የኮማንዶና አየር ወለድ ማሰልጠኛ ማዕከል የሴቶች ጉዳይ አመራር ናት – ሻምበል ትቅደም ወርቁ። የተወለደችው በኦሮሚያ ክልል፣ በቡሌሆራ ቡዳ መጋዳ አካባቢ ሲሆን፣ ያደገችው ደግሞ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ ነው። ትምህርቷን የተከታተለችው እዛው ዲላ ውስጥ ነው። ትምህርቷንም እስከ አስረኛ ክፍል ከተማረች በኋላ መከለከያን ተቀላቀለች።
ብዙዎቹ ልክ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ፍላጎታቸው የነበረው የመንግሥት ሥራ ፈልገው መቀጠር ነው የምትለው ሻምበል ትቅደም፣ እኔም ልክ እንደእነርሱ ሁሉ በመንግሥት መሥሪያ ቤት ተቀጣሪ መሆን የሚያስችለኝን ትምህርት ገፋ አድርጌ እቀጥላለሁ የሚል ነገር ነበረኝ ትላለች። ነገር ግን ይህ በሃሳብ ደረጃ የተያዘ እንጂ ምርጫዬ የነበረው ሀገሬን በውትድርናው ዘርፍ ማገልገል ስለሆነ አስረኛን እንዳጠናቀቅሁ ምርጫዬ ወደሆነው ውትድርና ለመግባት በቃሁ ስትል ትገልጻለች። እኔ ውትድርናን ምርጫዬ አድርጌ የገባሁት ዓላማ ስላለኝ ነው፤ ስገባም ነገሮች ቀላል ይሆናል የሚል እምነት አልነበረኝም›› ትላለች።
ወስኜ ገብቻለሁ፤ ለወሰንኩት ነገርም ዓላማ አለኝ። በርግጥ ነገሮች እንዳሰብኩት ላይሄዱ እንደሚችሉ እረዳለሁ፤ ይሁንና እሱ ግን ከውሳኔዬና ከዓላማዬ ቸል እንድል አላደረገኝም። እንደምወጣው አውቅ ነበር። ምክንያቱም ይታየኝ የነበረው የትልቅ ሀገር ልጅ መሆኔ ነው። ሀገር በእኛ አዕምሮ አይለካም። ስለዚህ ትልቅና ሰፊ የሆነውን ነገር ለመሸከም ትከሻዬ ሰፊ መሆን አለበት። ትከሻዬ ሲሰፋና አዕምሮዬ ሲዳብር እሰራለሁ ብዬ በገባሁት ነገር ላይ በቁርጠኝነት እደርሳለሁ ትላለች።
እኔ ሀገሬን በውትድርና ለማገልገል ስለመረጥኩ እጅግ ደስተኛ ነኝ። ወደዘርፉ የገባሁት ያለምንም ግፊት ራሴ ነኝ። የወሰነልኝ ማንም የለም። ዛሬ የሻምበል ማዕረግ አለኝ፤ ነገ ደግሞ ከፍ ያለው ቦታ ላይ እደርሳለሁ። ለዚህ ደግሞ ጾታዬ አይከለክለኝም፤ ትናንትም አልከለከለኝም ትላለች። በውትድርናው ዓለም 19 ዓመት የቆየች ሻምበል ትቅደም፣ ውትድርናውን የተቀላቀለችው በ1997 ዓ.ም ነው። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ትዳር መስርታ የሁለት ልጆች እናት መሆን ችላለች።
እርሷ፣ እናትነት በውትድርናው ዘርፍ ተሰማርቶ ሀገርን ከማገልገል አያግድም ትላለች። ሻምበል ትቅደም፣ ለሀገሯ ወታደር፤ ለልጆቿ ደግሞ እናት ናት። ሀገር ትጋቷን፤ ልጆች እናትነቷን ፈልገው አላጡም። እርሷ ለሁሉም ራሷን አልሸሸገችም። ሁሉም በሚፈልጓት ዓይነት ሁኔታ ተገኝታላቸዋለች። ይሁንና በዚህ መካከል አስቸጋሪ ጊዜያት አላለፉም ማለት እንዳልሆነ ትናገራለች። እነዚያን አስቸጋሪ ጊዜያት በብልሃት ማለፍ ችላለች።
በሥልጠና ወቅት ሴትነት ፈተና አይሆንም ብሎ መደምደም አይቻልም የምትለዋ ሻምበል ትቅደም፣ “ፈተናዎች ይኖራሉ። ነገር ግን እነዛ ፈተናዎች ከዓላማዬ አላስቀሩኝም። በተለይ ደግሞ ማዕረግ እየጨመረ፣ ልምድም እየዳበረ በመጣ ቁጥር ፈተናውም የዚያኑ ያህሉ ጠንካራ ይሆናሉ።” ትላለች።
