ታሪካችን እንዲህ ይጀምራል…
አገራችንን ዳግም የወረረው ፋሽስት ኢጣሊያ በአባት እና እናት አርበኞቻችን መራር ትግል ከአምስት ዓመታት ቆይታ በኋላ አንገቱን ደፍቶ ወደመጣበት ተመለሰ። ይህንን ተከትሎም በውጭ አገር በስደት የቆዩት ንጉሱ ወደ አገራቸው ገቡ፤ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም። ንጉሱም ይህንን ዕለት «ይህ ቀን የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የአዲስ ዘመን መክፈቻ ነው» ሲሉ ገለጹት። ይህንን ባሉ እርሳቸውም አገራቸው በገቡ በ33ኛው ቀን ከእርሳቸው ንግግር ተወስዶ «አዲስ ዘመን» በሚል ስያሜ ጋዜጣችን ግንቦት 30 ቀን 1933 ዓ.ም በዕለተ ቅዳሜ መታተም ጀመረ።
ይህ ከሆነ ዛሬ 78 ዓመት ተቆጠረ።
ይህ ዕለት የጋዜጣችን የልደት ቀን ብቻ አይደለም። ይልቁንም የኢትዮጵያ የህትመት እና የጋዜጠኝነት መሠረት የተጣለበትም ጭምር እንጂ። 78 ዓመታት በሕዝብ አገልግሎት መዝለቃችን ኩራታችን ነው። እነዚህ ዓመታት የስኬትም፣ የፈተናም፤ የመውደቅና የመነሳትም ሆነው አልፈዋል።
በአገራችን ባለፉት ሦስት መንግሥታት የታሪክ ሂደት ዕለታዊ ጋዜጣን ማሳተም ምን ያህል ፈታኝና አድካሚ መሆኑን በዘርፉ ያሉ ሁሉ የሚረዱት ሀቅ ነው። በአንድ በኩል የመረጃ እጦትና ንፉግነት በሌላ በኩል የህትመት ዋጋ ውድነት እየፈተነንና እያንገራገጨን እዚህ ደርሰናል። ጋዜጣችንን በየዘመኑ የመሩና ያስተዳደሩ ጋዜጠኞችና አመራሮች ይህ የአገር ልሳን የሆነ ህትመት እንዳይስተጓጎል በተለይም ዕለታዊ ሆኖ መታተም ከጀመረበት ከታኅሣሥ 20 ቀን 1951 ዓ.ም ጀምሮ የከፈሉት መስዋዕትነት ሁሌም ሲታወስ ሁሌም ሲዘከር የሚኖር ታሪካችን ነው።
ድርጅታችን ባሳለፋቸው 78 የህትመት ዓመታት ስመ-ጥር ደራሲዎችና ጋዜጠኞችን ያፈራ ስመ-ጥር ተቋም መሆኑን ስናስብ ኩራታችን ከፍ ይላል። ይህንን ታሪካችንን በሌላ ገጹ ስንመለከተውም፤ በአገራችን የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ያለው አስተዋጽኦ ላቅ ያለ ሆኖ እናገኘዋለን። «ኩራት እራት» እንደማይሆን ጠንቅቀን ስለምናውቅና ስለምንረዳም ጭምር በዚህ ዘመን ባሉ የድርጅታችን ጋዜጠኞች፣ በተቋማችን አመራርና ባልደረቦች የተባበረ ክንድ የዘመናችንን ታሪክ አስቀምጠን ለማለፍ እየሰራን ነው፤ እንሰራለንም።
ታሪካዊውን እና አንጋፋውን ጋዜጣ እዚህ አድርሰናል። ያለንበት ዘመን በድርጅታችን ከአዲስ ዘመን በተጨማሪ ዘኢትዮጵያን ሔራልድ፣ በሪሳ እና አልዓለም ጋዜጦች እንዲሁም ወርሀዊዋ ዘመን ጋዜጣ የሚታተሙበት ነው። እነዚህ ጋዜጦቻችንና መጽሔታችን የሕዝብ ልሳን ይሆኑ ዘንድ በርካታ ጥረቶችን አድርገናል። እንደ አገር የነበረውና ያለው የሚዲያ ነፃነትን ተጠቅመን መስራት ያለብንን ሰርተናል፤ እየሰራንም ነን። ይሁን እንጂ የመጣነውና ያመጣነው ለውጥ ከምንጓዘውና ከሚጠበቅብን ያነሰ መሆኑን ስለምንረዳ ለዘመኑና ለሕዝቡ የሚመጥን ልሳን ለመሆን ተግተን እንሰራለን። ለውጡንም ጀምረናል።
