር የሕይወት ልምድም ጭምር ይሆናል።
ብዙዎች የተለየ ሚስጢር እንደያዙ አድርገው ልምዳቸውን ይጠይቋቸዋል። ለሌሎች ሰዎች ተምሳሌትና ፣ ሞራል ይሆናሉ። የዛሬው የሴቶች ቀን ልዩ እትም እንግዳችን ከቤተሰቦቿ ያገኘችውን ጥቂት ሀብት ተጠቅማ የምትሠራዋን አርሶ አደር እና አርብቶ አደር የሥራዋን ጥንካሬ ሰምተን ቤቷ ተገኝተናል። ሰው አክባሪ እና ፈገግታ የማይለያት ናት። ሱሪዋን ታጥቃ ለከብቶቿ የሚሆን ገለባ ትከምራለች።
ሰላምታ ከሰጠችን በኋላ ወደ ቤቷ እንድንገባ ጋበዘችን። ቤቷን ላየ ባንዲት ትንሽዬ ቀበሌ ገበሬ ማህበር የሚገኝ አይመስልም። እጅግ አስውባ ሠርታዋለች። የቤት አያያዟም ታታሪነቷን ያሳብቃል። ማን ትሆን እያላችሁ እንደሆነ አስባለሁ። እንግዲህ እናስተዋውቃችሁ መልካም ንባብ …..
አስናቀች ያደታ ትባላለች። ተወልዳ ያደገችው ከአዲስ አበባ ከተማ በ140 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በሔጦሳ ወረዳ በኦዳ ጂላ ቀበሌ ውስጥ ነው። ለቤተሰቦቿ የመጨረሻ ልጅ ናት። እናትና አባቷ በልጅነቷ ሲለያዩ ልጆች የማሳደግ ሃላፊነት በብቸኛዋ እናቷ ላይ ይወድቃል። አራት ልጆችን ለብቻ ማሳደግ ቀላል ያልሆነላት እናት ሶስት ልጆቿን አያቶቻቸው ዘንድ ያድጉ ዘንድ ለወላጆቿ ሰጠች። ነገር ግን የመጨረሻ ልጇ የሆነችውን አስናቀችን ደግሞ ከእርሷ ጋር ለማሳደግ ወሰነች። የአስናቀች እናት ለብቻዋ የእንጀራ ምጣድ መክደኛ የሆነውን አክንባሎ እየሸጠች ልጇን ማሳደጉንና ኑሮዋን መግፋቱን ተያያዘችው።
አስናቀች ልክ እንደ እኩዮቿ ወደ ትምህርትቤት ብትገባም እስከ ስድስተኛ ክፍል ከተማረች በኋላ ግን ችግር ትምህርቷን እንድታቋርጥ አደረጋት። ከእናቷ ጋር የምትኖረው አስናቀች ችግርን ለመረዳት የእናቷን ጭንቀት ለማስተዋል ደርሳለች እና እንዲሁ መቀመጡ በጎ ሆኖ አላገኘችውም። ስለዚህም እንደ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ቤተሰቦቻቸውን ለመደገፍ እና ችግርን ለማሸነፍ እንደሚያደርጉት ወደ አረብ ሀገር አቀናች።
አስናቀች ፣ በአረብ ሀገር በመጀመሪያ የገባችበት ቤት ጊዜያዊ ነበር። በአረብ ሀገራት በየሰው ቤት የሚሠሩ ሴቶች ከአሰሪዎቻቸው ብዙ በደል እና ከፍተኛ የሥራ ጫና ይደርስባቸዋል። አስናቀችም በምትሠራበት ቦታ የነበረውን ጊዜም ስታስውስ ‹‹ደመወዜን ይከለክሉኛል፤ ሊደበድቡኝ ይነሳሉ።›› ትላለች። አስናቀች በዚህ ቤት ውስጥ ከአንድ ዓመት ከሶስት ወር በላይ ልትቆይ ባለመቻሏ ከአቅሟ በላይ ሲሆን ጠፍታ ወደ ሌላ አሠሪዎች ቤት ገባች። ከአንዱ ቤት ወደ አንዱ ቤት እየተንከራተተች በአረብ ሀገር ለአምስት ዓመት ያክል ቆየች። በዚህ መሀል ግን እናቷ ታመመች ፤ የናቷን መታመም ሰምታ በሰው ሀገር መቀመጥ አላስችል አላት። ወደ ትውልድ ሀገሯ ተመለሰች። ነገር ግን ከእናቷ ጋር መኖር ከጀመረች ብዙም ሳትቆይ ከአንድ ወር በኋላ እናቷ አረፉ። እናቷ በሕይወታቸው እስኪያልፍ ድረስ ትደግፋቸው የነበረችው አስናቀች ነበረች። አባቷም ያረፉት እናቷ ከማረፋቸው ከጥቂት ወራት ቀደም ብለው ነበር።
