
በአገራችንም ሆነ በክልል ደረጃ ያለው መረጃ እንደሚያመለክተው ከአጠቃላይ የህዝብ ብዛት ውስጥ ከ30 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከ15 እስከ 29 ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ናቸው፡፡ ከ30 ዓመት በታች ባለው ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት ቁጥራቸው ከ70 በመቶ በላይ እንደሆነ በተለያዩ ወቅቶች የተደረጉ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡
ከእነዚህ አጠቃላይ ህዝብ ብዛት ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙት የታዳጊዎችና ወጣቶች እምቅ አቅም፤ ብሩህ አዕምሮ፣ የምርምርና የፈጠራ ዝንባሌ ያላቸው አምራች ኃይል ናቸው፡፡ ከእዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሱ በጎና መጥፎ ሁኔታዎች የወጣቶች ስነ ምግባር ደረጃ ወሳኝ ድርሻ እንዳለው ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡
የወጣቶች ሥነምግባር፣ የሥራ ባህል እና የመጤ ባህል ጎጂ ተፅዕኖ ደግሞ የወጣቱን አምራች መሆን አለመሆን ብቻ ሳይሆን የአገርን ህልውና እስከ መገዳደር የሚደርሱ ገፊ ምክንያቶች ናቸው፡፡ አገሪቱም ሆነ ክልሎች ለእነዚህ ጉዳዮች ትኩረት በመስጠት መሥራት መቻላቸው ደግሞ ችግሩን ከመቀነስ ባለፈ የወጣቱን እምቅ አቅም በሚገባ ለመጠቀም ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡
ሰሞኑን የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ከሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያካሄደው ጥናት እንዳረጋገጠው ሥራ አጥነት በወጣቱ ዘንድ እየተስተዋለ ላለው ከፍተኛ የሥነ ምግባር ችግር ዋነኛው መንስኤ መሆኑን ነው፡፡
በክልሉ በተመረጡ ሰባት ከተሞች ውስጥ በትምህርት ተቋማት ውስጥና ከትምህርት ውጪ ሆነው በየከተሞቹ በሚኖሩ ወጣቶች ስነምግባር፣ የሥራ ባህል እና ከአሉታዊ የመጤ ባህል ጋር በተገናኘ ያሉ ችግሮችን በመቃኘት ይፋ የተደረገው ይህ ጥናት በእርግጥም በአገሪቱ ያሉ ሁሉም ከተሞች የሚጋሩት ጥሬ ሀቅ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡
የወጣቱ ሥነ ምግባርና የሥራ ባህል ነባራዊ ሁኔታን በሚመለከት በከተሞች የሚገኙ ወጣቶች በአጠቃላይ እና በተለያዩ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ ወጣቶች ከፍተኛ የሥነ ምግባር ችግሮች ያሉባቸውን፣ዝቅተኛ የሥራ ባህል እና የሥራ ተነሳሽነት ያላቸው መሆኑን ጥናቱ አሳይቷል፡፡ ይህ ሐቅ በከፍተኛ ትኩረት ሊያዝና ትርጉም ባለው መልኩ ለመፍትሔው መሥራት እንደሚገባ ያመላከተ ነው፡፡
ለወጣቱ የሥነምግባር ችግሮች በመንስኤነት የተቀመጠው የሥራ አጥነት መስፋፋትና የወጣቶች አልባሌ ቦታ መዋል፤ተማሪዎች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ አለመስጠት፤ አደንዛዥ እፆችን የሚነግዱ የንግድ ቤቶች መበራከት፣ የወጣቶች መዝናኛ ማዕከላት በቂ አለመሆን፣ የጓደኛ ግፊትና የሚዲያ ተፅእኖ ይገኙበታል።