በተለይ ደግሞ የአየር ወለድ ሥልጠና በቀላሉ የሚገመት አይደለም። ምክንያቱም፤ በምድር ላይ የሚደረጉ ሥራዎችም ሆኑ ሥልጠናዎች በብዙ ላይፈትኑ ይችላሉ። በእንቅስቃሴ ጊዜ እንቅፋት ቢመታን እንኳ የሆነ ነገር ይዤ አሊያም ታክኬና ተደግፌ እተርፋለሁ ተብሎ ሊታሰብ ይችላል። ተንደርድረን ልንቆምም እንችላለን። እንተርፋለን ብለንም ልናስብ እንችላለን ስትል የምታስረዳው ሻምበል ትቅደም፣ የአየር ወለድ ሥልጠናው ግን እንደእሱ ዓይነት ነገር አይታሰብም፤ ተንደርድሬ እቆማለሁ ማለት አይቻልም። የሆነ ነገር ይዤ እተርፋለሁ ይሉት ምኞት አይሰራም። ከአየር ላይ በገመድ መወርወር ነው። ይህ በራሱ አንድ ፈተና ነው። ይሁንና ያም ቢሆን ሴት አትችልም የሚል ነገር የለም፤ ሴትም እሱን ታደርገዋለች፤ አድርገዋለችም። እኔም ተወጥቼዋለሁ። አምስት ጊዜ በመዝለሌም ዊንጉን አግኝቻለሁ። ከዛ በላይ ግን ገፍቼ አልሔድኩም። ዊንግ ለማሻሻል የሚዘለለውን ሌላውን ዝላይ አልገፋሁበትም።” በማለት ትናገራለች።
እርሷ፣ ለሴቶች አንድ ምክር አለኝ ትላለች፤ ሴቶች አንድ ብሂል አላቸው፤ ከወንድ አላንስም የሚል። እሱ ነገር በፍጹም ሊኖር አይገባም ባይ ነኝ። እኔ የምለካው በእሱ አይደለም። እኔ የምለካው በእኔነቴ ነው። እኔ የምለካው በአቋሜ፣ በዓላማዬ እና በሥራዬ ነው። ስለዚህ ‘እሷ እኮ ከወንድ እኩል ናት። ከወንድ አታንስም’ የሚሉት ነገር ሴቶችን የሚገልጽ ነው ብዬ አላምንም። ሴት ሴት ለመሆን ፈልጋ አልተፈጠረችም፤ ወንድም እንዲሁ። ርግጥ ነው ሴቶች ላይ ተጽዕኖች የሉም ማለት አይደለም። አንዳንዴ የቱንም ያህል እውቀት ቢኖራትም ለዚህ ቦታ አትመጥንም የሚለው አካል ይበዛል። ይህ በራሱ ፈተና ነው። እንዲያም ቢሆን እኛን ሴቶች ምንም ዓይነት አባባል እንዲገድብን ዕድል አንስጠው። የምንሰራው ሥራ በፉክክር ዓይነት አካሄድ ሳይሆን በዓላማ ይሁን።” ትላለች።
ሀገርሽ የት እንድትደርስ ትፈልጊያለሽ
ሀገሬ! እምዬ! ታላቅ ደረጃ ላይ ደርሳ ማየት ምኞቴ ነው፤ ምኞት ብቻ ሳይሆን ኃላፊነቴን ለመወጣትና ሌሎች ለሚሰሩ መልካም ሥራዎች እተባበራለሁ። የሀገሬ አፈር ተቆርሶ የሚበላ ነው። የሀገሬ አየር ተቀድቶ የሚጠጣ ነው። ትርፍ ሀገር የለኝም፤ እንዲኖረኝም አልሻም። በፊት ልጅ እያለሁ ሰዎች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ይዘው ሲያለቅሱ የሚያስመስሉ እንጂ እውነት አይመስለኝም ነበር። አሁን አሁን ላይ የሀገሬ አፈር ጠረኑ ራሱ ለእኔ መድኃኒቴ እንደሆነ ተረድቻለሁ። ያለኝ አንድ ሀገር ነው። ሌላ የትም መሄጃ የለኝምና ሀገሬን አክብራለሁ ስትል ትናገራለች።
እንደ እርሷ አባባል፤ እኛ የሚያምርብን ስንዋደድ እንጂ ስንጋደል አይደለም። አንዳችን ለሌላችን እናስፈልጋለን፡ ፤ የሚያምርብን መስማማት ነው፤ ፍቅር ነው። ስለዚህ ተባብረንና ተግባብተን ሀገራችንን ትልቅ ደረጃ ላይ እናድርስ፤ ሀገራችን ትልቅ ደረጃ ላይ ደረሰች ማለት እኛም ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ እንችላለን ማለት ነው።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን የካቲት 29 /2016 ዓ.ም