አስናቀች ከዚህ በኋላ በእናቷ ቤት ሆና ኑሮዋን ቀጠለች። ‹‹እናቴ አክንባሎ ሽጣ ስላሳደገችኝ ሥራ አልንቅም›› የምትለው አስናቀች ከአባቷ ባገኘችው ውርስ የተሰጣትን አንድ ሄክታር ተኩል መሬት ይዛ ሥራ መሥራት ጀመረች። ከአረብ ሀገር ስትመጣ የነበራትን 60 ሺህ ብር ለእናቷ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ላይ አውጥታ ስለነበር በተረፋት ብር በአቅራቢያዋ ካሉ ሰዎች ትንሽዬ ጊደር እና አንድ በሬ ገዛች፣ የገዛቻት ጊደርም ማደጓ አልቀረም፤ አድጋ ወለደችላት። ከዛም ባለፈ ለመሥራት ከፍተኛ ጉጉት ስለነበራት የነበራትን ሰባት ግራም ወርቅ የአንገት ሀብል ሽጣ ጠምዶ ለማረስ ያስችላት ዘንድ አንድ ተጨማሪ በሬ ገዛች።
አስናቀች ከውርስ ያገኘችውን እና የእናቷን ሀብት ይዛ ሥራዋን እየሠራች ከዚያም ትዳርን መሠረተች። በትዳር በቆየችባቸው ዓመታት አንድ ወንድ ልጅ ልታፈራ ችላለች። ነገር ግን ልጅ ያፈራበት ትዳሯ ሊቆይ ባለመቻሉ ከባለቤቷ ጋር ተለያይታ እንደገና ሕይወቷን መኖር ቀጠለች። ባለቤቷም ከተለያዩ ከሁለት ዓመት በኋላ አረፈ። አስናቀች ችግር ብዙ ቢፈትናትም ካሰበችው እንድትቀር አያደርጋትም ኀዘኗንም ችግሯንም ይዛ ሕይወቷን ለመለወጥ የተለያዩ መንገዶችን ትፈልጋለች ትሞክራለች።
አስናቀች በአሁኑ ሰዓት የምትኖረው ከልጇ እና ከታላቅ ወንድሟ ጋር በሠራችው መኖሪያ ቤት ሲሆን ከወላጆቿ ያገኘችው መሬት ጦሙን ማሳደር የማይታሰብ ነው። ከእናቷ ያገኘችው ሁለት ሄክታር መሬት በዓመት እስከ 70 ኩንታል የስንዴ ምርት ታስገባለች። የምትዘራው እህልም እንደየወቅቱ ይለያያል። አስናቀች ለምታርስባቸው በሬዎች ውጪ ሁለት ወተት የሚሰጡ ላሞች እና አንድ ክበድ ላም አላት። አስናቀች አልባ ያዘጋጀችውን ወተት አንዳንዴም በባጃጅ በብዛት ግን በጋሪ ታደርሳለች። ራሷ ያለበችውን ወተት በቀን ሁለት ጊዜ ጋሪዋን እየነዳች ከምትኖርበት ቀዬ በሰባት ኪሎ ሜትር ርቃ ወተቱን ለሚረከቧት ሰዎች ታደርሳለች። በአንድ ቀንም እስከ 18 ሊትር የሚደርስ ወተት ታቀርባለች። ጋሪዋን እየነዳች ለሚያዩዋት እና እንድታቆም ለሚነግሯት ሰዎች አስናቀች ፍጹም ቦታ የላትም። በትንሹም ለምታቀርበው ወተት በቀን ውስጥ ከ500 እስከ ሁለት ሺህ ብር ገቢ ታገኛለች። አስናቀች በቤቷ ውስጥ እንዲሁ ፈረሶችም አሏት።
