ከቀናት መካከል በአንዱ የሌሊት ተረኛ ጥበቃ ላይ ተሰማርታለች። ጊዜው ውድቅት ነው፤ ከባድ የሚሉት ዓይነት ዶፍ ዝናብ ይጥላል። ልጇን በጀርባዋ አዝላለች፤ ከፊት ለፊቷ ደግሞ መሳሪያዋን አንግባለች። ከጀርባዋ ያለው የነገው ትውልድ ትኩረቷን ይፈልጋል፤ ወዲህ ደግሞ በአደራ የተሰጣት የሀገር ጥበቃ ተልዕኮ አስተውሎትዋን ይሻል። የነገውን ሀገር ተረካቢ በዝናብ ኮት ሸፍናዋለች፤ የሀገር ጥበቃ ሥራዋ ስኬታማ ይሆን ዘንድ መሳሪያዋን አነጣጥራ ተጋፋጣለች። በዚህ መልኩ ያሳለፈችው የዕለቱ የሥራ ኃላፊነት ከባድ እንደነበር ታስታውሳለች – የልዩ ኃይሎች ማሰልጠኛ ማዕከል በደረጃ ሁለት ሆስፒታል ሎጂስቲክ ኃላፊ የሆነችው ሻምበል ማዕረግነሽ መንግሥቱ።
ሻምበሏ፣ ያንን ኃላፊነትም ሳታጓድል ለመወጣት ችላለች። ውትድርና እንደዚህ ነው ትላለች። ሴት የትኛውንም ተልዕኮ መወጣት ትችላለች፤ መውለድም ሆነ ማግባት ከተሰጣት ተልዕኮ ያግዳትም ስትል ትገልጻለች። የነገው ትውልድን በጀርባዋ አገሯዋ ደግሞ ፊትለፊ አድርጋ ሌቱን በስኬት አልፋዋለች።
ሻምበል ማዕረግነሽ መንግሥቱ፣ ተወልዳ ያደገችው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን ነው። ከአንደኛ እስከ ሰባተኛ ያለውን ክፍል እዛው ያደገችበት አካባቢ የተማረች ሲሆን፣ የቀረውን ደግሞ በሻሸመኔ መሰናዶ ትምህርት ቤት አጠናቃለች። ጊዜው ከዛሬ 18 ዓመት በፊት በ1997 ዓ.ም አካባቢ ነው። ሰዎች የውትድርናውን ዘርፍ እንዲቀላቀሉ ቅስቀሳ ይደረግ ነበር። እርሷም ውትድርናውን የተቀላቀለችው በወቅቱ ይደረግ በነበረው ትልቅ የሆነ ቅስቀሳ ተነቃቅታ ነው።
ውትድርናን ለመቀላቀሏ ዋናው ምክንያት ገጠር አካባቢ የምታያቸው ሴት ፖሊሶች ተጠቃሽ ናቸው። በተለይ እያንዳንዷ የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉ ያኮሯት ነበር። ሻምበል ማዕረግነሽ፣ በእነርሱ ሁኔታ ከመደነቅና ከመኩራት ባለፈ ግን ውትድርናን ለመቀላቀል ውሳኔ ላይ መድረሷን ትናገራለች።
በአንድ ወቅት ገና ልጅ እያለች ያደረገችው አንድ ነገር ትዝ ይላታል። ጊዜው ከሁለት አስርት ዓመት በፊት ነው። የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ነበረች። ወደ ትምህርት ቤት እየሄደች ነው። ድንገት አንዲት ፖሊስ ከፊቷ እየሄደች ታያታለች። በአቋሟ ዘለግ ያለች ያች ሴት ፖሊስ፣ ቀልቧን ትገዛዋለች
በውስጧም “እንደ እርሷ ነው መሆን የምፈልገው” እያለች ታሰላስል ያዘች። ሳታስበውም ትምህርት ቤቷን አልፋ ፖሊሷን ተክትላት ዘለቀች። ስትከተላት ቆይታ ወደቀልቧ መለስ ስትል ትምህርት ቤት የምትገባበበት ሰዓት ይረፍድባታል። የመጀመሪያው ክፍለ ጊዜ ከመቃጠሉም በተጨማሪ በትምህርት ቤቱ ዩኒት መሪም ቅጣት ደርሶባታል። በቃ ይኸው ነው፤ የፖሊስነት ፍቅር። በወቅቱ ታደንቅ የነበረው ውትድርናን ሳይሆን ፖሊስነትን ነው። ይሁንና አሁን ላይ ራሷን ወታደር ሆና አግኝታዋለች።
ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ሻምበል ማዕረግነሽ፣ ልክ መከላከያ ተቋም እንደመሆኑ ትዳር የሚባለውም በራሱ ራሱ ተቋም ነው ትላለች። የሰው ልጅ በዚህች ዓለም ላይ ሲኖር ራሱን ተክቶ ያልፋል፤ ለዚህ ደግሞ አንዱ መስመር ትዳር ነው። ለሀገሬ ትልቅ ክብር እንዳለኝ ሁሉ ለትዳሬ ደግሞ እንዲሁ ትልቅ ፍቅርና ክብር አለኝ ትላለች።፡ ስለዚህም እናትነትና ውትድርና ትኩረቴን ሰጥቼ የማስተናግዳቸው ተግባሮቹ ናቸው ስትልም ትገልጻለች።
