አሁን ወቅቱ ከምንግዜውም በላይ አንድነታችንንና ሰላማችንን የምናስጠብቅበት፤ ወጣቶችን ለሚረከቧት አገር እውነተኛ ተስፋና ተተኪዎች እንዲሆኑ የምናበቃበት፤ የምንመኘውን እድገትና ብልጽግና እውን ለማድረግ ጠንካራ ስራ የምንሰራበት ነው።
ወቅቱ ከሚፈልጋቸው ጉዳዮች ዋነኛው ደግሞ ወጣቶችን ወደስራ እንዲሰማሩና ምርታማ እንዲሆኑ ምቹ መደላድል መፍጠር ነው። ይህ እንደየአካባቢው፤ እንደየሙያውና እንደየወጣቶቹ ዝንባሌ የሚወሰን ቢሆንም ዋናው ጉዳይ አምራቹ ሀይል ሊሰማራ የሚችልበትን አቅጣጫና መስክ አመቻችቶ ማቅረብ ይገባል።
የአገሪቱን የግብርና ዘርፍ አጠቃላይ ስራ በገመገመው አገር አቀፍ የግብርና ከፍተኛ አመራሮች የምክክር መድረከ ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አጽንዖት ሰጥተው “የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገት ከማረጋገጥ አኳያ ግብርናው የማይተካ ሚና አለው” ብለው ነበር። አዎን! አሁንም ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ይህ ዘርፍ ቀዳሚውን ድርሻ ይይዛል።
ከዚህም በመነሳት መንግስት በግብርናና ተያያዥ ሙያዎች ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመረቁ ወጣቶችን በመስኖ ልማት እንዲሰማሩ ከፍተኛ ፕሮጀክት ቀርጾ መተግበር ጀምሯል። በዚህ ፕሮጀክት በአጠቃላይ፤ በአገሪቱ ሃምሳ ሺህ ሄክታር መሬት በዘመናዊ መንገድ በመስኖ እንዲለማ፤ በማልማቱ ስራም ወጣቶች፣ በተለይም የተማሩ ወጣቶች ግንባር ቀደም ሆነው እንዲሰማሩ ታልሟል።
የፕሮግራሙ አንድ አካል የሆነውና በአፋር ክልል የሚገኙ በግብርናና ተያያዥ ሙያዎች ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተመረቁ ወጣቶች የተመለመሉበት ስልጠና በሰመራ ተጀምሯል። ይህ ፕሮግራም በአገር አቀፍ ደረጃ አስራ ሁለት የተለያዩ ፕሮጀክቶች ያሉት ሲሆን፤ የአፋር ክልል ፕሮጀክትም አንዱ ነው።
የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያረጋግጠው በመላ አገሪቱ አምስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር በመስኖ ሊለማ የሚችል መሬት እያለ፤ ከዚህ ውስጥ የለማው ግን ሃያ በመቶው ብቻ ነው። ሰማንያ በመቶው መሬት አምራች ይጠብቃል። አሁን በተያዘው እቅድና ስልት መሰረት ከአምራቹ መካከል በግብርናና ተያያዥ ሙያዎች የሰለጠኑ፤ ዕውቀት ያላቸውና በተለያየ ምክንያት ወደ ስራ ያልተሰማሩ ወጣቶች ይገኙበታል። እነዚህን ትኩስ ጉልበት ያላቸው ወጣቶች አሰልጥኖ ወደ ስራ ማሰማራቱ ተገቢ ነው።
በአፋር ክልል ተመልምለው ስልጠናውን የሚወስዱት ወጣቶች በግብርናና ተያያዥ ሙያዎች የተመረቁ ናቸው። ለነዚህም ወጣቶች በተንዳሆ የመስኖ ክልል ስድስት ሺህ ሄክታር የሚለማ መሬት ተዘጋጅቷል። በተጨማሪም ፕሮግራሙ የተማሩ ወጣቶችን በማደራጀት፣ መሬት፣ ቴክኖሎጂና ፋይናንስ በማቅረብ የመስኖ ልማት እንዲስፋፋ ለማድረግና ግብርናውን ለማዘመን የተያዘ መርሀ ግብር በመሆኑ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አስራ ሁለት ፕሮጀክቶች ተለይተዋል።
በእነዚህ ፕሮጀክቶች የሚከናወነው የመስኖ ልማት የሚሳካው በተለያዩ ግድቦች ተጠራቅሞ የሚገኘውን ውሃ በመጠቀም፤ የከርሰ ምድርን ውሃ በማልማት፤ ተፋሰሶችን ተከትሎ የሚገኙ ወንዞችን በመጥለፍ እንደሆነም መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ ትልቅ እቅድ ነው። በእቅዱ መሰረት ከተተገበረም በአንድ በኩል፤ ወጣቶች ወደ ስራ ተሰማርተው የላባቸው ተጠቃሚ ይሆናሉ። በሌላ በኩል በእነርሱ ሙያና ጥረት ዘመናዊ የመስኖ ልማቱን እውን አድርጎ ግብርናውን ማዘመን ይቻላል። ይህም የሁለትዮሽ ጥቅም የሚያስገኝ ነው።