ታታሪዋ አስናቀች የስድስት ዓመት ልጇን ታዲዮስ ኦሳን ትምህርት ቤት በትምህርቱ እንዲበረታ መክራ ትልከዋለች። ለብቻዋ በምትሠራው ሥራ እና በምትመራው ሕይወት ደስተኛ መሆኗን ትናገራለች።
‹‹ሥሰራ የሚያዩኝ ወንዶች ጎበዝ ነሽ ይሉኛል፤ ሴቶች ግን ትጎጃለሽ ተይ ይሉኛል። ›› ያለእረፍት ስትሠራ ከሚያዩዋት ሰዎች የሚደርሳት አስተያየት መሆኑን ትናገራለች። ልጆቻቸውን ለብቻቸው ለሚያሳድጉ እናቶችም ማንኛውንም ሥራ አትናቁ ምክሯ ነው።
በሀገራችን አሁንም ድረስ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ሴቶች ወደ አረብ ሀገር ያልፍልኛል ብለው ይሰደዳሉ። ‹‹ አረብ ሀገር ብዙ ፈተና አለ። በሰው ሀገር መሞትም ማጣትም አለ ሰው ሀገር ሄደው መንከራተትም አለ፤ ሴቶች የሚያገኙትን ገንዘብ ብቻ አይተው አይሂዱ።›› የምትለው አስናቀች በሰው ሀገር እየሠሩ ጉልበታቸውን ከሚፈጁ እና የሰው ሀገር ከሚያሳድጉ በሀገራቸው ከትንሽ በመጀመር መለወጥ ይችላሉ ትላለች። ‹‹ ሀገራችን ለሚያውቃት ሰው ወርቅ ናት። ለማያውቅ ሰው ደግሞ ይከብዳል።›› ይህ የአስናቀች ምልከታ ነው።
አስናቀች ከብቶች ትልቅ ሀብት በመሆናቸው እንደ አንዲት አርብቶ አደር እና አርሶ አደር አስፈላጊውን እንክብካቤ ሳትሰለች ታደርጋለች። የምታገኘውንም ገቢ በአግባቡ ታስተዳድራለች። አሁን የምትኖርበት ባለ56 ሉክ ቆርቆሮ ቤት የሠራችው ራሷ ናት። አሁን ያላት ባላት ሀብትም ሆነ ንብረት በቃኝ አላለችም። በዚሁ ሥራዋ ከዚህ የተሻለ ደረጃ ላይ ለመድረስ እና በከተማ ቤት እና መኪና በመግዛት ከዚህ የተሻለ ትልቅ ደረጃ መድረስ በእቅዷ ውስጥ አለ።
ከአረብ ሀገር ይዛ በመጣችው ገንዘብ የገዛቻቸው ጊደር እና ወይፈን አድገው ፣ መሬቷም እየታረሰ ምርቷን እየሰበሰበች ፣ ላሞቿም እየታለቡ ዛሬ ላይ ወደ ዘጠኝ የሚጠጉ ከብቶች ፣ ሁለት ፈረስ ፣ ሶስት አህያዎች ፣ የምታረባቸው ዶሮዎች እንዲሁ አሏት። ይህ እንዲሁ ሳይሆን በሥራ እና በትጋት ስለመሆኑ አስናቀች ማሳያ ናት ። ‹‹ አንድ ዶሮ ነው ያለችኝ ተብሎ ያቺን ዶሮ እንዲንቁ አልፈልግም። ምክንያቱም ያቺ ዶሮ እንቁላል ትጥላለች፣ እንቁላሏን ይሸጧታል። ከዚያ ደግሞ እቁብ ይገባሉ ፤ ሌሎች ዶሮዎች ይጨምራሉ እያደገ ይሄዳል። ›› ይህ ሲታይ የሚሆን የሚሳካ አልያም ቀላል ነገር ቢመስልም ማረጋገጫው ግን አስናቀች ናት። ‹‹ በመጀመርያ በአራት ሺህ 500 ብር የገዛኋት ላም ስትወልድ እሷን በ34 ሺህ ብር ሽጬ ለከብቶች የሚያገለግል ማደሪያ ሰራሁላቸው።” ትላለች። የነበርኩበትን እና አሁን ያለሁበትን ሰዎች ያውቃሉ የምትለው አስናቀች ‹‹ እናቴ አክንባሎ ሽጣ ስላሳደገችኝ ሥራ አልንቅም ›› መርኋ ነው።
መክሊት ወንድወሰን እና ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን የካቲት 29 /2016 ዓ.ም