ውትድርና አልጋ በአልጋ አይደለም። ብዙ የማይመቹ ሁኔታዎች አሉ። በአሁኑ ወቅት ወደቢሾፍቱ ለሥራ ተጠርቼ ስመጣ የተገኘሁት ልጄን ይዤ ነው። የሁለት ዓመት ልጅ ይዤ ብመጣም ያስቀመጥኩት ሰው ዘንድ ነው። ስለዚህ ውትድርናውን የምናስኬደው በዚህ መልኩ ነው ትላለች። ልጅ፣ ትዳርና ሥራ አለ። እነዚህ በሕይወቴ ውስጥ የሚያልፉ ሂደቶች ናቸው። ሂደቶቹ ጠንካራ የሚያደርጉ እንጂ የሚያኮስሱ አይደሉም። መልፈስፈስ ደግሞ ውጤት አይሆንም ስትል ትናገራለች።
እኛ ሴቶች ሥራችንን ስንሰራ በብርታት ነው። እንደዚያ የሚሆነው ችግሮች ሳይኖሩ ቀርተው ሳይሆን በዛ ችግር መካከል እንዴት ጠንክሮ መውጣት እንዳለብን ስለምናውቅ ነው ትላለች። ከዚህ አንጻር ሁሉንም የምታስኬደው እንደየአመጣጡ ነው። ቤተሰብን መምራትም ሆነ ሥራ መሥራትንም ጎን ለጎን አጣጥሜ የማስኬዳቸው ናቸው ትላለች።
እርሷ የመጀመሪያውን ደረጃ ለአየር ወለድነት የሚያበቃውን የፓራሹት ዝላይ ከዘለለች በኋላ በዝላዩ አልገፋችበትም። በርግጥ ስድስት ጊዜ በፓራሹት ዘላለች። ይህንንም ሴት ማድረግ እንደምትችል አሳይታለች። ሴት የትኛውንም ፈተና ተጋፍጣ የአሸናፊነትን ድል መቀዳጀት እንደምትችልም በልበ ሙሉነት ታስረዳለች። ወደ እኛ ወደ አየር ወለዱ ዘርፍ ስንመጣ ደግሞ ዝላዩን ሴት ከወንድ እኩል መዝለል እንደምትችል አስመስክራለች። በጥቅሉ ወንድ የሠራውን ነገር ሴት መሥራት ትችላለች። ዋናው የሥነ ልቦና ዝግጅት ነው። ከዚያ ውጭ ምንም ዓይነት መስፈርት አይጠይቅም ስትል የሴትን ብርታት ታስረዳለች።፡
እንደ ሻምበል ማዕረግነሽ አባባል፤ ሴት መምራት፣ ሀገር መጠበቅ፣ ማከም፣ ማስተማርም ሆነ ሌላ ሌላውንም ተግባር ማከናወን ትችላለች።፡ በየትኛውም የሥራ መስክ ብትሰማራ ማከናወን ትችላለች። እንዲያውም ሴቶች በሚያልፉበት ፈተና ውስጥ ወንዶች ቢገቡ እንደሴት ይወጡታል የሚል እምነት የላትም። ተፈጥሮ ራሱ ሴትን የሚያግዝ ነው ባይ ናት። ሴት በባህሪዋ አዕምሮዋ የሚያስበው አንድ ነገር ብቻ አይደለም። በአንዴ በርከት ያለ ነገር ማሰብም መሥራት ትችላለች። ስለዚህ ሴትነትን የምትወስደው በጥንካሬ ነው።
በሌላ በኩል ሴቶች በሰላም መስፈን ሂደት ውስጥ ያላቸው ሚና ቀላል አይደለም ትላለች። ለየትኛውም ነገር ሴቶች መሠረት ናቸው። ሌላው ቀርቶ በዚህ ሳምንት የተከበረው የዓድዋ ድል ላይ ሴት ትልቁን ሚና ተጫውታለች። ስለዚህ ሴት ሀገር ናት። ሴት እናት፣ እህት፣ የትዳር አጋር ናት። ሴት የሌለችበት ነገር ስኬታማነቱ አያስተማምንም ማለት ያስደፍራል። ሴት በአግባቡ የተካፈለችበት የትኛው መልካም የሆነ ሥራ የተሻለ መሆን የሚችል ነው የሚል እምነት አላት።
ሴቶችም ሆኑ ወንዶች ለዚህች ሀገር የሚከፍሉት መስዋዕትነት እኩል ነው። ሁሉም ደግሞ የሚጠበቅበትን ድርሻ ከተወጣ ነገ የተሻለችዋን ኢትዮጵያ ማየት እንችላለን። ነገ የተሻለችዋን ኢትዮጵያ ለማየት ደግሞ ዛሬ ላይ መካበበር፣ አንድነትና መተሳሰብ የግድ ይለናል። ሁሉም ለብሔሩ ሳይሆን ለሀገሩ የሚያደላ መሆን አለበት። ብሔርተኝነት የሌለበት፣ የወንድማማችነት ጥላቻ የጠፋበት ኢትዮጵያን ማየት እናፍቃለሁ ብላለች።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን የካቲት 29 /2016 ዓ.ም