በፕሮግራሙና በዕቅዱ መሰረት በቀጣይ የኦሮሚያ፣ የሶማሌና የጋምቤላ ወጣቶችን ጨምሮ በሁሉም አካባቢዎች ትግበራው እውን ሲሆን፤ የሚሰራው ስራ ከፍተኛ በመሆኑ አገሪቱ ተጠቃሚ ትሆናለች። በዘመናዊ ግብርና፤ በተለይም በመስኖ ልማት በሚመረቱ ምርቶች ከውጭ የሚገቡትን በመተካት የውጭ ምንዛሬ ማዳን ይቻላል። ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችንም ዓይነትና መጠን ያበዛል።
ይህም ከአገር ውስጥ ፍጆታ በተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት አንዱ መንገድ ነው። በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በውስጣቸው ለያዟቸው ፋብሪካዎች ግብዓት የሚሆኑ ጥሬ እቃዎችም ለማቅረብ አይነተኛ መንገድ ነውና ጠቀሜታው ዘርፈ ብዙ ነው።
መንግስት በአሁኑ ወቅት ዘመናዊ ግብርና እንዲስፋፋ የሚያደርገው ጥረት ይበል የሚያሰኝ ነው። አዎን! ዘመናዊ እርሻ እንዲስፋፋ አስፈላጊውን ግብዓት ለማሟላትና የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ የሚያደርገው ጥረትም ዕውቅና ሊሰጠው ይገባል። ይህ ብቻውን ግን ውጤት አያመጣም።
በዚህ ረገድ የክልል መንግስታት በውስጣቸው ላሉ ፕሮጀክቶች መሳካትና በአጠቃላይ ለአገር አቀፉ ፕሮግራም ውጤታማነት በከፍተኛ የሃላፊነት ስሜት ሊሰለፉ ይገባል። በመሆኑም፤ ወጣቶችን በፍትሃዊነት በመመልመልና አግባብነት ባለው የስራ መስክ እንዲሰማሩ ግንዛቤ በማስጨበጥ፤ በአብዛኛዎቹ ዘንድ ያለውን የተዛባ አመለካከት በማስተካከል በአምራችነት እንዲሰለፉ በማብቃት ረገድ ከፍተኛ ድርሻ ይጠበቅባቸዋል።
ይህ ፕሮግራም በእነዚህ ወጣቶች እና በጥቂት ጅምሮች የሚቆም ሳይሆን አገራዊውን የእድገት ራዕይ እውን ከማድረጊያ ቁልፍ ስልቶች መካከል አንዱና ዋነኛው በመሆኑ፤ ወጣቶች በባለቤትነት ሊይዙትና ሊተገብሩት ይገባል። የነገዋ ኢትዮጵያ የኛ ናት የሚሉ ወጣቶች በሙሉ ይህን ሃሳብ ተቀብለው የእኔ የሚሏትንና በአደራ ለቀጣዩ ትውልድ የሚያስተላልፏት አገር ትለማና ትበለጽግ ዘንድ በጊዜያቸው የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል።
አዎን! ዛሬ በአፋር ክልል በስድስት ሺህ ሄክታር መሬት የተጀመረው የመስኖ ልማት ሃምሳ ሺውንም ሄክታር በማልማት ይሰፋል። በዚህ ብቻ ግን መቆም የለበትም። ይልቁንም፤ በሚለዮን ሄክታር የሚገመተውን ጠፍ መሬት ለማልማት መስፈንጠሪያ መሆን ነው ያለበት፤
መንግስትም እንደጀመረው መቀጠልና ዕቅዱን ከግብ ማድረስ ይገባዋል። በዚህም አስፈላጊ የቴክኖሎጂና የፋይናንስ ግብዓት በማሟላት ለፕሮግራሙ ስኬት የራሱን ሚና መጫወት አለበት።
ፕሮጀክቶቹ የሚገኙባቸው የክልል መንግስታትም ውጥን የማይሰናከልባቸው፤ ጅምር የማይደናቀፍባቸው፤ ይልቁንም ውጤትና ፍሬ የሚታይባቸው እንደሆኑ ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ በፍትሃዊነትና በባለቤትነት መነሳት ይገባቸዋል። ወጣቶችም አገራቸውን አልምተው፤ ራሳቸውንና ማህበረሰባቸውንም ጠቅመው በትውልድ ሰንሰለት ውስጥ ለማለፍ የድርሻቸውን ሊያበረክቱ እና ፕሮጀክቱን ውጤታማ ሊያደርጉት ይገባል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2011