ዛሬ ለውጥ ላይ ነን። በህትመት ኢንዱስትሪው የነበረንን ፈር ቀዳጅነት ዛሬም በአገራዊ ለውጡ ማግስት ሌላ ፈር ቀዳጅ ታሪክ በታሪካዊው ጋዜጣችን ላይ ጀምረናል። ከሰባቱ ቀናት የአዲስ ዘመን ጋዜጦች ውስጥ በአንባቢዎቻችን ፍላጎት መሠረት የቅዳሜውን እትም በመምረጥ «አዲስ ዘመን ቅዳሜ» በሚል በአርበ ጠባብ መጠን ማሳተም ጀምረናል። አዲሱ ነገር ይህ አይደለም። ይልቁንም በጋዜጣዋ ውስጥ «አገልግል» በሚል ስያሜ ከማስታወቂያ ነፃ የሆነች ተጨማሪ ጋዜጣ ይዘን መውጣት መቻላችን ነው።
ይህ ከሆነ እነሆ አራት ወራት ተቆጠሩ። የጋዜጣችንን ለውጥ በአዲስ ዘመን ሳናበቃ በተመሳሳይ አቀራረብ በዘኢትዮጵያን ሄራልድም የእሁድ እትም ላይ ተግባራዊ አድርገናል። በዚህም ሳናበቃ አንጋፋዋንና በአፋን ኦሮሞ የምትታመውን በሪሳ ጋዜጣ በዚሁ ቅርጽና ይዘት ከነገ ጀምሮ መውጣት ትጀምራለች።
ይህ ለውጥ የለውጥ ጅማሬያችን ነው። ዋናው ለውጣችንና የለውጥ እርካታችን ሕዝብና መንግሥት የሚኮሩብን ልሳን ሆነን መቅረብ ስንጀምር ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ የለውጠን ጅራት ይዘናል። ለዚህ የመለወጥ ምክንያት የሆነንና በለውጡ ጅማሬያችን ላይ ተስፋ ያደረበት መንግሥትም ለዓመታት ሲንከባለልና አልሆን ብሎን የነበረውን የድርጅታችንን ማሻሻያ አዋጅ ለማጽደቅ ከጫፍ አድርሶልናል።
ለዚህ አዋጅ እዚህ መድረስ የተቋሙ አመራሮችና የሥራ አመራር ቦርዱ የከፈሉት መስዋዕትነት በታሪካችን ተመዝግቦ የሚያልፍ ነው። የዚህ አዋጅ ሥራ ላይ መዋል በተቋም ደረጃ የተያዙት የለውጥ ጅማሬዎችን በብዙ እጥፍ ያፋጥንልናል፤ ያሳካልናልንም ብለን እናምናለን። ተቋማችን ያለምንም የመንግሥት ድጎማ በራሱ ገቢ የሚተዳደር መሆኑን ስናስብና አዋጁ ሥራ ላይ መዋሉን የማይቀር መሆኑን ስንረዳ፤ የመንገዳችን ብሩህነት ለእኛም ብቻ ሳይሆን በዘርፉ ላሉ ጋዜጣና መጽሔት አሳታሚዎችም ጭምር ነው።
ዛሬ ጋዜጦቻችን የሕዝብ ልሳን መሆን ጀምረዋል። ነፃ ሃሳብ ያለ ገደብ እየተንሸራሸረባቸው ናቸው። ይህ ዝም ብለን የምንለው አይደለም። እማኞቻችን ሁሉም ጋዜጦቻችን ቢሆኑም በተለይም ደግሞ የአዲስ ዘመን ቅዳሜ፣ የእሁድ ሄራልድና እና የነገዋ በሪሳ ጋዜጣ አብይ ማሳያዎቻችን ናቸው።
ይህ ጅምር ለውጥ ከዳር ይደርስ ዘንድ የእኛ ብቻ ሳይሆን የእርስዎም ድጋፍ ያስፈልገናልና ሃሳብዎን፣ ጊዜዎንና ይጠቅማል የሚሉትን ሁሉ ይስጡን። ቀጣዩን 78 ዓመታትም ለዚህ ዘመን የሚመጥን ታሪክ በጋራ ሰርተን እንለፈው። በእስከዛሬው መንገዳችን በውስጥም በውጭም ሆናችሁ ውዱን ዘመናችሁን ከእኛ ጋር ያሳላፋችሁ ሁሉ በጋዜጣችን የልደት ቀን ላይ ሆነን ምስጋናችንን እናደርሳለን፤ እናመሰግናለን!
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2011