ከእነዚህ በተጨማሪ ቤተሰብና የሃይማኖት ተቋማት ኃላፊነታቸውን በተገቢው ሁኔታ አለመወጣታቸው፣ ለስነ ምግባር ትምህርት ትኩረት አለመስጠት እና የሉላዊነት ተፅዕኖ ለወጣቱ የስነምግባር መበላሸት ቁልፍ ምክያቶች ሆነው በጥናቱ ተነቅሰዋል፡፡
የጥናቱን ውጤት መሰረት አድርጎ ጉዳዩን ሀገራዊ መልክ አስይዞ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ለመፍትሔው የተጠናከረ ሥራ መሥራት ይገባል፡፡ በመሆኑም ባለድርሻ አካላት የሚመለከተው ቤተሰብ እንዲሁም የትምህርቱ ዘርፍ ባለሙያዎች ችግሩንም ሆነ የጥናቱን ውጤት በሚገባ በመገንዘብ የሚከተሉትን ሥራዎች መሥራት ጊዜ የማይሰጠው ሊሆን ይገባል፡፡
ትምህርት ቤቶች ቀለም መቁጠሪያዎች ብቻ ሳይሆኑ የህይወት ክህሎት፣ የፈጠራ፣ የሥራ ወዳድነት፣ የሥነ ምግባር ማጎልበቻና የዝንባሌ ማሳደጊያ ወዘተ ሊሆኑ ይገባል፡፡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የትምህርት ቤት ክበባት እና የመሳሰሉት እንደ ተጓዳኝ ሥራ ሳይሆን እንደ ቁልፍ የመማር ማስተማር ተግባራት ተደርገው እንዲወሰዱና እንዲሠራባቸው መሆን ይገባል፡፡
ወጣቱን የችግሩ ሰለባ ብቻ አድርጎ ከማየት የጉዳዩ ባለቤት እና የመፍትሔው አካል ማድረግ ሌላው ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ወጣቱ የሥራ ዕድል የመፍጠር ፣ራሱን ከአልባሌ ቦታዎች የማራቅ፣ከሱስ ራስን መጠበቅና የአመለካከት ለውጥ የመፍጠር ኃላፊነት ያለበት በመጀመሪያ ደረጃም ቢሆን ራሱ ወጣቱ ነው፡፡
በዚህም ራሱን ከመጤ ባህል ተፅእኖ የመጠበቅ አቅምም ሆነ የሥራ ባህልን የምናሳድግበት አንዱ ቁልፍ መንገድ ከወጣቱ ጋር ቁጭ ብሎ በመወያየትና በመፍትሔው ላይ ከእቅድ እስከ ትግበራ ስናሳትፈው ነው፡፡
ለወጣቱ በቂ የሥራ ዕድል መፍጠርና ሁለንተናዊ ተሳትፎውን ማሳደግ ከመፍትሔዎቹ ሁሉ አብይ ጉዳይ ነው፡፡ የወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግር ለመፍታት የተለያዩ ሥራዎች የተሠሩ ቢሆንም ካለው ሰፊ ሥራ አጥ ቁጥር አኳያ ብዙ ይቀራል፡፡ በተፈጠረው የሥራ ዕድልም ፍትሐዊ አይደለም የሚል ሰፊ ችግር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የአብዛኛው የአገራችን ወጣት ጥያቄ አሁንም ሰፊ፣በቂና ሁሉንም የሚያሳትፍ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚገባ አምኖ ከልብ መሥራት ይጠይቃል፡፡
በአጠቃላይ የደቡብ ክልል ያስጠናው ጥናት የወጣቱን ቁልፍ ችግር በግልፅ ያሳየ ነው። ይህ የሥራ አጥነት ጉዳይ በአንድ ክልል ብቻ የተገደበ ባለመሆኑ ሁሉም የአገራችን ክልሎች ሊጋሩት የሚገባ ሀቅ ነው፡፡ ከዚህ ሀቅ በመነሳት ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር፣ በሥነ ምግባር ላይ ያልተቋረጠ እና ሁሉንም አካላት በተለይ ወጣቱን በማሳተፍ መሥራት ከተቻለ መፍትሔው ሩቅ አይሆንም፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2011